ጌታቸው በቀለ | የጉዳያችን የጡመራ ገጽ አዘጋጅ
ርኩስ መንፈስን “በኢየሱስ ስም” እያሉ ሊያወጡት ሲሞክሩ መንፈሱ “ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው።የሐዋርያት ሥራ 19፣15
==================ሰሞኑን በኤርትራ በትግል ላይ የነበረው አርበኛ ዘመነ ካሴ ከኤርትራ ወጥቶ ሌላ ሀገር ሕክምና ላይ መሆኑን ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋው በፌስ ቡክ ገፁ ገለጠ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም በሎስ አንጀለስ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ በነበረ ሕዝባዊ ስብሰባ ይህንኑ ከጋዜጠኛ ሙሉ ቀን ቃል ጋር የማይጋጭ ቃል ተናገሩ። ጋዜጠኛ ሙሉ ቀን ስለ አርበኞች ግንቦት 7 አንዳች የሚነቅፍ ቃልም ሆነ ስም ጠርቶ የተናገረው ነገር የለም።ጋዜጠኛው በተለያዩ መድረኮች እንደምናገረውም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ ሲናገር እንደማውቀው እጅግ ቁጥብ፣ማንንም ክብር የማይነካ እና ለሁሉም የተቃዋሚ ኃይል ክብር የሚሰጥ ነው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋም ሆኑ ድርጅታቸው እስካሁን በድርጅት መግለጫ መልክም ሆነ በየትኛውም መድረክ የእከሌ ብሔር እንዲህ ነው ወዘተ የሚል ሕዝብ የሚያስቀይም ንግገር ሲናገሩ አልሰማሁም።ታጋይ ዘመነ ካሴም በለቀቀው ቪድዮ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት ላይ ያለውን ክብር ገልጦ በሙሉቀን የተጀመረው የገንዘብ ማሰባሰብ በእርሱ እውቅና መሆኑን ገልጧል። እነኝህ ዜናዎች ሁሉ ላይ አንዳችም የእርስ በርስ መቃረን አይታይም።ታጋይ ዘመነ ነገ የትግል ስልቴ ይህ ነው ብሎ አዲስ ሃሳብ ቢያመጣም (አመጣ ሳይሆን ያልኩት ቢያመጣም ነው) መብቱ ነው።ይልቁንም አርበኞች ግንቦት 7 አንድ አባሉ ያውም በኮማንደር ደረጃ ያለ አባሉ የፈለገውን መንገድ እንዲመርጥ በማክበር ምርጫውን በመስጠቱ ሊመሰገን ይገባዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክ አንድ አባል የእራሱን ምርጫ ቢመርጥ አይደለም ገና ለገና ከድርጅቱ ሊወጣ ያስባል የሚል ጥርጣሬ ካለ የሚወሰደው እርምጅ ምን እንደሆነ የቅርብ ድርሳናትን ማገላበጥ በቂ ነው።
ባጭሩ ምን ለማለት ነው የፈለኩት?
ሰሞኑን ጋዜጠኛ ሙሉቀን ያላለውን፣አርበኞች ግንቦት 7 ያልሆነውን አለ እና ተደረገ እያሉ የሚፅፉ እና በተለያየ የስውር ስም (anonymous) እየተጠቀሙ ወሬ ሲነዙ የነበሩ እነማን ነበሩ? የተሳሳቱም ካሉ ሳያጣሩ በመናገር እነማን አሳስተውብን ይሆን? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው። ይህ የዘመነ ካሴ ጉዳይ ለተቃዋሚ ጎራ አንድ አስተማሪ ጉዳይ ነው። በስውር ስም (anonymous) ፌስ ቡክ ስም የተፃፉ መልዕክቶች እንደ ዜና ምንጭ እያደረግን ለሌሎች የምናካፍል ጥንቃቄ እናድርግ።በስውር ስም ሳይሆኑ በስማቸው እየፃፉ ነገር ግን ትንሽ ጫፍ ይዘው የነበሩበት ለማስመሰል አንድ ገፅ የሚፅፉም ትዝብት ላይ እየወደቁ መሆኑን ቢረዱት ጥሩ ነው።ለጊዜው ግን ማለት የሚቻለው – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እናውቀዋለን፣ዘመነ ካሴን እናውቀዋለን፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ሙሉቀን ተስፋውንም እናውቀዋለን እናንተ ግን ማን ናችሁ?
“ኢየሱስን አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተ ደግሞ ማን ናችሁ?” አላቸው።የሐዋርያት ሥራ 19፣15
No comments:
Post a Comment