ዋዜማ ራዲዮ- ዛሬ ሚያዚያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም አለም አቀፍ ፕሬስ ኢንስቲትዩት ከቪየና በወጣው መግለጫ መሰረት እስክንድር ነጋ የግል ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ለንግግር ነፃነት የጎላ አሰተዋፅዎ ያበረከቱ ጋዜጠኞችን ለማክበር እና ለማወደሰ በየአመቱ የሚሰጠውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና ሽልማት እንዲሰጠው ተወስኗል። የሸልማቱ ሰነስርዓት በግንቦት 10 ቀን 2009ዓ.ም በጀርመን አገር ሃምቡርግ ከተማ ይከናወናል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ተደላድሎ የጋዜጠኝነት ስራውን ከሰራባቸው አመታት ይልቅ የታሰረባቸው አመታቶች ይልቃሉ፡፡መንግስት ብቻውን ማሰር አልበቃ፣ አላጠግብ ሲልው ከነመላው ቤተሰቡ አስሮታል በ1997ዓ.ም።
እስክንድር ነጋ ብቸኛ ልጁንም ወልዶ ለመሳም እንድ ማንኛውም ዜጋ የታደለ አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማርሚያ ቤት ከማዶ በተለምዶ “የእምጫት” ቤት ተብሎ በሚጠራው የሴት እስረኞች ክልል ባለቤቱ ሰታምጥጥ እስክንድር ቀበቶውን ፈቶ አብሯት አላማጠም። ለብቻዋ እስር ቤት ውስጥ አምጣ እንድትወልድ የተገደደችው ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲል በሰላም መገላገልን በወሬ ወሬ በሶሰተኛ ወገን ስማ እንጂ።
ልጁንም ክርስትና ለማስነሳት የሚያሰችል ወግ እና ማዕረግም አልደረሰው፡፡ ተወልዶ በአይኑ ያላየውን በእጁ ለማቀፍ የጓጓውን ልጁን ናፍቆት ብሎ የስየመውም ለዚሁ ነበር፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ በጋዜጠኝነት ሙያ እና ለንግግር ነፃነት መከበር ለሚደርስ በደል፣ ግፍ፣ መከራና ኢፍታዊነት የመጨረሻውን ፅዋ በትዕግስት በትህትና እንዲሁም በልዕልና ዜጎች የሚከፍሉትን የህይወት ዘመን ዋጋ እንድ ማሳያ ከሚሆኑ በርካታ ጋዜጠኞች መካከል አንዱና ዋንኛው ነው እስክንድር ነጋ፡፡
መስከረም ሶስት ቀን 2004 ዓ.ም ልጁን ናፈቆት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት እያመጣ ሳለ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ፖሊሶች ከልጁ ፊት ተይዞ ለእስር የተዳረገው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከታሰረ 2 ሺህ 35 ቀናቶች ተቆጥረዋል፡፡ የህግ ጠበቃ፣ የሃይማኖት አባት፣ ቤተስብ እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ መንገደኛ እንዳይጠይቀው እገዳም ተጥሎበታል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስኪርቢቶ፣ ወረቀት እና መፀሃፍ በጭራሽ እንዳይዝ የተከለከለው ጋዜጠኛ እስክንድር፣ ቃሊቲ አብረውት የከረሙ ሁሉ ስለመልካም ትህትናው፣ ለሰላማዊ ትግል ሰላለው ቆራጥነት እንዲሁም ከፍተኛ የፍትህ ጥማት በአንድ ቃል የሚመሰክሩ ቢሆንም መንግስት ግን እስክንድርን በሽብር ክስ ከመክሰስ ወደ ኃላ አላስቀረውም።
ጦማሪ እና ጋዜጠኛው እስክንድር ነጋ የሽብር ቡድን ተበሎ በፓላማ ከተሰየመው የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በህቡዕ ግንኙነት በማደርግ፣ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በማሰብ እና ቀሰቃሽ ፁሁፎቹን በመፃፍና በማሰራጨት የሚል ክስ በመንግስት ይመስረትበት እንጂ ወደ እስር ቤት እንዲገባ ዋንኛ መነሾ የሆነው የፀረ ሸብር አዋጁን መንግስት የተለየ ድምፆችን ለማፈን እንድሚጠቀምበት እስክንድር በተደጋጋሚ በመተቸቱ ነበር።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፀረ ሸብር አዋጁን አላግባብ በመጠቀም ጋዜጠኞችን እና ተቃዋሚዎችን ድምፅ ለማፈን እየተጠቀሙበት ሰለመሆኑ፤ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ርዕዮት አለሙ እንዲሁም የኢትዮጲያ መንግስት ያሰራቸው ሁለቱ የስዊዲን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብዬ እና ጆሃን ፐርሰን የፀረ ሽብር አዋጁ ተገን በማደረግ መንግስት የንግግር ነፃነታቸውን ተጠቅመው በመፃፋቸው ለእስር እንደዳረጋቸው በተደጋጋሚ ተችትና አሰተያየት መሰነዘሩን ተከትሎ እርሱም ለእስር ተዳርጓል።
የጋዜጠኞቹን መታሰር አሰመልክቶ እስክንድር በጊዜው ለአለም አቀፍ ፕሬስ ኢንስቲትዩት “የጋዜጠኞቹ መታሰር የፍራቻን ዘር ለመዝራት በስሌት የተደረገ እስራት ነው፡፡ አምባገነኖች የሚተማመኑበት መቋሚያቸው በህዝባቸው ውስጥ ፍርሃትን መንዛት ነው” ብሎ ነበር።
ጋዜጠኛ ውበሸት ታዬ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የ14 ዓመት እስራት ሲፈረድበት፣ ሁለቱ የሲውዲን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብዬ እና ጆሃን ፐርሰን ድግሞ አስራ አንድ አመት ተፈረዶባቸው ነበር፤ እስክንድር ነጋ ከሁሉም ከፍተኛ የሆነውን የአስራ ስምንት አመት ፍርድ ተሸክሟል።
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት እስክንድር ላይ በ 2004 ዓ.ም የአስራ ስምንት ዓመት ፅኑ እስራት እና የአምስት አመታት ህዝባዊ መብቶች እግድ ቢጥለበትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘፈቀደ እሰራቶችን የሚመለከተው ክፍል የጋዜጠኛ እስክንድር እሰራት ዓለም አቀፍ ህግጋቶችን የሚፃረር እንድሆነ በመገለፅ እስራቱን ኮንኗል።
የፍርድ ቤቱ አሰራር ከፍትህ የአሰራር ስርዓት ውጪ በአሰፈፃሚው ኢህአዴግ እንድሚዘወር ለማንም ሰው ግልፅ ቢሆንም ሁለቱ የሲውዲን ጋዜጠኞች ማርቲን ሽብዬ እና ጆሃን ፐርሰን በይቅርታ እንዲፈቱ ገዢው መንግስት ሲፈቅድ ጋዜጠኛ ውበሸት ታዬ እና እስክንድር ነጋ ግን በዝዋይ እና በቃሊቲ እስር ቤቶች መንግስትን በፅኑ በመተቸታቸው ብቻ አመታትን ይቆጥራሉ።
“አምባገነኖች ፊት ለንግግር እና ለሃሳብ ነፃነት ሲል ያለፍርሃት በእውነት በመቆሙ እና ለዓላማው ፅናት ፣ የኢትዮጲያ መንግስት የፀረ ሽብር አዋጁን ተቃዋሚዎችን እና የተለየ አተያይ ያላቸውን ወገኖች ለማፈን እየተጠቀመበት ስለመሆኑ በድፍረት በመናገሩ ለዚህም ላሳየው ትጋት ተሸልሟል፡፡” ብለዋል በመገለጫቸው የአለም አቀፍ ፕሬስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ባርባራ ትሪዊኒፊ።
ሽልማቱ የእስክንድር ነጋ ጀግንነትን ለማሰብ፣ መንግስት በተደጋጋሚ የሚያደርስበትን ጫናና ጭቆና እንዲያቆም ለመጠየቅ እንዲሁም መንግስት እስክንድር ነጋን እና ሌሎች እንደ እርሱ ሃሳባቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ብቻ የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲፈታ ለማሳሰብ እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጲያ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የገባችውን ቃልኪዳን እንድታከብር ጥሪ እንዲያቀርብ ለማስታወስ ያለመ ነው።
የእስክንድር ነጋ ባለቤት ጋዜጠኛ ሰርክዓለም ፋሲል በበኩሏ እስክንድር የተሸለመውን ሽልማት አሰምልክታ በመግለጫው “ለመናገር ነፃነት የከፈለው ከፍተኛ ዋጋ በአለም አቀፍ መደረኮች ትኩረት ሰላገኘ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። የሚከፈለው መሰዋዕትነት እንደሁ በከንቱ አልቀረም። “
“እርሱ በእስር ቤት የሚከፍለው ዋጋ እና መሰዋዕትነት ምንም እንኳን ለእኔ እጅግ አሰቸጋሪ ቢሆንም ሌሎችን ስለሚያበረታ እና ተከታዬችንም ሰለሚያፈራ ያሰደሰተኛል። ይህም ሽልማት የእርሱን ነፃነት የሚያፋጥን እና ለረጅም እስሩ መቋጫ እንድሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።”ብላለች።
ለንግግር ነፃነት መከበር ዝብ ለቆሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ ከፍተኛ ሽልማቶችን ሁሉ በየዓመቱ የሚሸለመው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ መንግስት ለስምንተኛ ጊዜ ሲያሰረው በተቃራኒው በ2004ዓ.ም ፔን አሜሪካ ከተባለ አለማቀፍ ድርጅት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐሓን ድባብ ውስጥ ሆኖ በመፃፍ ላደረገው አስተዋፅዎ “የመፃፍ ነፃነት ሽልማትን” ስጥቶታል።
በድጋሚ በዚሁ 2004 ዓ.ም አለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተማጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እስክንድር ነጋ የህሊና እስረኛ ስለመሆኑ አውጇል፡፡
በታህሳስ 2005ዓ.ም ደግሞ የሂውማን ራይትስ ዎች የነፃ ንግግር ሽልማት አሸናፊ ነው። በ36ተኛው አለማቀፍ የፀሃፊዎች ፌስቲቫል ላይም እስክንድር ነጋ የፔን ካናዳ “የአንድ ስብዓዊነት ሽልማት” አሸናፊ ነው።
አለም አቀፍ ጋዜጦች እና ዜና አታሚዎች ማህበር በበኩሉ በጥር ወር 2006 ዓ.ም የጎለደን ፔን ፍሪደም ሽልማትን ለእስክንድር ሸልሟል።
የአርባ ስምንት አመት ጎልማሳው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በመሰከረም ወር 2004 ሲታሰር አብሮት የታሰረው እና በጋራ ክስ የተመሰረተባቸው የቀደሞ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዱዓለም አራጌም የእድሜ ልክ እስራቱን በአዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እየገፋ ይገኛል።
No comments:
Post a Comment