Thursday, June 29, 2017

በአማራ ሕዝብ ትግል ውስጥ የብሔርተኝነትና የጽንፈኝነት አቋም እጅግ አስፈላጊነት! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

 


  
By ሳተናውJune 28, 2017 23:39



ከዓመታት በፊት ጀምሬ ባቀረብኳቸው ጽሑፎች ሊያከራክር በማይችል መልኩ የምዕራቡን ዓለም ሐሳብ ላይ እንጅ የዘር ልዩነት ወይም ብሔረሰብና ጎሳ ላይ ያልተመሠረተን የሠለጠነ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ተሞክሮ እንዲሁም የ26 ዓመታቱን የወያኔን አገዛዝ ተሞክሮዎችን በማነጻጸር ግልጥልጥ አድርጌ በማሳየት የዘር ልዩነት ላይ ወይም የጎሳና ብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ አደረጃጀትን ተፈጥሯዊ ኢዲሞክራሲያዊነት (ኢመስፍነ ሕዝባዊነት) ፣ ኢሰብአዊነት፣ ኃላ ቀርና ጠባብነት፣ ፀረ የሀገርና የሕዝብ አንድነት መሆንን ሳስረዳ መቆየቴ፤ ከጊዜ በኋላም አማራ በማንነቱ የተደራጀው አማራነቱ እንደወንጀል ተቆጥሮበት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ስለተዘመተበት ህልውናውን ለመታደግ እንጅ እንደሌሎቹ ጎሳና ብሔረሰብ ተኮር ጅርጅቶች ጠባብ ለመሆንና የሀገርን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል አለመሆኑን በሚገባ አስረድቻለሁና እዚህ ላይ ደግሜ ማብራራት አይጠበቅብኝም፡፡
አማራ በማንነቱ ስለመደራጀቱ፣ ስለ አማራ ብሔርተኝነት፣ ዛሬ ስለአስፈላጊነቱ ስለምገልጽላቹህ ስለ አማራ ጽንፈኝነት ቃላቶች (Terms) ስናሰማ በርካታ ሰዎች እነኝህን ቃላቶች ወይም ፅንሰ ሐሳቦች የሚረዱት የቃላቶችን ፅንሰ ሐሳብ ሌሎቹ የጎሳና ብሔረሰብ ድርጅቶች በሚያራምዱት አስተሳሰብና መረዳት እየታየብን የአማራ ሕዝብ ህልውናን የመታደግ ትግል ችግር ገጥሞታል፡፡ ይህ ችግርም እኛ የአማራን ህልውናውን ከፈጽሞ ጥፋት የመታደግ ትግልን ከማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር እንደሚጠበቀው ሁሉ ከአማራ ውጭ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲደግፉት ስንጠብቅ ጭራሽ አማራ የሆኑትም ትግሉን እንዳይቀላቀሉ እያደረገብን ይገኛል፡፡
ይህ በአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲያዝና ትግሉ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይጋጋል በማድረጉ እረገድ ሦስት አራት የሚሆኑ በአማራ ስም የተደራጁ የወያኔ ቅጥረኛ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ እነኝህ ሐሰተኛ የአማራ ድርጅቶች የአማራ ብሔርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ፅንሰ ሐሳቦች ሌሎች የጎሳተኮር ድርጅቶች በሚያራምዱት አስተሳሰብ ዓይነት እንዲታይበት አድርገዋል፡፡ እርግጥ ነው እነኝህ ቅጥረኛ ድርጅቶች የአማራ ሕዝብ በጥፋት ኃይሎች እየተወሰደበት ያለው እርምጃ አንሶት እራሱን በራሱ ሊያጠፋ በሚችልበት የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ለማስመጥ የቅጥረኝነት ዓላማቸውን ለማስፈጸም አሳቢ ተቆርቋሪ መስለው እየሠሩት ያሉትን ዕኩይ የባንዳ ሥራ፣ ከአማራ ሥነልቡናና ማንነት ጋር ተቃርኖ ያለው አስተሳሰብ በአማራ ሕዝብ ዘንድ በመታወቁ የሕዝብ ተቀባይነትን ሊያገኙ ባለመቻላቸው ከእንግዲህ ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ላይ ሲወራጩ እናያቸው ካልሆነ በስተቀር በሕዝብ ልብ ላይ ቦታ የላቸውምና የሚያንፀባርቁት አስተሳሰብ ፈጽሞ ከአማራ ሕዝብ የፈለቀ ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም፡፡
በዚህ ጽሑፍ ላይ የአማራ ሕዝብ ትግል እንዴትና ለምን በብሔርተኝነትና በጽንፈኝነት መመራት እንዳለበት፣ የአማራ ብሔርተኝነትና ጽንፈኝነት እንዴትና በምን ከሌሎቹ የጎሳ ብሔረሰብ ተኮር ድርጅቶች እንደሚለይ እናያለን፡፡ እያወራን ያለው አማራ በአማራነቱ ብቻ በጥፋት ኃይሎች እንዲጠፋ ታውጆበት ተፈጻሚ እየተደረገበት ካለው ኢሰብአዊ ጥቃት እራሱን መታደግ ስለሚችልበት ጉዳይ ነው፡፡ ልብ በሉ ለአማራ መጠቃት መንስኤ የሆነው ማንነቱ ወይም አማራነቱ ነው፡፡ ለአማራ መጠቃት መንስኤ የሆነው አማራነቱ ከሆነ እራሱን ለማዳን ከአጥቂዎቹ ሲከላከል የሚከላከለው አማራነቱን ማለትም ባሕሉን፣ ወጉን፣ ሥርዓቱን፣ ሃይማኖቱን፣ አስተሳሰቡን፣ ፍልስፍናውን፣ ሥልጣኔውን፣ ቅርሱን፣ ማንነቱን አጠቃላይ እሴቶቹን ነው ማለት ነው፡፡ ብሔርተኝነት ማለት ይሄ ነው ሌላ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ጤነኛ ያልሆነ ብሔርተኝነትም አለ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት እንደዚያ አይደለም፡፡ አማራ ብሔርተኛ ሳይሆን ለእነኝህ እሴቶቹ ሊቆጭ ሊቆረቆር ሊታገል አይችልም፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ማለት ለእነኝህ እሴቶች ተጠብቆ መኖር አስፈላጊውን ዋጋ ለመክፈል መነሣሣት ማለት ነው፡፡ አማራ ለመጠቃቱ ምክንያት ስለሆነው ስለአማራነቱ ሳይቆጭ ሳይንገበገብ (ብሔርተኝነት ሳይሰማው) ሊታገልና እራሱን ከጥፋት ሊታደግ አይችልም፡፡ የአማራን ብሔርተኝነት ከሌሎቹ የሚለዩት አምስት ዋና ዋና ነጥቦች አሉ፦
1ኛ. የአማራ ብሔርተኝነት እራሱን እየተፈጸመበት ባለው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጥቃት ፈጽሞ ከመጥፋት ለመታደግ የግድ መደረግ ያለበት በመሆኑ፡፡
2ኛ. የሀገርንና የሕዝቧን አንድነትና ህልውናን አደጋ ላይ የሚጥል፣ ለድርድር የሚያቀርብ ባለመሆኑ፡፡
3ኛ. እንደሌሎች ብሔርተኛ ኃይሎች ለሌሎች ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ይሄንን ወይም ያንን ብሔረሰብ ወይም ጎሳ በመሆናቸው ብቻ ምንም ዓይነት ጥላቻ የሌለው በመሆኑ (የጥፋት ኃይሎች የጥፋት ዓላማቸውን ለማሳካትና ለማስፈጸም አማራን በተመለከተ ብዙ እየፈጠሩ የሚያወሩት ነገር አለ፡፡ እውነታው ግን በእጅጉ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የአሥተዳደር ሥርዓት በነበረባቸው በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ያሉ የተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ቋንቋቸው፣ ባሕላቸው፣ እምነታቸው፣ ማንነታቸው በገዥዎቻቸው በኃይል እንዲጠፋ ተደርጎ የገዥዎቻቸውን ቋንቋ፣ ባሕል፣ እምነት፣ ማንነት እንዲይዙ እንዲወርሱ ሲደረጉ ማንም ማየት እንደሚችለው ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የትኛውም ብሔረሰብም ሆነ ጎሳ በኃይል እንዲጠፋ ሳይደረግበት ቋንቋውን፣ ባሕሉን፣ እምነቱን፣ ማንነቱን እንደያዘ ይገኛል፡፡ ይሄ ማለት ግን ብሔራዊ ቋንቋና ሃይማኖት ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም፣ የመናቅ ችግርም አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ መናቅ ወይም መናናቅ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ነውና የትም ሀገር ቢሆን እንኳን ጥንት ወደፊትም ይጠፋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምክንያቱ ይለይ ይሆናል እንጅ ይህ ችግር ሌላው ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ አባላት መሀከል እንኳ ያለ ችግር ነውና፡፡ ብቸኛው የትግሬ ንጉሥ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ለሚከተሉት ሃይማኖት ቀንተው ሳይሆን መጨረሻ ላይ የሚያጠፏቸው ወይም ለሕልፈት የሚዳርጓቸው እስላሞች እንደሆኑ የተነገረ ንግርት ወይም ትንቢት ስለነበረባቸው ይሄንን ንግርት ያስቀሩ መስሏቸው ወሎ ወርደው ግራኝ አሕመድ ያሰለማቸውን የወሎ እስላሞችን በኃይል ክርስቲያን ለማድረግ ከሞከሩት ድርጊት በስተቀር አንድም ንጉሥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን በኃይል እምነታቸውን ብቻም ሳይሆን ቋንቋቸውንም፣ ባሕላቸውንም፣ ማንነታቸውንም እንዲቀይሩ አድርጎ አያውቅም፡፡ ስላልተደረገ ነው አሁን ድረስ ማንነታቸውን እንደያዙ ሊገኙ የቻሉት፡፡ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ቋንቋቸው፣ ባሕላቸው፣ እምነታቸው፣ ማንነታቸው በቅኝ ገዥ እንዳይጠፋና ያልተነካካ ማንነታቸውን እንደያዙ እንዲገኙ አማራ ተነግሮ የማያልቅ መራር መሥዋዕትነትን ነው ሲከፍል የኖረው፡፡ ከዚህም በላይ ጥንታዊ ርስቱን በተለያዩ ምክንያቶች ወደሀገር ለገቡ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች አስረክቦ ተራራማ ሥፍራ የሰፈረ ቅን ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን “የግፍ ግፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ!” እንዲሉ ለዚህና ለሌላው ተነግሮ ለማያልቀው ውለታው ሁሉ አማራ የተከፈለው ዋጋ በገዛ ሀገሩ ተሳዳጅ ተባራሪ ከመሆን አልፎ ዘሩ እንዲጠፋ ማድረግ ነው፡፡)
4ኛ. ጠባብነትንና ጭፍን ወገናዊነትን ለራሱ እሴቶች ሳያሳይ እሴቶቹን የሀገር እሴት አድርጎ በማስመረጡ ሒደት ዳኝነትን ለልኅቀትና ለምሑራዊ ተዋስኦ በመስጠቱ፡፡
5ኛ. የቅጣት እርምጃውን ተጠያቂ በሆኑ አካላት ላይ ብቻ ያነጣጠረ በመሆኑ ወይም ጅምላ ጨፍጫፊ ባለመሆኑ ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል የጽንፈኝነትን መንገድ መከተሉን የግድ አስፈላጊ የሚያደርጉ አምስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦
ሀ.) ጠላቶቻችን እኛን ለማጥፋት የተነሡበት ቁርጠኝነት ጽንፈኛ በመሆኑና እሾህን በእሾህ እንዲሉ ጽንፈኛ ጥቃትን በጽንፈኛ የመከላከል እርምጃ ካልሆነ በስተቀር በልማዳዊ ወይም ለዘብተኛ አካሔድ መመከትና መከላከል ብሎም መቀልበስ ፈጽሞ የሚቻል ባለመሆኑ፡፡ ለዘብተኛው አኪያሔድ በጥይት አረር የሚፈጅን ጠላት በብትር ወይም በቆመጥ ለመመከት የመሞከርን ያህል ጅልነት ስለሆነ፡፡
ለ.) በአማራ ላይ ጽንፈኛ አቋም የያዙ የጥፋት ኃይሎች ካልጠፉ ካልተደመሰሱ በስተቀር ይሄንን ዕኩይና ጽንፈኛ አቋም ዓላማቸውን የሚተው ባለመሆናቸው፡፡ አቅም አንሷቸው ወይም ሁኔታው ሳይመቻቸው ቀርቶ የሆነ ወቅት ላይ የተዉ ቢመስሉ ምቹ ሁኔታ ባገኙ ጊዜ ይሄንን የጥፋት ጽንፈኛ ዓላማ አቋማቸውን መልሰው የሚያነሡ በመሆናቸው፡፡
ሐ.) አማራ በመሆናቸው ብቻ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን በጥፋት ኃይሎች የተፈጁ ወይም እንዲጠፉ የተደረጉ ወገኖቻችን ደም መመለስ ስላለበት ወይም ደመከልብ ሆኖ መቅረት ስለሌለበት፡፡
መ.) አማራ በተለያየ ጊዜ በሆደሰፊነት ያጣውን የተነጠቀውን ጥቅሙን እውነትን ታሪክን መሠረት ባደረገ ፍትሐዊ አሠራር መልሶ ማግኘት እንዲችል የጥፋት ኃይሎቹና ደጋፊዎቻቸው ፈጽሞ የማይፈቅዱ በመሆናቸው፡፡
ሠ.) ጽንፈኛ አቋምና ፍጹም ግፈኛ የጥቅም ፍላጎት ያላቸውን የጥፋት ኃይሎች ከስር ነቅሎ በማጥፋት ሀገራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከነዚህ የጥፋት ኃይሎችና ጠንቀኛ አስተሳሰባቸው ነጻ ማድረግ መገላገል አስፈላጊ በመሆኑ የሚሉት ናቸው፡፡
ወገን ሆይ! ወያኔንና ሌሎች የጥፋት ኃይሎችን መቃወምና አለመደገፍ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ተደራጅቶ መታገል የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም በዚያም በየቦታው ብንንጫጫ ከመንጫጫት ባለፈ ምንም ጠብ የምናደርገው ነገር የለም፡፡ በዚህም በዚያም በየቦታው መንጫጫታችንን እንደትልቅ ግብ ቆጥረን እሱላይ ብቻ ማተኮራችን ለውጥ ሊመጣ የሚችልበትን መላ እንዳናይ አድርጎናል፡፡ ሲጀመር ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔና በሌሎች የጥፋት ኃይሎች ማንነት ላይ ለአንድም ቀን ቢሆን ብዥታ ኖሮበት አያውቅም፡፡ ከማንም በላይ አሳምሮ ያውቃቸዋል፡፡ ሲጀመር የማናስተውል ሆነን ካልሆነ በስተቀር ግፉ የሚፈጸሙ በራሱ በሕዝቡ ላይ ሆኖ እያለ ሕዝቡ እንዴት አያውቅም ተብሎ ይታሰባል? የማያውቅ የመሰለው ማወቁን ማሳወቁ የሚያስበላው ስለሆነ ነው እንጅ ሕዝብ ወያኔንም ሆነ ሌሎችንም የጥፋት ኃይሎች አብጠርጥሮ ነው የሚያውቃቸው፡፡ በየቦታው እንደመንጫጫታችን ቢሆን ኖሮ ወያኔ እስከአሁን ድራሹ ጠፍቶ በነበረ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ለውጥ፣ ስኬት፣ ድል ልናገኝ የምንችለው በየቦታው በመንጫጫት ወይም ሕዝቡ የሚያውቀውን እውነት መልሰን ለራሱ በመንገር፣ በማስተጋባት ሳይሆን በኅቡዕ ወይም በስውርም በግልጽም እንደሁኔታው አመችነት ተደራጅተን የታገልን እንደሆነ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ወያኔ ባይደራጅ፣ ሕዝቤ የሚለውን አደራጅቶ ባይታገልና ደርግን እያማረረ፣ እያወገዘ በመንጫጫት ብቻ ቢቀመጥ ኖሮ ዛሬ እዚህ የደረሰበት ደረጃ ላይ ባልደረሰ ነበር፡፡
ነባራዊ ሁኔታው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ባካተተ መልኩ ውጤታማ ትግልን መታገል ባለመፍቀዱ ፈዘንና ደንዝዘን እጅግ ብንዘገይም ዛሬ ላይ ቢያንስ እንዴት መደራጀት እንዳለብን አውቀን የተደራጀንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ከተደራጀን በኋላ ግን ወያኔ ለስኬት በምንበቃበት መንገድ ላይ እንደቆምን ተረድቶ ትግላችንን ለማክሸፍ እንደ ቤተአማራ ያሉ ቅጥረኛ ድርጅቶቹን በአማራ ሕዝብ ስም አደራጅቶ ማሠማራቱ ይታወቃል፡፡ እነኝህ ቅጥረኛ ድርጅቶች ዛሬ ላይ ባወቅናቸው ደረጃ ቀደም ሲል ስላልታወቁና “የያዙትን አማራን ከኢትዮጵያ የመገንጠል የጥፋት የድንቁርናና የቅጥረኝነት አቋም የያዙት ከየዋህነትና ካለመብሰል ከሆነ እስኪ ቀርበን እንለውጣቸው!” በሚል ቅንና ኃላፊነት የተሞላበት ሐሳብ የአማራ ሕዝብ መድኅን ንቅናቄ (አሕመን) ይሄንን ውዳቂና ከአማራ ማንነት ጋር ተቃርኖ ያለውን አቋም አስተሳሰባቸውን እንደሚተው ቃል ካስገባ በኋላ ከቤተ አማራ እና ከአዴሀን ጋር ውሕደት ፈጽሞ “ቤተ አማራ መድኅን” የሚል ውሕድ ድርጅት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም የወያኔ ቅጥረኞች ናቸውና “ትተናል!” ያሉትን የደነቆረ አስተሳሰብ እንደገና በማንሣታቸውና ለወያኔ በሰላይነት ላይ ተሠማርተው በመገኘታቸው
አደጋዎችን በመጋረጣቸው ምክንያት ዓመት እንኳ ሳይሞላ ውሕደቱ ሊፈርስ ችሏል፡፡ አሕመን ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ የተጠበቀም ያልተጠበቀም ችግርና ፈተና ቢያጋጥምም ፈተና ትግል ውስጥ ከሚያጋጥሙ እንቅፋቶች አንዱና ዋናው በመሆኑ እንዲህና እንዲያ ያሉ የተለያዩ ዓይነት ፈተናዎች ቢያጋጥማቸውም የያዙት ትግል መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉና፣ ከመጋፈጥ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ጠንቅቀው ያውቃሉና ይሄና ያ ችግር ተከሰተ ወይም አለና ብለው አሕመኖች አልበረገጉም አልተፍረከረኩም፡፡ አሕመን አንድ የተጠናከረ የአማራ ኃይል እንዲፈጠር ይፈልጋል፡፡ የግድ አስፈላጊ ነውና፡፡ በመሆኑም በሒደት ላይ ያሉ የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና ለድርድር ከማያቀርቡ በአማራ ሕዝብ ስም ከተቋቋሙ የአማራ ድርጅቶች ጋር የመዋሐድ እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ስለ አሕመን ጥቂት መረጃ ለመስጠት ያህል ለአራት ዓመታት ያህል ጥልቅ ጥናት ከተደረገ በኋላ ከሁለት ዓመታት በፊት የተሟላ ሰብእና ያላቸው፣ በተቃውሞ ፖለቲካ ያለፉና ልምድ ያዳበሩ፣ ራሳቸውን ለትግሉ የሰጡና ዋጋ ለመክፈል የቆረጡ፣ በወገን ፍቅር የተቃጠሉ፣ የጠራና የበሰለ አቋም አስተሳሰብ የያዙ የተማሩና የጠነቀቁ ወጣቶች አሕመንን (የአማራ ሕዝብ መድኅን ንቅናቄን) መሥርተዋል፡፡ አሕመን ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ አባላትን በኅቡዕ ሲያደራጅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና እነኝህ የወያኔ ቅጥረኞች የያዙትን የቅጥረኝነት አቋም እንዴት የአማራን ሕዝብ ሊጠቅም እንደሚችል አብራርተው ሊያስረዱ ሊገልጹ የማይችሉትን የማይሆን፣ የማይበጅ፣ የደነቆረ የመገንጠልን ሐሳብ እየነዙ ሕዝባችን ላይ በፈጠሩት ብዥታ ምክንያት ሕዝባችንን በማንነቱ ወይም በአማራነቱ ለማደራጀት አሕመን በሚያደርገው ጥረት የሚፈለገውን ያህል የሕዝባችንን ንቁ ተሳትፎ ማግኘት ችሏል ማለት አይቻልም፡፡ በውጭ ያለውም እንቅስቃሴ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ወገን ሆይ! አሕመንን ተቀላቀሉ? ከምሁር እስካልተማረ፣ ከሴት እስከ ወንድ፣ ከሃይማኖት አባቶች እስከ ሕዝባዊ፣ ከተማሪ እስከ ሠራተኛ፣ ከነጋዴ እስከ ከያኔ ያላቹህ ሁላቹህም አማራና ኢትዮጵያዊነት ይበልጥብናል የምትሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መቀላቀላቹህ ግድ ነውና ጊዜ ሳታጠፉ አሕመንን (የአማራ ሕዝብ መድኅን ንቅናቄን) ትቀላቀሉ ዘንድ በፈጣሪ ስም በአክብሮት ትጠየቃላቹህ???
አማራን በአማራነቱ እንዲደራጅ በመደረጉም የአንድነት ኃይል ነን ከሚሉ አካላትም የሚመጣ ተቃውሞ አለ፡፡ አንድ ነገር ግን ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፖለቲካ ሰፍኖ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ኢትዮጵያዊነትን ከመጣል አልፈው ኢትዮጵያዊነትን እየተዋጉ ባሉበት፣ የሀገሪቱን አንድነትና ህልውና አደጋ ላይ በጣሉበት ወቅት፣ የሀገሪቱ አንድነትና ህልውና መሠረትና ዋልታ የሆነው የአማራ ሕዝብ እንዲጠፋ ተፈርዶበት በአራቱም አቅጣጫ ሰፊ ዘመቻ እየተወሰደበት ባለበት ወቅት የአማራ ሕዝብ ዘግይቶም ቢሆን ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ አስቀድሞ እራሱን መታደግ ቁልፉና አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተረድቶ ህልውናውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ በአማራነቱ ተደራጅቶ የሚያደርገውን ትግል መቃወም ወይም አለመደገፍ ማለት በእርግጠኝነት እነግራቹሀለሁ አማራ የሌለባት ወይም የጠፋባት ኢትዮጵያ እንድትኖር መስማማት ነው፡፡ አማራ በመጥፋቱ ውስጣቸው ደስተኛ ስለሆነ ካልሆነ በስተቀር ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራውያን) ነን ካሉ በኋላ ይሄንን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ግፍ ሊያጋልጡ፣ ሊናገሩ፣ ሊያስተናግዱ የማይችሉበት ምን ምክንያት አለ?
አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ እያደረገው ያለውን የአማራን የህልውና ትግል እየተቃወማቹህ ያላቹህ ወገኖች አውቃቹህም ይሁን ሳታውቁ እያደረጋቹህ ያላቹህት ይሄንን እንደሆነ ጠንቅቃቹህ ልታውቁት ይገባል፡፡ አማራ ያልሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ቢስማማ ላያስደንቅ ይችላል፡፡ “አማራ ነኝ!” የሚሉ ሆነው እያለ ግን አማራ የጠፋባት፣ የተወገደባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር መስማማት ወይም መፍቀድ ግን እጅግ አሳፋሪ፣ አስገራሚና የሚያቅለሸልሽ ጉድ አይደለም???
ሲጀመር በአማራ ላይ በሰፊው እየተወሰደ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚቃወም፣ የሚያወግዝና የሚያንገበግበው የአንድነት ኃይል ቢኖር እኮ አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ እራሱን ከመጥፋት ለማዳን መታገሉ አስፈላጊ ባልሆነ ነበር፡፡ የሆነውና እየሆነ ያለው ግን የዚህን ተቃራኒ በመሆኑ ነው በአማራነቱ ለመደራጀት የተገደደው፡፡ “የአንድነት ኃይል ነን!” የሚሉ ኃይሎች ከፊሎቹ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ከፈጸሙ እንደ ኦነግና ትሕዴን ካሉ የጥፋት ኃይሎች ጋር ጥምረትና አንድነት ሲፈጥሩ፤ ከፊሎቹ ደግሞ ይሄንን በአማራ ሕዝብ ላይ እየተወሰደ ያለውን በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋትና ማጽዳት የመጨረሻ ወንጀል እንኳንና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያጋልጡ ሊያስታውቁ ይቅርና ለገዛ ራሳቸው እንኳ ቢሆን ለአንድም ጊዜ ነግረውት የሚያውቁ አይደሉም፡፡ አፍነው ይዘው ነው ያስፈጁን፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር ደግሞ ጉዳዩ አሁንም እንደተዳፈነ ተፈጅተን እንድናልቅ ይፈልጋሉ፡፡
ያለው ሸፍጥ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ የአማራ ሕዝብ እንዴት ሆኖ ነው ይሄንን ሸፍጥና ግፍ በጸጋ ተቀብሎ በዝምታ ሊመለከትና ድምፅ ሳይሰማ እንዲያልቅ የሚፈቅደው??? ወይ አጀንዳውን (ርእሰ ጉዳዩን) እናንተው በአግባቡ አልያዛቹህት! ይሄንን ማድረግ ካልቻላቹህ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ተደራጅቶ የራሱን ጉዳይ እራሱ ይዞ መንቀሳቀሱን በምን ሞራላቹህ (ቅስማቹህ) ነው ልትነቅፉ፣ ልትቃወሙ፣ ልታወግዙ የምትችሉት??? ትንሽ እንኳን አታፍሩም??? ይሄ በደላቹህ ጠላት ካደረሰብን ግፍ የማይተናነስ እንደሆነ አታስተውሉም??? ኧረ ተው ተው ግፋቹህን በልክ አድርጉት??? ትንሽም ቢሆን እፍረት ይኑራቹህ???
እርግጠኛ ነኝ ዛሬ ላይ የአማራን አስገዳጅ ህልውናን የመታደግ ትግል እየተቃወሙ ካሉ አማሮች ሁሉም እንዲሁም ደግሞ ሰብአዊነትና ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው ሌላው ዜጋ ዘግይታቹህም ቢሆን ነገሩ ይገባቹህና የኋላ ኋላ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ይሄንን የአማራን ህልውናውን በመታደግ ኢትዮጵያን የመታደግ ትግል መቀላቀላቹህ ወይም መደገፋቹህ አይቀርም፡፡ ይሁንና ይሄንን መረዳት በምታገኙበት፣ በምትገነዘቡበት ወቅት ግን ወቅቱ በጣም የረፈደ ወይም የዘገየ ስለሚሆን ልትፈይዱ የምትችሉት ነገር ስለማይኖር እባካቹህ ነገ ነገሩ ሲገባቹህ መንቃታቹህና ለመቀላቀል መወሰናቹህ ላይቀር ነገር ለአዋቂ አንዲት ነገር ትበቃዋለችና በግልጽ ፈጠው የሚታዩ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነገ ሳይሆን ዛሬ እንንቃና በመዘግየታችን ሊደርስብን የሚችለውን አላስፈላጊ የሆነ ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ በማስቀረት እንታገልና በንጹሐን ደም የሚታጠቡትን የጥፋት ኃይሎችን፣ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ጠራርገን እናጥፋ! ህልውናችንንም እንታደግ፡፡
ግድ የላቹህም በኔ ይሁንባቹህ ሀገራችን ኢትዮጵያን ልንታደጋት የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቢሆን ደስ የሚል ነገር ግን የማይጨበጥ ሕልምና ምኞት ብቻ ነው፡፡ ይሄንን አትጠራጠሩ! ሞኞችም አትሁኑ፡፡ ትሰሙኛላቹህ? እንክርዳድ ተዘርቶ እያለ ስንዴን ለማፈስ ከመጠበቅ በላይ ምን ሞኝነትና ጅልነት አለ? ብዙ የማታውቁት ነገር አለ እንዴት ብየ ልግለጽላቹህ? ሁሉም እኮ አይነገርም፡፡ ዓይናቹህ የሚያየውን ጆሯቹህ የሚሰማውን ልብ ብትሉት እኮ ይሄ ሁሉ ጉድ ለመንቃት ከበቂ በላይ አንቂ ነገር ነበረ እኮ!
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱም አቅጣጫ ከገጠር እስከ ከተማ ተዘዋውራቹህ ብትመለከቱ በአማራ ላይ በኢሰብአዊ ርምጃዎች ታጅቦ እየተፈጸመ ያለው ጥላቻ እጅግ አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ ይህ ግፍ ከአማራም ተሻግሮ አልፎ አልፎ በሚታዩ ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅኑ የሌላ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ አባላት ላይም እየተፈጸመ ነው ያለው፡፡ ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያን ወዳጅ ኢትዮጵያውያንና ወያኔ የአማራ ክልል ብሎ ከሚጠራው የሀገራችን ክፍል ወጥተው የማያውቁ አማሮች ምን እየተካሔደ እንዳለ ቢያውቁም በሆነ ተአምር ነገሮች ድሮ በነበሩበት እንዲገኙ ካላቸው የዋህ ምኞት የትግላችንን አቅጣጫ ለመቀበል እየተቸገሩብን ተቸግረናል፡፡ ነገሮች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ራሳቸውን ንቁ በሆነ የግንዛቤ ዐውድ ላይ ባለማስቀመጣቸውና ከነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር እራስን በጊዜው ካለው ሁኔታ ጋር ማጣጣም (making self update) አለመቻል ካልሆነ በስተቀር በተለያየ መንገድ ከሚሰሙትና ከሚያዩት ነገር ዛሬ ያለው እውነታ እነሱ ከሚያስቡትና ከሚመኙት በእጅጉ የተለየ መሆኑን ለመረዳት ሳይችሉ ባልቀሩም ነበረ፡፡ ሁኔታው የዚህን ያህል እጅግ አሳሳቢ በሆነበት ሁኔታ ይሄንን ያህል መዘናጋትንና መጃጃልን ምን ይሉታል??? ነገሩ “ጥፊ ያላት ከተማ ነጋሪት ቢጎሰምባትም አትሰማ!” ሆኖብህ ይሆን ወገኔ??? ኧረ ከዚህ ያውጣን በሉ! በቃ እመኑንና አብረን እንታገል??? ተዉ በኋላ ይቆጫቹሀል ተዉ ተዉ ተዉ???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

No comments:

Post a Comment