ልዩ ፖሊስ በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ከፍተኛ ጭፍጨፋ እያካሔደ እንደሚገኝ ምንጮች ጠቆሙ፡፡ በዛሬው ዕለት ብቻ በኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል በሚገኘው ልዩ ኃይል በተከፈተው የተኩስ እሩምታ፣ ከሲቪል ነዋሪዎች በተጨማሪም ከኦሮሚያ ፖሊሶች መካከል የተገደሉ መኖራቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ያለ ማቋረጥ ግድያ እየፈጸመ የሚገኘው ልዩ ኃይል የተባለው ቡድን፣ ባለፉት ጊዜያት ያለ ማቋረጥ ግድያ ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ በዛሬው ዕለት የተፈጸመው ግድያም የሰሞኑ ተከታይ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡ ልዩ ኃይሉ በሚፈጽመው ግድያ የአካባቢው ነዋሪ መንገሽገሹን የሚገልጹት መረጃዎች፣ ነዋሪው በተደጋጋሚ ለኦሮሚያ ክልል መንግስት አቤቱታ ቢያቀርብም፣ የረባ ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡
በዚህም የተነሳ በህወሓት ልዩ ትዕዛዝ እና በኢትዮጵያው ሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ተባባሪነት የሚመራው ልዩ ኃይል፣ ያለ ማቋረጥ ግድያ እየፈጸመ እንደሚገኝ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ የዛሬውን ሳይጨምር ባለፉት ጊዜያት በልዩ ኃይሉ የተገደሉ ንጹኃን ሰዎች ቁጥር 61 መድረሱን የገለጹት ምንጮች፣ በልዩ ኃይሉ የሚገደሉ የኦሮሚያ ፖሊሶች ቁጥርም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡
ልዩ ኃይል የተባሉት እነዚሁ ፖሊሶች ከግድያ በተጨማሪ አስገድዶ መድፈር እና ዘረፋ ላይ መሰማራታቸውን የሚገልጹት መረጃዎች፣ በምስራቅ ሐረርጌ እያደረሱ ያሉት ግፍ እጅግ በዝቷል ይላሉ-መረጃዎቹ፡፡ በዛሬው ዕለት ጭፍጨፋ የተካሔደበት የምስራቅ ሐረርጌ ክፍል ሚኢሶ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች፣ ልዩ ኃይሉ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ማድረጉንም ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል፡፡ ከሞቱ የኦሮሚያ ፖሊሶች በተጨማሪም የቆሰሉ መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment