Monday, July 17, 2017

በኦሮሚያ ወረዳዎች የተነሳዉ ህዝባዊ የግብር ይቀነስ ጥያቄ ምላሹ ጠመንጃ ለምን ሆነ ?

  





በአንቦ፣ወሊሶ ፣በጉደር፣ጊንጪ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ግብርን በመቃወም ህዝብ ጥያቄ ማቅረቡ ለምን ወንጀል ይሆናል? ለምንስ በጥይት ያስደበድባል?
ያልተጻፈዉ የወያኔ ህግ ብዙ ነዉ::ምንም ጥያቄ ህዝቡ ቢጠይቅ በጥይት ይደበደባል:: አስደብዳቢዎቹ ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ስም የኦሮሞ ብሄረተኘነትን እናራምዳለን እያሉ የሚያናፉት እነ ኦህዴድ ናቸዉ::

አንድ ጊዜ በወልመራ ወረዳ የሚኖሩ ገበሬ የኦህዴድ ካድሬዎችን እንዲህ ሲሉ አፋጠዋቸዉ ነበር::”እናንተም ገደላችሁን ወይም ትግሬም ገደለን ያዉ ለእኛ ሞት ነዉ::ኦህዴድ ለምንድን ነዉ ከኦሮሞ ህዝብ ጎን ቆሞ የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄ የማያደምጠዉ?የወያኔን ትዕዛዝ ለመፈጸም ከምትራወጡ የህዝብ ጮህት ለምን አትሰሙም::”
ዛሬ የኝህ አርሶ አደር ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነዉ::
በኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ ከመቶ በላይ በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎችን ወያኔ ቀፍቅፋለች::እነዚህ በዬብሄሩ የተደራጁ ፓርቲዎች ግን ዋና ስራቸዉ በስሙ የተደራጁትን ህዝብ ማስፈጀት እና ማሳረድ ነዉ::የወያኔም ዋናዉ ግቡ የገደለህ የራስህ ብሄር ድርጅት ነዉ ብሎ እጁን በዉሃ ታጥቦ በመጨረሻዋ ሰዓት ፊቱን አዙሮ እብስ ማለት ነዉ::
ህዝብ ከህዝብ ቢተላለቅ: ኢትዮጵያ በሳት ብትያያዝ: ብሎም አጠቃላይ የሰበአዊነት ቀዉስ በዚያች ሀገር ዉስጥ ቢፈጠር ወያኔ ግድም አይሰጠዉ::ስልጣን ላይ እስካለ አንዴ በግብር: አንዴ በኢንቨስትመንት: አንዴ በድብቅ የሚዘርፈዉን ሀብት ማግበስበሱ ብቻ ነዉ አንድ ቁጥር አላማዉ::
አምቦ የአውቶቡስ መናኸሪያ እንዲህ ተጨናንቋል::

በኦሮሚያ ወረዳዎች የተነሳዉ ህዝባዊ የግብር ይቀነስ ጥያቄ ምላሹ ጠመንጃ ለምን ሆነ ? ብለን የጠየቅን እንደሆነ መልሱ አንድ ነዉ::ከወያኔ ባህሪ የሚመነጭ ነዉ::ይሄ ጥያቄ በየትኛዉም የሀገሪቱ ክፍል ቢነሳ መልሱ ጠመንጃ ነዉ::በየትኛዉም የሀገሪቱ ወረዳ ወይም ቀበሌ እንዲህ አይነት የእዉነት ህዝባዊ ጥያቄ ከተነሳ መልሱ የሚሆነዉ ጠመንጃ ነዉ::

ለምን? ወያኔ ህዝባዊ መሰረት ስለሌለዉ ህዝባዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ አይችልም::ገዳይ እና አስገዳይ አድርጎ የመለመላቸዉ እና በዬብሄረሰቡ ስም ያደራጃቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ህዝባዊ መሰረት ስለሌላቸዉ የህዝቡን ጥያቄ የሚያደምጡበት ጆሮም የላቸዉም::የወያኔን ትዕዛዝ ተቀብለዉ ህዝቡን ለመግደል ግን ቁርጠኛ ናቸዉ::
በእጅጉ የሚያሳዝነዉ ደግሞ በተቃዉሞ ጎራዉ የተሰለፈዉ ሀይልም ከግል ስሜቱ እና የፖለቲካ እይታዉ ከረጢት ዉስጥ ወጥቶ በጋራ በመምከር ሀገራዊ መፍተሄ የሚያመጣ እርምጃ ላይ ላለመስማማት ያለዉ ቁርጠኛ አቋም ነዉ:: ህዝቡ ግን ብዙ ህዝባዊ ጥያቄዎች አሉት::እያንዳንዱን ህዝባዊ ጥያቄዉን ባነሳ ቁጥር ደግሞ በወያኔ የሚያስገድለዉ ነዉ::

አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ህዝባዊ ጥያቄ ግን በአንድ ማዕቀፍ ዉስጥ የሚፈታዉ እና ህዝቡም እፎይታ አግኝቶ ወደ ብልጽግና መገስገስ የሚችለዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በእዉነት መፍጠር ከተቻለ ብቻ ነዉ:: ወደዚህ ግብ የሚሰሩ ተቃዋሚ ሀይላት እስካልተፈጠሩ ድረስ ኩነቶች ይቀጥላሉ::
ለጊዜአዉ እንኳን በጠባብ ፍላጎት አብጠዉ የሚመጡ ሀይላት አሸናፊ ቢሆኑም አስተማማኝ እና ሁል አቀፍ ህዝባዊ ምላሽ መስጠት አይችሉም::ትርምስ እና ትርምስምሱ ይቀጥላል::ህዝብ ግን ከዚህ መከራ የግድ መዳን አለበት::ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ ህመም መዳን አለባት::

No comments:

Post a Comment