በየትኛውም ዓለም ከተማ ውስጥ የሌለና ያልታዬ ታሪክ በአገራችን ዋና ከተማ በሆነችው አደስ አበባ ውስጥ ለበለጠ የህዝብ ልዩነትና አገራዊ ቀውስ የሚዳርግ እቅድ ሰሞኑን በወያኔ ካቢኔ በህግ ጸድቆ ይፋ ወጥቷል።ህጉን ምክርቤት ተብየው የወያኔ ሆድ አደር መንጋ ካሳለፈው ለዘመናት ኢትዮጵያውያን በደምና በአጥንታቸው፣በእውቀትና በሃብታቸው የገነቡትን የጋራ ከተማ የሚንድና የአዲስ አበባን ሁልንተናዊነት አጥፍቶና ንዶ የጠበበች፣ የግጭትና የልዩነት አውድማ አድርጎ የሚያደራጅ ነው።
የወያኔ ዘላቂ ዓላማ ኢትዮጵያን በታትኖ የራሱን ጠባብ ክልል አገር አድርጎ ለመፍጠር እንደሆነ ምርምር አያሻውም።በዚያው አኳያ በኢትዮጵያዊነት የተሰሩትንና የተገነቡትን እየናደ፣የሚያስተሳስረውን ድርና ክር እየመዘዘ ማዳከም ለዘላቂው ዓላማው መጀመሪያው እርምጃ ነው።ባይሆንልን ብትንትኗን አውጥተን እንመለሳለን ከሚለው ነባር ዓላማ ጋር የተያያዘ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።
የወያኔ መራሹ የጎሰኞች ስብስብ አገር አቀፍ ህዝባዊ ተቃውሞ ዓላማውን እንደሚያጨናግፍበት በመረዳት የትግሉን ትስስር ለመበጠስና ለማዳከም የተካነበትን የማለያየት ስልት፣አንዱን የጠቀመና መብቱን ያስከበረለት በመምሰል ሁሉንም የሚጎዳና ለበለጠ ግጭት የሚዳርግ ስልቱን ሰሞኑን በአዲስ አበባ አስተዳደር ዙሪያ በመጀመር ይፋ አድርጓል።በዚህ ይፋ ባደረገው አዲስ የህገመንግስት አንቀጹ አዲስ አበባ የሁሉም ከተማ መሆኗ ቀርቶ የአንድ ማህበረሰብ ከተማ እደሆነች በማመን ዘርና ጎሳን ተንተርሶ ያልወጣላት ስሟም የኦሮሞ ተገንጣዮች በሚጠሯት ስም ፊንፊኔ በሚለው ጭማሪ እንድትጠራ(ይህ እራሱን የቻለ ውዥንብር የሚፈጥር ነው፤የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በየትኛው ለመጥራት ግራ ይጋባል፤ከተማዋም ለሚኖራት ግንኙነት ሁሉ እንቅፋት ይፈጥራል)።ሁሉም ነዋሪ የሚጠቀምበትና የሚግባባበት ቋንቋ ቀርቶ አንድ ማህበረሰብ ብቻ የሚናገረው የኦሮሞ ቋንቋ የአስተዳደሩ ተጨማሪ የስራ ቋንቋ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅቱን ጨርሶ ህጋዊ ሽፋን ሰጥቶት መወሰኑን ባወጣው መንግስታዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።ይህ ተንኮል ግን ኦሮሞውን ለመጥቀም ሳይሆን የተነሳበትን ተቃውሞ ለጊዜው ለማብረድና በስፋት የያዘውን የዘረፋ ዕድሜ ለማራዘም ሆን ተብሎ የተተመነ ስልት ነው።የኦሮሞም ሆነ የሌላው ማህበረሰብ ተወላጅ ጥያቄው ቋንቋየን እየተናገርኩ ከሌላው ተነጥዬ ልረገጥ ሳይሆን የሰብአዊና የዜግነት መብቴ ይጠበቅ፣ከድህነትና ከዃላቀርነት የሚገላግለኝ የጋራ ስርዓት ይመስረት፣የዴሞክራሲ መብቶች ይከበሩ፣በጎሳ ማንነት መጠቀምና መጎዳት ይቅር ለወደፊቱም አይኑር፣ከትውልድ የወረስኩት መሬቴን እየተቀማሁ አልፈናቀል… የሚል ነው።
አዲስ አበባ የአገራችን የፖለቲካና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መዲና ፣የአገሪቱም የኤኮኖሚ እምብርት መሆኗ እየታወቀ የአንድ ነጠላ ማህበረሰብ ጥቅም ብቻ የሚከበርበት አንቀጽ ህጋዊ መመሪያ አድርጎ መደንገግ፣በከተማዋም ሁለገብ ህይወትና በነዋሪው እጣፈንታ ላይ የአንድ ማህበረሰብ የበላይነት ማስፈን ፍትሃዊና ለሰላማዊ ኑሮና ለህዝብ ጤናማ ግንኙነት የሚረዳ አይደለም።የከተማዋ እድገትና ህይወት ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለሃገሮችና የተለያዩ ማህበረሰቦች ተወላጆች ያበረከቱት ድርሻ ውጤት ነው።ከተማዋ የተገነባችው ከሁሉም ያገሪቱ ክፍሎች በሚሰበሰበው የግብርና የእውቀት መዋጮ ነው።ስለሆነም ሁሉም እኩል የባለቤትነት ድርሻ ሊኖረው ይገባል።ኦሮሞኛ ለሚናገረው ቅድሚያና ብልጫ ጥቅም ይሰጠዋል፣መብቱም ይከበርለታል ማለት በዘረኛው አፓርታይድ ስር እንደ ቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካና ከሚሊዮን ህዝብ በላይ በጎሳ ውዝግብ እንደተጨፈጨፈባት ሩዋንዳ ከባሰ ቀውስ ውስጥ የሚከት ነው።ለመሆኑ ኦሮሞኛ የማይናገረው አዲስ አበባ ውስጥ ተወልዶ ያደገው የኦሮሞ ልጅ ምን ይውጠው ይሆን?ኦሮሞኛ የሚናገረውስ የሌላው ማህበረሰብ ተወላጅ የጥቅሙ ተካፋይ ይሆን ይሆን?ወይስ የጀርባ አጥንቱ እየታዬ ለጥቃቱ ሰለባ ይሆናል?
በሌሎቹስ ክፍላተ ሃገሮች ውስጥ የተቋቋሙትና የተፈጥሮ ሃብት ምንጭ የሆኑት አካባቢ ህዝብ ተመሳሳይ መብትና ጥቅም ያገኛልን? የኤሌክትሪክ ምንጭ፣የወርቅና የተለያዩ ማዕድኖች ቁፋሮ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ህዝብ የጥቅሙ ተካፋይ የሚሆንበት አሰራርና ህግ መቼ ተፈጠረለት?የበይ ተመልካች ከመሆን ያለፈ ዕድል መች አገኘ?
ይህ እንደ አዲስ የወጣ የማጠናከሪያ ደንብና መመሪያ ምናልባት የኦሮሞውን ማህበረሰብ የሚጠቅም ሊመስል ይችል ይሆናል።አርቆ ለሚያስብ የኦሮሞ ተወላጅ ግን ተቃውሞውን ለመግታትና አገራችንን ለመበታተኑ ሂደት የመጀመሪያው መንደርደሪያ እንደሆነ፤ ብቻውን ነጥሎ የሚያስመታውና የሚያስጠቃው የወያኔ ሰይጣናዊ ብልሃት መሆኑንም ሳይረዳው አይቀርም።
የዘፈን ዳርዳሩ እስክስታ ነው እንዲሉ ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊት ከአጋሩ ከኦነግ ጋር ሆኖ በጀርመን አገር ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከፈረንጆቹ በኩል « ኦነግ ተሳክቶለት ስልጣን ላይ ቢወጣ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ከሁሉም ክፍለሃገር የተውጣጣ ህዝብ ምን ዕድል ይገጥመዋል?» ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ የኦነጉ መሪ የዛን ጊዜው አቶ የአሁኑ ዶክተር ዲማ ነገዎ(ዩሃንስ ነገዎ) የሰጠው መልስ «ለኦሮሚያ የሚጠቅመው መኖሪያ ፈቃዱን እያሳደሰ ሲኖር የማይጠቅመው ደግሞ ወደ መጣበት እንዲመለስ ቀዳዳ መንገድ(safe corridor) ይከፈትለታል» ብሎ ነበር።ይህንን ባለ በስድስት ወሩ ሻእብያ፣ወያኔና ኦነግ ከሌሎቹ በአማራው ስም ከተደራጁት አሽከሮቹ ጋር ስልጣኑንc ጨበጡ።ይህንን የተናገረው ዲማ ነገዎ(ዩሃንስ ነገዎ)የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆነና በውጭ አገር በመዘዋወር ስለተመሰረተው አገዛዝ መብራሪያ ለመስጠት በውጭ አገር እየተዘዋወረ በየስብሰባው መድረክ ላይ ብቅ አለ። በስብሰባ ላይ ያንን ቀድሞ ጀርመን የተናገረውን በአካል ካዳመጥነው ውስጥ አንዱ ቢጠይቀው« አይኔን ግንባር ያድርገው!፣እንዲህ ያለ ቃል ካፌ ወጥቶ አያውቅም» ሲል ሸመጠጠ።ይባስ ብሎም በጠያቂው ላይ በስብሰባው የተሳተፉት አብዛኛዎቹ የወያኔና የሻእብያ ደጋፊዎች እንዲዛበቱበት የግለሰቡን አስተያየት አጣጥሎ ለማቅረብ ሞከረ።
እውነትና ጀንበር እያደር ይጠራል! ነውና የኸው ዛሬ ከሃያ ሰባት ዓመት በዃላ የዚያ አስተሳሰብ እንቁላል ተፈልፍሎ በአደባባይ ይፋ ወጣ።
የአዲስ አበባ ከተማ በሸዋ ክፍለሃገር የምትገኝ እንጂ ኦሮሞ የሚል ክፍለሃገር እንዳልነበረና በዚያ ክፍለሃገር ውስጥ የምትገኝ ከተማ እንዳልነበረች ሁሉም ያውቃል።የሸዋ ክፍለሃገር ደግሞ ኦሮሞውን ብቻ ሳይሆን አማራውና የተለያዩ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ክፍለሃገር ነው።ስለሆነም የባለቤትነቱ ጥቅም ይከበርለት ቢባል እንኳን የዚያው የሸዋ ጠ/ግዛት ህዝብ ይሆናል እንጂ የአንዱ ማህበረሰብ ብቻ ሊሆን አይገባውም።
የከተማውንም አስተዳደር በሚመለከተው የአንድ ከተማ አስተዳደር የሚዋቀረው በነዋሪው ብዛትና አኳያ ሊሆን ይገባዋል።አዲስ አበባ በክፍለ ከተማ ና ወረዳ እንዲሁም ቀበሌና መንደር የተዋቀረች በመሆኗ፤በነዚህም የከተማዋ እርከኖች ውስጥ ከተለያዩ ማህበረሰቦች የፈለቀና የተዋለደ ህዝብ ስለሚኖር አስተዳደሩም(ማዘጋጃቤቱም)የነዋሪውን ገጽና ስብጥር የሚያካትት ሊሆን ይገባዋል።የሚጠቀምበትም የስራ ቋንቋ የከተማው ህዝብ የሚግባባበትና በአገሪቱ ህግ የጸደቀው የአማርኛ ቋንቋ ሊሆን ይገባዋል።ይህ ማለት ግን በከተማዋ ውስጥ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ቋንቋዎች አይነገሩ ማለት አይደለም።ማንኛውም ዜጋ ከጎሳው አባል ጋር እርስ በርሱ ሊግባባበት የሚችለውን ቋንቋ መናገሩ በህግ ብቻ የሚጸድቅ ሳይሆን ከቤተሰብና በትውልዱ ያገኘው ችሎታና መብቱ ነው።ኦሮሞው ከኦሮሞው ጋር ለመግባባት ኦሮምኛ ይቀለዋል፤እንደዚህም ያለው ግንኙነት ለዘመናት የቆየና ያለፉት ስርዓቶችም የከለከሉት አሰራር አልነበረም፤በወያኔ መራሹ ስርዓት ብቻም እውቅና የተሰጠውም አይደለም።ሰው ከሌላው ጋር ለመግባባት የሚመርጠው ቋንቋ ከሁኔታው ጋር የሚያየውና በግላዊ ውሳኔው የሚወስደው እንጂ በህግ ተገዶ የሚከተለው መሆን የለበትም።ብዙ ማህበረሰብ በሚኖርበት አገር ውስጥ የአንድ ማህበረሰብ ተወላጅ የሆነ ዜጋ በራሱ የጎሳ ቋንቋ ቢናገር ከጎሳው ተወላጅ በስተቀር ከሌላው ጋር ሊግባባ አይችልም፤ስለሆነም የሚግባባበት የጋራ ቋንቋ መኖሩ ችግሩን ያቃልልለታል።በታሪክ አጋጣሚ የሁላችን ቋንቋ የሆነው አማርኛ በሌሎቹ ማህበረሰብ ተወላጆች ላይ በግድ የተጫነ ሳይሆን በህብረተሰቡ ቅልቅልና መስተጋብር ሂደት ቃላት እየወረሰ ያደገና የተስፋፋ ቋንቋ ነው።
በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ የተወለደ የየትኛውም ማህበረሰብ ተወላጅ ኦሮምኛ ለመናገር ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።ይናገረዋልም።የሌላውም በሌላውም ቦታ እንዲሁ ነው።የሁሉም ቅልቅል በሚኖርባትም የአዲስ አበባ ከተማ ኑዋሪ በሚያግባባው የጋራ ቋንቋ በአማርኛ መናገሩ ሊሻርና ሊገደብ አይገባውም።በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በተቀሩት ክፍለሃገር ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ከየማህበረሰቡ የተውጣጣ በመሆኑ አንድ ቋንቋ አማርኛ መናገራቸው ከነጠላ ጎሰኝነት አጥር ውስጥ ፈልቅቆ ሊያወጣቸው ችሏል ለወደፊቱም ይችላል።የከባቢ ቋንቋ ብቻ ይነገር ከተባለ ከሰማንያ በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ሳይግባቡ ይኑሩ ብሎም በቋንቋቸው ተዋረድ የየራሳቸውን ክልልና መንግስት አቋቁመው እርስ በርሳቸው እየተጋጩና እየተዋጉ ይለቁ ብሎ መፍረድ ይሆናል።አዲስ አበባም ውስጥ የሚኖሩት አማራና ኦሮሞ ብቻ ስላልሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ አባል የጎሳዬ ቋንቋ የአስተዳደሩ ቋንቋ ይሁንልኝ የማለት ጥያቄ እንዲያቀርብ በር ይከፍታል። ወያኔና ግብረአበሮቹም የሚወጡት የሚወርዱት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ብሎም በአጠቃላይ በአገራችን ኢትዮጵያ በዚህ አይነቱ ዘዴ ትርምስምስ እንዲመጣ ለማድረግ ነው።በትርምሱ የሚያልቀው የፈረደበት ህዝብ ነው።እነሱ ቤተሰባቸውን ይዘው ቀድሞ ወዳዘጋጁት አገር ይሾልካሉ፤ቀድመውም የሾለኩና ያሾለኩ ብዙ ናቸው።።የደርግ መሪዎች የመጨረሻው ታሪክ ትዝ ሊለን ይገባል።የወያኔና ተባባሪዎቹ ገንዘብና ንብረት በውጭ አገር ማካበታቸው የሚታበል አይደለም።ህዝቡን ኦሮምኛ፣ትግርኛ… ተማር፣ተናገር እያሉ ሲያስጨንቁት ልጆቻቸውን ግን በሚሸሹበት አገር ችግር እንዳይገጥማቸው በከፍተኛ ወጭ በቤትና በውጭ አገር ት/ቤቶች ቋንቋ ያስተምራሉ። ሁለትና ሶስት የውጭ አገር ቋንቋ የማይናገር የባለስልጣን ልጅ ተፈልጎ አይገኝም።
የኦሮሞን ተወላጅ ጥቅም ለማስከበርና ለተጎዳው ካሳ መክፈል የሚለው የማታለያ ስልት ዕድሜን ከማራዘም ሌላ ትርጉም የለውም።በአዲስ አበባ መሬቱን የተነጠቀውና የተፈናቀለው ኦሮሞው ብቻ አይደለም።ከተማዋ ከተቆረቆረችበት ጀምሮ ለብዙ ዓመታት ከአያት ቅድመአያት ሲወርስ ሲወራረስና ገዝቶ ቤት ሰርቶ የኖረውም ኦሮሞ ያልሆነው ዜጋ የጥቃቱ ሰለባ ሆኗል።ወያኔና የሱ ባለሟል የሆነው የከተማዋን አስተዳደር በመያዝ መሬቱን እየነጠቀ ለከበርቴዎች በመሸጥ የባለስልጣኖች የገቢ ምንጭ ያደረገው ኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት( ኦፒዲኦ) የተባለው በኦሮሞ ህዝብ ስም ስልጣን ይዞ መልሶ ኦሮሞውን የሚያጠቃውና የሚያስጠቃው ቡድን ነው።ካሳ መክፈልም ያለበት ይኸው ድርጅትና የገበያው ሸሪኮቹ ናቸው። ካሳ ይከፈል ከተባለ ደግሞ መሬቱን የተነጠቀውና ቤቱ የፈረሰበት፣መጠለያ አጥቶ ለመከራ የተጋለጠውንና ጥቂት የገንዘብ መደለያ እንዲቀበል ተገዶና ተታሎ መሬቱ ለከፍተኛ ዋጋ የተሸጠበት ያዲስ አበባ ኑዋሪ ሁሉ ይመለከተዋል።በሌሎቹም ያገሪቱ ከተማዎች ተመሳሳይ ግፍ የተፈጸመ ሲሆን የካሳ ጉዳይ ከተነሳ በተመሳሳይ መንገድ ተግባራዊ ሊሆን ይገባዋል።
ቋንቋን በተመለከተ ኦሮምኛም ሆነ የሌሎቹ ቋንቋዎች ማደግ ተገቢ ነው ።ሌላው ቀርቶ የውጭ አገር ቋንቋዎች የሚሰጡበት ትምህርት ቤት በተከፈተበት ከተማ የኦሮምኛም ሆነ የሌሎቹ አገር በቀል ቋንቋዎች ትምህርት ቤት መክፈቱ ለቀና ዓላማ እስከሆነ ድረስ ጉዳት የለውም።የፈለገ ሰው ጎሳው ሳይታይ ሊከታተለው ይችላል።ለአማራውም ሆነ ለሌላው ኦሮሞ ላልሆነውም ቢሆን አማርኛ ከማይችለው ኦሮሞ ወገኑ ጋር የሚግባባበትን ዕድል ከፍ ያደርግለታል።ጥንቃቄ የሚያሻው ነገር የተገንጣዮች ዓላማ መሳሪያ እንዳይሆን መከላከሉ ነው።እውነት ለኦሮሞ ህዝብ የሚያስቡለትና የአፍላቂነት ችሎታ ቢኖራቸው ኖሮ ከነጮችም ተጽእኖ እንዲድን ቢፈልጉ ኖሮ የላቲን ፊደላትን አምጥተው ባልጫኑበት ነበር። ለኦሮሞ ህዝብ አዲስ የፊደል ባለቤት ባደረጉትና ሁላችንም ኢትዮጵያኖች የምንኮራበት ተጨማሪ እሴት እንዲኖረን ባደረጉ ነበር።የጠባብ ጎሳ ምሁራን ግን ቆምንለት ያሉትን ወገናቸውን ለውጭ አገር ባዕዳን ተጽእኖ በቋንቋው ጀርባ አሳልፈው ሰጥተውታል።እነሱ ግን አማርኛን ከአማራው በላይ እየተናገሩ በስልጣኑ ላይ የተቀመጡ ነበሩ፤ናቸውም።የቀና ልብ ባለቤቶች ቢሆኑማ ኖሮ ልዩነትን የሚፈጥሩ ነገሮችን እያጠፋ አንድነትን በሚያመጡት ላይ ማተኮር በቻሉ ነበር።የዓለም ህዝብ ሊግባባ የሚችልበትን ቋንቋ በፍላጎቱ እየተማረ ካገሩ ወጥቶ እየተግባባ ሲኖር የአንድ አገር ህዝብ የሚግባባበትን ቋንቋ እንዲጠላና በጎሳው ቋንቋ እየተናገረ እንዳይግባባ ማድረግ ጸረ አገር ብቻ ሳይሆን ጸረ ህዝብ አሰራር ነው።
የአዲስ አበባን አስተዳደር በሚመለከተው ዙሪያ የወጣውን መመሪያ ከሌሎቹ የሰለጠኑ የዓለም ከተማዎች አሰራር ጋር ሲነጻጸር የሌሎቹ በጎሳ ዙሪያ የተቀነባበረና የተዘጋጀ ሳይሆን የከተማው ነዋሪ የሚሳተፍበትና ብሎም የአገሪቱ ዜጋ ሁሉ የሚጠቀምበት ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።አስተዳደሩም የሚመሰረተው ከጎሳ አንጻር ሳይሆን የፖለቲካ ድርጅቶች በፍልስፍና ላይ በተመሰረተ መርሃ ግብር አኳያ በምርጫ ወቅት ባገኙት የህዝብ ድምጽ መጠን አንዱ ብቻውን ወይም ከሌሎቹ ጋር በጥምር ሁሉም የሚካፈልበትና የሚጠቀምበት አስተዳደር ይቋቋማል እንጂ አንዱን ነጠላ የጎሳ ማህበረሰብ ብቻ በሚጠቅም ሌላውን በሚጎዳ፣ባይተዋርና ባዳ በሚያደርግ እኩይ ጽንሰሃሳብ የሚመራ አስተዳደር አይመሰረትም።
በጣም የሚያስፈራውና የሚያሳስበው ነገር አዲስ አበባ የኦሮሞም ዋና ከተማና የአገሪቱም ዋና ከተማ እርስ በርሱ በሚቃረን በክልላዊነትና በአገር አቀፍነት መልክ ሆና መቅረቧ በሁለት የተለያዩ አስተዳደሮች በጥቅም ፍጥጫና ግጭት ለመፈራረስ በሚያስችል ተንኮል እንድትዋቀር ማድረጉ ነው። ይህንን አደገኛ በማር የተጠቀለለ መርዝ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውና የሚኮራው፣ለኢትዮጵያም አንድነት ህይወቱን ለመስጠት ወደ ዃላ የማይለው፣የጎሳን ፖለቲካ አንቅሮ የተፋውና የሚቃወመው የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወላጅ ከሌላው ማህበረሰብ ተወላጅ ጋር ተባብሮ ሊከላከለው ይገባል።በህብረት የመሰረታትን አገሩን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በቅድሚያ ምሰሶ የሆነችው አዲስ አበባ በጎሰኞች የተቀነባበረ ሴራ ለመፈራረስ ስትዘጋጅ በዝምታ ሊያየውና ሊያልፈው አይገባም።አሁን በተለያዩት በሰሜኑና መካከለኛው ያገሪቱ ክፍለሃገራት በተለይም በጎንደርና አካባቢው የተቀጣጠለውን ህዝባዊ ትግል ለመቅጨትና የአማራውን ማህበረሰብ ለማጥፋት የታቀደውን ዘመቻ ከኦሮሞው ኢትዮጵያዊው በኩል ተቃውሞና ከህዝቡ ትግል ጋር ተሳትፎ እንዳይኖረው ለማድረግ የተሸረበ ሴራ ነው።
«ከጠላት የጎረሱት በሶ ይወጣል ደም ጎርሶ» ነውና ወያኔና ግብረአበሮቹ የሚወረውሩት አሳሳች የጥቅም ፍርፋሪ የኦሮሞን ማህበረሰብ ከኢትዮጵያዊነት የሚነጥልና የሚያስጠቃ፣ተባብሮ በመታገል የእድገትና የእኩልነት ባለቤት ሊሆኑ ከሚችሉበት ሰልፍ ውስጥ የሚነጥል ስለሆነ« እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል» እንዳለችው አስተዋይ ጥንቸል የማዘናጊያውን መርዝና አደጋውን ተባብሮ ማክሸፍ ይኖርበታል።
ሌላው የአዋጁ አስፈላጊነት ወያኔና ግብረአበሮቹ ለገጠማቸው ውጥረት ማስተንፈሻና ምናልባትም በውጩ ግፊት ለውይይት ከተገደዱ ከጠንካራ አክራሪ አቋም(from a strong position) በመነሳት ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ የሚረዳቸው ስልት አድርገው ሊጠቀሙበት በማሰብ ይሆናልና ከወያኔ ጋር ተደራድረን ለውጥ እናመጣለን ብለው የሚያስቡ ከወዲሁ ምኞታቸውን እንዲያጤኑት ያስፈልጋል።ወያኔ ቀለሙን እንጂ ውስጣዊ ምንነቱን የማይቀይር እስስት መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።
በተቃዋሚውም ጎራ ከወያኔ ጋር ለመደራደር የሚሹ እንዳሉ አይካድም።ከነዚያም ውስጥ የኦነግ መሪዎች ለተመሳሳይ ዓላማ ስማቸውን ቀይረው በተመሳሳይ የጎሳ ስብስብ መልክ ተደራጅተው የመጡ ስለሆነ ለዳግመኛ የስቃይ ኑሮ ላለመዳረግ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጸረ ወያኔ ከሚያደርገው ትግል ጋር የነዚህንም ስብስብ ሊታገለው ይገባል።ወያኔን ተሸክመው አምጥተው ላለፉት 27 ዓመታት የስቃይና የመከራ ስርዓት እንዳሰፈኑት ሁሉ ለሌላ 27 ዓመታት ተመሳሳይ ስርዓት እንዳይጭኑበት ተባብሮ ወግዱ ሊላቸው ይገባል።የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚሉት ፈሊጥ አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ላይ አይሰራም።ትግሉ አገር የማዳን ስለሆነ አደጋውም በጎሰኞች ምክንያት የመጣ ስለሆነ ከነሱ ጋር ምንም አይነት የዓላማ አንድነት አይኖርም። ዓላማችንና ተልእኳችን ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያን የማዳን ሊሆን ይገባዋል።ያ ደግሞ በጎሳ ለተደራጀ ድርጅት አለርጅኩ ነው። በኢትዮጵያዊነታቸው የማያወላውል አቋምና ታሪክ ያላቸው ብዙሃን ስለሆኑ ድሉ የማታ ማታ የነሱ ይሆናል። እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም ነበር።
የወያኔንና የግብረአበሮቹን አደገኛ ስልት ተባብረን እናክሽፍ።
አገሬ አዲስ
No comments:
Post a Comment