በተመሳሳይ ዜና የንቅናቄው ሰኔ 4 ቀን 2009 ዓ/ም፣ ከቀኑ 5:00 ሲሆን በጭልጋ ወረዳ ሹታራ ቀበሌ ወደ ሚገኘው የኮማንድ ፖስት ጽ/ ቤት ሰርገው በመግባት የአካባቢውን ህብረተሰብ አፍነው በማምጣት የሚያሰቃዩበት አስር ቤት እና እንደ ጽ/ቤት የሚገለገሉበት ክፍል ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውን ድርጅቱ ገልጿል።በጥበቃ ላይ የነበሩ ፖሊሶች ራሳቸውን ለማዳን መሸሻቸውን ታጋዮችም በሰላም ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ባለፈው ባለፈው ቅዳሜ፣ ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም አንድ የአርበኞች ግንቦት 7 የአዲስ አበባ ህዋስ አዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ከቀድሞ ናዝሬት አውቶቡስ ተራ አጠገብ የሚገኘውን የህወሓትን የድብቅ ማሰቃያ ቦታ እና የመሣሪያ ማከማቻ ማውደሙን ድርጅቱ ገልጿል። ቦታው ቀደም ባሉ ዓመታት የጉምሩክ መጋዘን ሆኖ ያገለግል እንደነበር የገለጸው ድርጅቱ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቦታው ለፌደራል ፓሊስ የመሣሪያ ግምጃ ቤትነትና በስውር ማሰቃያነት እያገለገለ ነበር ብሎአል።
“በርካታ ወገኖቻችን ዓይኖቻቸው እየታሰሩ ወደዚህ ቦታ እየተወሰዱ ስቃይ (ቶርቸር) እንዲደርስባቸው በመደረጉ ለዘላቂ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ተዳርገዋል” ፣ ያለው ንቅናቄው፣ “በዚህ ግቢ ውስጥ በርካታ ወንድና ሴት እስረኞች እጅግ አሰቃቂና ኢሰብዓዊ በደል ተፈጽሞባቸዋል። በዚህ ግቢ ውስጥ በደሰረባቸው ስቃይ ምክንያት ዘር ማፍራት እንዳይችሉ የተደረጉ ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው። ህይወታቸው ያለፈው ዜጎች ቁጥርም በርካታ ነው። በዚህ ፀረ ትውልድ እና ፀረ ኢትዮጵያ ተቋም ላይ” የአርበኞች ግንቦት 7 የአዲስ አበባ ህዋስ እርምጃ ወስዷል ብሎአል።
በተወሰደው ጥንቃቄ የተሞላበትና የተጠና እርምጃ ሳቢያ በግቢው ውስጥ የነበሩ መጋዘኖች ከነመሣሪያዎቻቸው በእሳት እንዲጋዩ መደረጉን የሚገልጸው ድርጅቱ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ የተወሰደውን እርምጃ በዓይኖቹ እንዲያይና በህወሓት አምባገነን አገዛዝ የሚደርስበት ስቃይ ቁጭት እንዲወጣ እድል የፈጠረ እርምጃ ነበር ብሎአል። በተወሰደው እርምጃም የፌደራል ፓሊስ አባላት የህቡዕ እርዳታ ማድረጋቸውን ገልጿል።
ለወደፊቱም ተመሳሳይ እርጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ የአርበኞች ግንቦት 7 የአገር ውስጥ ህቡዕ አመራር ገልጾ፣ እያንዳንዱ አገሩንና ነፃነቱን የሚወድ ዜጋ በየተሰማረበት መስክ ሥርዓቱን የሚያዳክሙ የሕዝባዊ እምቢተኝነትና የሕዝባዊ አሻጥር እርምጃዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል።
በጥቃቱ ዙሪያ ከገዢው ፓርቲ በኩል የተሰጠ መልስ የለም።
ኢሳት ዜና
No comments:
Post a Comment