Friday, April 21, 2017

በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ተስፋፍቷል ሲል መንግስታዊው የዜና ወኪል ዘገበ





በመንግስት ቁጥጥር ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ባልተጠበቀ መልኩ የሚከተለውን ዘገባ አስፍሯል:: ያንብቡት እና አስተያየት ይስጡበት::
ሚያዝያ 12/2009 በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው በሚሰሩ ሴቶች ላይ የፆታ ትንኮሳና ሌላም በደል እንደሚደርስ በክልሉ ህፃናትና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የተካሄደ ጥናት አመለከተ።
ቢሮው በኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚቻልበት ላይ ያዘጋጀው ኮንፍረንስ በአዳማ ገልመ አባገዳ ተካሂዷል።
ጥናታዊ ጽሁፉን ያቀረቡት በቢሮው የህፃናትና አጠቃላይ የሴቶች ተቋማት ክትትል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ኡስማን ኢብራሂም እንዳመለከቱት ጥናቱ የተካሄደው በፊንፊኔ ዙሪያ፣ቡራያ፣ሰበታ፣ሞጆ፣ቢሾፍቱ፣ባቱና አዳማ በተመረጡ 10 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ነው።
ባለፈው አንድ ወር ውሰጥ የተካሄደው ጥናት በኢንዱስትሪዎቹ ተቀጥረው የሚሰሩ ሴትና ወንድ ሰራተኞች እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ማዕከል በማድረግ ነው፡፡
በጥናቱ መሰረት በኢንዱስትሪዎቹ ተቀጥረው በሚሰሩ ሴቶች ላይ ከሚደርስባቸው በደሎች መካከል የፆታ ትንኮሳ መብዛት፣ በአንድ አይነት ስራ ላይ ተመሳሳይ ክፍያ አለመኖር፣ የወሊድና የህመም ፈቃድ አለመስጠት ይገኝበታል፡፡
በማሽን ስራ ላይ ሲጎዱ አስፈላጊውን ኢንሹራንስ ላለመክፈል ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እስከ መግባትና ጨርሶ የማይከፈልበት ሁኔታም እንዳለ በጥናቱ ተመልክቷል።
ለደህንነት የሚገባቸው ቁሳቁሶችን የኢንዱስትሪ ባለቤቶች አሟልተው ባለመገኘታቸው ሰራተኞች በቀላሉ በፋብሪካ ውሰጥ በሚጠቀሙባቸው ኬሚካሎች ለጉዳት ይጋለጣሉ፡፡
ነፍሰጡሮች ከስራ የሚገለሉበት፣ የፆታ ትንኮሳ ፣ በቅጥር፣ በእድገት፣ በደመወዝ ጭማሪና በዝውውር ረገድም በደሎች እንዳሉ ነው ጥናቱ የዳሰሰው።
ኤች.አይቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ሴቶች ልዩ እንክብካቤ እንደማይደረግና በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መስፋፋቱም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
በኢንዱስትሪዎቹ የህፃናት ማቆያ ስፍራ አለመኖሩና ሌሎችም በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው በደልና ችግር እንዲፈታ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ወሳኝ መሆኑን በጥናቱ ከተመለከቱት መፍትሄዎች ይጠቀሳል።
የሴቶች ማህበራት በፋብሪካዎች የሚቋቋሙበትና የሚጠናከሩበት አቅጣጫ መቀመጥ እንዳለበት ጥናቱ ጠቁሞ በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ሊደረስ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የሚቋቋሙት ማህበራትም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ማደግና ሰላም መስፈን ሊታገሉ እንደሚገባ እንዲሁ።
የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አዚዛ አብዲ በበኩላቸው በሀገሪቱ ለተፈጠረው የኢንዱስትሪዎች እድገት መንግስትና ባለሀብቱ ትልቅ ደርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ በተለይ በሴቶች ላይ የተለያዩ ፆታዊ ትንኮሳና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ እንዳለ በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
ችግሩን በጋራ ማስወገድ በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ በመምከር መንግስት፣ ባለሀብቱና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በቀጣይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ኮንፍረሰንሱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሪት ፈትያ መሐመድ በሰጠችው አስተያየት በኢንዱስትሪ ውስጥ ተቀጥራ እንደምትሰራ ተናግራ የፆታ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸውና ከፍያቸውም ካለባቸው የስራ ጫና አንጻር ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ተናግራለች፡፡
መንግስት የሚደርስባቸውን በደል ተገንዝቦ እልባት እንዲሰጣቸውም ጠይቃለች።
ርካሽ የሰው ጉልበት አለ በሚል ከውጭ የሚመጡ ባለሀብቶች ለዜጎች ያላቸው ክብር እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ በሰራተኛው ላይ ከፍተኛ በደል እንደሚፈጸም ያመለከቱት ደግሞ አቶ ንጉሴ አበራ የተባሉት የመድረኩ ተሳታፊ ናቸው።
የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ጅሎ በክልሉ እየተስፋፋ በመጣው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የተፈጠረው የሥራ እድል ቀጣይነት እንዲኖረው መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ በአሠሪና ሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ የሚያስችላቸውን አሠራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው ኮንፍረንስ ከመንግስት፣ ከአሰሪዎች፣ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

No comments:

Post a Comment