የምንገኝበት ዓለምና ወቅት ምን ይመስላሉ?
ኢትዮጵያ በርግጥም በዓለም ውስጥ ተበታትኖ ለሚኖረው ጥቁር ሕዝብ ተስፋ ሰጪና አበረታች ምሣሌ ሁና ኑራለች። በአፍሪካ ውስጥ በተለይም ከሳሃራ በታች ባለው ክፍል በቅኝ ግዛትና በነጭ ወራሪዎች አገዛዝ ሥር ይማቅቁ ለነበሩት የነፃነት ትግል ኢትዮጵያችን የማይታበል ትልቅ አርዓያነት ነበራት። ኢትዮጵያውያን/ት ራሳችንም በተለይ ከ1983 ዓም በፊት የነበረው ትውልድ አባላት እጅግ በጣም በርካታዎቻችን በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተንና፣ በሄድንበት ሁሉ ራሳችንን በባህሪአችንና በተግባሮቻችን አስከብረንና ተከብረንም ነበር የኖርነው። እሰይ፣ የምሥራች የሚያሰኝ ነው፣ አሁን ደግሞ ልክ እንደ ወትሮዎቹ ለመብቱ የሚቆምና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ አዲስ ትውልድ እየበቀለልን ነው። ይህ የሆነው ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸው፣ ኢትዮጵያውያን/ት የምንኮራባቸውም ክህሎት፣ እሴቶች፣ ፀጋዎችና ቅርሶች ስለነበሩንና ስላሉንም ነው። እንዲያው ስለምንኩራራና ስለምንኮፈስ ብቻ አልነበረም። በዘመናዊው ትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በኤኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት፣ በፖለቲካ ሥርዓት ሀገራችን ኋላቀር መሆንዋን፣ በልማት ላይ በዋለ ቁሳዊ ሀብት ደሀ መሆንዋን እያወቅንም በሀገራችንና በማንነታችን፣ ማንነታችን ደግሞ በኢትዮጵያዊነታችን ጎልቶ ይገለጽ ስለነበር፣ ኮርተንና ታፍረንም ነው የኖርነው። ውድ ወገኖቼ እስቲ እነዚያን ያስከበሩንን ሀገራችንንም የነፃነት ቀንዲል ያደረጓትን የጋራ ማንነታችን መገለጫዎች የሆኑትን እሴቶቻችንን ተንከባክነንና ጠብቀን እናቆያቸው ብዬ ልማፀናችሁ፣ ፍቀዱልኝ። ይህን የምናደርገው ደግሞ ለራሳችን (ለኢትዮጵያውያን/ት)፣ ለጥቁር አፍሪካውያን፣ ለመላው ጥቁር ሕዝብ መጭ ትውልድ ስለሚያስፈልግ ነው ብዬ ያለጥርጥር አምናለሁ። ሳትሰለቹ ለጥቂት ደቂቃዎች ምክንያቶቼን ተመልከቱልኝ። እንደ ኢትዮጵያ ያለ አያሌ ትልቅነትን የሚገልጹ መስፈርቶችን የሚያሟላ ሀገር፣ ረጅምና አኩሪ ታሪክ ያለው ጥንታዊ ሀገር፣ እውቅ የሆኑ ባህላዊ ቅርሶች ያሉት ሀገር፣ በርካታ ብሔረሰቦችን፣ ቋንቋዎችን፣ ባህሎችን፣ ዕምነቶችንና ሃይማኖትችን፣ ያቀፈና በአንድነት ነፃነቱን አስከብሮ ለዘመናት የኖረ ትልቅ ሕዝብ ያለው ሀገር፣ ማንነቱ እየተደቆሰበት ላለው … በዐለማችን ለተበተነው ጥቁር ዘርና ለአፍሪካውያን ወደፊትም ተከብሮ ለመኖር እጅግ በጣም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ።
ምርምርና ፍለጋው አሁንም እየቀጠለ ቢሆንም፣ እስካሁን ሕይወት ያለባት መሆንዋ የተረጋገጠው አንዲት ዓለም ብቻ ናት ያለችው። እርስዋም መሬት የምትባለው ነች ። ዓየር፣ ውሃ፣ ምድር፣ ግዑዝ የሆኑና ህያው የሆኑ ነገሮችን ይዛለች። ተመራማሪዎችና አጥኚዎች እንደሚያስረዱን ዓለማችን ሕይወት ካላቸው ፍጡራን ማሰብና ማስተዋል መመራመር በሚችለው የሰው ዘር፣ ተግባሮች እየተበከለች እየተጎዳች፣ በመብዛታችንም እየተጣበበችም እየመጣች ነው። ሁላችንም ሰብአዊ ፍጡራን የምንጋራው ምድሪቱን የከበበው ዓየር፣ የሰለጠነው ዓለም ሕዝብ ካላዋቂነት ወይንም ከግዴለሽነት፣ አሁን ግን ከስግብግብነት፣ ከራስ ወዳድነትና ከማን-አለብኝነት የተነሣ በፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ባሉ ተግባራት (ሥራዎች ) በጣም፣ እጅግ በጣም ተጎድቷል። የዚህ አካባቢያዊ ዐየር (ኤንቫየርሜንታል) ብክለት ዋነኛ ሰለባዎች የሆነው በድሃ ሀገሮች፣ በቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ኋላ በቀረነው ፣ በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና፣ በኦሽያንያ ትንንሽ ደሴቶችና ሀገሮች ውስጥ የምንኖር ህዝቦች ነን። በነዚህ በተጠቀሱት ክፍለ-ዓለማት ያለው ሕዝብ ከተወሰኑ መጤዎችና ያለባለቤቶቹ ፈቃድ ከቆዩት አነስተኛ ክፍሎች በስተቀር የሀገሮች ነባር ባለቤቶች ባለቀለሞች ( ከለርድ ) ነን። ይህን የምለው ዘረኛነትን ለማራመድ ሣይሆን ያለውን ሁኔታ ለማሳየት ነው። ከተከባበርን ከተስማማን፣ ይህችን ምድር የምንጋራ ሁላችንም የሰብዓዊ ፍጥረት ክፍልፋዮችና ዝርያዎች ያለጥርጥር እኩል ባለመብቶች የሆን ሰዎች ነን። ችግሩ ያለው ዕውነታውን ካለማወቅ፣ ወይንም ከመካዱ ላይ ነው። ይህንን ዕውነታ ሁላችንም እናውቅ ይሆን ብለን፣ ካወቅነውስ እንቀበለው፣ እናምንበት ይሆን? ሰብዓዊ ፍጡር ምንጩም ውስጣዊ-ይዘቱም አንድ ሆኖ ሳለ፣ ታዲያ የሚጨንቀው ከፊሉ የሰው ዘር ፣ ገዥ፣ አዛዥ፣ በዝባዥ ፣ ፈንጋይ ፣ ጨቋኝ፣ ገዳይ፣ በቅኝ ገዥነት የሚወር፣ መሬትንና ሀብትን የሚቀማ፣ “ሌሎች” የሚላቸውን እስከማጥፋት የሚሄድ ሲሆን ነው። ሁላችንም ይህችን የምንኖርባትን ዓለም የተፈጥሮ ሃብትዋን ውሱንነት፣ በሕዝብ ብዛት እየተጨናነቅች እየተበከለችም መምጣትዋን፣ የሰው ልጅን ተፈጥሮ፣ ያለውን የዕውቀት ውሱንነት፣ የሰው ልጅ ገና በሙሉ፣ ሰብዓዊነቱን በየትኛውም የዓለማችን ክፍል እስከዛሬ አለማግኘቱን፣ ልንገነዘብ ግድ ይለናል !!
እስካሁን ባለው ጥናት የሰው ዘር አፍሪካ ውስጥ ተፈጥሮ ወደተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ይስፋፉም ወይንም በተመሳሳይ ሁኔታዎች የተለያዩ የሰው ዝርያዎች ተፈጥረው ዓለማችንን በሰው ዘር እንሙላው ሃቁ ግን አሁን ያለው የሰው ዘር ከቀለምና፣ ከውሱን የቅርጽ ልዩነቶች በስተቀር በተደረጉ የዲ ኤን ኤ. (ዘረ-መል) ጥናቶች እንደተረጋገጠው እጅግ በጣም ተቀራራቢና ተመሣሣይነት አለው። ይህም ሆኖ ግን የሰው ልጅ ምናልባት ጠቅላላ ዕውቀቱና፣ ሰብዓዊነቱ፣ ገና በበቂ አላደጉም፣ አልተሟሉም ይሆናል፣ ያገጠጠውን ዕውነታ መቀበሉ ላይ ትልቅ የአስተሳሰብ ችግር አለ። ስለዚህ በዓለማችን ውስጥ ትክክለኛ ባልሆነ ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ወይንም የተለየ ግብ ያላቸው ጉልበተኞችና ስግብግቦች በሌሎች ላይ ግፍና በደል ያደርሳሉ። ግለኝነት የተጠናወታቸው፣ አልጠግብ ባዮች ግዛትን፣ መሬትን፣ ጥሬሃብትን፣… ለመያዝና ለመቆጣጠር፣ ለመስፋፋት፣ የላቀ ሃብትና ንብረትን ለማካበት፣ …. ይራወጣሉ። ይህንን ለማድረግም “ሌሎችን” ሰዎች ይገድላሉ፣ ይበድላሉ፣ ይበዘብዛሉ፣ ምድሪቱን ውሃውን፣ ዓየርዋን በተለያዩ ሰው ሰራሽ መሣሪያዎችና ንጥረ-ነገሮች ያበላሻሉ፣ ይበክላሉ (ያወድማሉ)። ማንኛውም ጡንቻውን ያፈረጠመ፣ ሆኖም ግን ዓዕምሮው በበቂ ያላደገ ወይንም የጫጫበት ገዥ፣ እሱን መሰሎችን ወይም ዕድል አግኝቶ በዕውቀት ያላደጉና ያልበሰሉትን ታዛዦች አስተባብሮ በተወሰነ ሀገር፣ ክፍለ-አህጉር፣ ክፍለ-ዓለም አንዳንዴም በመላው ዓለም ላይ፣ በመላው የሰው ዘር ላይ፣ ከባድ ጉዳት ያደርሳል። የዓለምን ታሪክ እዚህ መዘርዘር አያስፈልገንም፣ ይህን ማድረግ የታሪክ ጸሐፊዎች ሥራ ነው። እያደረጉትም ነው። ትክክለኛ ታሪክ ጸሓፊዎች ሁሉ ምሥጋና ይድረሳቸው!
ጥቂት ምሣሌዎችን ብቻ በማመሳከሪያነት እንጥቀስ። እስቲ ለአንድ አፍታ ዓለማችን ውስጥ አንዱን ወይም ሌላውን ኃይማኖት ለማስፋፋት የተደረጉ የኃይማኖት ጦርነቶችን እናስታውስ። ማመን በደፈናው አንድን ነገር መቀበል ሲሆን፣ ያንኑ ነገር የማይቀበሉት ሊኖሩ ይችላሉ። ሁሉም እንደ ዕምነቱ እንዲኖር ሌሎች አልፈቀዱም፣ የራሳቸውን ዕምነት በሌሎች ላይ በግዳጅና በሃይል ለመጫን …. በርካታ ጦርነቶች ተካሂደዋል። ዛሬም ይካሄዳሉ!
የዓለም ሕዝብ በበርካታ ጦርነቶች፣ በሚሊዮኖችና በብዙ ሺዎች፣ በሚዘገንኑ ሁኔታዎች ጭምር አልቋል።ተፈጅቷል። በጣም አስከፊ የነበሩትን ጥቂቶችን እጠቅሳለሁ። ሁሉም አሃዞች መቶ በመቶ ትክክል ላይሆኑ ቢችሉም ለዕውንወቱ ተቀራራቢነት ያላቸውና በጥናቶች ዉስጥ የተገለጡ ናቸው። የጃፓን ኢምፔርያሊስት ገዢዎች ቻይናን ኮሪያን ወዘተ ወረው ወደ ስምንት (8) ሚሊዮን ሕዝብ ፈጅተዋል፡፡ የስፔይን ኢምፔሪያሊስቶች በደቡብ አሜሪካና በሌሎችም ከባቢዎች ወደ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ጨርሰዋል፡፡ የፖርቹጋል ኢምፔሪያሊስቶች ወደ አምስት ሚሊዮን የሚገመቱ በተለይ አፍሪካውያንን ፈጅተዋል። በተጨማሪ በሚዘገንን ሁኔታ ከሞት የተረፉትን ከሶስት ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን በባርነት ፈንግለው አግዘዋል፣ መገልገያዎች አድርገዋል። መነሻው ቱርክ የሆነው የኦቶማን ኤምፓየር በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሜንያዎችንና ዓረቦችን ፈጅቷል። የፈረንሳይ ኢምፔሪያሊስቶች በአውሮፓ እስያና አፍሪካ ውስጥ 10 (ዐሥር) ሚሊዮን ሕዝብ ጨርሰዋል። የሞንጎሊያው ጄንጂስካን ኤምፓየር 40 ሚሊዮን የሚቆጠሩ እስያውያንን ፈጅቷል፣ እስከ መሐከለኛው ምሥራቅ በመውረር። የጀርምርን ናዚስቶች አውሮፓ ውስጥ ባካሄዷቸው ወረራዎች ከፈጁት ከ40 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መሀል 6 ሚሊዮን አይሁዳውይን ይገኙበታል። የቤልጂየም ኢምፔሪያሊስቶች 10 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያንን በኮንጎ ሩዋንዳና ቡሪንዲ ፈጅተዋል። በሶቪየት አብዮት ወቅት፣ በተለይ በስታሊን ሥር ወደ 20 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ አልቋል።
የብሪቲሽ ኢምፔሪያሊስቶች በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ፣ በአፍሪካና በኦሸያንያ 150 ሚሊዮን ህዝብ ፈጅተዋል። ታስማንያ ውስጥ ነባሩን ህዝብ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ነው የፈጁት። የኢምፔሪያሊስቶች ወርሮና ሕዝቡን ፈጅቶ ሀገሮችን የመያዝ ወቅት አለቀ፡ ከተባለም በኋላ ጉልበተኛ ለመሆን የቻሉት አሜሪካኖች “ዓለምን ለዝርፊያ የተመቸች “ ለማድረግ በኢንዶቻይና፣ (ቪየትናም፣ ላኦስና ካምቦጂያ) የተራዘሙ ጦርነቶችን አካሂደዋል። ኮሪያን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስላልቻሉ ፣ ደቡቡን ክፍል እስከዛሬ በወታደራዊ ቁጥጥር ይዘዋል፡( የሰሜኑም ሕዝብ በአንድ ቤተሰብ አምባገነናዊ መዳፍ ሥር ይዳሽቃል። አካባቢው ዛሬም ሠላምና መረጋጋት እንዳጣ ነው ያለው። ትንሽትዋ ጣሊያን በእኛ በኢትዮጵያን፣ በሊቢያ ላይና በሶማሌዎች ላይ ያደረሰቸውን በመቶ ሺዎች የሚገመት እልቂት ከምሬት ጋር እናስታውሳለን፡፡ ትልልቅ የሆኑትን፣ ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን ዓይነት ፍጅቶች ያካሄዱት መሪዎች እንደኛው ሰዎች ናቸው። አሌ አይባልም። ጃፓናውያን፣ ስፓኒሾች፣ ፖርቹጊዞች፣ ቱርኮች፣ ፈረንሣውያን፣ ሞንጎላውያን፣ ጀርመናውያን፣ ቤልጂጋውያን፣ ራሽያውያን፣ እንግሊዞች፣ በኋላም የቀጠሉት አሜሪካውያን ናቸው፡፡ ለወረራው፣ ለፍጁት ተጠያቂዎች በየወቅቱ ገዥዎችና መሪዎች የነበሩት ናቸው። እንደ ህዝብ ሁሉም ክፉ ሆነው አይደለም። በአንዱ ወይም በሌላው፣ ሀገርና ወቅት የሚነሱት ገዢዎች በአምባገነናዊነት፣ በግብዝነት፣ በስግብግብነት፣ ራስን በማስቀደም፣ … ለተወሰነው ክፍል ጊዜአዊ ወይንም የረጅም ጊዜ ጥቅም ብለው፣ አለዚያም ዕምነታቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን ወረራ ያካሂዳሉ፤ ጦር ያዘምታሉ፤ ዕልቂትና ፍጅት ያደርሳሉ፤ ለቀሪው የዓለም ህዝብ አንዳንዴ የራሴ ነው ለሚሉት ሕዝብ ጭምር ምንም ዓይነት ርኅራኄ፣ ሀዜኔታ፤ ምንም “ሰብዓዊነትን” አያስዩም።
ዛሬ በዐለማችን በየሀገሮቹና አህጉሮቹ ዉስጥ ያሉት ሁኔታዎች በርግጥም በበርካታ ገጽታዎቻቸው ተለዋውጠዋል ለማለት ይቻላል። በሰው ዘር ዉስጥ የሚበቀሉ ራስን-ወዳዶች፣ ስግብግቦች፣ ደንታቢሶች፣ በጥቅሉ ጥፋተኞች “ኢሰብዓዊ “ ተግባራትን የመፈጸም ባህሪና ሥነልቡና ግን ጠፍቷል ወይንም የለም ለማለት አይቻልም። በተለያዩ ጊዜዎችና በተለያዩ ስፍራዎች በዛሬው ወቅት ሲከሱት የምናያቸው ሰብዓዊነት የጎደላቸው ተግባራት የሚያሳዩን ነገር ቢኖር፣ አሁንም ቢሆን በተወሰኑ ጥፋተኞች አማካይነት ሊመጣ የሚችለው አደጋው እንዳፈጠጠብን ያለን መሆኑን ነው።
ዓለም በሁለት ዋና ዋና ርዕዮተዓለም ጎራዎች ተከፍላ ለበርካታ አሥርት ዓመቶች የተካሄዱትን ፍልሚያዎች፣ የደረሱትን ጉዳቶች፣ መዘዞች፣ እስከዛሬ የቀጠለ ዓለማችንን በኑክሊየር ክምችት ያጨናነቀና አልፎ አልፎም ሊያወድም በተቃረበ ውጥረት ዉስጥ መኖራችንን በጥሞና እናስተውል። ዛሬም ሠላም በታጣበት ጦርነቶች በተበራከቱበት ዓለም ዉስጥ፣ አደጋው እያንዣበብን ነው የምንኖረው። በሣይንስና ቴክኖሎጂ እያደግን፣ እጅግ ብዙ ለሰው ልጅ ጠቃሚ የሆኑ ግኙቶችን እየፈጠርንና እያመረትን፣ ሆኖም ግን ግለኝነትን፣ ስግግብነትን፣ በዝባዥነትን፣ ዘረኛነትን፣ አግላይነትን፣ መግታት ስላልቻልን፣ ኢሰብዓዊነትን የሚገልጡ እኩይና ጎጂ ተግባራትን በየዕለቱ ሲፈጸሙ እናያለን። ይህች ዐለም ገና ጤነኛ አልሆነችም። የሰው ዘር ከእጦት፣ ከዕውቀት ማነስ ወይንም ዓላዋቂነት፣(በዘልማድ ድንቁርና ከምንለው) ከርሃብ፣ ከድህነት፣ ከበሽታ፣ በጥቂቶች ከሚነዛና ከሚሠራጭ ጥላቻ፣ ከጦርነት፣ … አደጋ አልወጣም። ሆኖም ግን ዛሬም ቢሆን በ ዐለማችን ዉስጥ ሰብዓዊና ምጡቅ የሆነ ራዕይ ያላቸው ሰዎች አሉ፣ ባይበዙም፣ ዛሬም ቢሆን ለመብታቸው፣ ለጥቅማቸው፣ ለበጎና ጠቃሚ ነገሮች ባጠቃላይ፣ የሚቆሙ የሚታገሉና መስዋዕትም የሚከፍሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፣ ዛሬም ዐለማችን ውስጥ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውና አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠርና የማግኘት ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ብቃት፣ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ በርግጥ አዳዲስ ፈጠራዎችና ግኝቶች ለበጎም ለክፉም ሊውሉ ይችላሉ። የመረጃና ዜና፣ እንዲሁም የዕውቀት ዝውውርና ስርጭት፣ በገዥዎች ሊገታና ሊታገድ የማይችልበት ደረጃ እየደረሰም ያለ ይመስላል። እነዚህ ክስተቶች ናቸው የሰውን ልጅ ተስፋ ሊያለመልሙት የሚችሉት እላለሁ።
ዐለማችን ከበርካታ ችግሮችዋ ጋር ነው እየተንገታገተች ያለችው። የምንኖርባት መሬት አልሰፋችም። እንዲያም በየወደቦቹ ጠርዛጠርዞች የመሬት መሸርሸር ሁልጊዜ እየተካሄደ፣ የከባቢ ዐይር ሙቀት በጨመረ ቁጥር፣ በረዶው እየቀለጠ የውቅያኖሶቹ ወሀ ከፍታ እየጨመረ ነው። ውቅያኖሶቹ በተለይ ትንንሽ ደሴቶችንና በአንዳንድ “ዝቅ” ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ትልልቅ የወደብ ከተማዎችን ጭምር ሊውጧቸው እየተቃረቡ ናቸው። ትልልቅና ታሪካዊ ከተማዎችንም ይጨምራል የመስመጥ አደጋው። የኔዘርላንዱ አምስተርዳም፣ የግብጹ አለክሳንሪያ፣ … ተጋርጦባቸዋል።
https://www.msn.com/en-us/news/world/sinking-cities-around-the-world/ss-BBAVt8J#image=1
አዲስ ዓለም ተገኝቶ ወደዚያ ለመሄድ የሚችሉት ሊሄዱ አልቻሉም። በዚህ ባለንበት በዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ ምናልባት ምድሪቱ መሸከም ከምትችለው በላይ እየተባዛ ከመጣበብና መጨናነቅ አላመለጠም። አሁንም በዚች ዓለም ውስጥ ኃይለኞች፣ ጉልበተኞች፣ ግፈኞች፣ዘረኞች….. የሚፈልጉትን ሁሉ እየወሰዱ፣ እያገኙ፣ እያደረጉም ናቸው። በዚህ ንጥቂያ፣ ቅሚያ፣ ሽሚያ… በሚካሄድበት ዓለም ዉስጥ ደካሞቹ ይጎዳሉ። ይህ ብቻ አይደለም። እነዚህ ጉልበተኞች የዕውቅትን፣ የምርምርን፣ የትምህርትን፣ የመረጃን ምንጮችና የስርጭት መንገዶችን የማምረቺያና የማትረፊያም ተቋሞች በማድረግ ውጤቶቻቸውን ለመቆጣጠር ያልተቋረጠ ጥረት ያደርጋሉ። የአዞ ዕንባ ማንባታቸው እንዳለ ሆኖ ከጥቅማቸው፣ ከፍላጎቶቻቸው ጋር ካልተጣጣሙ የምርምርና የጥናት ግኝቶችን ዕውነታዎችን ይክዳሉ። ዕውቀትን መጥነው መረጃንም መርጠው በመስጠት፣ የሚገዙትን የሚበዘብዙትን ሕዝብ ባልሆነ መረጃ አነሳስተው አንቀሳቅሰው ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እንዲሠማራ ያደርጉታል። አሜሪካን ከእንግሊዞች ጋር በመሆን፣ የተወሰኑ ሀገሮችን አስተባብራ ኢራቅን በወረችበት ወቅት የተደረደሩትን የሃሰት መረጃዎች ማስታወስ ትምህርታዊ ይሆናል። አሁን ደግሞ በዓለማችን ውስጥ ያለውን በሰው ልጅ ጥንቃቄ የጎደለው ተግባር የአካባቢ ዓየር ብክለት መድረሱን የሚክዱትን “እምቢተኞች” ያስተውሏል፡፡
የዓየር ሞገድን የሚጠቀም የራዲዮ ሥርጭት መኖር፣ የኢንተርኔት መስመሮች በሳተላይቶች ጭምር መዘርጋት፣ የዜናና የዕውቀት ስርጭት መንገዶችን አብዝቷል። ሆኖም ዛሬም ቢሆን ባለሀብቶች፣ ባለጉልበቶች፣ መገናኛ ብዙሃንን በአመዛኙ ይቆጣጠራሉ። አብዛኛዎች ትልልቅ የመገናኛ ተቋሞች ለትርፍ የሚሠሩ ናቸው። በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ደግሞ በመንግሥቶች (በአምባገነኖቹ) ጭምር ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው። በምእራቡ ዓለም ዩኒቨርስቲዎችም ለትርፍ የሚሠሩ ተቋሞች ናቸው። አለዚያም ለሚያበረክቷቸው ግልጋሎቶች በየጊዜው የገንዘብ ድጎማ፣ ርዳታ ከመንግሥታዊ ተቋም ወይንም ከኩባንያ ይፈልጋሉ። “ተመራማሪዎች” ያንን የገንዘብ ርድታ ለማግኘት መመቻቸት ሊገደዱ ይችላሉ። ለእንደዚህ ያለ ጥናት ነው ድጋፍ የሚደረገው ይባላሉ !!!
የመገናኚያ ብዙሃን በርግጥ ነፃነታቸው ይጠበቃል ወይ? ቀደም ብሎ የናዚስቱ ሂትለር ፕሮፓጋንዲስት ጎብልስን ማስተዋስ ይገባል። ውሸትን እየደጋገሙ በመንገር ሠፊውን ሕዝብ የሚነገርውን አምኖ፣ ዕውነት መስሎት እንዲቀበለው ለማሳመንና አቅጣጫውን ለማስቀየር፣ የመሪዎችን አመለካከት በሕዝቡ ላይ ለመጫን፣ ትክክል ያልሆነን ሃሳብ ለማስያዝ፣ የሚቻል መሆኑን መገንዘብ ይገባናል። የምዕራባውያንን በተለይም የአሜሪካንን፣ የእንግሊዝን ሁኔታ አብዛኞቻችን በአንፃራዊ መልክ “ነፃ” የሚባሉ መገናኛ ብዙሃን እንዳሏቸው እናምናለን፣ እንገነዘባለን። እነሱም ቢሆኑ ግን ዘዴአቸውና መንገዳቸው ይለይ እንጂ ተገዢው ሕዝብ ከገዥዎች ፍላጎት ጋር እንዲስማማ የማድረግ፣ የማነጽ ተግባሮቻቸውን ላፍታም አይዘነጉም። በእንግሊዝኛ እነርሱ የሚያደርጉት “ማንፋክቸሪንግ ከንሰንት” ( ???? ) የሚባለው ነው። አልሸሹም ዞር አሉ እንደሚባለው ? አንዳንድ ጊዜ ምስጢሮቻቸው ወይንም ነውሮቻቸው አፈትልከው በቆራጥ ዜጎች አማካኝነት ሲወጡባቸው የሚያሳዩት መደናገጥና መርበትበት በበቂ ሊጤን ይገባል። አሜሪካ ውስጥ የወተርጌት ቅሌት በኒክሰን ጊዜ፣ በኋላም ደግሞ ጁሊየን አሳንጅ የሚባለው ግለሰብ ያጋለጠው መመሳጠር፣ ከዚያም ኤድዋርድ ስኖውደን የሚባለው ያወጣቸውንና ገና እያወጣቸው ያሉትን ጉዶች ያስተውሏል። ገዢዎች ተገዢዎችን በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን በመደበቅ፣ በሃሰት አነሳስቶ የተወሰኑ ተግባሮቻቸውን፣ ርምጃዎቻቸው እንዲደግፉ ወይንም እንዲፈጽሙ በማድረግ ጭምር ከባድ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። የናዚስቶችን፣ የፋሽስቶችን፣ የጃፓን ሚሊታሪዝምን፣ … አነሳስ ማስተውል ያሻል።
ትልቁ ጥያቄ ገዢዎች፣ የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ሃይሎች፣ በተለይም በኃያልነታቸው የሚታበዩት፣ ዘርፈውም ሆነ በሆነ አጋጣሚ የበለጸጉ ባለሀብቶች ጋር፣ ( ከትልልቅ ኩባንያዎች፣ ከባንኮች፣ ከባለ ፋብሪካዎች… )፣ ጋር በመተሳሰርና በመዋሃድ የጉልበተኞች የጥቅም ወይንም የመደብ አንድነት ይፈጠራል፣ “የኔ” የሚሉትን ሃብት ለማሳደግ፣ ለመጠበቅ፣ ሲባዝኑና ማንኛውንም ግፍና ደባ ሲፈጽሙ ይስተዋላል። በወረራ የዘረፉትን ሃብት እንዴት እንዳገኙት፣ እንዴትስ እንደሚያሳድጉት፣ ማንም እንዲያውቅባቸው አይሹም። በተፈጥሮ ሀብት የበለጸጉትን ሀገሮች ወረውና ሚሊዮኖችን ፈጅተው፣ በጦር ሃይል ከያዙዋቸው በኋላ ሀገሮቹ በተለይም በከርሰ-ምድር የያዙዋቸውን ጠቃሚና ውድ ማዕድኖችን በርግጥም ተዘርፈዋል፣ ዛሬም ለየት ባለ መልክ፣ ታማኝና ተባባሪ የሚሆኑትን ተወላጆች በገዥነት ስም ሥልጣን ላይ በማስቀመጥ፣ ሀገሮችና የሀብቱ ትክክለኛ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እየተዘረፉ ናቸው። የአወሳሰዱ መንገድ ቢለወጥም መወሰዱ አሁንም ቀጥሏል። አሁን ግንኙነት “ወዳጅነት” ይባላል፣ ነፃ ከወጡት ሀገሮች ጋር ያስተሳሰረ ዓለም-ዐቀፍ ሥርዓት መሥርተዋል። የየሀገሮቹ ተወላጆች ከሆኑ ተባባሪዎች ጋር፣ እነሱን በትምህርት ቤቶች አንጸው፣ አሟልጠው ማለት ይቀላል፣ በቅድሚያ አስተሳሰባቸውን ለነሱ ያመቻቸ አቅጣጫ አስይዘው፣ ሲመቻቹለት ደግሞ ሰብዕናቸውን ጭምር በጥቅማ-ጥቅሞች ገዝቶ በማሠለፍ፣ ከነዚሁ የ“ኒዎኮሎኒያል” ብዝበዛው ተባባሪዎቹ ጋር ነው ከሶስተኛው ዓለም ሕዝብ የሚዘረፈው። ስሙም የኢምፔሪያሊዝም የእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ፣ “ኒዎ-ኮሎኒያዝም” ሲሆን፣ መገለጫው በተለያየ የሙክሻ ስም ቢጠራም ያው የኒዎ-ሊበራሊዝም ፍልስፍና ባነሆለለው የተማረ ወይም የተመለመለ አገልጋይ የሆነ ክፍል መሣሪያነት የሚፈጸም ምዝበራ ነው። ዝርፊያውን ህጋዊ አድርገውታል። ዐለማችን ከእንግዴህ በዚሁ መንገድ ነው መትመም ያለበት ብለው ሃያላኑ ወስነዋል። ለየት ያለ መንገድ ከቶ አይታሰብም ሲሉም ይደመጣሉ። የዓለም ሀብት በሙሉ ጉልበተኞቹ ከፈለጉት ሌላው ወገን ወደደም ጠላ፣ በራሱ የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጭምር ቁጥርጥር ስለሌለው፣ የሌሎች አንጡራ ሀብት “የእነሱ” ይሆናል። ለመውረር ሰበብ አያጡም።ስለዚህ ነው ዕውነትን ከህዝብ የሚደብቁት። እየዘረፍንህ ነው አይሉም። ይደብቃሉ/ይክዳሉ። እንበዘብዝሃለንም አይሉም፣ በሌላ ስም ነው የሚጠሩት። “ሥራ እንፈጥርላችኋለን” ይሉናል?! “እንረዳችኋለን” ይላሉ። ነገር ግን በርዳታ መልክ ለተባባሪዎቻቸው ከሚሰጡት የበለጠ በአንዱ ወይንም በሌላው መልክ “ከተረጅው-ሀገር” ይወስዳሉ!! በፊት በባርነት እየገረፉ እያዘዙ ያሠሩ ነበር። አሁን ደግሞ በሠራተኛነት በዝቅተኛ ክፍያ “ሠራተኛው” እንዲሠራ፣ እንዲያመርት፣ እነሱም ምርትንና ግልጋሎትን እየሸጡና እንዲከብሩበት ያደርጋሉ። ከበርቴዎችም ሰዎች ናቸውና ለምን ከፉ? ወይንስ የሚሠሩትን ነገር ሁሉንም ዐውቀውና አገናዝበው አይደለም የሚሠሩት? ለምንስ በሚመሳሰላቸው “ሰብዓዊ” ፍጡር፣ በሰው ልጆች ላይ፣ ይጨክናሉ ብለን መጠየቅ እንችላለን?! ለምን ይሆን ሁሉም ሰው “ ሰብዓዊነት” የምንለውን ባህሪ የማይላበሰው?? ለመሆኑ ሰውን “ሰው” ያደረገው የማሰብ ችሎታው የምክንያታዊነት መወላገድ የሚያሳየው ለምንድነው? ሁሉም የሰው ልጅ፣ ሰውን ሰው ያደረጉትን ገጽታዎችን ተላብሷቸዋል፣ እየኖራቸው፣ በተግባራት እየገለጻቸው ነው? ካልሆነስ ለምን?
በግለሰብ ደረጃ ጥቂት ሰዎች ከፍተኛ የዕውቀትና የሰብ ዓዊነት ርክርን ላይ ቢደርሱም ሁላችንም የሰው ዝሪያዎች፣ በማንኛውም የዓለም ክፍል እንገኝ፣ ገና ሰውን ምጡቅ ያደረጉትን ደረጃዎችና ባህሪያት፣ በተለይም የሰብዓዊነት ፀጋን፣ በበቂ አላገኘንም ብዬ አምናለሁ። የተወሰነው የሰው ክፍል፣ በአንዱ ወይንም በሌላው ሥፍራ ከሚፈጽመው ሌሎችን የሚጎዳ ተግባር እንደሚታየው፣ “ሰብዓዊነትን” በግብራችን የምንገልጽ አልሆንም። ያ የሰብዓዊነት ማማ እንደ ዓላማ ለወደፊት መዳረሽ ሆኖ የተያዘ፣ ገና አብዛኛው ሰው ያልደረሰበት ከሆነ፣ አሁን ያለንባት የጉልበተኞች ንብረት የሆነችውን ዓለም፣ ለሰፊው ሕዝብ ምቹና ተስማሚ ልናደርጋት ይገባል፣ ለዚህም በቀጣይነት ልንታገል ይገባል ማለት ነው፣ ዛሬ ግን ዓለማችን ለአብዛኛው ህዝብ ምቹ አይደለችም። በተለይ ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን በሚቆጣጠሩት፣ በገዢዎቻችን ተግባራት፣ አልፎ አልፎም በኅብረተሰቡ ውስጥም በግለሰቦች ወይንም በቡድኖች በሚፈጸሙ ተግባራት ስንለካ፣ “ሰብዓዊነት” እጅጉን ይጎድለናል። ከዕውቀት ማነስም ሆነ ከግለኝነትና ስግብግብነት ይመንጭ ብቻ በወገኖች ላይ የሚፈጸሙት ግፍና በደሎች፣ ያንን የሰብዓዊነትን ማማ፣ ገና እንዳልደረስንበት፣ እንዳልተጠጋነው ያሳየናል።
ለምን የሚለውን ከባድ ጥያቄ መመለሱ ቀላል አይሆንም። የአያሌ የምርምርና ጥናት ዘርፎች ቀጣይ ጥናትና ግኝትን ይሻል። እነዚህን ከበድ ያሉ የፍልስፍና፣ የስነ ልቦና (ሳይኪያትሪ)፣ የሳይኮሎጂ፣ የሶሽዮሎጂ፣ ዘርፎችን ትኩረት የሚጠይቁ ጉዳዮች…. ያነሳሁት እንድናስብባቸው፣ በየዘርፉም ዕውቀታችንን ማሳደግ አስፈላጊነት ለማስታወስ ነው። በየመስኩ በርካታ ጥናቶች ተደርገዋል፣ ወደ ትክክለኛ ዕውቀትና ግንዛቤ የሚያመሩ ግኝቶችም ግምቶችና የምርምር ውጤቶች አሉ ብዬ አምናለሁ።
በዐለማችን በርካታ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተካሂደዋል፤ ሰብዓዊ መብት ረገጣዎች በስፋትና በይፋ በገዥዎች ይደረጋሉ። ወረራዎች ይካሄዳሉ። ሃያላን ጥቅሞቻቸውን ለማረጋገጥ በሰበብ አስባቡ በተለይ በሦስተኛው ዓለም ዉስጥ ጦርነቶችን ይጀምራሉ፣ አንዱን ወይንም ሌላውን ተባባሪ እየተጠቀሙ በቀጥታና በእጅአዙርም አውዳሚ ጦርነቶችን ያካሂዳሉ፣ ሌሎችን በሰበባስባቡ በማጋጨት በኋላም ራሳቸውን ከጉዳት ለምዳን ሌሎችን እያጋፈጡ ቶርነቶች በቀጣይነት እንዲካሄዱም ያደርጋሉ።
ከዕውቀት አለመዳረስ ወይንም ማነስ፣ ከኢሰብዓዊ-ትምህርት (ሆን ተብሎ ወይንም ከ አላዋቂነት የሚሰጥ) … የተነሳ መሰናክሎች፣ እጥረቶች በተነሳም የሰው ልጅ በተፈጥሮአዊው ውስጣዊ ማንነቱና ይዘቱ እጅግ በጣም ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ዛሬም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በውጫዊ ገጽታቸው፣ በቅርጻቸው፣ በቀለማቸው ልዩነት የተነሳ ሲገለሉ፣ ሲናቁ፣ ሲበደሉ፣ ሲጨቆኑ፣ …. ይኖራሉ። አንዳንዴም የሚዘገንን ጭፍጨፋና ዕልቂት ይፈጸምባቸዋል።
ስለሆነም ሰው በተፈጥሮው በእኔ ዕምነት እኩል ሰውነትን የያዘና ፣ ማህብራዊ (ሶሽያል) ፍጡር ሆኖ እያለ የተወሰነው ክፍል ከህፃንነት ጀምሮ ግለኝነትን እንዲማር ፣ ተዛማጁ የሆነው ስግብግብነትን እንዲላበስ፣ ንፍገት እንዲቆራኘው እነዚህም “ኢሰብዓዊ ባህሪያት” ሰፍንገው እንዲይዙት ይደረጋል። የሰብዓዊ ባኅሪያቱን እንዲያጣ የተደረገ ሰው ሆኖ በትልቅ ተቃርኖ ዉስጥ ያድጋል፣ ይኖራልም። እኔ የተለየሁና የተሻልኩም ነኝ ብሎ ስለሚያምንም፣ የሚያስበው፣ የሚያልመው፣ በግብሩ የሚገልጸው፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፣ በይነግብሩም ያንኑ ዕምነቱን ያንጸባርቃሉ ማለት ነው። በተጻራሪው በግዞት በባርነት በአገልጋይነት እንዲያድጉ፣ እንዲኖሩ፣ … የሚደረጉት የበታችነት ስሜት ይዘው እንዲኖሩ ይደረጋሉ። ስለዚህም ማንኛውም ኅብረተሰብ ዉስጥ ዘረኝነት፣ ጎሰኝነት፣ ጠባብ-ብሔረትኝነት፣ ወይም ትምክህተኝነት፣ የዕምነት አክራሪነት (ቀኖናዊነት)፣ የበላይነት ስሜቶችና የበታችነት ስሜቶች፣ … ሆን-ተብሎ ለሁሉም ታዳጊ ወጣት በሚሰጥ ትምህርት፣ ወግና ልማድ፣ … የሚተላለፉ ስለሆኑ እነዚሁኑ የማስተማሪያ መንገዶችና ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በመለወጥ እስከሚወገዱ ድረስ፣ እንደ ተላላፊ ደዌ ሆነው ከሰው ወደ ሰው፣ ከወትውልድም ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ። በርግጥም ማንኛውም ክፋት፣ ወደ ጥፋት የሚያመራ ሃሳብ፣ ጦርነቱም የሚጀምረው እዚያው እሰዎች ዐዕምሮ ዉስጥ ነው።
በአንዳንድ አካባቢዎች፣ ወይንም ሀገሮች ዉስጥ፣ በተወሰኑ አጋጣሚዎች፣ በተጠቀሱት ዘረኛነትን፣ ጎሰኛነትን፣የመሰሉ “ተላላፊ በሽታዎች” የተለከፉ፣ ራሳቸው በማሰብና በማመዛዘን ከበሽታው መላቀቅ የተሳናቸው ወገኖች ኃይልና ጉልበት ሊያገኙ ይችላሉ። በዘረኛነት፣ በጎሰኛነት፣ በሃይማኖት አክራሪነት፣ ወይንም በጭፍን-ቀኖናዊነት (በርዕዮተዓለም ደረጃ) የበላይነት ባገኙባቸው የዓለም ክፍሎች ውስጥ፣ በቀለም ልዩነት፣ በቋንቋ ልዩነት፣ በኃይማኖት ልዩነት፣ በሌሎችም የዝንባሌ ልዩነቶች፣ ወይንም በአመለካከት ልዩነት ላይ የተመሠረቱ ጥላቻዎችን በማራገብ ተቧድኖ እስከ መተላለቅ ፣ አንዱ ዘር ሌላውን ዘር እስከማፋት የሚያደርሱ፣ ግፍና በደሎች ይፈጸማሉ፣ ጭፍጨፋዎች ይካሄዳሉ፣ ደከም ብለው በተገኙ ወገኖች ላይ ዕልቂት ሊፈጸም ይችላል። ጥቂት የተደራጁ አላዋቂዎች ወይንም መሃይሞች፣የዕምነት አክራሪዎች፣ የተለያዩ አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የአንድ ሀገርን መንግሥታዊ ሥልጣን ከጨበጡ፣ አዛዥና ናዛዥ፣ ፈላጭና ቆራጭ ሆነው የሚያዙትን ሃይል ለዚያው፣ ካላዋቂነት የያዙትን ዕምነትና መመሪያቸውን ለመተግበር በማሰማራት ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ። ከዚህ በፊት በ ዓለማችን ዉስጥ የተፈጸሙት ዕልቂቶችና ዛሬም በተለያዩ የ ዓለማችን ክፍሎች እየተፈጸሙ ያሉትን እልቂቶች ልናገናዝብ ይገባናል።
በአስተሳሰባቸው ቀኝ-አክራሪ የሆኑ፣ ነጭ ዘረኞች በአሜሪካ ( በትልቂቱና ሃያልዋ፣ በዴሞክራሲያዊነትዋ ከመኩራራት አልፋ በምትመፃደቅ ሀገር) ውስጥ ሥልጣን በያዙበት ፣ የእንግሊዝ ወግ-አጥባቂዎችና ዘረኞች መጤዎችን (ሌሎችን?) ከመጥላት የተነሳ ከአውሮፓ ኅብረት ሀገራቸውን (ዩናይትድ ኪንግደምን) ባስወጡበት ፣ በፈረንሳይ ዘረኖች (ናሽናል ፍሮንት) እንደፖለቲካ ፓርቲ ጠንክረው በመጡበትና የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ እስከማስጋት ደርሰው የነበረበት፣ በኔዘርላንድና ጀርመን ጭምር ፀረ- መጤዎች የሆኑ እንቅስቃሴዎች እየተጠናከሩ በመጡበት፣ ሶሽያል ዴሞክራቲክ ሥርዓት መስርተው ለበርካታ ስርቶች ማኅበራዊ ፍትኅ የሰፈነበት ኅብረተሰብ በመሰረቱት “ኖርዲክ” ሀገሮች ዉስጥ ጭምር፣ ፋሽታዊ አዝማሚያ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እየተጠናከሩ በመጡበት ወቅት ነው የምንኖረው። በመጤዎች ላይ ባጠቃላይ፣ በጥቁር መጤዎች ላይ በተለይ፣ ዘረኛ የሆኑ ነጮች ጥላቻቸውን በተለያዩ ጸያፍና ጎጂም በሆኑ መንገዶች እየገለጹ ይገኛሉ።
ሶስተኛው ዓለም (አፍሪካ፣ እስያ፣ ደቡብ-አሜሪካን፣ የኦሽያኒያ ትንንሽ ደሴቶች )
ሦስተኛው ዐለም በሚባለው ዉስጥ የቆዩና አዳዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ችግሮች እየተፈጠሩ ወይም እያገረሹ፣ በርካታ ሀገሮች የኃይማኖት አክራሪዎች፣ ዘረኞች ፣ ጠባብ ብሄረተኞች ፣ ጎሠኞች ፣ ተደራጅተው እንቅስቃሴዎች ፈጥረው፣ በግዳጅ “ የእኔን ኃይማኖት ተከሉ”፣ “ የእኔን የፖሊቲካ አመለካከት ተቀበሉ”፣ “የኔ ጎሳ ወይም ዘር ይግዛችሁ” … በሚል በይፋ በሚታወጁ ወይንም ታፍነው በሚቀጣጠሉ ጦርነቶችና ግጭቶች ዉስጥ ሕዝቡ እየተጎዳ ይገኛል፣ ሠላም አጥቷል። ቡድኖቹ የእነሱ ያልሆነውን ዕምነት፣ ርዕዮት (የፖሊቲካ አመለካከት )፣ ዘር፣ ብሔረሰብ፣ ያጥላላሉ፣ ያንኳስሳሉ፣ ጥላቻን ያስፋፋሉ። አፍሪካ ዉስጥ ብቻ ጦርነቶችና ትጥቅ-ያማዘዙ ግጭቶች በጣም ብዙ ናቸው። ሁለት መቶ ሃያ ሦስት (223) የሚሆኑ የታጠቁ ቡድኖች (ድርጅቶች፣ እንቅስቃሴዎች)፣ በሃያ ዘጠኝ ሀገሮች ዉስጥ በመዋጋት ላይ ናቸው። ዝርዝራቸውን ከነምንጩ በግርጌ ማስታወሻ መመልከት ይቻላል። (http://www.warsintheworld.com/?page=static1258254223)
በእስያም ውስጥ በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ በኢንዶኔዢያ፣ በካሽሚር (የተነሣ በህንድና በፓኪስታን መሐል)፣ በፊሊፒነስ፣ ….. ውስጥ ሕዝቡ የጦርነት ሠለባ ሆኖ ነው የሚኖረው። በኒያንማር ምንም እንኳን በምእራባውያን ተጽእኖ የፖለቲካ ምርጫ ቢደረግም፣ አገዛዙ ቢለወጥም፣ ዛሬም ከሕዝቡ የተወሰነው ክፍል ሰላም የለውም። ለረጅም ጊዜ በወታደራዊ ፍጥጫ ላይ ይውሚኖሩት ሁለቱ ኮሪያዎች ከራሳቸው ተርፈው አካባቢውንም ያጣቀሰ ውጥረት ላይ ናቸው። ዘውዳዊ አገዛዝ በሚመስል በአንድ ቤተሰብ አምባገነናዊ አገዛዝ ሥር የሚገኘው ሰሜናዊው ኮሪያ ባለ ኒኩሊየር መሣሪያ ሆኗል፣ ስለዚህም በአካባቢው ላይ የፈጠረው ስጋት ጨምሯል። ደቡባዊው ክፍል ለበርካታ አስርት ዐመቶች የአሜሪካ ወታደሮች ሰፍረውበት ነው የሚኖረው። በአሜሪካ ሥልጣን የጨበጡት ራሳቸውን በትክክልና በይፋ ያልገለጡ፣ ፋሽስታዊ አዝማሚያዎች የሚታዩባቸው ገዥዎች አካባቢውን ይበልጥ ማተራመስ ወይንም የማይፈልጉትን ለመጨፍለቅ ከቃጡና ከተተናኮሱ ከአካባቢው አልፎ ወደ ሌላው የዓለም ክፍልም የሚዘልቅ ከፍተኛ ውድመት ሊከተልም ይችላል።
ማንኛውም ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የተነፈገ ግለሰብ፣ ቡድን፣ ኅብረተሰብ ይህንኑ የተነጠቀውን ወይንም ያጣውን መብቱን ለማግኘት የመብት ጥያቄዎችን አንስቶ መብቱን የነጠቀውን ሃይል፣ መቃወምም ሆነ መታገል ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ማንኛውም ዜጋ ሊኖረው የሚገባ መብት ደግሞ የሌሎችን ዜጎች መብት የሚጎዳ የሚችል ሊሆን አይችልም።ሀገርን መሽራረፍ፣ መሸንሸን፣ መገንጠል፣ … የሁሉንም ዜጎች መብት ይጎዳል። የማንኛውም ትግል ዓላማው ያንን የተነጠቀውን መብት ማስመለስ፣ በፊት ያልነበረ መብት ከሆነም መብቱን ማግኝት ሊሆን ይገባል እንጂ ሀገርን፣ መኖሪያን፣ ማፍረስ ሊሆን አይገባም። ጤነኛ አዕምሮ ያለው ማንኛውም የሦስተኛ-ዓለም ዜጋ፣ ዛሬ ባለንበት እጅግ በጣም አስጊና አስከፊ ወቅት በሀገሩ ህላዌ አንድነትና ሠላም ቁማር ሊጫወት አይገባም እላለሁ። አፍሪካ ዉስጥ የተስፋ ጭላንጭል የሚታይበት ሀገር ማግኘት ይከብዳል። ከዘረኛነት አገዛዝ (አፓርታይድ) በከባድና ረዥም ትግል የተላቀቀችው ደቡብ አፍሪካ እንኳን የሚጠበቀውን ያህል አልሆነችም። ማንዴላን የሚመጥን ተኪ ወይንም የኤ. ኤን. ሲን ህዝባዊነት መልሶ የሚያለመልም ክስተት እስካሁን አልታየም። እደቡብ አሜሪካ በአንዳንድ ሀገሮች ዉስጥ አንዳንድ ሕዝባዊ ሃይሎች ተፈጥረው ግብግቡ ቢጠናከርም የሕዝቡ መብትና ጥቅም ሊረጋገጥ የቻለበት አካባቢ አለ ለማለት ይታስቸግራል። አሁንም ሰፊው ሕዝብ ከባዕዳኑ የጭቆናና ብዝበዛ ኃይሎች ጋር በተሳሰሩ አድሃሪ ወግ-አጥባቂና በዝባዥ ሃይሎች ጥቃት እየተቃጣበት ወይንም እየተካሄደበት ነው። ብራዚልንና ቬኒዙኤላን ያጤኗል። ኩባን ተሳክቶላቸው ገና አላፈረስዋትም፣ እየተናነቋት ናቸው። በሰሜን አፍሪካ፣ በመሐከለኛው ምሥራቅ፣ ሀገሮች በአሜሪካና አጋሮቹ ጣልቃገብነት ፍርስርሳቸው ወጥቶ በርካታ ሚሊዮኖች መግቢያና መውጫ ባጡበት ወቅት ነው ያለነው። በቱርክ ፣ በግብጽ አምባገነናዊነት እየተጠናከረ ባለበት ወቅት ፣ በናይጀሪያ፣ በሴንትራል አፍሪክን ሪፐብሊክ በማሊ፣ በሶማሊያ፣በሊቢያና በተዋሳኝ የሰሜን አፍሪካ ሀግሮች ውስጥ በአምባገነን ገዥዎች፣ ወይንም በውጭ ጣልቃገቦች ድብደባ ትርምሳቸው ከወጣ በኋላ፣ የእስልምናን ስም ያጎደፉ አክራሪ ቡድኖች ሕዝቡን ሰላም እየነሱት ናቸው።ጦርነት፣ ውድመት፣ ዕልቂት፣ ስደት፣ ሠላም ማጣት፣ መጠጊያ ማጣት፣ ርሃብ ወይንም ችጋር፣ ተስፋ አጥቶ መንከራተትና መዋተት የሚሊዮኖች እጣና ፈንታ በሆነበት ወቅት ዉስጥ ነው የምንገኘው። በቀሩትም፣ ስማቸውን እላይ ባልጠቀስኳቸው በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ሕዝቡን ሰላምና ተስፋም ያሳጡ ግጭቶች አሉ፡፤ ( ሱዳን በዳርፋር ውስጥ ፣ ደቡብ ሱዳን በሁለቱ ጎሠኛ መሪዎችና ቡድኖች መሀል ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ በአምባገነኑ የካቢላ መንግሥትና በተቃዋሚዎቹ መሐከል፣ በሞዛምቢ ወዘተ… እየቀጠሉ ያሉ ጦርንርቶች አሉ። አብዛኛው የአፍሪካ ሕዝብ፣ ተፈጥሮ ያደለውን ሀብት ራሱ ሊጠቀምበት አልቻለም። በባርነት ተሽጦ፣ በኮሎኒያሊስቶች ተቀጥቅጦ-ተገዝቶ ያሳለፈው የመከራ ጊዜ ያነሰው ይመስል፣ ካብራኩ የተፈጠሩ፣ አርቆ ማየት የተሳናቸው የባዕዳን መሣሪያዎችን በተባባሪነት እያሰማሩ ሕዝቡ እስከዛሬ እየተቀጠቀጠና እየተቦጠቦጠ እንደተዋረደ፣ እንደደኸየም ይኖራል።
**1 (http://www.warsintheworld.com/?page=static1258254223)
በሀገራችን ዉስጥ የነበሩትንና ዛሬም ያሉትን ሁኔታዎች ሳናድበስብስና ሳናውገግር ሳንዋሽና ሳንካካድ በዕውነተኛነት ግልጥልጥ አድርገን አፍረጥርጠን ብንገልፃቸውና ብናውቃቸው ሁላችንን ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያ በታሪክዋ የአንድ ብሔረሰብ (ወይንም ጎሳ ወይንም ዘውግ) ብቻ ሀገር ሆና አታውቅም። በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ቢያንስ አያሌ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ብሔረሰቦች፣ ጎሳዎች፣ ዘውጎች … አብረው ወይንም ጎንለጎን ድንበር ሳይካለሉ ኖረውባታል። በተለያዩ የተፈጥሮ ወይንም ሰው ሠራሽና ምክንያቶች የአንዱ ወይንም የሌላው ማኅበረሰብ አባላት ወደ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች መኖሪያ ከባቢዎች በግለሰብ፣ በትንንሽ ቡድኖች ሲሄዱ፣ በርከት ብለው ሲሰደዱ፣ ሲፈልሱ፣ ነው የኖርነው። ዝውውሮቹ፣ ጉዞዎቹ፣ ሽግሽጎቹ ሁሌም ሠላማዊና በስምምነት የሚካሄዱ አልነበሩም። ለከብቶች መዋያ ግጦሽ ፍለጋ፣ ለሰውም ሆነ ለከብት የሚሆን ወሀ ፍለጋ፣ ወይንም ለም መሬት ፍለጋ፣ … ሲንቀሳቀሱ፣ ሲዘዋወሩ፣ ሲሠፍሩም ነው የኖሩት። በርከት ብለው፣ ፈልሰው፣ ወደ አዲሱ አካባባቢ የመጡ ከሆነም ቀደም ብለው ከሚኖሩት ጋር ግጭቶች ሊኖሩ ይችላል። የሕዝብ ፍልሰት ያለበቂ ምክንያት ይደረጋል ብሎ መገመት ያዳግታል። ፍልሰት ከሌላ ጦረኛ ለመሸሽ፣ ወይንም በአንድ አካባቢ አዝመራ ወድሞ (በድርቅ፣ በዋግ፣ በተምች፣ በአንበጣ … ) ህይወትን ለማዳን ምግብ ፍለጋ ሊደረግ ይችላል። በእንደዚህ ያለ ሁኔታ የሚመጡትን ጎረቤቶች አለመቀበል አስነዋሪም ስለሚሆን ይህኛው ግጭትን ላይጋብዝ ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
ስለጎሳ፣ ስለ ብሄረሰብ፣ ስለ ዘውግ፣ ወ.ዘ.ተ. መብት መናገር ነውር ሊሆን አይችልም። ስህተትም አይደለም። አንድ የኅብረተሰብ ክፍል መገለጫ ናቸውና ስለመብታቸውም ማንሳቱ አግባብ አለው። ችግሩ የሚመጣው ስለ አንድ ጎሳ፣ ስለ አንድ ብሄረሰብ፣ ስለአንድ ዘውግ ብቻ መበደል ወይም መጎዳት ስናወራና እሱን እንደተጠቂ፣ ሌላውን ወይንም ሌሎችን ደግሞ “ሾላ-በድፍኑ” እንደ አጥቂ በዳይ፣ አድርገን ስንከስና ስንወቅስ ነው። የሌሎችን ተመሳሳይ ብሔረሰቦች ወይንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁኔታ ሳናገናዝብ፣ በቋንቋና ባህል ከገዥ ወገን ጋር በመመሳሰሉ/ላቸው ላይ ተንተርሰን አንዱን ወይም ሌሌሎችን ብሔረሰብ/ቦች፣ ዘውግ/ጎች፣ በጅምላ ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር፣ መወንጀል ትክክልም፣ ፍትኃዊም አይደለም። ሰው ማንነቱ የሚወሰነው በአንዱ ወይንም በሌላው መገለጫው ብቻ ሊሆን አይችልም። ማንኛውም ሰው ድርብርብ ማንነት ነው ያለው። እኛ ኢትዮጵያውያን በርግጥ መጀመሪያ ሁላችንም ሰዎች ነን። በተጨማሪም ጥቁሮች ነን፣ አፍሪካውያንም ነን። ከበርካታ ሌሎች መሰሎቻችን ጋር አንዲት ሀገር ዉስጥ ስለምንኖር የዚች ሀገር፣ የኢትዮጵያ ዜጎችም ነን። ከዚያም በጾታ ወንድና ሴት፣ በተለያዩ ዕምነቶች (ኃይማኖቶች) ተከታይነት፣ በሥራችን (አርሶ-አደሮች፣ ላባደሮች፣ አገልግሎት-ሰጭዎች፣ ባለንዋዮች (ካፒታሊስቶች)፣ ምሁራን፣ ከያኒዎች፣ አስተማሪዎች፣ ተማሪዎች፣ … ወ.ዘ.ተረፍ. ልንመደብና ልንታወቅ እንችላለን። ቋንቋን ብቻ የልዩነት መሠረት አድርገን መቧደን የአስተሳሰብ ስህተት ይመስለኛል። ድፍረት አይሁንብኝና የሃሳብ ደሀነትም ይመስለኛል። በቋንቋ ተከፋፍለን፣ ርስ-በርስ እየተወነጃጀልን፣ እየተጋጨን፣ ለማንኛውም ባዕድ ወይንም በባንዳነት የተሠለፈን በዳይ የሆነ ገዥ ቡድን ደባ ተመቻችተን በመገኘት የጋራ ሀገራችንን፣ በዚች የጋራ ቤታችን ዉስጥ ያሉንን የማይገረሰሱ መብቶች ተንከባክበን የማቆየት አቅም ያንሰናል፣ ለንቋሳዎች እንሆናለንና!! የምንጎዳው ሁላችንም ነን ብዬ አምናለሁ።
በባልሥልጣኖች ወይንም ገዥዎች በአንዱ ወይንም በሌላው ጎሳ፣ ብሄረሰብ፣ ዘውግ … በርካታ ወይንም አብላጫ አባላት ላይ ግፍና በደል ተፈጽሞባቸዋልና ያንን እናስወግድ ብለን ታግለናል። እኛም ሀገር ዉስጥ በተወሰኑ፣ በቁጥር አነስተኛ በሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ ግን ያለጥርጥር ግፍና በደል በሁሉም ኢትዮጵያዊ ብሄረሰቦች፣ ዘውጎች አባላት ተሳትፎ፣ … በተጠቂዎቹ የኅበረሰቡ አባላት በሁሉም ላይ ሊባል በሚችል ደረጃ በደል ተፈጽሟል፣ እስከዛሬም ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት ይቸግራል። ለምሳሌ “ወይጦዎች”፣ “ፉጋዎች”፣ “ዋታዎች”፣ “ሚድጋኖች”፣ … ላይ ግፍድና በደል መፈጸሙን ሁላችንም አምነን ተቀብለን ተገቢው ካሳ ለኅብረተሰቦቹ ሊከፈል ይገባል እላለሁ። ምናልባት ከአንዱ ወይንም ከሌላው አካባቢ በጥንታዊ ጦርነቶች የተማረኩ ኢትዮጵያውያንና ወገኖቻችን ናቸው። እንደ ኅብረተሰብ ሰለባዎች ሆነው ኖረዋል፣ በሁሉም ሲናቁና ለውርደትም ሲዳረጉ ኑረዋል። እነሱን በተመለከተ መላው ዜጋ የሚጋራቸው የተወሰኑ ጥፋቶች እንዳሉ መቀበል ያስፈልጋል። ከነዚህ አናሳ ማኅበርሰቦች ውጭ ግን በማንኛውም ወቅት በታሪካችን አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሙሉ-በሙሉ ገዥ የሆነበት፣ ሙሉ-በሙሉም ሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችን የበደለበት ጊዜና ሥፍራ አልነበረም። በአንዱ ወይንም በሌላው ብሔረሰብ ስም የሚገዙ፣ የሚዘርፉ፣ የሚበዱሉ፣ … ገዥዎች ናቸው ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባው። እነዚህ ገዥዎች ደግሞ የሁላችንንም አያቶችና ቅድመ-አያቶች ያካትታሉ። ጥሩም ተግባሮቻቸው ሆኑ በዛሬው የእኛ ዐይን መጥፎ የሚባሉት፣ ሁሉም፣ ተግባሮቻቸው የተሪካችን አካል ናቸው።
በዘረኛነት፣ በጠባብ-ብሔረኛነት፣ በትምክህተኛነት፣ በጎሰኛነት፣ በሃይማኖት አክራሪነት፣ … ላይ የተመሠረቱ አስተሳሰቦች፣ እንቅስቃሴዎች፣ በተለይም ትምህርትና ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋባቸው ህብረተሰቦች ዉስጥ “ስሜተኛነትን” በመቀስቀስ፣ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ሰለባቸው አድርገው የጥፋት መሳሪያቸው ሊያደርጉት ይችላሉ። ሁሉም ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸውን አመለካከቶች አምነውባቸውም ሆነ በመሳሪያነት የሚጠቀሙ ቡድኖች፣ “ሌሎች”፣ “እነዚያ”፣ … በሚሏቸው ላይ ጥላቻን የመፍጠር፣ የማጠልሸት፣ የማግለል፣ ክስና ወቀሳዎችን የመደርደር፣ .. ቅስቀሳዎችን ነው የሚያደርጉት፣ ሂደቶችን ነው የሚከተሉት።
ጥላቻ ደግሞ ሥነልቡናን ይበክላል፣ የሚመለከታቸውን ሁሉ ያስከፋል፣ ከፊሉን ያስቆጣል ፣ በምላሹም ሌላ ጥላቻን ይፈጥራል ። በኃይማኖትም ሆነ በርዕዮተ ዓለም አክራሪነት ፣ በጭፍን ዕምነት፣ አቀንቃኝነትና አራማጅነት የተነሳሱ ክፍሎች በድርጅትና በእንቅስቃሴ ከዚያም አልፎ የመንግሥት ሥልጣን በያዙ “ዘዋሪዎች/አሽከርካዎች” መልክ ገዝፈው ሲከሰቱ በተወሰኑ አካባቢዎችና ሀገሮች ዉስጥ አደገኛ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ። ግጭቶች፣ ጦርነት፣ ዕልቂትም ይከተላል። ዛሬ በዓለም ውስጥ አያሌ ሀገሮችና አካባቢዎች በተደራጁ የኃይማኖት አክራሪዎች፣ ዘረኞች ፣ ጠባብና አክራሪ ብሔረተኞች …. ጉልህ እንቅስቃሴዎችና ተግባሮች ሥጋት ላይ ወድቀዋል ወይንም እየወደቁ ነው።
ከአንድ ወይንም ሁለት ሀገሮች በስተቀር በሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ፦
- የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች በዘፈቀደ (በአብዛኛዎቹ ሀገሮች) ዉስጥ ይረገጣሉ፣
- አሁንም በበርካታዎቹ ሀገሮች ስመ-ምርጫዎች ቢደረጉም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቶች (በአብዛኛዎቹ ሀገሮች) ውስጥ የሉም።
- ከየሀገሮቹ ዜጎች ዉስጥ አብዛኛዎቹ በድህነት አረንቋ ውስጥ ይኖራሉ፣ እንዲያውም ይማቅቃሉ ማለት ይቀላል። በጣም ጥቂት ባለሥልጣኖችና ባግባብም ሆነ ያለአግባብ ሃብት ያካበቱ ዉሱን ሰዎች ናቸው ቅንጡ ኑሮ ያላቸው።
- በየሀገሮቹ የሥራ አጦች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ያውም የወጣት ሥራ አጦች ብዛት ከፍተኛ በመሆኑ ወጣቶቹ ሥራ አግኝተው በየሀገሮቻቸው ዉስጥ ለመኖር የመቻል ተስፋ እያጡ በገፍ እየተሰደዱ ናቸው። እየተሰደዱ ከማለት እየነጎዱ ማለቱ ይቀላል!! በመሰደድ ላይም ሰበኣዊ ክብር ከማጣታቸውም፣ከመሰቃየታቸውም በላይ፣ በአስከፊና አስዛኝ ደረጃ እያለቁም ነው።
- ምናልባት ከአንዲት ታንዜንያ በስተቀር፣ በሁሉም ሀገሮች ውስጥ መጠነ-ሰፊ ሙስና፣ አድላዊነት፣ ዝርፊያ፣ ግለኝነት፣ በሕዝቡ ሃብትና ንብረት ላይ የሚፈጸም ብክነት፣…. በገዢዎችና በግብረ አበሮቻቸው አማካይነት ተበራክቷል፡፡
- ምግባረ ብልሹነት ተስፋፍቷል፣ በገዥነት በተሰየሙት ሃላፊነት የማይሰማቸው ባለሥልጣኖች መሐል ይህ ነው የሚባል ተጠያቂነት አለመኖሩ ደግሞ የሕዝቡን የመሻሻልና የማደግ ተስፋ እያጨለመበት ነው።
- ሕዝብ ከመንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ግልጋሎት አያገኝም። ጥቂትም ቢሆን ግልጋሎቱን የሚያገኙት ከገዢዎች ጋር በአንዱ ወይንም በሌላው ብልሹ መንገድ የተያያዙት ወይንም ጉቦ የሚከፍሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ናቸው። የአገዛዝ ሥርዓቶቹ ዳር-እስከዳር ብሉሹ ናቸው።
- ከውጭ ሀገሮች በርዳታ መልክም ሆነ በብድር የሚገኘው ገንዝብ በባለሥልጣናቱ ይዘረፋል፤ ወደ ግለሰብ ሃብትነትም ይለወጣል፣ ከሌቦቹ ዋሻዎች ዉስጥ በአንዱ ወይንም በሌላው ውስጥ ይደበቃል!! አባሪና ተባባሪ የሆኑት የዋሻዎቹ ከበርቴዎች ይገለገሉበታል።
- የተፈጥሮ ፣ ሃብት ፣ በተለይም ማዕድናት በተገኙባቸው ሀገሮች ውስጥ ሥልጣን
የሚጨብጡት መሪዎች ፣ ፓርቲዎች ፣ ቡድኖች፣ ወገኖች፣ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎች
ወይም ከአዳዲስ ባዕዳን ኩባንያዎች ጋር በመተሳሰርና በመመሳጠር በሙስና የተወሰኑ ክፍያዎችን በግል እየተቀበሉ በውጭ ሀገር ባንኮች ውስጥ በማጠራቀም፤ የሀገራቸውን ሃብት ያስዝርፋሉ፣ እነሱ ፍርፋሪውን እያገኙ!!
ኢትዮጵያ
እኛ ኢትዮጵያውያን/ት፣ የሰው-ዘር መመንጪያ ነን፣ የሰው ዘር የመጀመሪያው የሆነው ፍጡር ፣ ሆሞ ሳፒያን የሚባለው ፣ መነሻ ከመሆናችንም በላይ፣ ሰውን ሰው ያደረጉት በርካታ አዎንታዊ ባህርያት (ተሰጥዖዎች) አሉን ብዬ አምናለሁ። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን/ት፣ ጠልቆ የሚያስብ ዐዕምሮና የሚያመዛዝን ኅሊናም አለን። ሁሌም ሁላችንም በበቂ ደረጃ በዐዕምሮአችንና ኅሊናችን እንጠቀምባቸዋለን ወይ ብሎ መጠየቅ ግን ያስፈልጋል፣ ይቻላልም? የእኔ መልስ በበቂ ወይንም ሁሌም የተጠቀምንባቸው “አይመስለኝም” የሚል ነው። በሩቅም ሆነ በቅርብ አብሮን ያለውን፣ ምስያችንን፣ ሰውን እንዲሁም ተግባሮቹን፣ በሚመለከት በተጨባጭ እየሆነ፣ እየተከሰተ፣ ፊታችን ላይ ያለውን ገሃዱን ዕውነታ፣ ለማየት ካልቻልን ችግር አለ ማለት ነው። ያለውን ሁኔታ በክፍት ልቦናና ብሩኅ ዐዕምሮ ለማየትና ለመረዳት መቻል አለብን፣ እንችላለንም ብዬ አምናለሁ። ከፊት ለፊት ያለውን ጉልኅ እውነታ እንወቀው፣ የቻልነውን ያህል ደግሞ ምንነቱን፣ ሁሉንም ገጽታዎችን ከነይዘታቸው፣ ጥልቀቱን፣ ውስብስብነቱን ተረድተን በተለይም፣ ለወገናችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ እናስረዳ፣ በበቂ አለማወቅ ሊያስከትላቸው የሚችሉትን መዘዙዞቹንም እናገናዝብ። ስለራሳችን፣ ስለኢትዮጵያውያን/ት ችሎታ ርግጠኞች ሆነን፣ ተማምነን ለመሄድ እንድንችል፣ አሁንም ድፍረት አይሁንብኝና፣ እስቲ ከረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ስለኛ የሚመሰክሩ ተግባሮቻችንን በመጠኑ እንመልከት፣
ከጥንት ጀምረን የተደራጀ ፣ በሥርዓት የሚመራ ማኅበረሰብ ፈጥረናል ፣ በባላባቶች ፣ በጦር አለቆች ወይም አዝማቾች፣ በንጉሶች… የሚመሩ፤ ወጥነት ባይኖራቸውም፣ በሀገራችን በመሐከለኛ ክፍሎችና በጠርዞች ላይ አንዳንድ ልዩነቶች ባይጠፉም፤
በከብት ርባታና በርሻ፣ ለማዳ እንስሶሶችን አርብተን፣ ዱር የቀሩትን አድነን ፣ አዝርዕትን ዘርተንና አምርተን፣ ተክሎችን አብቅለን… ለጥቅም / ለምግብነት አውለናል። ከሌሎች የወረስናቸውንም ለጥቅም አውለናል። ከተክሎች ቅጠላቅጠልና ስራሥር የተለያዩ መድኃኒቶችን በአስተዋይነትና በዘዴ እየመረጥን ተጠቅመናል። “ባኅላዊ መድሃኒቶች”ን ለመለየት መቻል ምርምርና አስተዋይነትንም ይጠይቃል።
ብረታ ብረትን አቅልጠን ምሣሮችንና መሣሪያዎችን ሠርተናል፣ መገበያያ ገንዘብ አድርገናቸዋል።
ቋንቋን መጻፍ፣ ሃሳብን በጽሁፍ መግለጥ፣ ጠቃሚነትና አስፈላጊነት በመረዳት ፊደላትን ፈጥረን ብራናን አዘጋጅተን፣ ቀለማትን ቀምመን ፣ በጥብጠን ፣ ለመጻፍ ችለናል።
አያሌ ዕምነቶችን፣ በኋላም ቢያንስ ሦስት ትልልቅ ኃይማኖቶችን ጭምር፣ “ሕይወትን በሞራላዊ ሥርዓት መምራት ጠቃሚነቱን በመረዳት” ሕዝቡም ገዥዎችም እየተቀበሉ ይዘናቸው ተጉዘናል።
ዜማዎችን በመሣሪያዎች ጭምር እንዲቀመሩና እንዲዜሙ አድርገናል።
የላሊበላዎችን ውቅር አብያተ ክርስትያን ቀርጸናል፣ የአክሱምን ሃውልት አቁመናል፤ የጎንደርን ግንብ ሰርተናል፣ የሐረርን ግድግዳ አቁመናል፤
በዐለም ዉስጥ በስነመስተዳድርና በሥነ መንግሥት ዘርፍ ዕውቅና እያገኘ የመጣውን “የገዳ-ሥርዓት” በተወሰነው የሀግራችን ክፍል መስርተናል።
የሀገርን ምንነት ጠቃሚነት በመረዳት የኛ የምንላትን ሀገር ለማስፋትና ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረቶች አድርገናል። ከሌሎች ተቀናቃኞች ተጋፍቶ ሀገርን አስፍቶ መያዝ በኔ ዕምነት ነውር ሊሆን አይችልም። አርቆ የማየት ውጤት እንጂ!!
የእኛ በሆነችው ሀገራችን ውስጥ ከኢትዮጵያኑ ውጭ፣ ባዕዳን የሆኑ ፣ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ መጥተው እንዳይወሩን ፣ ሀገራችንን እንዳይዙብን ፣ እኛንም ባለቤቶችን የበታቻቸው አድርገው እንዳይዙን ተከላክለናል። ማለትም በሀገራችን ውስጥ ያለማንም ባዕድ የበላይነት ፣ በነፃነት ለመኖር ችለናል። ( ከአምስት ዓመት የጣሊያን ወረራና ያልተቋረጠ የአርበኞቻችን ተጋድሎ ወቅት በስተቀር )
በተለይም በጦር መሣሪያ ኃይል ከእኛ እጅጉን ይበልጡ የነበሩትን፣ የጣሊያን ፋሽስት ወራሪዎችን ( አውሮፓውያን )፣ በአድዋ ድል አሸንፈን፣ ለጥቁር ሕዝብ ፣ ለአፍሪካዊ በሙሉ የነፃነት ኮከብና ምሣሌ ለመሆን በቅተናል። ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን /ት ሁላችን ነን የዚች ጥንታዊት ፣ ታሪካዊት፣ ባለ አኩሪ ባህልና ቅርሶች የሆነች ሀገር ባለቤቶች።
አያትና ቅድመ-አያቶቻችን ታዋቂና ተደማጭ የሆነች ሀገርን፤ ንዑድ የሆነውን ነፃነትንና ከነዚህም የመነጨ ክብርን በከባድ መሥዋዕት ዋጅተው አቆይተውልናል። ዘላለማዊ ክብርና ምሥጋና ይድረሳቸው። እነሱ በኖሩበት ወቅትና ሁኔታ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው ብለው ያመኑበትን አድርገዋል።
ሆኖም ታዲያ ኢትዮጵያ አማኞች በምናባቸው የሚያዩት፣ የኃይማኖት መጻሕፍት በተለያዩ መንገዶች የሚገልጹት ዓይነት “ገነት” አልነበረችም። በርግጥም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንዱ ወይንም በሌላው ገዥ ክፍል ግፍና በደል ደርሶበታል።ግፍና ጭቆና ከገዥዎች በስተቀር በሁሉም ላይ በተለያየ ጊዜ ደረጃ ደርሷል። የሀገሪቱን አንድነት ለማምጣትና ለመጠበቅ፣ ሀገሪቷን ከወራሪዎች ለመከላከል፣ የተቀናቃኞችን ማፈንገጥም ለመግታት፣ ገዥዎች ያኔ መደበኛ የሆነ ጦር ባይኖራቸውም ተከታዮቻቸውን አደራጅተው ጦር መርተዋል፣ ተዋግተዋልም። ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሲገጥማቸውም ያንን በሃይል ጨፍልቀዋል። ታዲያ በሌሎች ክፍለ-ዓለሞችና ሀገሮችም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሰፊና ህብረ ብሔር የሆነ ሀገር ሲመሠረት ሁሌም በሠላም፣ በውይይትና በድርድር ብቻ አልነበረም። ድርድርና ውይይት ብቻ በቂ ሆነው ሳይገኙ ውጊያዎችም ተካሂደዋል። ማስፈራራት፣ ማስገደድ፣ በጦርነት አቸንፎ “እምቢኝ” ያለውን ወገን የሀገር አንድነትን አማራጭ እንዲቀበል ማድረግ የነበረ ነው። ዛሬ ባለንበት ወቅት ዕይታና መስፈርት የጥንቱን ሁኔታ ስንመረምር፣ የሁኔታዎችንና አስተሳሰቦችንም ልዩነት ማገናዘብ ይገባናል።ሀገራችን ዉስጥም በሀገር አንድነት አራማጆች የተደረገውና የሆነው አንድነትዋን የጠበቀች ትልቅ ሀገር የማቆየትን አስፈላጊነት በማስቀደም፣ በሃይል ጭምር ሀገራችንን አተልቆና ራስዋን ለመከላከል ተገቢ ተግባር ብቁ አድርጎ የማቆየት ተግባር ነበር። በዚህ የሃይልና ጉልበት አጠቃቀም ሁኔታና ሂደት ንፁሃን ዜጎችም ጭምር ሞተዋል፣ በርግጥም ጉዳት ደርሷል። ያንን ዋጋ አያቶቻችን የከፈሉት ነፃነትዋንና ሀገራዊ አንድነትዋን አስከብራ የኖረች፣ ራስዋን ከባዕዳን ወራሪዎች ለመከላከል የቻለች፣ ነፃ ሀገር ለኛ ለማቆየት ነው። ይሄ ታዲያ የአኩሪ ታሪካችን አንዱ አካል ነው።
ኢትዮጵያውያን እንደሌሎች ረጅም ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች በበርካታ የታሪክዊ ሂደቶች፣ ሁኔታዎች፣ ክስተቶች፣ በይነግብሮች ውስጥ አልፈናል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎችና ሂደቶች ውስጥ ተፍጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ድርጊቶች ጫናዎችን ፈጥረውብናል፣ መግባቢያ አዳዲስ ቋንቋንዎች ተፈጥረዋል፣ አድገዋል። ባህልና ልምዶች ዳብረዋል፣ ተዋርሰዋል፣ ተማግለዋል ። በነዚህ ሂደቶች መሐል ያደጉና የዳበሩ ቋንቋዎች ባህሎች አሉ። እንዲሁም እየጫጩ የመጡ ፣ ወይንም የጠፉ ቋንቋዎች አሉ። ትልልቅ አደጋዎች በከባድ ርዕደ መሬት ፣ በእሳተ ጎሞራ በከባድ ዶፍ ወጀብ ማዕበልና ጎርፍ በከፍተኛ ድርቅና በተከታታይ የህዝብና የእንስሳት ዕልቂት፣ በአንበጣና ተምች በሰብል ላይ በሚደርስ ውድመት ፣ በተስቦ በሽታ በሚደርስ ጉዳት …. በኢትዮጵያውያን ላይ የታወቁና የተመዘገቡ ወይንም ከጉዳቶች ክብደት ፣ ከደረሱት ጥፋቶች ግዝፈት የተነሳ “ “ ለወሬ ነጋሪ “ ያላስቀሩ ውድመቶች ደርሰውብን ይሆናል። በኃይማኖት መጽሐፎች እንደሰማነው “ የኖኅ ጊዜ ጥፋት “ ዓይነት በሀገራችንም በተለይ ደርሶ ይሆናል!?
እዚች ሀገራችን ዉስጥ በርግጥ በርካታ ጉድለቶች ነበሩ። የዜጎች እኩልነት የተሟላ አልነበረም። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አልነበረንም፣ እስከዛሬም የለንም። ሀገራችን ሰብዓዊ መብት የተከበረባት ሀገር አልነበረችም፣ ዛሬም አይደለችም። የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት ሀገርም አልነበረችም፣ ዛሬ እንዲያውም ከወትሮው ብሷል ማለት ይቻላል። ማኅበራዊ ፍትኅ አልነበረም። ዛሬም ደብዛው ጠፍቷል። አብዛኛው ሕዝብ በድህነት ነበር የሚኖረው፣ዛሬም ቢሆን አብዛኛው ሕዝብ ከድህነት አልተላቀቀም። ድህነት ሰፊ ስለነበር አብዛኛው ህዝብ ልጆቹን ለማስተማርም ሆነ የህክማና አግሀልግሎት ለማግኘት አልቻለም ነበር። በተለይ ዋናው የሀገሪቱ የምርት ዘርፍ ግብርና በሆነባት ሀገር ዉስጥ የመሬት ይዞታው እጅግ በጣም የተዛባ ነበር። መሬት አልባነት፣ ጢሰኝነት፣ የሀገራችንን ዋና አምራች ሃይል፣ አራሹን ገበሬ፣ በከፍተኛ ችግር ዉስጥ እንዲኖር አድርጎት ነበር። እነዚህን የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ለመለወጥ ነበር አንድ ትውልድ ከተማሪ እንቅስቃሴ እስከ አብዮታዊ መራራ ትግል ለማድረግ የተነሳሳው። ዝርዝሩን ለታሪክ ጸሐፊዎች እንተወው።
ከዚያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መብትና ክብር ከቆመ፣ ህብረብሔራዊ ይዘት ከነበረው፣ ያለጥርጥር ምጡቅ የሆነ ራዕይ ከነበረው፣ ለማኅበራዊ ፍትኅ ከቆመ፣ ለዜጎች እኩልነት በግንባር ቀደምነት ከተፋለመ፣ ወጣት አብዮታዊ ትውልድ ጋር በተመሳስይ ወቅት በዚያቹ ምድር የተፈጠሩ፣ ራዕዩን የማይጋሩ፣ ከዚያ ባለራዕይ ትውልድ መሐል እንደ አረም የበቀሉም እንደነበሩ ዛሬ ገሀድ ሆኗል። ያንን የባለ ራዕይ ትውልድ ቡቃያ ደርግ የሚባል ቸነፈር መታው፣ የጠባብ-ብሄረተኞች አረምም ባለራዕዩን ወጣት እንደ ዳዋ እየዋጠው መጣ። ዛሬ ሥልጣን የጨበጡት ጠባብ-ብሄረተኞች የዚያን ትውልድ ራዕይ አምክነው ታሪኩን አውገርግረው፣ ከዚያም አልፈው ሀገሪቱን ማጥፋት ይዳዳቸዋል!! በአንድነት በቃችሁ እንበላቸው!! ያ ለማኅበራዊ ፍትኅ የቆመ ባለራዕይ ትውልድና ዛሬ ኢትዮጵያን በማጥፋት ላይ ያሉት “የመልካም ሃሳብ ደሀ” የሆኑ ጠባብ-ብሄረተኞች በፍጹም አንድ አይደሉም። በተመሳሳይ የጊዜ ምዕራፍ ዉስጥ ከመኖራቸው በስተቀር! ከጠባቦቹ ጋር ተሳስተው ተቀላቅለው የነበሩትን ራዕይ ያላቸው ግለሰቦች ሁሉ በመሠሪነት አጥፍተዋቸዋል ወይንም ህይወታቸውን ለማዳን ጥለዋቸው ወጥተዋል።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ህይወት ለማሻሻልና ሀገሪቱንም ለማሳደግ፣ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎች በወገን ላይ “መቅሰፍት” በሆኑ ጠባብ-ብሔረተኞች ተጨናገፉ።ራሱ ባለራዕዩ ትውልድም አያሌ ያደረጃጀት፣ ያሠራር፣ የትግል ሥልት ስህተቶችን ስለሠራ ለደርግና ሌሎችም የጥፋት መልክተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጠረላቸው። ጠባብ-ብሔረተኞቹ ቋንቋን መሠረት ባደረገ ሽንሸናና ሀገርን በመበተን ዓላማና ተግባር ላይ በሙሉ ሃይላቸው ተሠማሩ። ኢትዮጵያዊ የሚባል ሕዝብ የለም እስከማለት ደረሱ፤ ሀገሪቱም ሀገራዊ ሉዓላዊነቷና አንድነቷም ሊጠበቁላት አይገባም ብለው አሴሩብን። ኢትዮጵያዊ ወይንም ሀገራዊ ራዕይ የሌላቸው ጠባብ ብሔርተኞች ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ሥልጣን በመያዛቸው ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ትልቅ አደጋ ተጋርጧል፡፡ የብሔረሰብ ጭቆናን አንግበው ይነሱ እንጂ እስከዛሬ የህወሓት መሪዎች ያንን የብሔረሰብ ጭቆና ከኢትዮጵያ ለማጥፋት አይደለም የሠሩት። የጋራ ቤታችንና መከበሪያችን የሆነችውን ኢትዮጵያችንን ለመበተን፣ ሕዝቧን ለመከፋፈል፣ ርስበርስ ለማጋጨት ነው እስከዛሬም እየሰሩ ያሉት ። ሀገራችንን ወሮ የነበረው ፋሽስታዊ ጣሊያን እኮ ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ ለማዳከምና አቸንፎ ለመግዛት ነበር፣ የጠባብ-ብሔረተኛነትን አስተሳሰብ በሕዝባችን ዉስጥ ለመዝራት የተነሳሳው። እነዚህ የህወሓት ጥቂት መሪዎች ታዲያ ያንኑ መርዝ ለምን እስከ ዛሬ ይግቱናል። ይህ ተግባራቸው ብቻ በርግጥም የፋሽስት ጣሊያን መልዕክተኞች፣ ባንዳዎች፣ ወይንም የሌላ ጠላት መሣሪያዎች ያደርጋቸዋል።
ዛሬ ደግሞ አባቶቻችን መሥርተው ያቆዩልንን ኢትዮጵያ የምትባል ረጅም ዕድሜ ያላት አያሌ ዕምነቶችን የሚከተሉ በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ኢትዮጵያውያንን ያቀፈች ሀገር በነፃነትዋ እንድተከበረች መጠበቅና ማቆየት ፣ ኢኮኖሚዋን ማሳደግና ማልማት፣ የሕዝብዋን መብትና ዕኩልነት ማረጋገጥ፣ ዕውቀትን ሣይንስንና ቴክኖሎጅን በማሳደግ ማኅበራዊና ባህላዊ ሁለንተናዊ ዕድገዋትንና ልማትዋን ለማምጣት ማረጋገት ሲገባን ፣ በከባድ አሌ በማይባል የሃሳብ ድህነትን በሚገልጥ፣ በጎሥኛነት፣ በጠባብ ብሕሄርተኝነት ፣ በተገንጣይነት ልክፍት ህዝቡን ከፋፍለን አቧድነን በማፋጀት ላይ ነን። ልብ እንግዛ፣ ኢትዮጵያውያኑን ርስ-በርስ አናፋጅ፣ ኢትዮጵያንም አንበጫጭቃት!!
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሌሎች ሕዝቦች በአያሌ ማህበራዊ ክፍሎች የተደራጀ ነው በቤተሰብ፣ በቤተዘመድ፣በደብር በጎሣ፣ በብሄረሰብ፣በመደብ፣ በሀገር ከዚያም እየሰፋ በመጣ አህገራዊና መሰል ስብስቦች ተደራጅቶ የሚኖር ሕዝብ ነው። አንዳንዶች ማህበራዊ፣ አንዳንዶች ባህላዊ፣ አንዳንዶቹ ኢኮኖሚያዊ፣ ሌሎች ደግሞ ፖሊቲካዊ ሊሆኑ ይችላሉ።
የሰው ልጅ በአስተሳሰቡም በዕውቀቱም በግኝቶቹም፣ በበይነግብሩም ….እየተለወጠ መጥቷል። ዛሬ በምንገኝበት የዓለም ሁኔታ ፣ በኢኮኖሚና ተክኖሎጂ ያደጉት ሀገሮች እንኳን ብቻቸውን ለመቆም በሚቸገሩበት ሁኔታ ውስጥ ፣ ሰፊ ገበያ ለማግኘት የተለያዩ ኅብረ-አህጉር የሆኑ ስብስቦችን ለመፍጠር/ለማቆየት በሚጥሩበት ወቅት፣ በጠባብ በሔርተኛነት ርዕዮት ተመሥርቶ ሌሎችን የሀገሪቱ ዜጎች ( የሀገር ልጆች ) ማግለል፣ መጥላት፣ ማጥላላት ፣ ሀገርን ወደ ማናጋት ፣ ሕዝቡን በየብሔረሰቡ ተቧድኖ እንዲጋጭ ወይንም እንዲተላለቅ ማድረግ በእኔ ዕምነት የመጨረሻው የአስተሳሰብ ድህነት ነው።
የመንግሥት ሥልጣን የጨበጡት ጠባብ-ብሔረተኞች ይህንን የአስተሳሰብ ደሀነታቸውን በሌሎችም ላይ በመጫን ኢትዮጵያን የማፍረስ ተል ዕኳቸውን ለማሳካት የተለያዩ ዘዴዎችንና መንገዶችን እየተጠቀሙ ነው። ኢትዮጵያን ማፍረስ የሚችሉት ሁሉም እንደ እነሱ ሲጠብላቸው ነውና ሌሎችን በዘር/በብሔረሰብ፣ በዘውግ እንዲደራጁ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ለሁሉም ወገኖቼ የማሳስበው ኢትዮጵያንና ሕዝብዋን በበቂ እንድናውቅ ነው። ዘለፋ እንዳይመስልብኝ፣ ከይቅርታ ጋር! የኢትዮጵያን ሕዝብ ትልቅነት እንላበስ እላለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአስተሳሰቡ በፊትም ትልቅ ነበር፣ ዛሬ ደግሞ ከወትሮውም በበለጠ አድጓል ። የህወሐት መሪዎች ከሕዝቡ ብዙ ለመማር ይችሉ ነበር፣ እንደደነቆሩ ጠበው መቅረትን የመረጡት ሀገሪቷን የማፍረስ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ስለሚያልሙ ቢሆን ነው።
የህወሓት መሪዎች በግብራቸው ከሚገልጧቸው ባኅሪያት ሲታዩ በማንኛውም መስፈርት የኢትዮጵያውያንን የአስተሳሰብ፣ የዕምነት፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የሞራል ፣ የሥነምግባር … ከፍተኛ ደረጃና እሴቶች አይገልፁም፣ አይመጥኑም፣ አይወክሉም ።
- 1 – ኢትዮጵያውያን አብዛኛው ሕዝብ ያለጥርጥር ወገኑንና ሀገሩን ይወዳል፣ ለወገኑና ለሀገሩ የህይወት መስዋዕት በመክፈል ደጋግሞ አረጋግጧል። እነሱ (የህወሐት መሪዎች) ግን የሀገር ፍቅር የላችውም፣ ለወገን ሞትና እልቂት አይሳሱም፣ ማስረጃዎች በጣም በርካታ ናቸው!
- 2- የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ውሸትን ቅጥፈትን ይጠላል፣ የህወሐት መሪዎች ግን በየቀኑ ካልዋሹ ቢያንስ ይታመማሉ። መንግሥትን እየመሩም ሁሉም ያውም በደንብ ለሚያውቃቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዋሻሉ! ያምታታሉ፣ ይቀጥፋሉ!
- 3- የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ስርቆትን፣ ሌብነትን ይጠላል። ክህወሐት መሪዎች መሀል የማይሰርቅ ከተገኘ ተአምር ሊያሰብል ይችላል። በይፋ የሕዝቡንና የሀገሪቱን ሀብት እየዘረፉ ፣ እየሰረቁ፣ ወደ ባዕድ ሀገሮች አሽሽተዋል ። በተለያዩ ስሞች ደብቀዋል፣ ካራቆቱት ሕዝብ እንደገና በየዕለቱ “ጉቦ” ካልተቀበሉ የሚገባውን አገልግሎት አይሰጡትም ። ይህ ገላጭ ባህርያቸው ሆኗል !
- 4 – የህወሐት መሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪካዊ እሴቶች ከሆኑት መሐከል ይሉኝታ፣ ሃፍረት፣ ስህተትን መቀበል፣ የሚባሉትን አያውቋቸውም። ከዚያ ጨዋ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ጨዋነቱ የትግራይን ሕዝብም ይጨምራል፣ አብራክ ቢፈጠሩም እሴቶቹን ግን አልወረሱም!!
- 5 – በርግጥ ጭፍጨፋ፣ ሕዝቡን ፣ በሰበብ በአስባቡ በብዛት መግደል ኢትዮጲያ ውስጥ በእነሱ አልተጀመረም ። ከእነሱ በፊትም የነበሩት ገዢዎች አድርገዋል። ተቃዋሚ ድርጅቶችም በተለያዩ ምክንያቶች በግለሰቦች ላይ ግድያዎችን ፈጽመዋል። ነገር ግን በብሔረሰብ እየነጣጠሉ ብሄረሰብን ማጥቃት፣ የተወሰነ ብሔረሰብን በሌላው ላይ ሆን ብሎ ማነሳሳትና ሕዝቡን እርስ በርስ ማፋጀት የህወሐቶች መሪዎችና ከእነሱ በፊት ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛታቸው ለማድረግ የመጡት የጣሊያን ፋሽስቶች ብቻ ልዩ ስልቶች ናቸው!!
6- የትግራይ ሕዝብ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ አይደለም፣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ነው። የህወሓት መሪዎች የትግራይን ህዝብ በፍጹም አይወክሉም። ሕዝቡን ሰለባቸው አድርገውታል! እነዚህ ጥቂት ኢሰብዓዊነት የተጠናወታቸው የህወሐት መሪዎች በአጓጉል ሥራቸው የትግራይን ህዝብ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ሊያጣሉት በጣም እየሞከሩ ነው። ለምሣሌ ወልቃይትን ከፊል ወሎን በፊት በወረራ ( ከደርግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኅብረትና ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ ጋር ተዋግታው) በመያዝ፤ አሁን ደግሞ ከትግራይ አስተዳደር ሥር በማድረግ የትግራይን ሕዝብ ከጎንደር ሕዝብ ጋር እያጋጩት ነው። የወሎ ሕዝብም ከአገው ፣ ከአማራ ፣ ከትግሬ ፣ከኦሮሞ፣ ሌሎችም የተደባለቀ ይሁን እንጂ በወረራ በጉልበት በህወሐት መያዙን፣ ፈቅዶ አልተቀበለውም ። ሕዝቡን አፍነው በኃይል በመያዛቸው፣ ያለርኅራኄ ጨፍጫፊና አማቂም በመሆናቸው፣ ለጊዜው በጉልበትና ሃይል፣ በአፈና፣ “ረጭታ” መፈጥሩን፣ ሠላምና መረጋጋት የተፈጠረ መስሏቸው ከሆነም እጅጉን ተሳስተዋል ። ከዚህ ቅዠት ሊላላቀቁ ይገባል እላለሁ። ለሁሉም የሚበጀው በሀገራችን ዉስጥ በሠላም የሁኔታዎች መስተካከል ስለሆነ የህወሓት መሪዎች ከአስተሳሰብ ደሀነታቸው፣ ከዕብሪታቸው፣ ከምግባረ-ብልሹነታቸው፣ ከአጥፊነት ተግባሮቻቸው እንዲላቀቁ ያስፈልጋል እላለሁ።
7- የህወሐት መሪዎች በበርካታ ተግባራቸው ደጋግመው እንደገለጹት ሰብዓዊ ርኅራኄ የላቸውም። ገና በትግል ላይ ሆነው በደረሰው ድርቅ ወቅት በስሙ ለሚጠቀሙበት የትግራይ ሕዝብ ጭምር መቆርቆር፣ ሃዘኔታ ርኀራኄ የሌላችው መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ያለበቂ ዝግጅት ሕዝቡን ወደ ሱዳን (ወዲ ከውሊ)እንዲወጣ አድርገው ለከባድ ዕልቂት መዳረጋቸው፣ እስካሁን በህዝቡ ላይ የሚያደርሱት ግድያ፣ድብደባ፣ ውስራት፣ ማሰቃየትና ከፍተኛ በደል በቂ መረጃዎች ናቸው።
ህወሐት ከአጋሮቹ ከኤርትራዊ ሕዝባዊ ግንባርና ከሱዳን ጋር ሆኖ፣ ወደ መጨረሻም ኢህአደግ የሚባል ስብስብ ፈጥሮና እሱኑ በመቆጣጠርና እንደአስፈላጊነቱም በመጠቀም ነበር በ1983 ዓም በኢትዮጵያ ውስጥ የፖሊቲካ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው። በተለይም የአሜሪካንና የእንግሊዝን ይሁንታ፣ ድጋፍ ትብብር አግኝቶ በነሱም አማካኝነት የምዕራባውያን ድጋፍና እርዳታም እንዲያገኝ ተመቻችቶለት ነው የተቆናጠጠው። ዛሬም ቢሆን ህወሐት ኢሕአደግ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍና ይሁንታን አግኝቶ አይደለም እየገዛ ያለው።
በተለይም በግንቦት 1997 ዓ.ም. ምርጫ ህወሐት / ኢሐአዴግ በኅብረትና በቅንጅት መሸነፉን አልቀበልም ብሎ በጭፍጨፋና እመቃ ወደ መግዛት ከተሠማራ በኋላ፣ ኢትዮጵያውያን ለህወሐት /ኢሕአደግ የነበራቸውን ጥቂት ድጋፍ እንኳን ያለጥርጥር ነፍገውታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በፀጥታው በፖሊስ ፣ እንዲሁም በወታደራዊ ኃይሉ አፍኖ ይዞ ነው፣እየገዛ ያለው። ህወሀት/ ኢህአደግ የመንግሥትን መዋቅር የተለያዩ ዘርፎች ( እንደ አንድ የኩባንያ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ) በአንድ ዕዝ ውስጥ አስገብቶ በሥልጣን ላይ ያሉት (የህወሐትና የኢህአድግ አባል ድርጅቶች) ማለትም የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ መስተዳድሩ (ጠቅላይ ሚንስትሩና ሚኒስተሮቹ)፣ ፓርላማው ፣ እንዲሁም የዳኝነት ሰጭው ዘርፍ ከስማቸው ልዩነት በስተቀር ሁሉንም ታማኞችን ወይም ታዛዦችን በየስፍራዎቹ አስቀምጠው አቆራኝተው ነው የሚያንቀሳቅሷቸው። በፊት ያለእወጃ፣ አሁን ደግሞ በአዋጅና በይፋ ኢትዮጵያን በወታደራዊ አምባገነን አስተዳደር ሥር አስገብተዋታል። ሁሉም ዜጋ ነፃነቱን አጥቷል። አድርባዮችና ታዛዦችም ቢሆኑ እየፈሩና እየተሽቆጠቆጡ ነው የሚኖሩት።
በታሪኩ ታላቅነትን የተላበሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ ጥቂት የህወሓት መሪዎች፣ ኢሰብዓዊነት የተቆራኛቸው ጠባብ-ብሔረተኞች፣ የራዕይ-ደሀዎች፣ ኅሊና-ቢሶች፣ ምግባረ-ብሉሹዎችና አምባገነኖች በቀጣይነት ሊገዛና ሊሠቃይ አይገባውም። ዛሬ በጎልማሳነት ዕድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኝ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ በተለይም በወጣትነት ዕድሜ ክልል ያላችሁት ኢትዮጵያውያን በሙሉ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከነዚህ አጥፊዎች ለማላቀቅና አንድነትዋ የተጠበቀ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ታሪካዊ ተልዕኮ ስላለባችሁ በሙል ልባችሁ ቆርጣችሁና እጅለጅ ተያይዛችሁ ልትታገሏቸው ይገባል እላለሁ። እኛ አዛውንቶችም ጉዳዩ ስለሚመለከትን፣ ልንተባበራችሁና አቅማችን በፈቀደልን መጠን ልናግዛችሁ ይገባል እላለሁ።
የሀገራችንን ሁለንተናዊ ሁኔታዎች በበቂ ካለመረዳት፣ ከጠቅላላ ዕውቀት ወይንም ከተመክሮ ማነስ፣ ከራዕይ ደሀነት፣ ከኋላቀርነት፣ከርዕዮተ-ዓለማዊ ቀኖናዊነት፣ … ባላፉት የትግልና የለውጥ ዓመቶች ዉስጥ በ አያሌ ተዋናዮች ስህተቶች ተሠርተዋል። አሁን መሰል ስህተቶችን ልንሠራ አይገባንም።
- በአሁኑ ወቅት ለዐለማችን፣ በተለይም “ሦስተኛው” ዐለም ለሚባለው፣ ከዚያም በላቀና በጎላ ደረጃ ለአፍሪካ … ትልቅ ሕዝባዊ ራዕይ ያላቸው፣ ሰብአዊነት ያላቸው (የሚሰማቸው)፣ በሰው ልጅ እኩልነት የሚያምኑ፣ ለማኅበራዊ-ፍትኅ የቆሙ፣ ዕውቀት ያላቸውና ሁሌም ለመማር ዝግጁ የሆኑ፣ በሥነ-ምግባር የታነፁ(የማይሰርቁ፣ የማይቀጥፉ፣ ግለኞችና ስግብግቦች ያልሆኑ፣ … )፣ የባዕዳን አገልጋዮች ያልሆኑ፣ መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ፣ … መሪዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም ሃይሎች፣ ያስፈልጋሉ።
- እንደዚህ ያሉ መሪዎች ወይንም የፖለቲካ ድርጅቶች/ሃይሎች ካሉ፣ እነሱን ፈልጎ መቀላቀል፣ መደገፍና ማጠናከር፣ ከሌሉም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕት ከፍሎ መፍጠርና ማጠናከር ያስፈልጋል እላለሁ። ድልን ለመቀዳጀት የጠንካራ ድርጅት መኖር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነውና!!
- ለተለያዩ ዓላማዎችና በተለያዩ መልኮች መደራጀት ይቻላል። ሆኖም ግን የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ አጠቃላይ ሁኔታዎችን ለመለወጥ የሚቻለው በቅድሚያ ለዚህ ዓላማ ብሎ የተደራጀ፣ ብቁ አመራር ያለው፣ ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅት ሲኖር ነው። የሙያ ማኅበራትም ያስፈልጋሉ፣ ሚናቸው ለየት ያለ ቢሆንም። እነደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ድርጅቶች ባሉበት ሀገር ደግሞ የድርጅቶች በኅብረት መታገል በጣም አስፈላጊ ነው እላለሁ።
- እንደ ኢትዮጵያ ያለች ትልቅና ታሪካዊ ሀገር የተፈጠረችው ከሕዝቡ አብራክ የወጡ ትልልቅ ራዕይ የነበራቸው ሰዎች ስለነበሩ ነው። ሌላ ተዓምር የለውም። በዛሬው፣ አንዳንዴም በራሳችን ውሱን አመለካከትና የተዛባ መነፅር የወትሮዎችን የታሪካችን ፈጣሪዎች ለማየት እየሞከርን፣ የግንዛቤችንን ልዩነት ያመጣው ምን እንደሆነ በውል ሳናጤን፣ የቀደምት መሪዎችን ሚና መካድ፣ ማኮሰስ፣ አለ አግባብ ማባዘት ዉስጥ እንገባለን። ሚዛናዊነት ሊኖረን ይገባል። ሀገርም ሆነ ሕዝብ ለለጣቂ ህላዌአቸው በጎ ጎኖቻቸው ጎልተው የሚታዩ ታሪካዊ መሪዎችን ዐርአያነት ይፈልጋሉ። በዚህ ረገድ የኛ ትውልድም ትልልቅ ስህተቶችን ፈጽሟል።
- ዐለም በአንድ በኩል አብዛኛዎቹ በተወሰኑ የሠለጠኑና የዳበሩ ሀገሮች ዉስጥ በሚገኙ ሀብታሞች እጅ በተትረፈረፈ ሀብት የሚጨማለቁባት፣ በሌላ በኩል በአመዛኙ በሦስተኛው ዐለም ዉስጥ የሚገኙ ዐዕላፍ ሚሊዮኖች በድህነት ማጥ ዉስጥ እየነፈሩ የሚገኙባት፣ በሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ በዴሞክራሲያዊ መብት እጦት፣ በእኩልነትና የሕግ የበላይነት አለመኖር፣ በማኅበራዊ ፍትኅ እጦት፣ … እየተሰቃዩ ያሉባት ናት!? በመሀከሉ ጥረውና ግረው መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን አሟልተው የሚኖሩ የሕዝብ ክፍሎችም አሉ። ሠራተኞች፣ አራሾች፣ አምራቾች፣ አዳዲስ ነገሮችንም ፈጣሪዎች፣ ግልጋሎት ሰጭዎች፣ ቀረጥ ከፋዮች፣ ዕዳውን ሁሉ ተሸካሚዎች ሆነው ሀገርን ይታደጋሉ።
- መላው የዐለም ሕዝብ በኑክሊአር አውዳሚ ጦርነት አደጋ ዉስጥ ነው የሚኖረው።አብዛኛው የሦስተኛው ዐለም ሕዝብ ሠላም አጥቶ በየአካባቢዎቹ በተቀጣጠሉ ጦርነቶችና ግጭቶች እየታመሠና እየተደቆሰም ነው የሚገኘው። እነዚህ ጦርነቶች ዉስጥ የሚሳተፉ የተበደሉና የተከፉ ክፍሎች፣ አለዚያም እዚሁ ጽሁፍ ዉስጥ በተዘዘሩ ሌሎች ምክንያቶች የተነሳሱ የየአካባቢዎቹ ተወላጆች ቢኖሩም፣ በቀጥታም ሆነ በስውር ጦርነርቶች እንዲቀሰቀሱ ወይንም እንዲባባሱ የሚያደርጉ በሁኔታዎች ተጠቃሚ የሆኑ፣ የየሀገሮችን የተፍጥሮ ሃብት መዝረፍ አለዚያም መቆጣጠር የሚሹ፣ በግል ጥቅም የታወሩ፣ የሚፈጽሙት ግፍና በደል ደንታ የማይሰጣቸው መሠሪ ሃይሎች ዐለማችን ዉስጥ ዛሬም አሉ። የእነዚህን ሃይሎች ተንኮልና ደባ በመቋቋም ዐለም ዉስጥ፣ በተለይም ሦስተኛው ዓለም ዉስጥ፣ ሕዝቡ የተጠማውን ሠላም ለማምጣት ከባድ ትግል ሊደረግ ይገባል። ይህ ደግሞ ባለ-ራዕይ መሪዎችን፣ ጠንካራና “ድርጅታዊ ነፃነቱን” ጠብቆ ለቆመለት ዓላማ የሚፋለም የፖለቲካ ድርጅት መኖርን ይጠይቃል። የባዕዳኑ ታዛዥና ሎሌ ያልሆነ፣ በፍርፋሪ የማይገዛ አመራር ያለው ማለት ነው።
- የኃይማኖት አክራሪነት፣ ዘረኛነት በተለይም አሁንም እያቆጠቆጠ ያለው የነጭ ዘረኛነት፣ ጠባብ-ብሔረተኛነት፣ ጎሰኛነት፣ አክራሪ ርዕዮተ-ዐለማዊ ቀኖናዊነት፣ … በእኔ እምነት የዕውቀት ማነስ፣ የሀሳብ ደሀነት ውጤቶችና በአንድ ሀገር፣ ወይም ሠፋ ባለ አካባቢ፣ በአህጉር ደረጃ እውንዲሁም በዐለም ሕዝብ ላይ ጥፋትና ጉዳትን የሚያመጡ ያለጥርጥር ጎጅ ክስተቶች ናቸው። እኛን ኢትዮጵያውያንን አይጠቅሙምና በሚያቆጠቁጡባቸው ወቅቶችና አካባቢዎች ሁሉ ምንነታቸውን በማሳየት በሃሳብ ደረጃ ጠንካራ ትግል ተደርጎ ባዶነታቸውን፣ ጎጅነታቸውን፣ በማሳየት በተባ ክርክር ሊሸነፉ ይገባል።
- በኔ ዕምነት አሁን እያደገ እየጎለመሰና እየበሰለም በመምጣት ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ ወጣት ትውልድ፣ በሕዝቡ የተተፋውንና እየተንገዳገደም ያለውን የህ.ወ.ሓ.ት/ኢ.ህ.አ.ዴ.ግን ሥርዓት በትግል አስወግዶ፣ በምትኩም የኢትዮጵያን ሀገራዊ አንድነት የሚጠብቅ፣ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን/ት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚያከብር፣ የዜጎችን እኩልነት መብት በሁሉም ዘርፍ የሚያከብር(የእምነት፣ የቋንቋ፣የባኅል፣የፆታ … )፣ የሕግ የበላይነትን ያለ ማወላወል የሚያረጋገጥ፣ አሁን ያለውን በቅራኔዎች የተወጣጠሩ የቋንቋ ክልሎች “ፌደሬሽን” በሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ፣ አስተዳደራዊ-ምቹነት፣ … ሚዛኖች ተጠንቶ በሚቋቋም ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚተካ፣ የፖለቲካ ሥልጣን በኢትዮጵያውያን ነፃ፣ ርትዓዊና፣ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ብቻ የሚመነጭበት ሥርዓት ለማምጣት በሙሉ ልቡ ሊታገል ይገባዋል። ወጣቱ ትውልድ ለሀገራዊ አንድነቱና ነፃነቱ ቀናዔ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ያገናዘበ ሀገራዊ ዓላማ አንግቦ፣ በሙሉ ልቡ ቆርጦ ከተነሳና፣ በሚመጥን ደረጃም ነፃነቱን በትግሉ እያረጋገጠ ተደራጅቶ ከታገለ ድል የማይቀዳጅበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ታዲያ ማንኛውም ትልቅ ነገር ዋጋ አለውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከቀጣይ መከራ፣ ሀገራችንን ከጥፋት የመታደግ ክቡርና ንዑድ ዓላማ ደግሞ ያለ ጥርጥር መስዋዕት ያስከፍላል። ይህ የማይቀር ነው! ተገቢ መስዋዕት ነውና ሊያስፈራን ግን በጭራሽ አይገባም እላለሁ።
መርሻ ዮሴፍ
No comments:
Post a Comment