Thursday, April 27, 2017

ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ100ሺሕ ብር ካሳ ይከፈለኝ በሚል በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በመሠረተው የፍትሐ ብሔር ክሥ ተረታ

    


ጠቅላይ ቤተ ክህነት: የ100ሺሕ ብር ካሳ ይከፈለኝ በሚል በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ በመሠረተው የፍትሐ ብሔር ክሥ ተረታ

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ ኹለተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ በከሣሽ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና በተከሣሽ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ መካከል፣ በስም ማጥፋት ክሥ ጉዳይ የነበረውን የፍትሐ ብሔር ክርክር ሲመለከት ቆይቶ፣ ዛሬ፣ ሚያዝያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጠ፡፡
ፍ/ቤቱ የግራና ቀኙን ክርክር በመመርመር፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰ የስም ማጥፋት የለም፤ ስለዚኽም ተከሣሹ አቶ ፍሬው አበበ የሚከፍሉት ካሳ የለም፤ በማለት ተከሣሽን በነጻ አሰናብቶታል፡፡
ለክሡ መነሻ የኾነው፣ በሰንደቅ ጋዜጣ፣ 11ኛ ዓመት ቁጥር 551፣ ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም፣ «ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድህነት ስጋት» በሚል ርእስ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተጻፈውን ጹሑፍ ጋዜጣው በማተሙ ምክንያት፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ጹሑፉ፥ የፓትርያርኩን መልካም ሰምና ዝና ያጠፋ ነው፤ በማለት ዋና አዘጋጁ የ100 ሺሕ ብር የኅሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፍላቸው ክሥ መመሥረታቸው ነው፡፡
ተከሣሽ ለፍ/ቤቱ ካቀረባቸው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚዎች መካከል፣ «የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ፓትያርኩን ወክሎ የስም ማጥፋት ክሥ ሊመሠረት አይችልም፤ አያገባውም» በሚል ያቀረበውን መቃወሚያ ፍ/ቤቱ ተቀብሎ፣ በክሡ ውስጥ ፓትርያርኩን የሚመለከት ጉዳይ ወጥቶና ክሡ ተሻሽሎ እንዲቀርብ በሰጠው ብይን መሠረት ክሡን አሻሽሎ አቅርቧል፡፡
ዳኛ ዮሲያድ አበጀ የተሠየሙበት ፍ/ቤት፣ በክሡ ላይ ግራና ቀኝ ወገኖችን ሲያከራክር ከቆየ በኋላ ተከሣሽ በጋዜጣው ላይ ያቀረበው ጹሑፍ፣ የስም ማጥፋት ይዘት የለውም፤ በዚኽም ምክንያት የሚከፍለው ካሳ የለም፤ በማለት ውሳኔ ሰጥቶ ጋዜጠኛውን በነጻ አሰናብቷል፡፡
ቀደም ሲል፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቀረበለትን የስም ማጥፋት ወንጀል ክሥ ሲመለከት ቆይቶ፣ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም በሰጠው ውሳኔ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ክሥ ውድቅ በማድረግ ጋዜጠኛ ፍሬው አበበን በነጻ እንዳሰናበተ መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡
ዳኛው፣ በንባብ ያሰሙት የችሎቱ ውሳኔ ከ15 ገጾች ባላነሰ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በቀጣይ ዝርዝር ዘገባ የሚቀርብበት ይኾናል፡፡

No comments:

Post a Comment