Tuesday, November 7, 2017

በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው መከላከያ ወታደር እየከዳ መምጣቱ ታወቀ

 

የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር መከላከያውን እየከዳ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በመከላከያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስጋት ተፈጥሯል። በጄነራል ሳሞራ የኑስ የተመራው ከፍተኛ የጦር አዛዦች የተገኙበት ስብሰባ ላይ ከወታደሮች መክዳት ጋር በተያያዘ ሰፊ ውይይት እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል።
በተለያዩ ክፍለ ጦሮች ውስጥ የወታደሩ መክዳት በከፍተኛ ሁኔታ መስተዋሉንና ባሉትም ወታደሮች መሀል የመንፈስ ጥንካሬ መዳከሙ በስብሰባው ላይ በሰፊው ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ሆኗል። የክፍለ ጦር አዛዦች የወታደሮችን መክዳት የመከላከል ሃላፊነት የነሱ ድርሻ እንደሆነና ከአሁን በኋላም እድገት የሚሰጠው ወታደሮችን በማቆየት አመርቂ ውጤት ላመጡ አዛዦች እንደሚሆን ጄነራል ሳሞራ ገልጿል። በመከላከያ ውስጥ ከመክዳት ጋር ተያይዞ እየተፈጠረ ያለው ችግር ሃገሪቷ ከገባችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ጋር የተቆራኘ እንደሆነ መከላከያ ውስጥ ያሉ የጦር አዛዦች እርስ በርስ ሲያወሩ የሚገልጹት ቢሆንም በስብሰባው ላይ ደፍሮ የተናገረ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል። እንዲሁም የመከላከያ ሃይል ከምንጊዜም በላይ ጠንካራ እንደሆነ በሳሞራ የኑስ የቀረበው ገለጻ በስብሰባው ላይ የተገኙ አዛዦችን ሊያሳምን እንዳልቻለ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተል የነበረ ወኪላችን ተመልክቷል።
በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የጄነራል ሳሞራን ስም እያነሱ ሲያሞጋግሱ ተስተውሏል። ከስብሰባው በኋላ የጦር አዛዦች እንዴት ተኩኖ ነው እየከዳ ያለውን ሰራዊት ማስቆም የሚቻለው፤ ሰራዊቱ ልቡ ከኛ አይደለም፤ በዚህ ሁኔታ መከላከያ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው በማለት ጭንቀታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። በመከላከያ የተለያዩ ክፍለ ጦሮች ውስጥ የሚገኙ ወታደሮች በከፍተኛ ቁጥር መከላከያውን እየለቀቁ መምጣታቸውን ተከትሎ በአሁኑ ሰአት አንድ ሬጂመንት ጦር መያዝ ከሚገባው 700 የሰራዊት ቁጥር ውስጥ ከ400 በላይ እንዳልሆነ ከመከላከያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment