Monday, August 14, 2017

የሜቴክ ሌብነት በትራንስፖርት ሴክተር



የሜቴክ ሌብነት በትራንስፖርት ሴክተር (ክፍል አንድ) በበዛብህ ሲሳይ , ሀይድራባድ ህንድ (2009)
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑ በቀድሞ የስርዓቱ ልሳን በነበረው በአቶ ኤርሚያስ ለገሰ ያስነበበን ሜቴክ ከንግድ መርከብ ስለገዛቸው ሁለት መርከቦች እና ሊያቋቁመው ስላሰበው የውሃ ትራንስፖርት ንግድ ስራ እንዲሁም በአገሪቷ ላይ ያደረሰውን ኪሳራ ካየሁ በኃላ ነው፡፡ እውነት ነው ተቋሙ ሲቋቋም ጀምሮ ለገዢው ጉጅሌ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ እንዲያመጣ ተብሎ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ተወላጆችን በሰሜን በኤርትራዋኖች ለይ እንዲሁም በደቡብ ደግሞ በሰፊው የኢትዮጰያ ህዝብ ላይ የፖለቲካዊ ልእልና እንዲኖራቸው በማሰብ ጭምር ነው፡፡
ስለዚህ አቶ ኤርምያስ እንደ አስቀመጠው የሜቴክ መሪዎቹ ሲጋራን በቄንጥ ሚያጨሱ ብቻ ሳይሆኑ ለዚህ እኩይ አላማቸው የሚሳተፉላቸውን ሆድ-አደር ምሁራንን ወይም ባለሰርተፊኬቶችን እንዴት ማስተዳደርና መጠቀም እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ሌብነቱ እጅግ የረቀቀ እንዲሆንና ጉዳቱም የብዙ ቀጣይ ትውልዶች መስዋትነት የሚጠይቅ እንዲሆን አስችሏል፡፡ ለዚህ እኩይ አላማቸውም አንዳንዳዴም የፈረንጅ ጫማ ላሾችንም (Bootlikers) ይጠቀማሉ ለምሳሌ እንደነ ዴቪድ ዴጎር ያሉ የአለም ባንክ ሰራተኛ ሳይሆኑ ከመንግስት ሌቦች ጋር በድለላ በመሳተፍ ሌብነቱን የሚያጧጥፉትን ያቀርቧቸዋል፡፡
ይህ ግለሰብ በተለይ ለአርከበ፣ ለመኩሪያ፣ እንዲሁም ለወርቅነህ እጅግ ቅርብ እንደሆነ እና ተቀማጭነቱን ደቡብ አፍሪካ አድርጎ የሌብነት ድለላውን በቢሊየን ዶላር የሚያጧጥፋ ነው፡፡ በነገራችን የአለም ባንክ ሆኑ ሌሎች አበዳሪ ተቋማት እንደነዚህ አይነት የት እንደሚሰሩ ማይታወቅ ግለሰቦችን የሚጠቀሙት በሚፈጸመው ወንጀል ላለመጠየቅ ነው፡፡ ሌሎች ከአገር ዉስጥ ደግሞ የሲ.አይ ኤ ትክሎች ከሆኑት አንድሪያስ እሸቴ፣ አብዱ እንዲሁም በስመ ኢኮኖሚስት የሚነግደው ዘመዴነህ ንጋቱ የድለላውን ስራ ከሚያቀላጥፉት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህና በሚቀጥለው ፅሁፌ ሜቴክ በትራንፖርት ሴክተሩ የሚፈፅመውን ሌብነትና እነማን በ ‘ምሁር-ነን’ ሰበብ ተልዕኮውን እንዲያሳካ እንደሚረዱት እናያለን፡፡ መልካም ንባብ! ገዥው ህውሃት ለሃያ ስድስተ አመታት ሲያራምደው እንደነበረው የሌብነት ፖሊሲ ሜቴክም መቆጣጠር የሚፈልገው የኢኮኖሚ አውታር በዋነኝነት ከአገር ውስጥ ወይም ከዉጭ ሃገር ልዩ የፋይናንስ ድጋፍ ያላቸውን የኢኮኖሚ ሴክተሮች ሲሆን ትራንስፖርት ደግሞ አንዱና ዋነኛ ነው፡፡
የአለም ባንክ፣የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የቻይና ኤግዚም ባንክ አብዛኛውን ብድራቸውን የሚሰጡት ለዚሁ ለትራንስፖርት መሰረተ-ልማት ግንባታ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሜቴክ ገና ጥርሱን ሳይነቅል ዘሎ ዝርፊያውን የጀመረው የቀድሞ ኢትዮ- ጂቡቲ ባቡር ሃዲድ በመንቀልና በመመዝበር የሆነው፡፡ ለዚህም አዛኝ መስሎ የተበተነውን የቀድሞ የባቡር ሰራተኞችን ደሞዝ እከፍላለሁ በሚል ተልካሻ ሰበብ ድርጅቱን በስውር በመውረስ ጅቡቲን ያህል አገር መስዋዕትነት የከፈልንበትን ታሪካዊውን የባቡር ሃዲድ ወረሰው፡፡ ሃዲዱም በ1907 የተመረተ ንፁህ የባቡር ሃዲድ ብረት ነበር፡፡ ይህንን ውንብድና ለማገዝ አዲሱ የባቡር ፕላን ሆን ተብሎ የድሮውን ወደ 12 ቦታ እንዲቆርጠው በማድረግ የቀድሞው መስመር መልሶ ለአገልግሎት እንዳይውል ለአንዴና ለመጨረሻ ወንበዴው ሜቴክ ወሰነበት፡፡
የሚያሳዝነው ይህ የቀድሞ የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2006 ከአውሮጳ ህብረት በተገኘ የ50 ሚሊዮን ዩሮ ብድር የመልሶ ማልማት ስራ ጀምሮ የነበረ ሲሆን ሜቴክ ሲያቋርጠው ብዙም ስራ ተሰርቶ ነበር (ግርጌ ፎቶውን ይመልከቱ)፡፡ በመስኩ የተሰማሩ ባለሞያዎች እንሚሉት የቀድሞ የባቡር መስመር በትክክል ቢሰራ ኢትዮጵያ የምታስገባውንም ሆነ የምታስወጣውን ጭነት በአስተማማኝ ከማስተናገዱ አልፎ ሃገሪቱ በሚቀጥሉት ሃያ አመታት ልታመጣው የምትችለውን (የሚባለውን የ7%)የኢኮኖሚ እድገትም መሸከም የሚችል ነበር፡፡ ይሄ ለጄ/ር ክንፈ እና ዶ/ር አርከበ የሚገባ ስሌት አይመስለኝም፡፡ አራቱን የሂሳብ ስሌቶች እንኳን በቅጡ ማስላት እንደሚከብዳቸው ከነሱ ጋር የሰራ ሁሉ ያውቃል፡፡ ለዚህም ነው የአዲስ አበባ ባቡርም በሰዓት ሃያ ሺህ ህዝብ ያመላልሳል ብለው ቡፋያቸወን ነፍተው አመት እንኳን ሳይሆነው ከ41 ባቡሮች 19ኙ በመለዋወጫ እጦት እንደማይሰሩ ሪፖርተር ያስነበበን፡፡ ወደ ኢትዮ- ጂቡቲ ባቡር ስንመለስ ሌላ ቢቀር እንኳን ታሪካዊነቱ ታይቶ ልክ በሰለጠኑት አገራት እንደሚገኙት የድሮ የባቡር መስመሮች ለቱሪዚም አገልግሎት መዋል ይችል ነበር፡፡
በተለይ አዲስ ከተዘረጋው መስመር በበለጠ በብዙ ከተሞች ላይ ማረፊያ ተሪሚናሉች ስላሉት ከተሞችን በበለጠ በንግድ በማስተሳሰር ከፍተኛ አስተዎጽኦ ማምጣት ይችል ነበር፡፡ይሄም አዲሱ ባቡር ወደ 32 በሚሆኑ ቦታ/ከተሞች ላይ ብቻ ሲያርፍ የቀድሞ ባቡር ግን ከ100 በላይ ቦታዎች/ከተሞች ላይ በማረፍ የባቡር መስመሩን ተከትለው በተቆረቆሩት ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን በበለጠ የኢኮኖሚና የማህበረሰብ ትስስራቸውን ያጠናክር ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ለታሪክ ምንም ደንታ የሌላቸው የትግራይ ጉጅሌዎችን ያቀፈው ሜቴክ ታሪካዊዉን የበቡር ሃዲድ ብረት ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ስልቅጥ አድርጎ በላው፡፡ በሚቀጥለው ፅሁፌ ደግሞ ሜቴክን ከጀርባ አዝለው ስለሚንቀሳቀሱ ሆድ-አደር ምሁሮችና የረቀቀ የሌብነት ሴራቸውን የአዲስ አበባ የመንገዶችና ትራንስፖርት ቢሮን እንዲሁም የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ኤጀንሲን ዋቢ በባድረግ ለማሳያየት እሞክራለሁ፡፡ ሰላም ሁኑ!

No comments:

Post a Comment