“በመሳም ያልመለስሃትን ሚስት በዱላ መመለስ አትችልም።” ….(የወሎዎች አባባል!!)
ሀ/ የፀጋዬ ረጋሳ መንገድ ከየት ወዴት?
ዶ/ር ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳን የማውቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ት/ቤት ሲያስተምር ነው። ፀጋዬ የቋንቋ ችሎታው ምጡቅ ሲሆን፣ እንደ አብዛኛዎቹ( ሁሉም አላልኩም) የህግ ት/ቤቱ መምህራን ሁሉ ምክንያታዊና የሞራል ሰው ነበር። ከዚህ በላይ ዶ/ር ፀጋዬ በተማሪዎቹም፣ በሌሎች መምህራን እና የአስተደደር ሰራተኞች ዘንድ ተወዳጅ ሰው ነበር። ከዚህ የተነሳ ይመስላል ፀጋዬ ሁሌ ደስተኛነቱን ከፊቱ ማንበብ ይቻል ነበር።
ፀጋዬ አሁን አሁን በተለይ ደግሞ ለሦስተኛ ዲግሪው ትምህርት አውስትራሊያ ከሄደ በኃላ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በማጉላት በሚሰጠው የመረረ ወይም የከረረ አስተያየት በሌላው ጫፍ ባለው ወገን በኩል የተወደደ አይመስልም። ምንም እንኳን ፀጋዬ የፈለገውን የፖለቲካ እምነት የመያዝ መብቱ ማንም የሚሰጠው እና የሚነሳው ባይሆንም፣ እየተወገዘበት ያለው ሁኔታ ግን ትክክል ካለመሆኑም በላይ አሳዛኝ ጭምር ነው። ምክንያቱም የስው ልጅ ከእንስሳ ወይም ከግዑዝ ነገር የሚለየው የተለያዬ አስተሳሰብ መያዝ መቻሉ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን መቀሌ ሄደው ወጣቶችን ባነጋገሩበት ጊዜ የሚቀርብላቸው ጥያቄ አንድ አይነት ቅኝት ያለው በመሆኑ ተገርመው “ሰው እንዴት ስው ሆኖ ተፈጥሮ በፋብሪካ እንደተመረተ ሳሙና እንዴት አንድ አይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል” እንዳሉት ፀጋዬ የሌላውን አስተሳሰብ የመያዝ ግዴታ የለበትም።
ፀጋዬ በአሁኑ የዘውግ መደብ ሲመዘን በአባቱ በኩል ኦሮሞ ሲሆን በእናቱ በኩል ግን አማራ እንደሆነ በቅርብ የሚያውቁት ብቻ ሳይሆን እራሱም የሚክደው አይደለም። ስለሆነም ፀጋዬ ዘረኛ ነው አማራን አይወድም ማለት ፀጋዬ የራሱን ግምሽ ዘር አይወድም እንደማለት ስለሆን አሳማኝ አይደለም። ሆኖም ፀጋዬ አሁን እያራመደው ያለው የፖለቲካ አቋም ከየት መጣ የሚለውን ለማወቅ አንድም እራሱን ፀጋዬን መሆን ያስፈልጋል፣ አለበለዚያም ፀጋዬን እንደወንድም ክብር በመስጠት አቅርቦና ቀርቦ መነጋገር ይገባል።ምናልባትም ፀጋዬ እንደሚለው አባቱ ኦሮሞ በመሆኑ ንቀት ውይም ማግለል ደርሶበት ይሆን ይሆናል። ሁላችንም እንደምናውቀው እኛ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ከሌላው ዘውግ የሚመዘዘውን ሰው ይቅርና ከራሳችን ዘውግ የሆነውን በክፍለሃገር ፈርጀን የምናገል እና የምንበድል መሆናችን ስለሚታወቅ ፀጋዬ የሚለው ነገር ውሽት ነው ልንለው አንችልም። የውድቀታችን እና የኃላቀርነታችን መንስኤስ መናናቃችን አይደለምን?። በመሆኑም ወሎየዎች ” በመሳም ያልመለስሃትን ሚስት በዱላ አትመልሳትም ” እንዲሉ ፀጋዬንም ሆነ ሌላውን ኢትዮጲያዊ ክብር በመስጠትና ሀሳቡን ብቻ በመሞገት መግባባት እየተቻለ፣ ፀጋዬን በማዋረድ ከጉዞው ወይም ከመንገዱ ማስቆም አይቻልም። ሰውን የሚያክል ፍጡርም በማንኛውም ምክንያት ቢሆን አካላዊ ስብእናውን ማዋረድ ትክክል አይደለም።
ለ/ አዲስ አበባ የማናት ፖለቲካ፦
አዲስ አበባ ይህን ሁሉ ትኩረት እየሳበች የመጣችው ቅድስት እየሩሳሌም ወይም መካና መዲና ስለሆነች ወይም ውስጧ በነዳጅ እና በበለጸጉ ማዕድናት የከበረች ሆና ሳይሆን እየተንከባለለ በመጣው የከተማ ፖሊሲ እጦት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ከዚህ በፊት ኢትዮጲያን የገዟትም ይሁን አሁን እየገዛት ያለው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የሚረባ የከተማ ፖሊሲ የላቸውም። በዚህ የተነሳም ይመስላል አዲስ አበባ ከሌሎች ከተሞች በበለጠ ብቻ ሳይሆን የሌሎች ከተሞችን ህመምና በረከት ለብቻዋ ይዛ ልትፈነዳ የደረሰችው። አዱስ አበባ የሀገሪቱ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የኢንዱስትሪ እና የሌሎች ነገሮች ብቸኛ ማዕከል ናት። በኢትዮጲያ ውስጥ የከተሞች ፖሊሲ ቢኖር ኖሮ አዱስ አበባ ይህን ሁሉ ሽክም እንድትሽከም ባልፈረድንባት ነበር። ለምሳሌ አሜሪካኖች ከፖለቲካ መናገሻቸው ዋሽንግተን ዲሲ የበለጡ ከተሞችን በመመስረታቸው እና በአንድ ቦታ ላይ ሁሉም ነገር እንዳይከማች ባለማድረጋቸው በሁሉም ቦታ የተመጣጠነ የኢኮኖሚ እና የመስረተ ልማት መስህብ አለ። በመሆኑም በረከቱም ሆነ መርገሙ በመናገሻ ከተማቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ግዛት ላይ የወደቀ ነው።
በኢትዮጲያ ውስጥ ግልፅ እና ፍትሃዊ የከተማ ፖሊሲ ያለው መንግስት ቢኖር ኖሮ ዛሬ “የአዲስ አበባ የእኔ ናት” ፖለቲካ ባልኖረ ነበር። ነቀምት፣ ጅማ፣ አሮጊቷ ሀረር፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ አዲግራት፣ ደሴ፣ ጎንደር ፣ደብረ ማርቆስ ወዘተ የአዲስ አበባን ጭንቀትም ሆነ በረከት ይካፈሉላት እና ያስተነፍሷት ነበር። በመሆኑም የሚመጣው መንግስት ፍትሃዊ የከተማ ፖሊሲ እስኪያመጣ ድረስ ዝንቦችን ቆሻሻ፣ ንቦችን አበባ እንደሚስባቸው ሁሉ አዲስ አበባም ሁሉንም ሰው እየሳበች መቀጠሏ አይቀርም።
አዲስ አበባ በቀድሞው የጠቅላይ ግዛት ( ክፍለ ሃገር) አስተዳደር መሰረት የሽዋ ጠቅላይ ግዛት አካል ስለነበረች በሽዋ ውስጥ ለነበሩት አማሮች፣ ኦሮሞዎች፣ ጉራጌዎች፣ ስልጤዎች፣ ከንባታዎች፣ሃድያዎች እና ወዘተ ነበረች። በኢ.ህ.ዲ.ሪ ( ደርግ) አስተዳደር ደግሞ “የአዲስ እበባ አስተዳደር አካባቢ” ተብላ የራሷ የፖለቲካ አስተዳደር ስልጣን የነበራት ከተማ ስለነበረች ባለቤቶቿ አዲስ እበባዊያን ነበሩ። ነገር ግን አሁን ባለው አከላለል መሰረት አዲስ አበባ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ናት ብሎ የወያኔ/ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ህገ መንግስት ከዛሬ 22 ዓመት በፊት ደንግጓል።
በመሆኑም ይህ ህገ- መንግስት እስካልተቀየረ ድረስ አዲስ አበባ በወረቀት ደረጃ ቢሆንም እንኳን የኦሮምያ መንግስት (State of Oromia) ናት። ከዚህ ተነስተን የአዲስ አበባ መሬት፣ ወንዞች፣ ተራሮች፣ ህንፃዎች፣ቤተ መንግስቱ፣ ኑዋሪዎች፣ አየሩ፣ እና ሰማዩ ሁሉ የኦሮምያ መንግስትነው። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ህገ መንግስቱ አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ናት ይበል እንጅ ባለቤቷ የኦሮሞ ህዝብ ነው ማለቱ ይሁን እይሁን ወይም የኦሮምያን መንግስት የፈጠረው ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ማለቱ ግልጽ አይደለም። (The EFDR Constitution Article 49(5) provides that Addis Ababa is within the State of Oromia. It doesn’t say Addis Ababa is for the people of Oromo): ለምሳሌ፦ ይህ ህገ መንግስት በአንቀጽ 40 (3) ላይ የመሬት ባለቤትነት መብት ለመንግስት እና ለህዝብ እንደሆነ በግልጽ ደንግጓል።(….is exclusively vested in the State and in the peoples of Ethiopia)
ይሁንና ዶ/ር ፀጋዬም ይሁን ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ የኦሮሞዎች ናት ብለው መከራከራቸው እንደወንጀልም ሆነ እንደ ሃጥያትም ሊቆጠርባቸው አይገባም። ይህንን ክርክር ማቅረባቸው መብታቸው ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ይሄ ግራ የገባው ህገ መንግስት ያመላከታቸው በመሆኑ ጭምር ነው።
የዘውግ/ ቋንቋ ፖለቲካ ትክክል ነው ብሎ ለተቀበለ እና ለራሱ ዘውግ የሚታገል ሰው የእነ ፅጋዬ ረጋሳ መንገድም ሆነ ይህ ህገመንግስት ሊቅረቁረው አይገባም። በጣም የሚገርመው ግን በዶ/ር ፀጋዬ ላይ ከሚቀርቡትን አብዛኛዎችን ተቃውሞዎች እና ክብረ ነክ ስድቦች የሚያቀርቡት የዘውግ ወይም የቋንቋ ፖለቲካ በሚያራምዱ ሰዎች ነው። በዘውግ / በቋንቋ የፖለቲካ ጭቃ ውስጥ ተዘፍቆ ሌላውን ጭቃ ነክቶሃል ብሎ የስውን ክብር መንካትስ ጤነኝነት ነውን? የፀጋዬ መንገድ አዲስ አይደለም እንጅ ቢሆን እንኳ በዚህ መንገድ ክብሩን በመንካት ፀጋዬን ከመንገዱ ማስቆም ይቻላልን?? በእኔ እምነት ግን አይቻልም።
ሐ/ እንደ መውጫ ……የኦሮሞ ህዝብ ትግል እኩልነት እና ፍትህ ወይስ የስም ለውጥ?
ልክ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የኦሮሞ ህዝብ በአጠቃላይ የወለጋ እና የምእራብ ሽዋ ህዝብ ደግሞ በተለይ በዚህ ስርዓት ጭቆና፣ ብዝበዝ፣ አድሏዊነት እና የፍትህ እጦት ደርሶበታል። አብላጭ ቁጥር ያለው ህዝብ እንደመሆኑ. እንኳን የኢትዮ9ያ ምንግስትን ስልጣን ይቅርና የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን እንኳ እድልም ሆነ የፖለቲካ ስልጣን ሊያገኝ አልቻለም። የወለጋ ህዝብ የራሱን የተፈጥሮ ሀብት እራሱ መጠቀም ባልቻለበት ሁኔታ፣ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን ባልተደረገበት ሁኔታ የአዲስ አበባ ስም ፊንፊኔ ተባለ ኒው ዮርክ የሚያመጣለት ጥቅም አይታየኝም። ዛሬ የኦሮሞ ህዝብም ሆነ ሌላው. የሚጠይቀው እና የሚታገለው፣ በየቀኑ እየተገደለ ያለው ለእኩልንት እና ንፃነት እንጅ ለስም ልውጥ አይደለም። ዮሓንስ የሚባለውን ሰው ጆን ወይም የኑስ ብትለው በስሙ ለውጥ ብቻ በሰውየው ላይ የሚመጣ መሰረታዊ ለውጥ የለም።
ዋናው መዘንጋት የሌለብን ጉዳይ ግን ይህንን በዘውግ/ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ከተቀበልነው የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ዘውጎች አብላጫ ቁጥር ያለው እንደመሆኑ እና አሁን ያለው የኦሮምያ ክልልም ሰፊውን የኢትዮጲያ ግዛት እንደመያዙ ኢትዮጲያን የመግዛትም/ የመምራት የስልጣን ተራ እና እድል ለኦሮሞዎች መሰጠት አለበት። የእነ ፀጋዬ መንገድም በዚህ ላይ እንጅ በትናንሽ ነግሮች ላይ ማጠንጠን የለበትም። ኦሮሞዎች ኢትዮጲያን መምራት እንዲችሉ እድሉ ቢሰጣቸው ማን ያውቃል የኢትዮጲያ ችግር በእነሱ በኩል ሊፈታ ይችል ይሆናል።ምክንያቱም በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ኦሮሞዎች ጠንካራ ማህበረሰብም በመገንባት አስመስክረዋል። በተጨማሪም በዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ዘመን ፍታውራሪ ሃብተጊዎርጊስ ደናግዴን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የኦሮሞ የካቢኔ አባላት ጠንካራ ግዛት ያላት ኢትዮጵያን ሰርተው አሳይተውናል።
በመሆኑም ፀጋዬን እና ሌሎችን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ስብእናቸውን በማዋረድ ሳይሆን እንደ ኢትዮጲያዊ ወንድሞች አቅፈን፣ተንከባክበን እና ሞራል ሰጠን ሁለንተናዊ የፖለቲካ ስልጣን እንዲይዙና ኢትዮጲያን መምራት እንዲችሉ ልናበረታታቸው ይገባል። ይህንን የማናረግ ከሆነ ኢትዮጵያን እንወዳታለን የምንለው እውነት አይደለም። በሌላ በኩል እነ ፀጋዬ የፖለቲካ ቅኝታቸውን ቅርንጫፉ እና ቅጠሉ ላይ ከማተኮር ይልቅ ዋናው ዛፉ ላይ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በሌላ አነጋገር የኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጲያን የመግዛትም ሆነ የመምራት የሞራልም ሆነ የህግ ድጋፍ ስላለው የኦሮሞን ህዝብ ከጭቆና ለማላቀቅ የሚጠቅመው ጥቃቅን የመብት ጥያቄዎች እንዲከበሩ ጉልበት በመጨረስ ሳይሆን የመንግስት ስልጣን በመያዝ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። እነ ፀጋዬ. የኦሮሞ ህዝብን እንደ ባዕድ ህዝብ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲገለል የሚሽረብውን ሴራ እንደ እውነት ተቀብለው የሚሰሩ ክሆነና በጥቃቅን ነገሮች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ከሆነ እንደታላላቆቻቸው ሁሉ መጭው የኦሮሞን ትውልድ መውቀሱ አይቀርም።
No comments:
Post a Comment