በኢትዮጵያ የሚታየው የኑሮ ልዩነት እጅግ በጣም እየሰፋ ነው፤ የሀብታም እና የድሃው ልዩነት የትየለሌ ነው። እኔ ልጅ እያለሁ ሀብታምና ድሃን የሚለየው ቴሌቪዥን ብቻ ነበረ፤ ሀብታም ከሆነ ቴሌቪዥን ይኖረዋል ድሃ ከሆነ አይኖረውም ከዚህ ውጭ አብዛኛው የድሃና የሀብታም ልጅ በሚመገበው ምግብ በሚለብሰው ልብስ ብዙም ልዩነት አልነበረም፤ አሁን እድሜ ለህወሃት የተባለሸ ስርአት በኢትዮጵያ በልቶ ማደር የማይችል እና አለም አቀፍ ሀብታሞች ተፈጥረዋል። በጣም የሚያሳዝነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የናጠጡ ሀብታሞች ሀብት ያከማቹበት መንገድ የድሃውን መሬት እና የየእለት ጉርስ በመቀማት ላይ የተመሰረተ ነው፤ ቺቺኒያ ብትሄዱ የዘመኑ ሰዎች ልጆች እንደሆሊውድ ተዋንያኖች ገንዘብ ሲበትኑ ትመለከታላቹህ በአንፃሩ ስንት ረዳት የሌላቸው ህፃናትና አዛውንት እዛው ቺቺኒያ አስፓልት ላይ የቆሸሸ ነጠላ ለብሰው ሲለምኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች ብርዱን ለመከላከል ቤንዚን ሲስቡ ትመለከታላቹህ፤ በነገራችን ላይ ቺቺኒያ ትንሿ መቀሌ ከሆነች ቆይታለች መግባቢያው ሁሉ ትግሬኛ ሆኗል በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ሰሞን ፌስቡክ ላይ በዝታ የነበረች ፈገግ የምታደርግ ቀልድ አለች።
አንዱን ምስኪን ሎተሪ አዟሪ የሕወኃት አባላት የሚዝናኑበት ቺቺኒያ የሚገኝ አንድ የመዝናኛ ቦታ ላይ ሎተሪ ለመሸጥ ሲገባ ጥበቃው እንዳይገባ ይከለክለዋል ለምን እንደማይገባ ሲጠይቅ የተሰጠው መልስ “እዚህ መዝናኛ ማእከል ያሉት በሙሉ ሎተሪ የወጣላቸው ናቸው” የሚል ነበር። አዎ የህወሃት አባላት ሎተሪ ወጥቶላቸዋል እነርሱ ሲጨፍሩ የተቀረው ወገናችን በረሐብ እና በስደት እያለቀ ነው።
ህወሃት በኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሣይሆን በማህበራዊ ህይወትም ትልቅ መመሰቃቀል ፈጥሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ እየተጨካከነ እንዲኖር ተደርጓል ለምሳሌ በየጎዳናው ላይ ዝናብ እየተደበደበ ታክሲ የሚጠብቅ ሰው እያየ ሙዚቃውን ሞቅ አድርጎ ሊፍት ለመስጠት የሚጠየፍ ብዙ ባለመኪና ተፈጥሯል፤ ከዚህ ቀደም መኪና ያለው ሰው ሰፈሩ ውስጥ ከተገኘ በሕመም፣ በሐዘን እና በደስታ ለጎረቤቶቹ እርዳታ መስጠት አለበት የሚል ያልተፃፈ ህግ ነበረ አሁን ያ ተቀይሯል በሰው ህመም ኑሯቸውን ለመቀየር የሚሯሯጡ ብዙዎች ናቸው። ያለፉት 26 አመታት የባከኑ የኢትዮጵያ ጊዜያቶች ናቸው፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ አንዱ ጎሣ በልቶ ለማደር ሌላው መራብ አለበት የሚል መርህ ተፈጥሯል። የመንግሥት ሠራተኛውን ኑሮህን ለማሻሻል እየሰራሁ ነው በሚል ተስፋ ለችግር ዳርገውታል፤ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣለ የጥንቸል ግልገል ሆኗል። ይህንን ስርአት ለመታገል እንዳይቻል እንኳን ፖለቲካውን የግል ስኬታቸው እንጂ የህዝብ በደል ምንም በማይመስላቸው የሰው ባክቴሪያዎች ቁጥጥር ስር ውሏል። ወዴት እንደምናመራ ሳስበው ይገርመኛል። መንገዳችንን ስተናል።
#ኤርሚያስ_ቶኩማ
No comments:
Post a Comment