Monday, April 24, 2017

ግብፅ 130 ሺህ ጦር በኤርትራ ልታሰፍር ነው ተባለ

ግብፅ 130 ሺህ ጦር በኤርትራ ልታሰፍር ነው ተባለ – ግብፅ በኤርትራ የጦር ሠፈር በመገንባት ከ20 ሺህ እስከ 130 ሺህ የሚደርስ ጦር ለማስፈር ማቀዷ የተዘገበ ሲሆን የኤርትራ መንግስትም ፈቃደኝነቱን መግለጹ ተጠቁሟል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ግብፅም ሆነ ሌሎች አገራት በአካባቢው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ስጋት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግብጽን እንዲጎበኙ በፕሬዚዳንት አብደል ፈታህ ኤልሲሲ መጋበዛቸውን የጠቆመው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፤ ጠ/ሚኒስትሩም ግብዣውን እንደተቀበሉት አስታውቋል፡፡
የቀይ ባህር አፋር ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ለሱዳን ትሪቡን በሰጠው መረጃ፤ በቅርቡ በኤርትራ ጉብኝት ያደረገው የግብፅ ልኡካን ቡድን፣ግብጽ በኤርትራ ምድር የጦር ሰፈር ለመገንባት በሚያስችላት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን የኤርትራ መንግስት፤ግብጽ በዳህላክ ደሴት ላይ የጦር ሃይሏን እንድታሰፍር ፈቅዷል ብሏል፡፡
ግብፅ ቀደም ሲል ተመሳሳይ የጦር ሰፈር ጥያቄ  ሶማሊያን፣ ሶማሌ ላንድንና ጅቡቲን ጠይቃ የነበረ ቢሆንም እንዳልተሳካላት ይታወቃል፡፡
ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እያሰፋች መምጣቷ፣ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የህዳሴውን ግድብ ለማስተጓጎል ነው ሲሉ አንዳንድ ወገኖች ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ አይስማሙም፡፡ ግብፅን ጨምሮ ሳኡዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ በኤርትራ የጦር ሰፈር ማቋቋማቸው በኢትዮጵያ ላይ ስለሚፈጥረው ስጋት የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የባህረ ሠላጤው አገራት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ስጋት እንደማይሆን ጠቁመው፣ ጉዳዩ በሶማሊያና በኤርትራ ካለው ሁኔታ ጋር መገናኘቱም ተገቢ አይደለም ብለዋል። የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለመገምገም ከአጠቃላይ የአካባቢው ጂኦፖለቲካ አንፃር ማየት እንደሚገባ የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ከዚህ አንፃር የአገራቱ እንቅስቃሴ ስጋት አይሆንብንም ብለዋል፡፡
ከግብፅ ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ ግንኙነታችን እየተጠናከረ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ እንዲያውም መቀመጫቸውን ግብፅ አድርገው ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚሰሩ የሚዲያ ተቋማት ላይ ሀገሪቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ እርምጃ መውሰድ ጀምራለች ብለዋል፡፡ OMN በተባለው ሚዲያ ላይ የነበሩ ግለሰቦችም በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ፣የተወሰኑትም በግብጽ መንግስት  መታሰራቸውን ገልጸዋል – ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
በሌላ በኩል የግብጹ ፕሬዚዳንት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም አገራቸውን እንዲጎበኙ ጥሪ እንዳቀረቡላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ለአዲስ አድማስ ያስታወቀ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩም ግብዣውን እንደተቀበሉት ጠቁሟል፡፡
ሰሞኑን በግብጽ የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት ንግግር፤”ኢትዮጵያና ግብጽ ዕጣ ፈንታቸው የተያያዘ ነው፣አንዱ ለምቶ ሌላው ችግር ውስጥ እንዲሆን መፍቀድ ተገቢ አይደለም፤ የሁለቱ አገራት ዕጣ ፈንታ የተሳሰረ ነው፤ ወይ አብረን እንለማለን ወይ አብረን እንጠፋለን፤ ወይ አብረን እንዋኛለን ወይ አብረን እንሰጥማለን፤ ስለዚህ አማራጩ ተባብሮ መሥራት ነው” ብለዋል – የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ባደረሰን መረጃ፡፡ በግብጽ ሳንታና አሌክሳንደርያ አይሲስ በክርስትያን ምዕመኑ ላይ የፈጸመውን የሽብር ጥቃት የኮነኑት ዶ/ር ወርቅነህ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በዚህ ፈታኝ ወቅት ላይ ከግብጻውያን ወንድሞቹና ወገኖቹ ጎን ይቆማል ብለዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ መገናኘታቸውን የጠቆሙት የግብጹ ፕሬዚዳንት፤ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በተለያየ ወቅት ያደረጉት ውይይት ግንኙነቱ በመተማመን መንፈስ ላይ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል። “ኢትዮጵያና ግብጽ ታሪካዊ ወዳጆች ናቸው፤ ሥልጣኔ ያላቸው አገራት ናቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክርስቲያን እንዲሁም የእስልምና ሃይማኖት የተሳሰሩ ናቸው፤ ይሄን ወዳጅነት የበለጠ ማጠናከር ለሁለቱ ህዝቦች ጠቃሚ ነው” ብለዋል፤የግብጹ ፕሬዚዳንት –

No comments:

Post a Comment