Thursday, June 1, 2017

በሳዑዲ አረቢያ ምሬቱ እና መጉላላቱ እንደቀጠለ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ገለጹ


    

(ቢቢኤን) ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አስፈላጊውን ፕሮሰስ ማለፍ ያለባቸው ስደተኛ ኢትዮጵያውያን፣ አሁንም ከመጉላላት እና ከምሬት አለመዳናቸውን ተናገሩ፡፡ እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገለጻ ከሆነ፣ በጂዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤትም ሆነ በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚዲያ የሚናገረው እና በተግባር እየሰራ ያለው ስራ የተለያየ ሲሆን፣ ወደተጠቀሱት ቢሮዎች የሔዱ ኢትዮጵያውንም አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ በምሬት እየገለጹ ናቸው፡፡
በተለይ ደግሞ በየቀኑ ለመሳፈሪያ 100 ሪያል እያወጡ ከመኖሪያቸው ኤምባሲ እና ቆንጽላ ጽህፈት ቤት መመላለሱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሚገኝ የገለጹት ኢትዮጵያውያኑ፣ በየቀኑ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ቢመላለሱም ጉዳያቸውን ማስፈጸም እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ያወጣው የምህረት አዋጅ ሊጠናቀቅ ከአንድ ወር በታች የሆኑ ቀናት በቀሩበት በዚህ ሰዓት፣ ፕሮሰሳቸው መሔድ የሚገባውን ያህል አለመሔዱ እንዳሰጋቸውም ገልጸዋል፡፡ ቆንጽላውም ሆነ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚያወጡት ተደጋጋሚ ማስታወቂያዎች ላይ፣ ስደተኞችን በተቀላጠፈ ሁኔታ እያስተናገዱ እንደሆነ የሚናገሩት ሁሉ ውሸት መሆኑን የሚናገሩት ስደተኞቹ፣ ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
የምህረት ቀኑ እያለቀ መምጣቱ ያሰጋቸው ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ፣ በለቅሶ ጭምር አቤቱታ ሲያቀርቡ የሚያመላክቱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወጥተዋል፡፡ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፣ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ደፋ ቀና እያሉ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ሳዑዲ ውስጥ እየተደረገ ያለው ነገር ግን ባለስልጣናቱ ከሚናገሩት ጋር ፍጹም የተቃረነ መሆኑን የዓይን እማኞች ይገልጻሉ፡፡ የኢትዮጵያ አምባሲ እና ቆንጽላው ለስደተኞች ደንታ የሌላው መሆናውን የሚናገሩት ስደተኞቹ፣ ዜጎች እንዴት መስተናገድ እዳለባቸው ከሌሎች ሀገራት ኤምባሲዎች እንዲማሩ ተናግረዋል፡፡ በሳዑዲ አረቢያ ከ300 ሺህ በላይ ወረቀት አልባ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ይገለጻል፡፡ የምህረት አዋጁም እነዚህን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ,ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን በእጅጉ ትንሽ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

No comments:

Post a Comment