Monday, April 3, 2017

የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኦሮሞው በማንነቱ በስሙ ጭምር እንዲሸማቀቅ ይደረግ ነበር?… ለምን? (ኤርሚያስ ቶኩማ)


ሳተናው
By ሳተናውApril 3, 2017 04:49

 2  544  546

ቴዲ አፍሮ የቀድሞ ነገስታትን ስም ጠርቶ ክብር መስጠቱን ተከትሎ አንዳንድ አዛውንት ፖለቲከኞች ያንን የኢቢኤሱን ጋዜጠኛ ጨምሮ ደጋፊዎቻቸውን ለማሳመን የሚጠቀሟቸው ቃላቶች ያስቁኛል። ከእነዚህም መካከል አንደኛው በቀድሞው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኦሮሞው በማንነቱ በስሙ ጭምር እንዲሸማቀቅ ይደረግ ነበረ የሚለው ትልቁ ማሳመኛቸው ነው ሆኖም ይህ ደጋፊን ለማፍራት ሆን ተብሎ የተቀመረ ማሳመኛ ነው፤ ሰው በስም መጠሪያው እንዲሸማቀቅ ይደረግ የነበረው አሁንም የሚደረገው በኦሮሞው ላይ ብቻ ሣይሆን በደቡቡም በአማራውም ላይ ጭምር ነው።
ጥሩ ምሳሌ ልንገራችሁ ድምፃዊ ኤልያስ ተባባል የተወለደው ጎንደር ነው አዲስ አበባ ሔዶ የሙዚቃ ካሴት ሊያሳትም አሳታሚዎችን ሲጠይቅ ትክክለኛ ስሙን ልዋጥህ ተባባልን ካልቀየረ  ህዝቡ ካሴቱን እንደማይገዛው ተነግሮት ነው ከልዋጥህ ተባባል ወደኤልያስ ተባባል የቀየረው። የማዲንጎ አፈወርቅም ስም ተቀይሮ እንደሆነ ሰምቻለሁ እርግጠኛ ባልሆንም ትክክለኛ ስሙ ተገኝ አፈወርቅ ነው የሚል ነገር ሰምቻለሁ።
ማዲንጎ አፈወርቅ ስሙን ብቻ ሳይሆን ስታዲየም ዙሪያ ይዞት ይዞር የነበረውን ማሲንቆና የለበሰውን ቁምጣ ሁሉ ጥሎ ሁለት ጆሮውን ተበስቶ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ እንዲሄድ ከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል።
በርካታ የአማራ ተወላጅ አዲስ አበባ ሲገባ ከድላርጋቸው ወደዳጊ ከእማዋይሽ ወደኤሚ ከፈለቀ ወደፊሊሞን ከአንዳርጋቸው ወደኤንዲ ከሙላቱ ወደሙለር ስሙን ይቀይራል። ይህንን የሚያደርጉት በስማቸው ምክንያት አዲስ አበባ ላይ የሚያጋጥማቸውን ነገር በመፍራት ነው። በኦሮሞውም ላይ የሆነው ተመሳሳይ ነው በርካታ ኦሮሞዎች አዲስ አበባ ሲሔዱ ስማቸውን ከጋዲሳ ወደጌዴዮን ከአቶምሳ ወደአትናትዮስ ይቀይራሉ።
በነገራችን ላይ ሰውን በስም ማሸማቀቅ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሀገር ያለ ነው ለምሳሌ የጀርመንን ብንመለከት Schartzmugel የሚለው ስም መጠሪያቸው የሆኑ ሴቶች በብዛት በስማቸው ይቀልድባቸዋል የእነርሱ ስም ዘመናዊ እንዳልሆነና እንዲቀይሩት ሲነገራቸው ልትሰሙ ትችላላችሁ በአንፃሩ Katrina በጣም ተወዳጅ የጀርመን ሴቶች ስም ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው በስሙ እንዲያፍር የሚደረገው ጎሣ እየተመረጠ አይደለም ከሁሉም ጎሳዎች ስም እየተመረጡ አዲስ አበባ ላይ ሰው ለመቀለድ ይሞክራል የእስራኤል ስሞች እንደዘመናዊ ስም ሲታዩ ሀገርኛ ስሞች መሸማቀቂያ ናቸው።
ደሚቱ የሚለው የኦሮምኛ ስም ሲተረጐም ማሪቱ እንደማለት ነው ሆኖም በዚህ ሰአት ልጅህን ማሪቱም አልካት ደሚቱ ስሟን ሰምቶ የሚስቅ ሰው አታጣም ይህ የሰው ልጅ ለስም ካለው ግምት የሚነሳ ነው እንጂ አንዱን ጎሣ በመናቅ ሌላውን ለማሞገስ ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም አልነበረምም።
የቀድሞ ነገሥታት የፈጸሟቸው ስህተቶች መኖራቸው እሙን ነው ሆኖም ኢትዮጵያን እንደኢትዮጵያ ለማቆየት የከፈሉት መስዋዕትነት ከሰሩት ስህተት ይበልጣል ለዚህ ደግሞ አሉባልታ እያወሩ ሊለያዩን የሚሞክሩትን እንደኢቢኤሱ ጋዜጠኛ ያሉትን በሥራቸው እንዲያፍሩ በማድረግ እንደቴዲ አፍሮ እና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ያሉ ሀገር ወዳዶች ለሚሰሩት ሥራ ክብር ልንሰጣቸው እንጂ ልንወርፋቸው አይገባም።
ኢትዮጵያውያን ከሚለያዪን ነገሮች ይልቅ የምንመሳሰልባቸው ነገሮች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ ሊለያዩን የሚሯሯጡትን እያስወገደን አንድነታችንን ማጠናከሩ ለሁላችንም መልካም ነው።
ኤርሚያስ ቶኩማ

No comments:

Post a Comment