Wednesday, November 8, 2017

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዲቪ ቪዛ ሎተሪ እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት ኢትዮጵያ ተጎጂ ነች ተባለ።

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዲቪ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ግብጽ ዋነኛ ተጎጂዎች ይሆናሉ ተባለ። እነዚህ ሀገራት በመርሃ ግብሩ መሰረት ብዙ ኮታ ከሚያገኙት ግንባር ቀደሞቹ መካከል መሆናቸውም ታውቋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥያቄውን ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት አንድ የኡዝቤክስታን ተወላጅ ኒዮርክ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገሪቱን የተወካዮች ምክር ቤት የዲቪ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት መርሃግብሩ የሚቀር ከሆነ በአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ግብጽ ዋነኛ ተጎጂዎች እንደሚሆኑ ታውቋል። ባለፈው ሳምንት አንድ ...የኡዝቤክስታን ተወላጅ በእቃ መጫኛ መኪና ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎችን በኒዮርክ ከተማ ከገደለ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወዲያውኑ የሀገሪቱ ምክር ቤት የዲቪ ቪዛ ፕሮግራምን እንዲሰርዝ ጠይቀዋል። የኡዝቤክስታኑ ተወላጅ ሳይፉሎ ሳይፓቭ የዲቪ ሎተሪ እድለኛ በመሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ወደ አሜሪካ መምጣቱ ታውቋል። በዲቪ ሎተሪ ወደ አሜሪካ የመጡ ሰዎች ጥቃት ሲፈጽሙ ይሄ ለ6ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ይመስላል የዲቪ ሎተሪ ጉዳይ በአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ዘንድ እንደገና መነጋገሪያ እየሆነ ነው። በተለይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሰዎች የዲቪ ሎተሪው ወንጀለኞች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ቀላል መንገድ ፈጥሯል ባይ ናቸው። በአሜሪካ ምክር ቤት ያሉ አባላት የፕሬዝዳንቱን ሃሳብ እንደሚቀበሉትም ባልፈው ሰኞ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኒዮርክ የደረሰውን ጥቃት እንደሰሙ ይህ የሎተሪ መርሃ ግብር ሰዎች በችሎታቸው ሳይሆን እንደ እድል ዕጣው ስለደረሳቸው ብቻ የሚመጡበት ነው ብለዋል። አፍሪካ በአንደኝነት የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ስትሆን አውሮፓና ኢሲያ ደግሞ ይከተላሉ። ባለፈው አመት ከአፍሪካ ከግብጽ 2 ሺ 855 ሰዎች የዕጣው አሸናፊ ሲሆኑ ከዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ 2 ሺ 778 ሰዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺ 143 ሰዎች የዕጣው እድለኞች በመሆን በ3ኛ ደረጃ ተመዝግባለች። በየአመቱ ወደ 50ሺ የሚጠጉ ሰዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሆኑም ታውቋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2001 በኒዮርክ ከደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት 10 አመት ቀደም ብሎ በ1990 በፕሬዝዳንት ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽ ፍርማ ህግ ሆኖ የወጣው የዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው የሚመጡ ጥቂት ሰዎች እያደረሱ ባለው የሽብር ጥቃት ምክንያት መርሃ ግብሩ እንዲያከትም ግፊት እየተደረገ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment