Tuesday, August 29, 2017

በሚኢሶ በኦሮሞ አርሶ አደሮችና በሱማሌ ልዩ ታጣቂ ሃይል ውጊያ ተከፈተ-ቄሮዎች ለሀገር አቀፉ አድማ ዝግጁ ነን አሉ – በወንድወሰን ተክሉ


By ሳተናውAugust 29, 2017 07:59


 

በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን በሀረርጌ ሚኤሶ ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ በኦሮሞ አርሶ አደሮችና በሱማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሚሊሺያ መካከል ለሰዓት የዘለቀ ውጊያ መካሄዱን ኢሳት ከስፍራው የነበሩትን ተሳታፊዎች ድምጽ ጠቅሶ የዘገበ ሲሆን የግጭቱም መንስኤ የድንበር ውዝግብ እንደሆነ ለማወቅ ተችላል።
ባለፈው ሳምንት ከረቡእ እስከ ዓርብ ለሶስት ቀናት ዘልቆ የነበረውና በመላ ኦሮሚያ ተግባራዊ የሆነው የስራ ማቆም አድማ ካነሳቸው ሶስት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው በሱማሌ ክልል በኩል እየተካሄደ ያለውን ድንበር ዘለል ጥቃትና የመሬት ወረራን መንግስት በአስቸካይ እንዲያቆም የሚጠይቅ ሲሆን በዚህ የመሬት ይገባኛል ውዝግ ላይ ከአካባቢው ነዋሪዎች የተውጣጡ ሽማግሌዎች የአቤቱት ማመልከቻ ይዘው ለጠ/ሚ/ሩ እና ለተወካዮች ምክር ቤት ለመስጠት አዲስ አበባ መሄዳቸው መገለጹ ይታወሳል።
መላው ኦሮሚያ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የስራ ማቆም አድማ ከተጥለቀለቀበት አንዱ በሆነው የኦሮሚያና ሱማሌ ክልል የድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቶ በሚኤሶ ባሉት ሁለት ቀበሌዎች ላይ ለማጥቃት ከመጣው የሱማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ ሃይል ጋር የአካባቢው አርሶ አደር ለሰዓት ያህል ለመዋጋት እንደተገደዱ ማወቅ የተቻለ ሲሆን በውጊያው ሶስት አርሶ አደሮች የመቁሰል አደጋ እንደገጠማቸውና አንደኛው በጸና በመቁሰሉ ለህክምና ወደ አዳማ እንደተወሰደ ኢሳት ዘግባል።
በእኛ በኩል የረባ መሳሪያ የለንም ያሉት የኦሮሞ አርሶ አደሮች የሱማሌው ልዩ ፖሊስ ግን መንግስት ባስታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ እራሱን ያስታጠቀ መሆንኑ ገልጸው ከፌዴራሉም ሆነ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስም ሆነ ሰራዊት እንዳልተገኘ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
የሱማሌ ክልል ለረዥም ግዜ በምስራቃዊው የኦሮሚያ ግዛት ባቢሌ ጉርሱም አካባቢ ይገባኛል ያላቸውን የኦሮሚያን ግዛቶች በወረራ ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ ውጊያዎች በመክፈት የሚታወቅ ሲሆን የኦጋዴንን ክልል ነዋሪዎችን በተለይም የስርዓቱ ደጋፊና አባል ባልሆኑት ላይ አሰቃቂ እርምጃ በመውሰድ ጭካኔው የሚታወቅ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ወጣቶች በተለምዶ አጠራር ቄሮዎች እየደረሰብን ያለውን በደል በግላችን ብቻ በመታገል ሳይሆን ከሌሎችም ጋር ተባብሮ በመታገል እንፈተዋለን ብለው እንደሚያምኑ የገለጹ ሲሆን የፊታችን መስከረም የኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት በታቀደው ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ተዘጋጅተናልም ሲሉ በተለይ ለኢሳት ገልጸዋል።
ቄሮዎቹ በአማራ ክልል ወጣቶች በተጠራው ሀገራዊ የስራ ማቆም አድማን በንቃት እንደሚሳተፉ ተናግረው ይህን ስርዓት በህብረት ትግል እንጂ በተናጥል ትግል ጥያቄያችንን እንዲመልስ ማድረግ አይቻልም ሲሉ ተደምጠዋል።
በአማራ ክልል ወጣቶች የተጠረው ሀገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ በመጪው መስከረም 2-3 እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment