Thursday, June 22, 2017

በአማራ ላይ የተሰለፉ አምስተኛ ረድፈኞች! (ቬሮኒካ መላኩ)

ሳተናው June 21, 2017 23:55      


የሰው ልጅ ታሪክ እንደሚያስረዳን አለም በመንታ ባህሪያት የተዋቀረች ትመስላለች። ሰማይ ስንል መሬት አለ። እሳት ስንል ውሃ አለ ፣ ብርሃን ብለን ጨለማ አለ ፣ አርበኛ ብለን ባንዳ አለ እንደዚህ እንደዚህ እያልን ብዙ ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን።
እነዚህ ባህሪያት መገለጫ አንዱ ሰው ነው። የሰውም ባህሪ እንደዚሁ ለየቅል ነው። በሰው ውስጥም ክፋትና በጎነት ፣ታማኝነትና ክህዴት ፣ ሁሉም ተቃርኖ አለ። በአንድ ብሄር ፣ ማህበረሰብ ፣ እንድሁም ቤተሰብ ውስጥ የአስተሳሰብ ዝምድና ከሌለ የስጋ ዝምድና ብቻውን ሰዎችን ማወዳጄት ፣ በአንድ አላማ ስር ማሰባሰብ እንደማይችል ከአንድ ማህበረሰብ ብሎም ቤተሰብ የተገኙ ልጆች እርስ በርሳቸው ሲቆራቆሱ እና ሲጨራረሱ የአለም የትግል ታሪክ ያስተምረናል።
ሰሞኑን ከአማራው አብራክ እየወጡ ራሱን አማራውን ከጀርባ በጦር የሚወጉትን ቡድኖች ወዳጄ ዶ/ር GM Melaku “ዋለልኞች” ብሎ ስም አውጥቶላቸዋል። እኔ በበኩሌ ከስፔኖች ተውሼ “አምስተኛ ረድፈኞች ” በማለት ልሰይማቸው።
ዛሬ በወዳጄ በ GM Melaku ስያሜ መሰረት “ዋለልኞች” በእኔ አጠራር ደሞ ስለ አምስተኛ ረድፈኛ አጠር አድርጌ ልፅፍ ነው። ይችን አጠር ያለች ጦማር መፃፍ ያስፈለገኝ ከሁሉም በላይ የአማራ ብሄርተኝነትን ደንቃራ እና ጋሬጣ ሆኖ እየጎዳው ያለው ” አምስተኛ ረድፈኛ ” የሚባለው ቡድን ነው ብዬ ስላመንኩኝ ነው። አማራን የሚጎዳው በይፋ በጉያቸው ሾተል ፣በጭናቸው ክላሽንኮቭ በያዙ ጠላቶቹ ብቻ ሳይሆን ከጉያው በወጡ የወዳጅ ጠላትም ጭምር ነው።
አምስተኛ ረድፈኛ ማለት ፤ አንድ በሚስጥር የተደራጀ ቡድን ወይም ግለሰብ ሲሆን ፣ ለጠላት በመወገን የራሱን ሕዝብ ጥቅም በማንኛውም መልኩ ከመሀል ሆኖ የሚቦረቡር ማለት ነው።
እንደዚህ ዐይነቱ ጠላት ደግሞ ከለየለት የውጭ ጠላት የበለጠ አደገኛ ነው። ለዚህም ነው አማራ ሲተርት “ፈጣሪዬ እኔ ከጠላቶቼ እራሴን ስከላከል አንተ ከወዳጅ ጠላት ጠብቀኝ” ተብሎ የሚፀለየው።

አምስተኛ ረድፍ የሚለው ሀይለ ቃል በመጀመሪያ ለውስጥ ቦርቧሪዎችን ለመግለፅ የተጠቀመው ስፔናዊው የፋሽስት ጀኔራል ሞላ ነው። ከ1936 እስከ 1939 በተካሄደው የስፓኝ የርስ በርስ ጦርነት ጊዜ ማድሪድ ስትከበብ ፋሽስቱ ጀነራል ሞላ በውስጥ አርበኝነት ስለሚያገለግሉት ደጋፊዎቹ ሲናገር “እኛ ማድሪድን በአራት ረድፍ እያጠቃናት ነው። በከተማይቱ መሃል ደሞ 5ኛ ረድፍ አለን” በማለት ከገለፀው የተወሰደ ነው።
በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክም “አምስተኛ ረድፈኛ” አማራውን ፍዳ ሲያሳየው፣ ወገኖቹን ሲያስጨፈጭፍና ፣ ለጠላት አጋልጦ ሲሰጠው ታሪክ መዝግቦታል።
አረብ ፋቂህ የተባለው የኢማም አህመድ የግል ፀሃፊ በአረብኛ “Futuh al-habasha” በማለት ፅፎት “the conquest of Abyssinia” በሚል ርእስ ወደ እንግሊዚኛ የተመለሰው መፅሃፍ እንደሚከተለው ያለ “የአምስተኛ ረድፈኞች ” አሰቃቂ ድርጊት ተመዝግቦ አንብቤአለሁኝ … …
“ኢማም አህመድ ጠንካራውንና የማይደፈረውን የአምባ ግሸን ምሽግ ለመስበር ብዙ ሞከረ። እዚህ ምሽግ ውስጥ የሰለሞናዊ ስርዎ መንግስት የነጋሲ ልጆች፣ የልጅ ልጆች፣ ዘመዶች እና ብዙ ሀብት ይገኝ ነበር። ኢማሙ ከቱርክ እና ከፓኪስታን በመጡ መድፍ ተኳሾች ቢሞክርም የክርስቲያኖቹ አምባ የማይደፈር ሆነ። ወታደሮቹም አለቁበት። 3 ወር ሙሉ አምባ ግሸንን ለመስበር ሞከረ የማይቻል ሆነ። ወደ አምባው መውጫ ያለው ሁለት በር ብቻ ስለነበር በሩን ይዘው አልበገር አሉ። በመጨረሻ ኢማም አህመድ (ግራኝ) የአምባ ግሸንን ምሽግ ለመያዝ በውጊያ መሞከርን ትቶ አምባው ካሉ የክርስቲያን ተዋጎዎች መካከል አምባውን አሳልፎ የሚሰጠው ከሃድ መፈለግ ጀመረ። በወርቅ እና በገንዘብ የተደለለ ሰውም ተገኘ።በዚህም መሰረት የግራኝን ጦር በስርቆሽ በር በኩል እየመራ ወደ አምባው በድብቅ አስገባቸውና የክርስቲያኑን ጦር ከጀርባ በኩል አስጨፈጨፋቸው። የአምባ ግሸንም ጠንካራ ምሽግ ተሰበረ።” እያለ ይቀጥላል። The conquest of Abyssinia. Page. 345.
ይሄ ከመፅሃፉ የጠቀስኩት ቁራጭ ታሪክ የሰዎችን፣ የከሃድያንን እርቃነ ማንነት እና የሚያደርሱትን ወሰን የለሽ ጉዳት የሚያመለክት ነው። በአገራችን ውስጥ በታሪካችን ዘርዝረን መንዝረን ሳንመለከተው እየቀረን ይሆናል እንጅ የዚህ አይነት የትውልድ አራሙቻዎች ሲከሰቱ ተስተውሏልም እንማርበትም ዘንድ ተመዝግቧል።
አሁን ከአማራ ህዝብና የአማራን ብሄርተኝነት ለመገንባት በምናደርገው ትግል “የአማራ አምስተኛ ረድፈኞች ” ምን ማለት እንደሆነ የተግባባን መሰለኝ። ያልገባው ካለም አምስተኛ ረድፈኛ ” ማለት ከአማራ ህዝብ አብራክ ወጥተው አማራን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡ ፣ ከጀርባ የሚወጉ ( backstabbers) የአማራን ለምድ ለብሰው እንደ ተኩላ የሚተውኑ ማለት ነው።
አስተውላችሁ ከሆነ እነዚህ አጎብጓቢ ረድፈኞች ሲፅፉም ሆነ ንግግር ሲጀምሩ እንድህ በማለት ይጀምራል… “እኔ አማራ ነኝ ነገር ግን በብሄር መደራጀት አላምንም።” ይላሉ። ይች የአነጋገር ዜዬ መለያ ባህሪያቸው ናት። ለእኔ አደገኛው ይሄ ነው። እነዚህ ሰዎች “አማራ ነኝ” ብለው ይጀምሩና “በብሄርም መደራጀት አላምንም ” ብለው ድስኩራቸውን ቀጥለው የኦሮሞውን፣ የሱማሌውን፣ የትግሬውን፣ የወላይታውን፣ የ80 ውን ብሄር መደራጀት ችግር የለውም ብለውን እርፍ ይላሉ የአማራውን መደራጀት ግን በርበሬ እንዳጠኑት ልጅ ሲያስነጥሳቸው ይውላል።
ከ 500 አመታት በፊት ጠላቶቻችን ፈ ት ለፊት ተጋፍጠው ማሸነፍ ስለማይችሉ እየተጠቀሙ ያሉት በዚህ “በአምስተኛ ረድፈኛው” ቡድን በኩል ነው።
የአማራ አምስተኛ ረድፈኞች የሚሰሙኝ ከሆነ ጥቂት ምክር ቢጤ ጣል ላድርግና ፅሁፌን ልዝጋው። ረድፈኞች ከእናንተ ጋር የአንድ ቤተሰብ እና የአንድ ወገን ልጆች ብንሆንም በአስተሳሰብ አንገናኝም። የአንድ ክልል ፍሬ ብንሆንም ጎራችን ለየቅል ነው። የአንድ ወጥ ባህል ልምድና አካባቢ ውልዶች ብንሆንም ግባችን የተለያየ ነው። ባንድ መልክ ያደግን ብንሆንም በተዥጎረጎረ ባህሪይ ጎልምሰናል። ለእኔ የሚጣፍጠኝ ለአንተ ይመርሃል። ለእኔ የሚጥመኝ አንተን ያቅርሃል። ህዝባችን ያለበት አስከፊ ሁኔታ ቆራጥነትን የሚጠይቅ ሌላው ቀርቶ ከአንድ አብራክና ከአንድ መሀፀን የተገኙትን የአንድ አባትና የአንድ እናት ልጆች የሚያታግል ነው። ነፃነት የሚባለውን ክቡር ነገር ለማግኘት ጠላትን ብቻ ሳይሆን የወዳጅ ጠላትንም መፋለም የግድ ይላልና ትግላችን “ከአምስተኛ ረድፈኞች” እና “ዋለልኞች “ጋርም መሆኑ መታወቅ አለበት።

No comments:

Post a Comment