Thursday, November 9, 2017

በኢትዮጵያ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ


Filed under:   
      
ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በአሁን ሰዓት በመንግስት ካዝና ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ አንድ ግለሰብ ባለሀብት ካለው ገንዘብ ጋር እንኳን የማይወዳደርበት ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አገዛዙ ለመስራት አቀድኳቸው ካላቸው ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ ቀጥ ብለው መቆማቸው ታውቋል፡፡ ጉዳዩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስደንጋጭ ነገር ሊከሰት እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው ከባድ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጥላውን ካጠላባቸው የመንግስት ተቋማት አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተነሳ ከፊል ስራውን ማቆሙም ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ ከውጭ የተበደረውን ገንዘብ መክፈል አቅቶት፣ የአበዳሪዎቹ ዓይን እየገረፈው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተቋሙ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ለመስራት አቅዶት የነበረው ዕቅድ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ሳይሳካ መቅረቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ተናግረዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ የተቋሙ አጠቃላይ የስራ መዋቅር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
‹‹የካፒታል ወጪያችን አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው፡፡›› ያሉት ዶ/ር አንዱዓለም፣ ቀጠል አድርገው ‹‹በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ግዥዎቻችን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተይዘው ነው የተቀመጡት፡፡  ግዥዎቻችን የሚከናወኑት ከውጭ ገበያ ነው፡፡ እነዚህን ዕቃዎች ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ዕቃዎች ግዥዎች ባንክ ውስጥ ሠልፍ ላይ ነው ያሉት፡፡›› በማለት በሀገሪቱ ውስጥ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከውጭ ተገዝተው የመጡ የባቡር ሐዲዶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ቤት ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ስራውን መስራት እንዳልቻለ ያማረረ ሲሆን፣ በሌሎች የመንግስት ተቋማት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደኋላ እየጎተተው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የአንድ ዶላር ዋጋ በ27 የኢትዮጵያ ብር እንዲመዘነር አዲስ ህግ ካወጣ በኋላ፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ መቃወሱን መረጃዎች እየጠቆሙ ናቸው፡፡
ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንዳልሆነ በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች አንዱ የሆነው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከሶስት ሳምንት በፊት ከሀገር ውስጥ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ከባንክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለው ውጣ ወረድ እና ሰልፍ አሰልቺ መሆኑን በምሬት ተናግሮ ነበር፡፡ ኃይሌ ‹‹በዚህ ሁኔታ ስራ መስራት ይከብዳል›› ሲልም ተማሮ ተናግሮ ነበር፡፡
BBN News November 9, 2017

No comments:

Post a Comment