ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010) በሳውዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለው ጸረ ሙስና ዘመቻ ምርመራ ካለአግባብ የባከነው ገንዘብ 100 ቢሊየን ዶላር መሆኑን አጋለጠ። በሌብነት ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች ቁጥርም 199 መድረሱን የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታውቋል። ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የተጀመረው ተጠርጣሪ ልኡላንን፣ሚኒስትሮችንና ነጋዴዎችን ኢላማ ያደረገው የጸረ ሙስናው ዘመቻው በ32 አመቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን የተመራ ነው። በዘመቻው ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ሼህ መሀመድ አላሙዲን እንደሚገኙበት ይታወቃል። ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ሼህ ሳውድ አል ሞጀብን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው 100 ቢሊየን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሀገሪቱ በተደራጀ መንገድ በተፈጸመ ዝርፊያ ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ባክኗል ብለዋል። ዝርፊያ ስለመፈጸሙ...ም ጠንካራና አስተማማኝ መረጃ አለን ብለዋል። በዝርፊያው የተጠረጠሩት የንጉሳዊ ቤተሰቦችና ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው በሀገሪቱ ያለውን የዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳላወከው አስታውቀዋል። የተጠርጣሪዎቹ የግል የባንክ ተቀማጭ ሂሳብ መዘጋቱንም ተናግረዋል። እስካሁን 1700 የባንክ ተቀማጭ የሂሳቦች መዘጋታቸውም ታውቋል። የጸረ ሙስና ኮሚቴውም ወደ ሚቀጥለው የምርመራ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ሕጋዊ ፍቃድ እንዳለው ተናግረዋል። አቃቢ ሕጉ አክለውም እስካሁን 208 የሚሆኑ ሰዎች ለጥያቄ መቅረባቸውንና ሰባቱ ሳይከሰሱ በነጻ መለቀቃቸውን አስታውቀዋል። በሐገሪቱ ንጉስ ትዕዛዝ የተዋቀረው የጸረ ሙስና ኮሚቴም ስራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። ባለፉት ሶስት አመታት በተካሄደው ምርመራም 100 ቢሊየን ዶላር በተደራጀ ዘረፋ መባከኑን የሀገሪቱ አቃቢ ህግ ጨምረው ገልጸዋል። የተጠርጣሪዎቹን የሕግ መብት ለመጠበቅ ሲባልም በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳቸው ፈጽመውታል ተብሎ የሚጠረጠረውን ወንጀል ግን ከመግለጽ እንቆጠባለን ሲሉ ተናግረዋል አቃቢ ሕጉ። ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንዱ የሆኑት የሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ጉዳይ በኢትዮጵያ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ሲቀጥል የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዝምታን መርተዋል። የሕወሃት ድምጽ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግን ጉዳዩን በተመለከተ ዘገባዎችን ሲያወጣ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በዲፕሎማሲ መንገድ የሚመጡ መረጃዎችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከዚህ ውጪ ግን ሳውዳረቢያ ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሌላ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment