የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች የተሳሳተ መረጃ ሰጠ፡፡ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በተገኙበት በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል በተካሔደው ወይይት ላይ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች ተገኝተው ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ለማድረግ በስብሰባው ላይ ቢገኙም፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የተለያዩ ነባራዊ ሁኔታዎችን አዛብተው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት የፖለቲካ ምስቅልቅል እና የህዝብ ተቃውሞ እየበረታ ቢመጣም፣ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ግን ለዲፕሎማቶቹ ገለጻ ባደረጉበት ሰዓት፣ ሀገሪቱ ፍጹም ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹በሀገሪቱ የተከሰተውን ግጭት አስቁመናል፡፡›› ሲሉ የተናገሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ህዝብ ላነሳው ጥያቄዎችም መንግስታቸው ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም የዶ/ር ወርቅነህ መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ንጹኃንን በአደባባይ እየገደለ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ስለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለጻ ባደረጉበት ሰዓት ደግሞ፣ ‹‹መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እየተደራደረ እንደሚገኝና፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንደተደረሰም›› ተናግረዋል፡፡ ከመንግስት ጋር እየተደራደሩ ይገኛሉ የተባሉት ተቃዋሚዎች ግን፣ በህዝብ ዘንድ ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው፣ ከሊቀ መንበራቸው እና ከራሳቸው ሰራተኞች በቀር ሌላ ደጋፊም ሆነ ተከታይ ህዝብ የሌላቸው ፓርቲዎች መሆናቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡
ዶ/ር ወርቅነህ ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪም፣ በሀገሪቱ በጠቅላላ አሁን ላይ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ፣ የህዝቡም ጥያቄ በመንግስት አመራሮች እየተመሰለ እንደሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ አስተዳደር እንደሰፈነ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ ድርጅት ተወካዮች ገለጻ አድርገዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ ያደረጉበት ውይይት እጅግ የሚያሳፍር እና አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን በዲፕሎማቶች ፊት በዚህ ደረጃ ይዋሻሉ ተበሎ ያልተጠበቀበት እንደነበር ውይይቱን የተከታተሉ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡ ወይይቱ በጠቅላላ በተሳሳተ መረጃ እና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማይገልጹ ቃላት የታጨቀ እንደበር ታዛቢዎቹ አክለው ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment