Friday, June 2, 2017

በሲያትሉ ጉባኤ በፕሮፌሰሩ የተብጠለጠለው አፄ ቴዎድሮስ ነው [ቬሮኒካ መላኩ]




… ሌላው በሲያትሉ ጉባኤ በፕሮፌሰሩ የተብጠለጠለው አፄ ቴዎድሮስ ነው ። ክሱ የሚለው ቴዎድሮስ አምባገነን ስለነበር ህዝብ ጠላው ይላል ። ፕሮፌሰሩ ከ 150 አመታት በፊት የነበረው ቴዎድሮስ “ዴሞክራት ” እንድሆን ጠብቀው ነበር መሰለኝ ። አስቂኝም አስገራሚም ነው።
በዚሁ ወቅት እኮ ስልጡን የነበረችው ፈረንሳይ ጊሎቲን የተባለ አንገት የሚቀላ ማሽን ፓሪስ አደባባይ አስቀምጣ ህዝቡን እንደ ሸንኮራ የምትቀላ አገር ነበረች ። አሜሪካ በዚሁ ዘመን አካባቢ አገሪቱን ለመገንባት በእርስ በርስ ጦርነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝቧን ቅማለች ።
እስኪ አፄ ቴዎድሮስ ከሞተ ከ50 አመታት በኋላ ስለነበረው የሩሲያ መሪ ጆሴፍ ስታሊን እናውራ ።
በ1879 ዓ.ም ጐሪ በተባለች የጆርጂያ የገጠር ቀበሌ የተወለደው ስታሊን
ከሌኒን ሞት በሁዋላ የኮሙኒስት ፓርቲውን የዋና ፀሐፊነት ስልጣን ተቆጣጠረ። ስታሊን ስልጣን ላይ እንደወጣ ተፎካካሪና ተቀናቃኞቹን የነበሩትን ስመጥር የሶቪየት ህብረት ግንባር ቀደም ታጋይ አብዮተኞች እና ህዝቡን ጨፈጨፈ ።
በ1940 ዓ.ም ትሮትስኪን ወደር በሌለው ጭካኔ ሜክሲኮ ድረስ ቅጥረኛ በመላክ በመጥረቢያ አስፈልጦ አስገደለው። በሚሊዮን የሚቆጠር ሩሲያዊ ድራሹ ጠፋ የተረፈውም ወደ ሳይቤሪያ እየተላከ በበረዶ ማጎሪያዎች ተቀፈደደ ።
ለድፍን ሠላሳ አንድ አመታት አንድ መቶ ስልሳ ሚሊዮን የሆነውን የሶቪየት ህብረትን ህዝብ ወደር በሌለው ጠንካራ የብረት ክንድ ሰጥ ለጥ አድርጎና አንቀጥቅጦ ገዛው ።
ጆሴፍ ስታሊን አምባገነን የነበረ ቢሆንም ለአገሩ የነበረው ፍቅር ወሰን አልነበረውም። ሩሲያን ከሃያላን አገሮች የፊት መስመር እንድትሰለፍ ያደረገ መሪ ነበር ። የሩሲያን ድንበር አልፎ ግዛቱ የገባውን የናዚ ጦር እንክትክቱን እያወጣ በርሊን አድርሶ የሰባበረው የጆሴፍ ስታሊን ቀይ ጦር ነው። የአለምን የሃይል ሚዛን የቀየረውን ሁለተኛው የአለም ጦርነት በማሸነፍ ሩሲያን ሃያል እና ተፈሪ አገር አደርጓል ።

የመጀመሪያ ልጁና የአብራኩ ክፋይ ያዕቆብን በሁለተኛው የአለም ጦርነት በናዚ አገሩ ስትወረር “አባትህ አገርህ ነው እንጅ እኔ አይደለሁም ” በማለት በወታደርነት ዘምቶ አባት አገር ሩሲያን ከጠላት እንድከላከል ላከው ።
ያእቆብ ከወራሪ ናዚወች ጋር ሲዋጋ በጀርመኖች ተማረከና ተገደለ ።በእነ ያእቆብና ብዙ ሺዎች ሩሲያውያን መስዋእትነት አለም ከናዚ ጭፍጨፋ ዳነች ።
ዛሬ ሩሲያ ሞስኮ ውስጥ የስታሊን ሃውልት አምሮና ደምቆ ይታያል ። ሩሲያኖች መሪያቸው አምባገነን እንደነበረ እና ሚሊዮኖችን እንዳስጨፈጨፈ እያወቁም አገራቸውን ታላቅ አድርጓታል እና ያከብሩታል ።

ስታሊንን እና ሩሲያውያንንን ማንሳቴ ምኒልክ ገደለን ቴዎድሮስ ፈለጠን እያሉ ለሚነፋረቁ የኢትዮጵያ ልሂቃን አብነት የሚሆኑ ከሆነ ብዬ ነው። ቴዎድሮስ ቆረጠም ፈለጠም ከተባለ የእኛዎቹን ( የአማራ) ቅደመ አያትና ምንጅላት ነው ። ይሄን ያደረገው አገር ቀና እንድል እና እንድገነባ ነውና መይሳውን እንረዳዋለን ። ስታሊን ለአገሩ ለሩሲያ ልጁን ያእቆብን መስዋእት አደረገ አፄ ቴዎድሮስ ደሞ ለአገሩ ለኢትዮጵያ አንድ ህይወቱን ሰጠ ።

No comments:

Post a Comment