Wednesday, July 12, 2017

አጼ ሀይለስላሴ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም አይደለም ለምን አሉ? – ሸንቁጥ አየለ


አጼ ሀይለስላሴ
በአንዳንድ ንግግሮች: ጽሁፎች እና የሀሳብ ልዉዉጦች ዉስጥ አጼ ሀይለስላሴ “እኛ ኢትዮጵያዉያን ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም አይደለንም” ብለዋል በማለት ንጉሰ ነገስቱን እና ኢትዮጵያዊነትን የማብጠልጠል ነገር አልፎ አልፎ ይስተዋላል:: አጼ ሀይለስላሴ ኢትዮጵያዊ ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም አይደለም ለምን አሉ? ኢትዮጵያዊነት የቀለም ጉዳይ እንዳለሆነ ለመግለጽ ነዉ እንጅ ጥቁርን ወይም ነጭን ንቀዉ አይደለም:: ኢትዮጵያዊነት ከዘር ከቀለም በላይ የሰዉ ልጅነት መሆኑን ለማጠዬቅ ነበር::
ይሄን ጉዳይ የቀደሙ ኢትዮጵያዉያን አባቶች በወንጌል አንደምታ ዉስጥ ግሩም አድርገዉ ገልጸዉታል:: ቅዱስ ጳዉሎስም አይሁዳዊ የለም: ባሪያ የለም: ጌታ የለም: ነጭ የለም ሲል ስለ አንድ የሰዉ ዘር ለመናገር መነሳት ወሳኝ መሆኑን በሚገባ አብራርቷል::
የቀደሙ ኢትዮጵያዉያን እራሳቸዉን ከጥቁር ወይም ከቀይ : ወይም ከነጭ ቀለም በላይ አድርገዉ ያስተዉሉ ነበር:: እራሳቸዉን የሰዉ ሰር እንጅ የዚህ ወይ የዚያ ቀለም ወኪል አድርገዉ አያሥተዉሉም ነበር:: አጼ ሀይለስላሴ የተናገሩትን ጥልቅ የሰዉ ልጅ ማንነትና ከፍ ያለ ፍልስፍና በአሁን ዘመን ያለን ሰዎች በተሳሳተ መልክ በመረዳት ኢትዮጵያዊ የዚህ ቀለም ወይም የዚያ ቀለንም የሚንቅ ይመስለናል::ወይም ከጥቁር ወይም ከነጭ ቀለም የሚሸሽ ይመስለናል::
ሀይለስላሴ ለማለት የፈለጉት እኛ ኢትዮጵያዉያን የአዳም ልጆችን ሁሉ እኩል ነዉ የምናያዉ:: እሳቸዉ ማለት የፈለጉት ኢትዮጵያዉያን የዚህ ቀለም ወይም የዚያ ቀለም ተብለን መከፈል አንፈልግም:: ጥቁርም ነጭም : ቢጫም የሰዉ ዘር በእኛ አይን የአዳም ልጅ እስከሆነ ድረስ ለኢትዮጵያዊ ያለዉ ዋጋና የሰዉነት ቀረቤታ እኩል ነዉና:: ኢትዮጵያዊነት ከቀለም በላይ ነዉ ለማለት ነበር የፈለጉት::
የሆነ ሆኖ በዚያ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ምሁራን የአጼ ሀይለስላሴን አባባል ከኢትዮጵያዊነት ትምክህተኝነት ጋራ በማገናኘት ; እንዲሁም ከጥቁር ዘር ኢትዮጵያዉያን ለመራቅ የፈለግን በማስመሰል አቅርበዉት ነበር:: አንዳንዱም አሁን ድረስ ኢትዮጵያዉያንን ለማጥቂያነት ይጠቀምበታል:: የሆኖ ሆኖ ግን በዚያኛዉ ዘመን ኢትዮጵያዊያን የነበራቸዉ ጥልቅ የሰዉ ልጅ አመለካከት ከፍ ያለ ስለነበረ ኣጼ ሀይለስላሴ እኛ ኢትዮጵያዉያን ጥቁር ወይም ነጭ ቀለም ብለን እራሳችንን አንከፍልም አሉ::እሳቸዉ ብቻ ሳይሆን በርካታ የቀደሙ ታላላቅ አባቶቻችን ይሄን አስተሳሰብ ያራምዱት ነበር::
እኛ እራሳችንን የምናዬዉ እንደ አንድ የአዳም ልጅ ሲሆን የማንኛዉንም ቀለምም የምንመለከተዉ እንዲሁ ነዉ የሚል አንደምታ ያለዉን የአጼ ሀይለስላሴ ንግግር በተሳሳተ መንገድ የተረዳቸዉ ሰዉ ብዙ ነበር::
የሆኖ ሆኖ ግን እኛ በዚህ ዘመን የምንኖር ኢትዮጵያዉያን ይሄን የመሰለ የአጼ ሀይለስላሴን ንግግር በአግባቡ ተረድተን ለሌሎችም በዚህ መልክ ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጅ እኛ ኢትዮጵያዉያን የተለዬን ዘሮች ነን ብለን የተሳሳተ አስተሳሰብ ዉስጥ መግባት የለብንም::ወይም አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያዊነት ለማጥቃት በሚነሱበት ጊዜ እና ይሄን የመሰለዉን ታላቅ የአባቶቻችንን አስተሳሰብ በስህተት መንገድ እየተረጎሙ አንሻፈዉ ኢትዮጵያዊነትን ለማጣጣያነት ሲጠቀሙበት የአስተሳሰቡን ምጥቀት ማስረዳት ይጠበቅብናል እንጅ እልህ ዉስጥ በመግባት ሌሎች የሚፈልጉትን አሉታዊ ስሜት ማጸባረቅ አይገባም::
እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደማንኛዉም የሰዉ ዘር የሁሉም የሰዉል ጆች ወገን ስንሆን አንዳንድ የአለም ክፍሎች ለጥቁር ወይም ለነጭ ቀለም ከፍ ያለ ዋጋ እንደሚሰጡት ግን ለቀለም ዋጋ በመስጠት ይሄን ወይ ያን ወገን አናዳንቅም:: ከዚያ ይልቅ የሰዉ ልጅነት ከቀለም በላይ ነዉ ብለን እናስተምራልን:: እንናገራለን:: ይሄ የቀደሙ ኢትዮጵያዉያን አባቶች አስተምህሮት ነዉ እንጅ የኔ አስተምህሮት እንዳልሆነ ይሰመርበት::

No comments:

Post a Comment