መንግስት በህዝብ ላይ የጫነው የአቅም በላይ ግብር ጉዳይ ነገር መቀስቀስ ከጀመረ ይኽው ሁለት ሳምንት አልፎታል:: አስቀድመው ነጋዴዎች በአዲሱ ሕግ መሰረት መክፈል የሚጠበቅባቸው ግብር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በብዙ እጥፍ በመጨመሩ ቅሬታቸውን ለገቢዎች ቢሮ አቅርበው ነበር:: ይህ ቅሬታቸው ሰሚ ጆሮ በማጣቱ ወደ ተቃውሞ ያመራ ጀመረ:: በኦሮሚያ የጨለንቆ ነጋዴዎች ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ይኼን ህዝባዊ ተቃውሞ ጀመሩ::የጉደር ህዝብ ደግሞ ስራ የማቆም አድማ አወጀ:: እነ ጊንጪ አምቦ ወሊሶ እና በአካባቢው የሚገኙ ከተሞች ተከተሏቸው:: ተቃውሞው ነቀምቴ ከተማ ተሻግሮ ከተማዋን ፀጥ ረጭ አረጋት:: ይኼው ህዝባዊ ተቋውሞ ዛሬ ወደ ጊምቢ ደንቢ ዶሎ መንዲ ተሻግሯል:: አንድ በአንድ ኦሮሚያን በአጠቃላይ በማዳረስ ላይ ይገኛል:: ይኼ በአይነቱ አዲስ የሆነ የግብር ጭማሪ እስካሁን በይፋ ለነጋዴዎች ግልፅ የተደረገው በኦሮሚያ እና በፊንፊኔ ከተማ ብቻ ነው::ምንም እንኳ የመጟተት አዝማሚያ ቢታይም በፊንፊኔ አንዳንድ አካባቢዎችም ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ተቋውሞውን ተቀላቅለዋል::
–
በመንግስት በኩል እስካሁን አሳማኝ የሆነ ሀሳብ አልቀረበም::ግብር በጭራሽ አልጨመርንም እና መጨመሩ ልክ ነው የሚሉ የሚጋጩ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ይገኛሉ:: ከተለያዮ ወቅታዊ ምክንያቶች እና ሁኔታዎች በመነሳት ህዝቡ ያምፃል ብለው አልገመቱም ነበር:: በአቸኳይ አዋጁ እና ሲወሰድ በነበረው የሀይል እርምጃ ምክንያት ህዝቡ ሞራሉ ተሰብሮ ተፀፅቶ በተሸናፊነት ስሜት እጁን ሰጥቷል ብለው በእርግጠኝነት አስምረውበት ደምድመው ስለ ነበር እንደዚህ አይነት ተቋውሞ ሊነሳ ይችላል ብለው አልጠረጠሩም ነበር:: ዛሬ ነገ ይቆማል ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ነበር:: አሁንም የያዙት አቋም ‘የነገውን ውሎ አይተን የሚቀጥለውን እርምጃችንን እንወስናለን’ አይነት ነገር ነው::
–
የግብር ጉዳይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አጥንት የሚነካ በመሆኑ ተቋውሞው እንዲው በቀላሉ መንግስት እንደሚመኘው ሊቆም የሚችል ነገር አይደለም:: መንግስት ተስፋ መስሎ የታየው ቀድመው ስራ ያቆሙ ከተሞች ወደ ስራ መመለሳቸው ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን ይህ ስህተት ነው::በሰላማዊ ትግል ውስጥ ህዝቡ በአንድነት በሀገር ደረጃ ሆነ ወይም በየቦታው እና በየተራ የሚያደርገው የገበያ ማቆም አድማ ሁለቱም ውጤታማ የትግል መንገዶች ናቸው:: በአንድነት የሚካሄደው ወቅታዊ እና ፈጣን (immediate and sharp) ተፅእኖ በመፍጠር መንግስትን እጅ የሚያሰጥ ሲሆን በየተራ የሚደረገው ደግሞ ፍጥጫውን በማርዘም በሂደት እያደገ የሚሄድ ተፅእኖ ይፈጥራል:: በተለይም ይች መንግስት ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅብብሎሹ አካሄድ የበጠ ሊጎዳት ይችላል:: ምክንያቱም ሀገሪቷ ተረጋግታለች ብለው ህዝቡን እና የውጭ ሀገራት መንግስታትን ለማሳመን የሚያደርጉትን የፕሮፓጋንዳ ትግል ያከሽፈባቸዋል:: በአንድ ቀን አንድ ሁለት ከተሞች ንግድ ቢያቆሙ ወሬው በሚዲያ ስለሚለቀቅ እያስጨነቃቸው ይሄዳል:: መርዘሙ ደግሞ ከተሞች እያረፉ ስርአቱን እያዘናጉ እንዲሄዱ ይረዳቸዋል:: ይህ በቅብብሎሽ እየተራዘመ የሚሄደው ዘዴ ሌሎች ጥያቄዎች እየተነሱ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ትግሉን እንዲቀላቀሉ መንገድ ስለሚከፍት ያንኑ ያክል ተፅእኖ እየፈጠረ ይሄዳል:: ስለዚህ ከተሞች በተለያየ ቀን አመፁ ላይ መሳተፈቸው ይጠቅመኛል ብላ ካሰበች እቺ መንግስት ተሳስታለች:: ይህ ማለት ግን ህዝቡ በተበታተነ ሁኔታ ይሂድ ለማለት ሳይሆን ነጋዴዎች ተወያይተው ተስማምተው ይመቸናል ያሉትን ቀን እየወሰኑ መሄድ ፈይዳ ይኖረዋል::
እስካሁን የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህዝባዊ አመፁ ለሚቀጥሉት 3 ቀናት እየተስፋፋ እንዲሄድ ተደርጎ እንደታቀደ ያሳያል:: ይህም አርብ እና የሰንበት ቀናቶቹ የገበያ ቀን ስለሆኑ የሚወሰደው የአመፅ እርምጃ ጠንካራ ተፅእኖ ይኖረዋል::
–
ለግዜው መንግስት ትንሽ ቆይቼ ልየው (wait and see) የሚል ዘዴ በመጠቀም ላይ ትገኛለች:: በዚህ ዘዴ ግን ከአንድ 3 ቀናት በላይ አስችሏት መቆየት አትችልም:: ለራሷ ጥቅም ስትል የህዝቡን ጥያቄ መመለሷ የማይቀር ነው:: ከላይ እንደተጠቀሰው ውሎ ሲያድር የህዝቡን አቅም ይበትናል ብላ ተስፋ ብታደርግም ያለው እውነታ ህዝቡ በአሁኑ ሰአት መጠቀም የጀመረው ዘዴ የራሱን አቅም እየቆጠበ የመንግስትን ግን እያዳከመ ለመሄድ ይረዳዋል:: ካለፉት ሁለት አመታት የተቀሰመው ልምድም ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ አስፈላጊ ነው::
–
በሚቀጥሉት ቀናት ከተሞች ልክ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ አመፁን እንዲቀላቀሉ ይመከራል:: ቀድመው የጀመሩ ከተሞች አቅማቸው በደከመ ግዜ እረፍት መውሰድ ትክክለኛ ዘዴ ነው:: ስነ ስርአት የዘዴ መረጣ ብስለት (wise tactical selection) እና የአካሄድ አንድነት አስፈላጊ ነው:: የሚቀጥሉት 3 ቀናት በጣም ወሳኝ በመሆናቸው እስካሁን አድማው ላይ ያልተሳተፉ ከተሞች በፍጥነት ዝግጅታቸውን አጠናቀው እርምጃ ቢወስዱ ተጨማሪ ተፅእኖ ለማምጣት እና እርስ በእርስ በሞራል ለመተጋገዝ ወሳኝነት አለው::
No comments:
Post a Comment