Tuesday, July 11, 2017

የአገራችን ፖለቲካ – ግርማ ካሳ

   




(ይሄን ስጽፍ የማይስማሙ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገባኛል። ጠንካራ ተቃዉሞ ቢመጣ ችግር የለኝም። አንዳንድ ስሜታዊ የሆኑ፣ የዳያስፖራ ጽንፈኝነት ያሰከራችው ያው የለመዱት ስድብ ላይ ዘለው ሊሄዱ ይችላሉ። ሆኖም ግን አላማዬ፣ ዝም ብለው የሚጮኹትን ለማባባል ሳይሆን ሳይለንት ማጆሪቲው ላይ ነው። በርግጠኝነት ሳይለንት ማጆሪቲው ብሶት ማሰማትን ሳይሆን መፍትሄን፣ ጥላቻን ላይ ሳይሆን ፍቅርን ፣ ዘረኝኘት ላይ ሳይሆን አንድነት፣ አማራ፣ ትግሬ ፣ ኦሮሞ መባባልን ሳይሆን ኢትዮጳዊነትን፣ ማክረርን ሳይሆን መቻቻልን ፣ ጦርነትና ረብሻን ሳይሆን ሰላምን የሚፈለግ ነው።ስለዚህ የሚሳደበው ሰው ምን ይለኛል ካለለ አሥር አመት ይሳደብ።እኛ እንደው ፈርተን እና ተሸማቀን መጦመራችንን አናቆምም)
“ላለፉት 12 አመታት ያደረግነው ተሳትፎ ምን ዉጤት አመጣ ? ወደፊት አገርንና ህዝብን ለመርዳት በየት በኩል ብንቀሳቀስ ነው የሚሻለው ? ከፖለቲካው ነጻ መሆን አይቻልም። ግን በቀጠታ ከፖለቲካው ጋር ሳይገናኝ፣ በሌሎች መስኮች አስተዋጾ ማድረግ እንችላለን ወይ ? ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሳ ከዚህ በኋላስ የምናደርገው አስተዋጾ ፋይዳ ይኖረዋል ወይ ከወያኔ ያልተሻለ፣ በጥላቻ የተሞላ፣ የተለይ አስተያየትን የማይታገስ፣ መርህ የሌለው የተቃዋሚ ስብስብ በበዛበት፣ እንዴት መቀጠል ይቻላል? ..” የሚሉ ጥይቄዎችን በመጠየቅ ቆም ብሎ ነገሮችን መመርመር እንደሚገባ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ገልዤ ነበር።
I. ላለፉት 12 አመታት ያደረግነው ተሳትፎ ምን ዉጤት አመጣ ?
ላለፉት 12 አመታት የነበረኝን የፖለቲካ ተሳትፎ ስገመግመው ውጤት አስገኝሁ ማለት አይቻልም። ነገሮች እንደጠበኩትና እንደተመኘሁት፣ ተስፋ እንዳደረኩት አልሆኑም። በተቃራኒው እየባሰባቸው ነው የመጡት። ኢትዮጵያዊነትን ሰበክን፣ ጎጠኝነትና ዘረኝነት ተስፋፋ። ትላንት ኦነግና ሕወሃት ጋር ነበር ዘረኝነትን የምናየው፤ አሁን የአማራ ብሄረተኝነትን እያየን ነው። ጨዋታውና ሂሳቡ በዘር ብቻ ሆኗል። ሁሉም ነገር አሁን የሚታየው በዘር መነጽር ዉስጥ ነው።
ሰላምና ብሄራዊ መግባባትን፣ እርቅን ሰበክን። ነገር ግን ጥላቻው አደገ። ፖለቲካው እንዲረግብ እንደ ህዝብ ተያይዘን አገራችንን በፍቅር እንድናሳድግ ግፊት አደረግን። አሁን ግን ፖለቲካው እጅግ በጣም ከረረ። ከነጮችና ከቻይናዎች፣ ከፓኪስታኑና ከሕንዱ ጋር በሰላም አብረን ፣ እርስ በርስ ግን በሰላም መኖር አልቻልንም። ሌሎችን እያከበርን የአገራችንን ሰው ግን በዘሩ ምክንያት መጥላትና መናቁን ገፋንበት።
ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄድና የምርጫ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ እንድንሰለጥን ብዙ ሰራን። አገር ቤት የሚገኙ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መደገፍና አበረታታን። ሆኖም ግን የፓርቲ መሪዎች ለጥቅምና ለስልጣን ሲሉ ሲከፋፈሉ አየን። በአንጻራዊነት ጠንካራ የነበሩትን ( እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉትን) ደግሞ አገዛዙ በሃይል ጨፈለቃቸው። አሁን የሰላማዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ ቆሟል ማለት ይችላል። እርግጥ ነው እንደ ኢዴፓ፤ መኢድ፣ ሰማያዊ ..ያሉ ድርጅቶች አሉ። ግን እነዚህ ድርጅቶች ስማቸውን ይዘው ከማቆየትና በጽ/ቤቶቻቸው አንዳንድ መጠነኛ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ዉጭ ፣ ቢፈልጉም እንኳን፣ ብዙ ሊሄዱና ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ የለም። አገሪቷ በአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ አዋጅ ስር ነው ያለችው።
II. ከወያኔ ያልተሻለ፣ በጥላቻ የተሞላ፣ የተለየ አስተያየትን የማይታገስ፣ መርህ የሌለው የተቃዋሚ ስብስብ በበዛበት፣ እንዴት መቀጠል ይችላል ?
በጭራሽ መቀጥል አይቻልም። በተለይም የዳያስፖራ ፖለቲካ የሚያስጠላ ነው። የተለየ ሐሳብን የማስተናገድ ችሎታ ያንሰናል። የሰለጠነ ፖለቲካ ድሆች ነን። ያሉ ድርጅቶች ተጠያቂነትና ግልጽነት የጎደላቸው፣ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ ምን ሰራን ብለው ራሳቸው የማይገመግሙ ናቸው።
አንዳንዶች በዉጭ ያሉ ወይንም አስመራ የተከሉ ድርጅቶችን ተስፋ የሚያደርጉ አሉ። ለነዚህ ወገኖች ከማዘን ዉጭ ምንም የምለው አይኖረኝ። እነዚህ ድርጅቶች በአብዛኛው በብሶት ላይ የተመሰረቱ፣ የተወሰኑ ጥቂት የዳያስፖራ ወገኖችን ሪሳይክል እያደረጉ የሚንቀሳቀሱ፣ አብዛኛዉን ሳይለንት ማጆሪቲ ማሳተፍ ያልቻሉ ናቸው። በእጃቸው፣ በሜዳቸው ያለውን የዲፕሎማሲ ሥራ እንኳን ዉጤት ባለው መልኩ መስራት አልቻሉም። ነገር ግን አገር ቤት ያለዉን ትግል ከዉጭ ለመምራት ይሞክራሉ። በኔ እይታ እነርሱን ተስፋ ማድረግና ከነርሱ ጋር ጊዜ ማጥፋት ፈረስ በሌለበት ጋሪን ማሰማራት ነው።
III. ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሳ ከዚህ በኋላስ የምናደርገው አስተዋጾ ፋይዳ ይኖረዋል ወይ ?
የሰላም በር በመዘጋቱ አሁን የአመጽ እንቅስቃሴዎችን በስፋት እያየን ነው። በተለይም በጎንደር የታጠቁ ሃይሎች እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። አገራችን ቀስ በቀስ ወደ ገደል እየሄደች ነው። “ነገሮች በጣም ከመበላሸታቸው የተነሳ ከዚህ በኋላ የምናደርገው አስተዋጾ ፋይዳ ይኖረዋል ወይ?” ለተባለው ጥያቄ፣ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፣ ከአሁን በኋላ የኛ አስተዋጾ፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት ጥሪና ጉትጎታ፣ በተለይም የፖለቲክ ስልጣን በተቆጣጠሩት ሰዎች ዘንድ፣ ምን ፋይዳ የሚያመጣ አይመስለኝም። ሰዎቹ ግትር ናቸው። ለሰላም አለርጂክ የሆኑ።
ዘረኝነቱን በተመለከተ አሁንም በመንግስት ደረጃ ስር የሰደደ ሁኔታ ነው ያለው። ሕገ መንግስቱ ራሱ የተመሰረተው በዘር ላይ ነው። ይሄ መሬት የዚህ ዘር፣ ያ ምሬት የዚያ ዘር እያሉ አገሪቷን ሸንሽነዋታል። በመንግስት ደረጃ እንደ መዋቅር የተዘረጋ፣ ላለፉት 25 አመታት የተሰራበት ፣ የዘር ፖለቲካ የብዙ ወጣቶችን አስተሳሰብና አመለካከት አበላሽቷል። ከዚህ በኋላ በምን መልኩ ማቅናት እንደሚቻል አላውቅም።
IV. ከፖለቲካው ነጻ መሆን አይቻልም። ግን በቀጠታ ከፖለቲካው ጋር ሳይገናኝ፣ በሌሎች መስኮች አስተዋጾ ማድረግ እንችላለን ወይ ?
በሚገባ ይቻላል። ያለው ስርዓት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ባሉት ቀዳዳዎች በመጠቅም አገርን መርዳት ይችላል። ብዙ መንገዶች አሉ። አንድ ኢትዮጵያዊ አለ ለምሳሌ ከ Books for Africa ጋር በመተባበር በርካታ መጽሐፍቶች ኢትዮጵያ እንዲገቡ አድርጓል። አንድ እኔ የማወቀው አንድ ጓደኛዬ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ይዞ ሄዶ ለአንድ ዩኒቨርሲቲ አበርክቷል። ካሊፎርኒያ የሚኖር ኢትዮጵይአዊ ቤቱን ሸጦ አርሲ ውስጥ ትምህርት ቤት ከፍቷል። አንዲት ከካንሰር የዳነች ኢትዮጵያዊት በሸኖ የካንሰር ክሊኒክ ከፍታ ሕዝብ እንዲገለገል አድርጋለች።
እርግጥ ነው ሙስና ሌብነት ሕግ አልባነት በበዛበት አገር፣ አገርን እና ህዝብ እንጥቀም ብለው ዜጎች ሲንቀስቀሱ ብዙ መጉላላት ይደርስባቸዋል። ጉቦ እንዲሰጡ እየተፈለገ፣ ወይንም ሕወሃቶች ከኛ ጋር ሥሩ እያሏችው፣ ስለተቸገሩ ጥለው የተመለሱም ጥቂቶች አይደሉም። ሆኖም ግን እንደዚያም ሆኖ መሰናክሎች እያለፉና እየተቋቋሙም ማገልገል ይቻላል። ፖለቲካው ሃሪፍ ቢሆን ኖሮ የበለጠ አሥር እጥፍ መስራት ይቻል ነበር። ግን ካልሆነም ደግሞ ቅዠት ተፈርቶ ሳይተኛ አይድርም እንደሚባለው፣ ከአሁን ለአሁን አገዛዙን እንቃወማለንና አገርን እንደሚጠቅም እያወቅን ከመስራት መቆጠብ የለብንም።
V. ወደፊት አገርንና ህዝብን ለመርዳት በየት በኩል ብንቀሳቀስ ነው የሚሻለው ?
ዉጭ አገር የምኖር እንደመሆኔ ልሰራና ላደርግ የምችለው በጣም የተወሰነ ነው። ሆኖም ግን አንድ ነገር በጣም እርግጠኛ ነኝ። ፋይል ዘግተን አንቀመጥም። ለአገርና ለሕዝብ ማበርከት የምንችለውን ሁሉ ከማበርከት ወደኋላ አንልም። ከአሥራ ሁለት አመታት በፊት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ፣ ዜጎችን የመደብደብ፣ የማሰር፣ የማፈናቀል ተግባራት እንዲወገዱ፣ ዉጤት ያምጣም አያምጣም፣ ማድረግ ያለብኝ ሁሉ እናደርጋለን።
ሆኖም ግን የተሻለ ፣ ውጤት ሊያመጣ፣ ለአገር የሚበጅ አማራጭ ተይዞ መሆን አለበት ባይ ነኝ።
በኔ እይታ አማራጩ የሚከተሉት ባገናዘበ መልኩ ቢሆን ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ፡
1. ኢትዮጵያዉይን በተቻለ መጠን ከዘር ፖለቲካ መውጣት መቻል አለብን። የዘር ፖለቲካ በማራገብ የሚጠቅሙ ጥቂቶች አሉ። የነርሱ ሆስቴጅ መሆን የለብንም።አንዲት አገር ነው ያለችን። ኢትዮጵያ። ለአገራችን ብቻኛ መፍትሄው የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ነው። የአማራነት ፖለቲካ፣ የትግረኔት፣ የኦሮሞነት ፖለቲካ ከብሶት ፖለቲካ የመነጨ የኋላ ቀርነት ፖለቲካ ነው። ዜጎች በዘራቸው ስር ለመሰባሰባቸው የራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም ለዘለቄታው ግን የሚያዋጣ ነው ብዬ አላምንም።
ለምሳሌ የኦሮሞ ተቃዉሞን ተመልከቱ። በምእራብ አርሱ፣ በሃረረጌ፣ በባሌ፣ በወለጋና በምእራብ ሸዋ ነው በብዛት እንቅስቃሴ ያደረገው። ሆኖም የኢትዮጵያ ብሄረተኛ የሆኑ ኦሮሞዎችና ሌሎች ማህበረሰቦች በብዛት በሚኖርባቸውና የኦሮሚያ አካባቢዎች ድጋፍ ስላላገኝ ገፍቶ መሄድ አልቻለም።በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ በጂማ ፣ በአሰላ …. በመሳሰሉት ቦታዎች የሰልፍ ጥሪዎች ቀረበው ሰው አልወጣም። ለምን የኦሮሞ አክቲቪስቶች የሌላው ድጋፍ አያስፈልገንም በሚል ከሌላው ጋር ለመስራት ፍቃደኛ አለነበሩም።
የአማራ ተጋድሎን ካየን ወደ ሸዋና ወደ ወሎ አልፎ ሊሄድ አልቻለም። ያ የሆነበት አንዱ ምክንያትም የአማራ ብሄረተኝነት ፖለቲካ ከልክ በላይ ስለተለጠጠ ነው። ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነትን ይዞ ነበር የተነሳው። ግን ጥቂቶች የሕዝቡን ጥያቄ ሃይጃክ አድርገው አማራነትን እያቀነቀኑበት ነው።
2. ፖለቲካችን ምክንያታዊና በእዉነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ስንቃወም ሆነ ስንደገፍ በምክንያት መሆን አለበት። ኢሕዴግን መቃወም የለብንም። መቃወም ያለብን በኢሕአዴግ የሚደረገዉን ኢፍትሃዊነት፣ አምባገነናዊነት፣ ግፍና ጭቆናን ነው። ኢሕአዴግ ለአገር የሚጠቅም ስራ ከሰራ ለዚያ እውቅና የመስጠት አቅም ሊኖረን ይገባል። አለበለዚያ ፖለቲካችን በመርህ ላይ ሳይሆን በጥላቻ ላይ ነው የተመሰረተው ማለት ነው። ያ ደግሞ ጎጂ ነው።
3. አገር ቤት ያሉ ሰላማዊ ድርጅቶች አሁን ከማንም በላይ ብዙ ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። እነርሱን ማጠናከር አስፈላጊ ነው። በአገር ቤት ጠንካራ የተቃዋሚ ስብስብ መኖሩ ለአገር በጣም ጠቃሚ ነው። በዘር የተደራጀ ስብስብ ሳይሆን ( ለዚያ ኢሓዴግ አለ) ኢትዮጵያዉያንን ሁሉ በአንድ ጥላ ስር ሎያሰባስብ የሚችል ስብስብ። ይህ ስብስብ በተለይም ጥጉን ይዞ የተቀመጠው የተማረው ሃይል እንዲቀላቀለው ማድረግ ያስፈለጋል። ይህ ስብስብ ዳያስፖራው ምን ይላል በሚል ስሌት ሳይሆን ለሕዝብ ምን ይጠቅማል በሚል የሚንቀሳቀስ መሆን ይኖርበታል። የዳያስፖራ ጽንፈኛ ፖለቲካ በጣም አደገኛ ፖለቲካ ነው። የስብረው፣ የቁረጠው ፖለቲካ ላለፉት 25 አመታት የትም አላደረሰንም።
4. በዉጭ አገር በስሜት ላይ ሳይሆን በተግባር ላይ የተመሰረተ፣ በበሰለ የዲፕሎማሲ ቅኝት የተቃኘ የዉጭ አገር ማህበረሰብን የማቀፍ ስራ መሰራት አለበት። ይኸው ዶር ቴድሮስ አዳኖም ተመረጡ አይደለም። በቅርቡ ደግሞ የእንግሊዝ መንግስት አንድ የግንቦት ሰባትን አመራር በቁጥጥር ሥራ አድርጋም አልነበረም። አያችሁ ፤ አገዛዙ በዲፕሎማሲ ከተቃዋሚዎች በእጅጉ መብለጡን አስመስክሯል። ያ ሁሉ የተማረ ሰው፣ ያ ሁሉ ፕሮፌሰር፣ ያ ሁሉ አክቲቪስት እያለ በዚህ መልኩ የዲፕሎማሲ ሽንፈት መከናነባችን ፣ ቆም ብለን ስትራቴጂዎቻችንን እንድንመረምር ሊያደረገን ይገባል።
5. ፖለቲካን ከልማት መለየት መቻል አለብን። በኢትዮጵያ የሚሰሩ ማናቸዉንም አይነት የልማት እንቅስቃሴዎች መደገፍ እንጂ መቃወም አያስፈለግም። በየትም የአገሪቷ ግዛት ማናቸውም አይነት ህዝብን የሚጠቅም ስራ ከተሰራ እሰየው ማለት አለብን። የልማት እንቅስቃሴዎች ፍትሃዊና አድሎዋዊ ከሆኑ፣ ልማቱን ሳይሆን አድሎዉን ማጋለጥና መታገል እንችላለን።ተገቢም ነው።
6. በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የሚኖሩ አብዛኞቹ ከፖለቲካው የራቁ ናቸው። አገርቸውን ስለማይወዱ ወይንም የድርሻቸውን ማበርከት ስለማይፈለጉ ሳይሆን፣ ግራ ስለተጋቡ ነው። ይሄ ሳይለንት ማጆሪቲ ማንቀሳቀስ ያስፈለጋል። አብዛኛው ሳይለንት ማጆሪቲውብዙ ጊዜ የሚሰሙት ጥቂቶች እንደሚያስቡት አይደለም የሚያስበው። አንደኛ ሞደሬሽንና የሰለጠነን ፖለቲካ ይፈልጋል። ሁለተኛ አርቆ የሚያስብ ነው። አገዛዙ እንዲለወጥ ቢፈለግም፣ የሚተካውስ ማንነው የሚለው ያሳስበዋል። በመሆኑም ይሄ ማጆሪቲ ለማቀፍ ብስለት ያለው፣ በማጭበርበር ላይ ያልተመሰረተ ሥራ መሰራት አለበት።
7. በሻእቢያ በኩል የሚመጣ ሰላምና ነጻነት አይኖርም። ሻእቢያ አዲስ አበባ ካሉ ገዢዎች በባሰ ግፈኛ አገዛዝ ነው። እኛው ኢትዮጵያዊያን እያለን፣ ወርደን የራሱን ዜጎንች እያረደ ካለ ወንበዴ ጋር ማበር ማቆም አለብን። ይሄን በድጋሜ እጽፋለሁ፤ ሻእቢያ እርግማናችን እንጂ መዳናችን አይሆንም።
8. ኢሕአዴግንና በዉስጡ ያሉ ድርጅቶች አባላት ለለዉጥ እንዲዘጋጁ ግፊት ማድረግና ማበረትታታ አስፈላጊ ነው። እነርሱ ዉስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚሰሩት አብረን የምንወቅጣቸው ከሆነ አስቸጋሪ ነው። የኢሕአዴግ አመራሮች፣ የፓርላማ አባላት አድራሻ(ስልክ፣ ኢሜል …) በማሰባሰብ፣ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ግፊት ማድረግ ይረዳል።
በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያዊነት፣ የሰለጠነ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ፣ ሰላማዊ የሆነ፣ የፍቅርና የእርቅ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሰሩ ወይንም ለመስራት የተዘጋጁ ወገኖች ካሉ በዳያስፖራ አብሬ ለመስራት ሁልጊዜ ዝግጁ ነኝ። በተጓዳኝም ያለኝ ብቸኛው መድረክ ሜዲያው ስለሆነ፣ በተለያዩ መድረኮች ከላይ የተጠቀሱትን መርህዎች የበለጠ በማስፋት፣ የመፍትሄ ሐሳቦች በማቅረብ፣ በአገር ቤት ያለውን ሁኔታ በማሳወቅ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲኖር ጥረቴን እቀጥላለሁ። አገር ቤትን በተመለከተ ከፖለቲካው ውጭ ላደርጋቸው የምችላቸው ስራዎች እንደተጠበቁ፣ በፖለቲካው አንጻር መኢአድ፣ ሰማያዊን እና ኢዴፓን መደገፍ እፈልጋለሁ። ሌላው ቢቀር አገር ቤት ያሉ ናቸው። ከህዝቡ ጋር።

No comments:

Post a Comment