Tuesday, August 22, 2017

በባህርዳር ግብር ያልከፈሉ ነጋዴዎች በመታሰር ላይ መሆናቸው ታወቀ


By ሳተናውAugust 21, 2017 19:59



(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 15/2009)በባህርዳር ግብር ያልከፈሉ ነጋዴዎች በመታሰር ላይ መሆናቸው ታወቀ።
በተለያዩ ክፍለከተሞች በሚገኙ የቀበሌ እስር ቤቶች ከ500 በላይ ነጋዴዎች ታስረው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የባህርዳር ፖሊስ ቦምብ ያፈነዱትን ይዣለሁ በማለት የጀመረው የቪዲዮ ቀረጻ የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ በክልሉና በብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሚቀርብ ታውቋል።
በሌላ በኩል በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ጥብቅ ፍተሻ ሲደርግ ውሏል። በባህርዳር ነዋሪው የሌሊት ጥበቃ ሮንድ በፈረቃ እንዲደርሰው ሊደረግ ነው።
ግብር መክፈል ያልቻሉ አንዳንድ ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተው እየተሰወሩንም ነው ተብሏል።
ባህርዳር አሁንም በውጥረት ላይ መሆኗ ይነገራል። ነጋዴዎች በጅምላ እየታሰሩ ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እየታፈኑ ተወስደዋል።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንዳረጋገጡት በባህርዳር በየቀበሌው በሚገኙ እስር ቤቶች በትንሹ 500 የሚሆኑ ነጋዴዎች ታስረዋል።
የተራዘመው የግብር መክፈያ ቀነ ገደብ ካበቃ በኋላ፡ በየሱቅና መደብሩ የሄዱት የመንግስት ታጣቂዎች ግብር አልከፈላችሁም በሚል ነጋዴዎቹን እያፈሱ መውሰዳቸው ታውቋል።
ነሀሴ 1 የተገደሉ ሰማዕታትን ለማሰብ ከተጠራው የስራ ማቆም ጋር በተያያዘ የታሰሩት ከፍተኛ ነጋዴዎች በዋስ መለቀቃቸው በተገለጸበት በዛሬው ዕለት ግብር ያልከፈሉ ነጋዴዎች በየእስር ቤቱ መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ጨለማን ተገን በማድረግ በተለያዩ የባህርዳር ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶችን በማፈስ ወደአልታወቀ ቦታ መወሰዳቸውን ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
ወጣቶቹ አመጽ ታስተባብራላችሁ፡ በሚል የታፈሱ ሲሆን ከዚህ ቀደም በነበረው ህዝባዊ ንቅናቄ ምክንያት ታስረው በብር ሸለቆ ማሰልጠኛ ካምፕ ቆይተው የተፈቱትም በድጋሚ መታሰራቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ በተከታታይ የደረሱትን የቦምብ ፍንዳታዎች ፈጽመዋል በማለት 17 ግለሰቦችን ማሰሩን የባህርዳር ፖሊስ አስታውቋል።
አደጋውን እንዴት እንዳደረሱ የሚያስረዳ ዘጋቢ ፊልም እየተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች አንደኛው ወጣት በዚህ ዓይነት ድራማ አልሳተፍም በማለቱ ለእስር እንደበቃ መገለጹ ይታወሳል።
ከግብር ጋር በተያያዘ በሌሎች የምስራቅ ጎጃም ከተሞች ፍጥጫው አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስሩን በመሸሽ ነጋዴዎች ከአከባቢው የተሰወሩ መሆናቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ሱቃቸውን ዘግተው ሀገር ጥለው የተሰደዱም እንዳሉ የኢሳት ምንጮች ያረጋገጡ ሲሆን በአብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢዎች ግብር እንዳልተከፈለ መረጃዎች አመልክተዋል። በቅርቡ አንድ የደጀን ከተማ የመንግስት ሃላፊ ግብር የከፈለው ነጋዴ ከ4በመቶ አይበልጥም ማለታቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል በደጀን መንገድ፡ በዓባይ በረሃና ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ በሚወስዱ መንገዶች ላይ ጥብቅ ፍተሻ ዛሬ ሲካሄድ እንደነበረ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ድንገተኛ ፍተሻው ታይተው በማይታወቁ ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ወታደሮች የተካሄደ ነው ተብሏል። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልታወቀም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በባህርዳር በየቀበሌው በሚገኙ እና በተለያየ ቦታ በየጊዜው በሚመደቡት የማህበረሰብ ፖሊሶች አማካኝነት ማንኛውም ሰው ሮንድ(የምሽት ጥበቃ) እንዲያደርግ በወረፉ ተመድቦ ግዴታ እንደተጣለበት ከምንጮች ዘገባ ለማወቅ ተችሏል። ይህን ግዴታ የማይወጣ የገንዘብ ቅጣትና በቀበሌ በኩፖን የሚገኙ ስኳርና ዘይት የሚከለከል እንደሚሆን ተገልጿል።
ምናልባትም ሮንድ ያልወጣ በፀረ ሰላም ሀይሎች ተባባሪ ተብሎ የእስር እርምጃ ሊወሰድበት ይችላልም ተብሏል።
በቀበሌ ካድሬዎች እና የኮሚኒቲ ፖሊሶች አማካኝነት አዲስ ዙር የቤት ለቤት ምዝገባ የተጀመረ ሲሆን የተከራዮች መታወቂያ ጨምሮ የቤተሰብ አድራሻ ተመዝግቧል።
እነዚህ ተከራዩችም ሮንድ እንዲወጡ ግዳጅ ተጥሏል። ሮንድ የሚወጡትን ደግሞ በየቀጠና የሴቶች ተጠሪዎች ከሚኒሻ እና ከፖሊሶች ፣ ልዩ ሃይል ጋር በሚደረግ የምሽት ጥበቃ እንዲሰልሉ እየተደረገ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት በጎንደር በተደረገው ስብሰባ የተለየ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለጠየቁት የትግራይ ተወላጆች የአማራ ክልል ፖሊስ ፍቃደኛ አለመሆኑን ተከትሎ የአማራ ክልል ደህንነት ሰራተኞች ለስልጠና አዲስ አበባ መግባታቸውም ይነገራል።
የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት በአማራ ክልል ደህንነት፡ ልዩ ሃይልና ፖሊስ ላይ እምነት ያጣ ሲሆን ተቃዋሚዎች የተሰገሰጉበት ሲልም በስጋት እንደሚመለከተው ታውቋል።
በባህርዳር፡ በጎንደርና በሌሎች ተቃውሞ ተለይቷቸው በማያውቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ ታጣቂዎች እንዲሰማሩ መደርጋቸው ስርዓቱ የገባበትን አጣብቂኝ ያሳያል ብለዋል ታዛቢዎች።

No comments:

Post a Comment