ከአሰፋ እንደሻው (ለንደን፣ እንግሊዝ)*
እንደአዲስ የትግል ፈሊጥ ሆኖ አማራን ለብቻው በተቃዋሚነት እናደራጀው የሚል ክስተት ከተሰማ ውሎ አድሯል፡፡ ከዚያም አልፎ የአማራ ሬዴዮ ሆነ ቴሌቪዥን ወይም ሌላ መገናኛ አውታር ለብቻው በተቃዋሚነት ማቋቋም ይገባናል የሚል ተናፍሶ የተባሉት ነገሮች ብቅ ብቅ ብለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሩጫ አላማው ጥቃትን ለመቋቋም፣ ያማራን መብት ለማስጠበቅ ነው እስከተባለ ድረስ ምንም ክፋት የለውም። በመንግስቱ ስር እንደተቋቋመው ሁሉ በተቃዋሚዎችም ሊመሰረት ይችላል። የኦሮሚያ መገናኛ መረብ ባገር ውስጥም በውጭም አለ። ሌሎችም ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም አማራን ለብቻው ማቋቋም ምንትስ እያሉ የሚነሱትና ሃሳቡን የሚደግፉት አስፈላጊውን አስተዋጽኦ ከማድረግ የሚከለክላቸው የለም። ደግሞስ ዴሞክራሲ ሲባል የህዝብን መብትና ፍላጎት ለመቅረጽ የሚያስችል ማናቸውም ጎዳና መጠቀም ስለሆነ እንዴት ተቀባይነት ሊነፈገው ይችላል? የተሻለ ሃሳብ ይኖራል ከሚል አንጻር ካለሆነ በስተቀር ምንስ ክርክር ያስነሳል;
ይሁንና ግልጽ መሆን ያለበት አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ። ስለ አማራ ማንነት ብዙ የተምታታ ነገር ሲሰራጭ ኖሯል። ከጎሳነት፣ ከነገድነት ጋር የሚያያይዙት በርካታ ናቸው። የአማራነት እውነተኛውና አሳማኙ ገጽታ ግን ከአክሱም አገዛዝ ምስረታና መስፋፋት ጋር የተያያዘና በኢትዮጵያ አቻ የሌለው አፈጣጠር መጎናጸፉ ነው። ስለአማራ አወላለድና እድገት ከመዘርዘራችን በፊት ጎሳ፣ ነገድ፣ ብሄረሰብና ብሄር እንዲሁም አገር እንዴት እንደሚለያያሉ እናሳይ። እነዚህን ማምታታት አይገባምና!
ማህበራዊ (የህብረተሰብ) አደረጃጀትና አገራዊ (ያገዛዝ ወይም ያስተዳደር) አደረጃጀት የተለያዩ ናቸው። ማህበራዊ አደረጃጀት መነሻው በይበልጥ የተፈጥሮ ጉዳይ ነበር። ጥንት በህብረተሰቦች ታሪክ በተፈጥሮ ብቅ ያሉት ጎሳዎች፣ ነገዶች ነበሩ። መጽሃፍ ቅዱስ በወጣበት ዘመን እነዚህ እንደነበሩ አገላብጦ ማየት ይቻላል።
ከዚያ ወዲህ እስከአውሮጳ 15ኛው መቶ አመት ድረስ ይኸው ሁኔታ ቀጥሎ ባውሮፓ ነገዶች እየተዋዋጡ ባንድ አገዛዝ ስር በርካታዎች ተሰባስበው ነበር። የግብርና ስልተምርት (ኢኮኖሚ) እየተለወጠ መጀመሪያ ንግድ ከዚያም ኢንዱስትሪ ባውሮፓ ሲስፋፋ የማህበራዊ አደረጃጀቱም ተለወጠ። በኢኮኖሚው መለዋወጥ ምክንያት ጎሳዎችና ነገዶች እየተጨፈለቁ ከከተማ መስፋፋት ጋር ብሄር ብቅ አለ። የፈረንሳይ ብሄር፣ የእንግሊዝ ብሄር ከሁሉም ቀዳሚዎች ናቸው። ከነሱ ተከትለው በኢኮኖሚያቸው ወደኋላ የቀሩት ሩሲያ፣ ጀርመን፤ ጣልያን ወደብሄርነት ተሻገሩ። ሌሎች ያለም ክፍሎች ይህንን ሽግግር ለማካሄድ ባለመቻላቸው እስካሁንም እየተውተረተሩ ይገኛሉ።
የብሄር መፈጠር ከጎሳና ከነገድ መፈጠር የሚለየው በኢኮኖሚው መለዋወጥ (ንግድና ኢንዱስትሪ) ፍጥነት ምክንያት ብዙ ጎሳዎችንና ነገዶችን በመዋጡ ነው። ያለኢኮኖሚ መለዋወጥ ማለትም ከግብርና ወይም አርብቶአደርነት አልፎ መሄድ ካልተቻል ማንም ህዝብ ብሄር ሊሆን አይችልም። ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ሽግሽግን የሚያቅፍ ክስተት ነው፡፡ ያለምንም መስፈርት አንድን የቋንቋ ስብስብ “ብሄር” በማሰኘት የሚያምር ስምና ማእረግ ለመስጠት ወይም ለመሸለም ወይም የመኩረራት መንፈስ ለመፍጠር የሚቃጣ አይደለም።
በርግጥ ከጎሳነትና ከነገድነት አልፈው የሄዱት ነገር ግን ሽግግሩን ያልጨረሱትን የማህበራዊ ሳይንስ ተጠባቢዎች ብሄረሰብ የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሶስተኛው አለም ባጠቃላይ ባብዛኛው ብሄረሰቦች ናቸው ያሉት። ስለሆነም አንዱን ወይም ማንንም ብሄረሰብ ለይቶ ብሄር ሊያሰኝ የሚችል ሁኔታ ሳይኖር ለመንፈስ እርካታ ተብሎ እንደሹመት የአማራ፣ የትግራይ፣ የሶማሌ ብሄር ብሎ መጥራት የተሳሳተ ነው።
እዚህ ላይ ጽንሰ ሃሳቡ በአማርኛ እንዴት ሊመረጥና ሊገለጽ እንደቻለ ልናነሳ እንወዳለን፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ህብረተሰባችን የተጓዘበትን ማህበራዊ አደረጃጀት ራሳችን አጥንተን በበቀል ቋንቋዎቻችን ስያሜ (መገለጫ) ስላላዎጣንላቸው የውጭ (በተለይ የእንግሊዝኛ) አባባሎችን ወስደን ትርጓሜ ይሆናሉ ያልናቸውን ስንጠቀም ቆይተናል። ለምሳሌ ብሄር የሚለው የግእዝ ቃል ሆኖ የስር ትርጓሜው በውል ሳይታሰብ ለእንግሊዝኛው “ኔሽን” እንደአቻ ተወስዶ ዛሬ ከሊቅ እስከደቂቅ የሚጠቀምበት ሆኗል። እንደፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ያሉ የግእዝ አዋቂዎች ብሄር የሚለውን ቃል አበሻቅጠው ጭራሽ ጎሳ የሚለውን እንድንጠቀም ይጎተጉታሉ። ቃሉ አስቀድሞ በግእዝ ምን ትርጓሜ እንዳለው ተመዝኖ የተወሰደ አለመሆኑ ማንንም ሳያግድ ዛሬ በአማርኛ ቋንቋ ውስጥና በተራው ህዝብ መካከል የማይናወጥ ተቀባይነት አግኝቷል። ግእዛውያን ወደዱ ጠሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ብሄረሰብ የሚለው ቃል በጥንታውያኑ ዘንድ የባሰ ጉድፍ ያዘለ ይሆንባቸዋል። “ብሄር” የሰዎች ስብስብ መሆኑ እየታወቀ “ሰብ” የሚለውን በመጨመር ብቻ ፍጹም የተለየና ራሱን የቻለ ጽንሰሃሳብ እንደሚገልጽ መወሰኑ ሊያበሳጫቸው ይችላል። ነገር ግን እላይ እንዳልነው የራሳችን ምሁራን አጥንተው ተገቢ ስያሜ ስላልሰጡን ተብሎ ህብረተሰቡ ቆሞ አልጠበቀም። የተማሪው ንቅናቄ ለእንግሊዝኛዎቹ ጽንሰሃሳቦች አቻ ትርጓሜ ለማብጀት በመገደዱ ዛሬ የምንገለገልባቸውን ትቶልናል። ስያሜው በዛሬ አይን ሲታይ የሚነቀፍ ቢኖረውም፡፡ ደርግም እነሱኑ ስያሜዎች ወይም ጽንሰሃሳቦች ተረክቦ በህብረተሰቡ አእምሮ ውስጥ ከቷቸዋል። ይሁንና ጎሳ፣ ነገድ፣ብሄረሰብ፣ ብሄር ከተሰኙት መሰረታዊ የህብረተሰባችን ክፍልፋዮች በተጨማሪ ብቅ ጥልቅ የሚሉ ሎሎችም መሰማታቸው አልቀረም። ዘር፣ ዘውግ፣ “ዘመድ”፣ “ወገን” (እነዚህ ሁለቱ ከጌታቸው ሃይሌ በአቻ ትርጔሜነት የቀረቡ ናቸው) ሌላም እየተሰነዘሩ በንግግርም በጽሁፍም እየገቡ አናያቸዋለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ከውጭ ቃላት ጋር ባቻነት እንዲገቡ የተደረጉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በምን መልክና ይዞታ በህዝብ መሃል እንዲሁም በቀለም ቀመሱ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኙ አስቀድሞ ለመናገር አይቻልም። ያው ሁሉም የመሰለውን ከማቅረብ የሚከለክለው ሃይል ስለሌለ፡፡
ባገሪቱ ከሚታየውና ከሚሰማው እውነታ ከተነሳን ግን በህብረተሰቡ ውስጥ ብሄርና ብሄረሰብ የሚሉት ስያሜዎች በእኩልነት ተስፋፍተው በተራው ህዝብ አስተሳሰብና አነጋገር ላይ ተሳፍረዋል፡፡ ባገሪቱ ዳር እስከዳር፡፡ ይሁንና በተለይ በአጼው ዘመን ጀምሮ በውጭ አገሮች ተሰራጭተው የሚኖሩት ወገኖች እንዲሁም አልፎ አልፎ በቀለም ቀመሱ መካከል መምታታቱ እንደቀጠለ ነው። ብሄርና ብሄረሰብ ከውጭ የመጡ ስያሜዎች እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ፡፡ ስለዚህም ያው ጎሳና ነገድ የሚለውን በመጠቀም የውጭ “ተጽእኖን” ለመቋቋም የወሰኑ አይታጡም፡፡ የብዙሃኑ ህዝብ አጠቃቀም እያደር እየገነነ መሄድ ግን ህብረተሰቡ ይመስላል የስያሜውን ውዝግብ የሚዘጋው፡፡ (የእንግሊዝኛውን ቃሎች “ትራይብ” “ክላን” ቅኝ ገዥዎች ያመጡብን ነው የሚለው ሙግት እያየለ ቢሄድም በብዙ ያፍሪካ አገሮች ቀለም ቀመሶች ዘንድ አሁንም በስራ ላይ እየዋለ ነው፡፡ በስነጽሁፍ ውስጥ ግን ኤትኒክ ወይም አዝማድ የሚለው ተክቶታል፡፡ ባንድ በኩል ጎሳነት የኋላቀርነት ሽታ አለው በሚል መንፈስ፡፡)
እላይ እንደተባለው ያገር ወይም ያስተዳደር አደረጃጀት ከማህበራዊ አደረጃጀት ይለያል። እንደስልጣን ባለቤቶቹ አቅም፣ ግዛቱ ሊስፋፋ ወይም ሊጠብ ስለሚችል። የፖለቲካ ሃይሎቹ ንጉሳዊ፣ ሪፑብሊካዊ፣ ቀሳውስታዊ፣ ሸካዊና ሌሎች ሆኑ አልሆኑ በአገር ደረጃ ከላይ ወደታች የስልጣን እርከኖች ፈጥረው ስለሚገዙ ህዝባዊ መሰረታቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ያሻቸውን ያከናውናሉ።
በኢትዮጵያ ከአክሱም አገዛዝና ስራዊት መደራጀትና መስፋፋት ጋር የተፈጠረው አማራ የተባለው ህዝብ ሆነ ከሱው በፊት ጀምረው አገሪቱ ውስጥ የኖሩት ሌሎች (ጥቂቶችን ለመጥቀስ አገው፣ አጋመ፣ ባሪያ፤ ኩናማ፣ ትግራይ፣ ትግረ፣ አፋር፣ ኩናማ፣ ሳሆ፣ ሶማሌ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ሃዲያ፣ ከምባታ፣ ካፋ፣ ህናሮ፣ ቤኒ ሻንጉል) ኢትዮጵያን በሃገርነት አካለው ይዘው ቆይተዋል። ላሊበላ ላይ ከተዋቀረው ብቸኛው የአገዎች ስርወ መንግስት ጀምሮ ከመካከላቸው ስልጣንን የተቆናጠጠው ወገን ሁሉ አማርኛን “ልሳነ ንጉስ” እያደረገ በጎሳና በነገድነት ከዚያም አልፎ በብሄረሰብነት የተቋቋሙትን አሰባስቦ ሲገዛ የ1966 አብዮት ድረስ ቆይቷል። ሆኖም የአገሪቱን ጎሳዎች ወይም ነገዶች እንዲሁም ብሄረስቦች መብት ማስጠበቅ አንዱ የፖለቲካው ህይወታችን ገጽታ እንዲሆን የሚያምኑትና የሚሹት ሁሉ በምን መልክ አገዛዙ እንደሚዋቀር እስካሁንም ንትርካቸውን አልቋጩም።
በሌላ በኩል ግን አማራ የሚባለውን ህዝብ በተመለከተ ዛሬም ብዙ የተምታታ አስተሳሰብ እንደሰፈነ ነው፡፡ እቅጩን ለመናገር፣ አማራ ተጀምሮ እስኪጨረስ ጎሳ አይደለም። አልነበረምም። አንዳንድ የቆዩና እንዳዲስ የተነሱ የአማራ እንቅስቃሴዎች መሪ ነን የሚሉ ሰዎች በጽሁፎቻቸውና በንግግሮቻቸው ይህንን እጅግ መሰረታዊ ጽንሰሃሳብ አልጨበጡም። አማራ ባፈጣጠሩ ከሌሎች የህዝብ ስብስቦች (ትግሬ፤ ኩናማ፣ ሳሆ፣ ኦሮሞ ወዘተ) የተለየ ነው። እላይ እንደጠቀስነው አማራ የሚባል ህብረተሰብ የተቋቋመው የአክሱም ጦር ሰራዊት ከየጎሳውና ከየነገዱ እየመለመለ በያቅጣጫው ሲሰማራ ነው። የአክሱም መንግስት ራሱ የውጭጩ መንግስት ነበር። አክሱም የአገው ከተማ ቢሆንም መንግስቱ ግን ከየጎሳው የተውጣጣ ነበር። አገዎች ያካባቢው ትልቁ ጎሳ ስለነበሩ በስራዊቱና በመንግስቱ ውስጥ ተሳትፎዋቸው ትልቅ ነበር። ነገር ግን ለብቻቸው መንግስቱን አልያዙም። ባጭሩ የአክሱም መስፋፋትና የጦር ስራዊቱ ከያካባቢው ጎሳዎች እየመለመለ አስተዳደሩን በያቅጣጫው መዘርጋት በሰራዊቱ ውስጥ ለታቀፉ የተለያዩ ጎሳዎች መቀላቀል ብሎም ለአዲስ ቋንቋና ህዝብ መፈጠር ምክንያት ሆነ። ልብ አድርጉ መጀመሪያ ቋንቋው ነው የተፈጠረው፣ ከዚያ ቀጥሎ ህዝቡ ተከተለ። አማርኛን የሚናገረውና በተለይ ደግሞ ክርስቲያን የሆነው ራሱን አማራ ማለት ጀመረ። (ይህን ታሪካዊ ሂደት አጠር ባለ መልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ደራሲው አክሱም ↔ ኢትዮጵያ–የህዝቦች ስብጥርና የአገዛዞች አወቃቀር አጭር ታሪክ በሚለው መጽሃፉ አቅርቦታልና ያንን መመልከት ያሻል፡፡)
የአክሱም አገዛዝ አገዎችን እንደመነሻ፣ መረማመጃና ድጋፍ ይዞ ሲስፋፋ መዋቅሩን ከስር መሰረቱ ሳያዛንፍ የተለያዩ ስርወ መንግስታትን በዘመተበት ቦታ ሁሉ በማቋቋም ነበር። ከሱ በፊት ከነበሩት ዳማት ምናልባትም ፑንት ወይም ዳሞት አገዛዞች በመከተልና በመቀጠል ስለተዘረጋ ከአክሱም ላይ የተቋቋመው አገዛዝ ከቤጃዎችና ከኦሪታውያን አገዎች ጋር ባካሄደው ተደጋጋሚ ጦርነት ሲሸነፍ እሱም በተራው መጀመሪያ ወደሮሃ (የዛሬዋ ላሊበላ)፤ ከዚያ ወደሰል (አምባሰል)፣ ቀጥሎ ወደአንኮበር፣ ወጂንና ፊንፊኔ (በኋላ አዲስ አበባ) መንበረ መንግስቱን አዝምቷል። (በአህመድ ኢብራሂም የተመራው የምስራቁ ቆላ ህዝብ እንቅስቃሴ ባስነሳው ጦርነት ሳቢያ ከወጂን ማለትም ደቡብ ምስራቅ ሸዋ ተነቅሎ ወደበጌምድር የተሻገረው ስርወመንግስት ወደመቀሌ ቀጥሎም አንኮበር መዘዋወሩን ሳንረሳ፡፡) በነዚህ ዋና ዋና የመስፋፋት ጉዞዎች ሰራዊቱ ጎሳን ከጎሳ ነገድን ከነገድ እያዋሃደና እያዋዋጠ ሲገሰግስ አማርኛን እያሰራጨና እያጠናከረ ሄዷል። የዚያ ውጤትም ራሳቸውን ከየጎሳዎች አባልነት ይልቅ አማራነት የሚሰማቸው የህዝብ ስብስቦች የበዙ ሆኑ፡፡ እምነታቸው ክርስትና በመሆኑም አማራነትና ክርስቲያንነት ያንድ አካል ሁለት ስሞች እንደሆኑ ተደርገው ቀጠሉ።
ዛሬ በአራቱ የአጼው ጠቅላይ ግዛቶች (ማለትም በሸዋ፣ ወሎ፣ በጌምድርና ጎጃም) ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች አማራ ነን የሚሉት ቁጥራቸው ብዙ ነው። በኦሮሚያ ውስጥ እንኳን 10 ሚሊዮን እንዳሉ ተደጋግሞ ተወርቷል። በሌሎችም ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ። ባጭሩ አማራነት ከደም ጥራት ወይም ስጋነት ጋር ሳይያያዝ ከቋንቋው ጋር በተቆራኘ መልክ ባገሪቱ ሲስፋፋ የቆየና አሁንም ያልቆመ ነገር ነው። አሰፋ ጫቦ ባንድ ቃለ ምልልስ ላይ በጋሞ ጎፋ ራሳቸውን አማራ ብለው የሚጠሩት “ነፍጠኞች” ከሸዋ የዘመቱ ኦሮሞዎች እንደነበሩ የመሰከረው ለዚህ አባባል ዋቢ ነው። እንደገና በኦሮሚያና በደቡብ ከተሞች አብዛኛው የከተማ ኗሪ ባልሳሳት ራሱን አማራ አድርጎ የሚቆጥር ነው። ከዚህም በተጨማሪ በትውልዱና በጎሳው በተለይ ደግሞ የተቀላቀለውና የተዋለደው ይኸ ወይም ያ ብሄረሰብ ነኝ ብሎ መናገር የሚያቅተው ሁሉ ራሱን አማራ ወይም ኢትዮጵያዊ አድርጎ ይቆጥራል።
ባንጻሩ ግን አገሪቱ ውስጥ በተቀሰቀስው የዴሞክራሲን ስርአት የመመስረትና የማስረጽ ትንቅንቅ ውስጥ ሁሉንም ብሄረሰቦች በማስተባበር ከመታገል ይልቅ በየዘሩና በየጎሳው የመከለል ሙከራ ፋይዳ እንደሌለው እየታየ ነው። በይበልጥ ደግሞ በታሪኩና በተከሰቱት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውጥንቅጦች የተወለደውን አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ እንደጎሳ እየቆጠሩ ና ለብቻህ ተቀፍድደህ ቁም፣ ተቆጠር ማለት አላዋቂነት ነው። ሁሉም የአለም ህዝቦች እየተቀራረቡና አየተዋዋጡ ባሉበት የመረጃ አብዮት ዘመን በኢትዮጵያ ከየብሄረሰቡ እየተውጣጡ እየተቀላቀሉ ያሉት ሁሉ ራሳቸውን አማራ ነን ወደሚል ሲተሙ ያንን ሂደት ለማደናቀፍ መሞከር ጅልነት ነው። የማይሳካ ከመሆኑም ሌላ በአይናችን እያየን ለሚካሄደው ማህበራዊና ፖለቲካዊ መለዋወጥ ጀርባ መስጠት ነው።
በሌላም በኩል በአለም ያልተቋረጠ ብቸኛ ትልቅ ታሪክ ከነበራቸው ከግብጽ፣ ኢራንና ከቻይና ጎን የምትሰለፈው ኢትዮጵያ በውስጧ የተፈጠረውን (የተፈለፈለውን) ሰው ስራሽ ማህበራዊ ስብስብ (አማራን) ማንም ሊያጠፋው ቀርቶ ሊገድበው አይችልም። አማርኛን ባገሪቱ የመገበያያ ቋንቋነት ያስቀመጠው ዘርፈ ብዙ ሂደት ተቀልብሶ ወደሌላ መሽጋገር የማይቻለውን ያህል በዚያ ቋንቋ ዙሪያ የሚሰባሰበውን ህብረተሰብ በጠባብ ክፍል ውስጥ ለማሸግ የሚደረገው ማናቸውም መወናጨፍ ከተራ ልፈፋ አያልፍም። ለለፋፊዎቹ አልታያቸው ስላለ እንጅ ከተሜነት ራሱ ከአማራነት ጋር የተቆላለፈ ሂደት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባገሪቱ ዳር እስከዳር ከተሜነት እየተስፋፋ ሲሄድም ያማራነትን መለያ የሚላበስ ክፍል እየጨመረ ያለሰው ሰራሽ (ብሎም መንግስታዊ) አስገዳጅ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡
በዚሁ አኳያ አንዳንድ ቀባጣሪ የፖለቲካ ማይም እየተነሳ ላማራ ለብቻው “የጎሳ” መብት ለማሰጠት እንታገል፣ እንደራጅ ሲል ዝም ማለት አይገባም። አማራው ማንንም አይመን፣ ብቻውን ተደራጅቶ ይንቀሳቀስ የሚሉት ፈሊጥ የት እንደሚያደርሳቸው መገመት ባለመቻላቸውና ከአለም ስልጣኔ ሰፊ ጎዳና ወጥተው ራሳቸው በሚያበጃጁት ዋሻ ውስጥ ስለሚከታቸው የትም አይደርሱም ሊባሉ አይችልም። በምድሪቱ ላይ ያሉት የመንግስቱ ተቀናቃኞች በሙሉ ወደአንድ አቅጣጫ ማለትም ህብረት ፈጥረው ስልጣኑን መውሰድ (መረከብ) ወደሚያስችል ጎዳና እንዲገቡ ስንወተውት ኖረን ያንን ጥረት ለመበተን የሚሟዘዙትን በመናቅ ብቻ መተው ተገቢ አይደለም፡፡ የጎንደር፣ የባህርዳር ህዝብ “በቀለ ገርባ ይፈታ፣ መሪያችን ነው”፣ “የኦሮሞ ደም የኛም ደም ነው” ሲል መልእክቱ ምን እንደሆነ እንዴት መረዳት ያቅታል?
የፈረደበትን ኦነግን ዛሬም እንደበፊቱ የስልጣን ተጋሪና ወሳኝ ተብሎ እየቀረበ፣ ካመቸው ከወያኔ ጋር ተመልሶ እንደሚተቃቀፍና አማራን እንደሚወጋ የሚለውም ጊዜ ያለፈበት ቅዠት መሆኑን በድፍረት ማጋለጥ ይጠበቃል፡፡ የዴሞክራሲን ፈለግ ከሚከተል ሁሉ። ባሁኑ ወቅት ኦነግ በመንፈስነት (በባንዲራ) ከመራገቡ በላይ የኦሮሞ ፓለቲካ እንቅስቅሴው አደራጅና መሪ አይደለም። ከዚህም በላይ የኦሮሞው ህዝብ ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ አገዛዝ ወደዴሞክራሲ መግባቱ ለራሱም ሆነ ለሁሉም ብሄረሰቦች አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን እየተረዳ ነው። የኦሮሞው ቀለም ቀመስ ልሂቃኑ ይበልጥ ይህንን እየተገነዘበ ነው። (ይኸ ጉዳይ ራሱን የቻለ ትንታኔ የሚያስፈልገው ስለሆነ በሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን፡፡)
የትግራይን ህዝብ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ቆርጠን እንጣል ይል የነበረውን እብድ ዛሬ ሌላ ተከታዮች እየተገኙ መሄደቸውና ህዝቡ ላይ የሚነዙት መርዘኛና የጥላቻ ወግ እጅግ አሳዛኝ ነው! ወያኔ መነሻው ከትግራይ መሆኑ የወጣበት ህዝብ እንዴት ወንጀለኛ እንደሚባል ጭንቅላት ላለው ሰው አስቸጋሪ ነው። ደራሲውንና ፖለቲከኛውን ሁሉ ከህዝብ መሃል ስለወጣ ዘሩን ፈልገን እናውግዝ? ምን አይነት የድንቁርና ዘመን ውስጥ ተመልሰን ልንገባ ይሆን እንዲህ አይነት መርዞች በየቦታው ሲረጩ!
ያገሪቱ ህዝብ እድል እንደገና በተቀናበረ እጁ ሊገባ እየተቃረበ ባለበት ወቅት ከፋፈይና በታኝ ቅዠቶችን ማሰራጨት ተቀባይነትም ተገቢነትም የለውም። ይልቁንስ የትግል ህብረቶች እንዲዳብሩ ህወሃት/ ኢህአዴግም በሰላማዊ መንገድ (ማለትም ከጦርነት መለስ) ስልጣኑን እንዲያስረክብ ዘዴዎችና ስልቶች መቀየስ ሲጠበቅ ሁሉም ተበታትኖ የግዛት ዘመናቸው እንዲቀጥል መሞገት የወጣለት መሰሪነት ነው።
No comments:
Post a Comment