Wednesday, August 2, 2017

ማለቂያ የሌለውና፣ አሰልቺው የህወሃት/ኢህአዴግ ‘ጸረ-ሙስና’ ዘመቻ -አበጋዝ ወንድሙ



  
August 1, 2017      
 

ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት አንደከዚህ ቀደሙ፣ ዘንድሮም የጸረ- ሙስና ዘመቻ በሚል  በትልቅ ጭጫታ አጅቦ አዲሱን ዘመቻውን  ይዞ  ብቅ ብሏል። የህወሃት/ኢህአዴግን ምንነት በቅጡ ያልተረዱ ወይንም የዘነጉ ወገኖች፣ እከሌ ታሰረ፣እከሌ ቀረ፣ እከሌማ ካልታሰረ ዘመቻው የምር አይደለም… ወዘተ የሚል አላስፈላጊ ውይይት ውስጥ ገብተው ሳይ ፣ ጎበዝ አንዘናጋ ለማለት እፈልጋለሁ።
ሙስና፣ የህውሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት መሰረታዊ  መገለጫ ባህሪው በመሆኑ፣ ይሄ ቡድን  ከስልጣን አስካልወረደ ድረስ አብሮን የሚኖር ፣ በሂደትም አየባሰበት በመሄድ ሀገራችንን  አጅግ በጣም አስቸጋሪ ወይንም ልንወጣው ወደማንችለው አዘቅት ውስጥ ሊከት አንድሚችል መገንዘብ የግድ ይላል።
ዛሬ አርባና  ሃምሳ ሰዎች በቁጥጥር ስር አድርጎ  የኢትዮጵያ  አራት ቢልዮን ብር ሊደርስ የሚችል ገንዘብ (እርግጥ ለኛ አይነት ደሃ ሃገር ገንዘቡ ብዙ ነው፣ መምዝበሩም ያሳዝናል ) ባክኗል ወይንም መንግስት እንዲያጣ ተደርጓል በሚል ቡራ ከረዩ የሚለው መንግስት፣ የዛሬ አምስት ዓመት የአውሮፓ ድርጅቶች ባወጡት ጥናት ከኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ 11 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ወደውጭ መውጣቱን ይፋ ሲያደርጉ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፉን ስናስታውስ፣  የዘንድሮው ዘመቻም ሙስናን ከመዋጋት ጋር ቀጥተኛ  ግንኙነት እንደሌለው እንረዳለን።
የህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት የሚጠቀምባቸውን ማደናገሪያ ተረቶችና በየጊዜው የሚታወጁ ዘመቻዎችን  ወደጎን ስናደርግ፣በሀገራችን የሙስናው ምንጭ ሌላ ነገር ሳይሆን፣ ከመሬትና ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን አንገነዘባለን። ይሄንን መሬትንና የመሬት ባለቤትነትን በሚመለከት የጠራ አመለካከት አስካልያዝን ድረስም በሀገሪቱ የተንሰራፋውን የሙስና ስርዓት ለማወቅ፣ አውቆም ለመታገል ያዳግተናል።
አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 40 ቁ 3 ‘የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የህዝብ ብቻ ነው። መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው።‘ ቢልም፣ በመሬት ላይ ያለው ገሃድ ሀቅ ግን፣ ላለፉት 26 ዓመታት መሬት በህውሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ከችርቻሮ አስከ  ጅምላ የሚቸበቸብ ተራ ሸቀጥ መሆኑ በማያወላዳ መንገድ ይታወቃል ።
 በስም፣ ባለቤት ተብለው በዚሁ ሀገ-መንግስት የተንቆለጳጰሱት ‘ብሔር  ብሔረሰቦችና ህዝቦች’ የደረሳቸው እጣ ፈንታ ደግሞ ከተማ ያሉት ከሶስትና አራት ትውልድ ወይንም ከዛ በላይ ከኖሩባቸው ቤቶችና ሰፈሮች በልማት ስም በጅምላ ተፈናቅሎ ወደ ከተማ ዳርቻ መወርወር፣ በአዲስ አበባ አካባቢ የሚኖሩ አርሶአደሮችንም አንዲሁ ጭብርብርና ጉልበት የታከለበት ያለበቂ ካሳ መፈናቀል፣ በበርካታ የሀገሪቱ  ግዛት የሚኖሩ አርሶ አደሮች ደግሞ፣ ለውጭ ባለሀብት በልማት ስም ‘የሚሰጥ’  መለስተኛ የአውሮፓ ሀገር የሚያህል መሬት ለማመቻቸት  ሺዎች በጉልበት መፈናቀልና ለስደትም መዳረግ ነው።
ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ስር ነቀል  ጸረ-ሙስና ዘመቻ አያካሄድኩ ነው ብሎ ሲያውጅ የዘንድሮው ሶስተኛ ወይንም አራተኛ ጊዜው ነው። ከባለፉት ዘመቻዎች የተረዳናቸው ነገሮች ቢኖሩ ፣ሙስናን መዋጋት የሚሉ ዘመቻዎች መንስኤ በጥቅሉ  ሶስት ሲሆኑ፣ አንዳቸውም ግን በቅንነት ሙስናን የመዋጋት አላማ የላቸውም።
አንደኛው ምክንያት የህዝብ ብሶት ጠንክሮ ወደ እንቅስቃሴ ሲያመራ፣ ለማስተንፈስ ወይንም አቅጣጫ ለማስቀየስ ፣ ሁለተኛ በውስጣቸው ያለው የስልጣን ወይንም የበላይነትን  የማስፈን ሽኩቻን መቋጫ፣ የተወሰኑ ሰዎችን ወህኒ የሚወረውሩበት ወይንም ከስልጣን ገሽሽ  የሚያደርጉበትና፣ ሶስተኛው ቅጥ ያጣ ዘረፋ አንደሚካሄድ በማየት እየደገፍናችሁ አታሳጡን፣ ለሚለው የምዕራብ ሀገሮች ተማጽኖ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው ለማለት የሚካሄዱ የይስሙላ ዘመቻዎች ናቸው።
ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት መሬትና የመሬት ባለቤትነት በሀገሪቱ የተንሰራፋው የሙስና ስርዓት ዋና ምንጭ መሆኑን ስለሚያውቅ በየጊዜው ማደናገሪያ ለመፍጠር ቢሞክርም፣ ይሄንን ተገንዝበውና ተረድተው ግን  የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስትን የሚያጋልጡና የሚታገሉ ወገኖችን  እንደ ደመኛ  ጠላቶቹ እንደሚያይ የበቀለ ገርባ ምሳሌ ያሳየናል ።
የኦፌኮና የመድረክ መሪ የነበረው በቀለ ገርባ የዛሬ ሰባት ዓመት ለምርጫ በተደረገ ክርክር ወቅት ይሄንን ሃቅ፣ ማለትም የሙስና ምንጭ የህውሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት መሬትን አንዴ ግል ሃብት በመቁጠር ፣ከሱ ጋር ለተጣቡት ሽልማት ፣የተወሰኑትን ለማማለልና ድጋፍ ለማግኘት ለጥቂቶች የቁርጥ ቀን ልጆቹ ደግሞ ‘በብርሃን ፍጥነት ተዝቆ ወደማያልቅ ሀብት የተመነጠቁበት መንኮራኩር ‘ አንደሆነ በማጋለጡ ይሄው አስከዛሬ ምክንያት አየተፈለገ በአስር አንዲማቅቅ ተደርጓል ።
ዛሬ ከህዝብ ተዘርፎ በተቸበችበ መሬት የህወሃት ቁንጮ ባለስልጣናት፣ወታደሮችና የጥቅም ተጋሪ በመሆን፣ በፍጥነት በመመስረትና በማደግ ላይ ያለው አዲስ የገዥ መደብ አባላት የሆኑ፣ ከልዩልዩ ብሄረሰብ የተውጣጡ ባለጊዜዎች በሚልዮንና በቢሊዮን ስለሚቆጠር ሃብት አንዱ ከአንዱ የሚፎካከሩበት ዘመን ደርሰናል።
የተቃዋሚ ሃይሎችና ህዝብም መንግስት የሚያካሂደውን ውዥንብር ፈጠራ ወደጎን በማድረግ ፣ትግሉን በቀጥታ የሙስና ምንጭ የሆነው መሬትና የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ፣ የዚህ አቀነባባርና መሪ ተዋናይ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ መሆኑን በመገንዘብ የመታገያ አጀንዳ
በማድረግ ሊታገሉት ይገባል።

No comments:

Post a Comment