የራቀ ይመለስ!
ኢትዮጵያ ከተባበረ ሕዝብ ትግል ወዲያ መድኅን የላትም !!
ተደጋግሞ እንደተባለዉ የሕዝብ ጉልበቱ - ሕብረቱ ነዉ ። በአንድ ያበረ ሕዝብ ለመብቱም ሆነ ለነጻነቱ በሚያደርገዉ ትግል በቀላሉ ድልን ይቀዳጃል። የዚያኑ ያህል፤ ተነጣጥሎ ከተገኘ ደግሞ ሳይወድ በግድ የጠላቶቹ መጫወቻ መሆኑ አይቀሬ ነዉ። ይህን በሚገባ የተገነዘበዉ የወያኔ አገዛዝ በተገኘዉ የድክመት ቀዳዳ ሁሉ እየሾለከ መሠሪ ስልቶቹን በመተግበር እጅግ የሚያስፈራዉን ህብረታችንን ሲሰነጣጥር ቆይቷል ። እንዲያዉም ፤ወያኔያዊዉ አገዛዝ፤ የጸረ ሕዝብነቱንና የጸረ ኢትዮጵያነቱን ያህል፤ በአፍጢሙ ሳይደፋ እስከዛሬ ድረስ ከሥልጣን ተቆናጥጦ የመቆየቱ ምስጢር ሌላ አይደለም። ተረጋጮቹን ተገዢዎች በኃይማኖት ፤ በቋንቋና በባህል ከፋፍሎ ርስ በርሳቸዉ በጥርጣሬ እንዲተያዩና እንዳይቀራረቡ በሰይጣናዊ ትጋት ሳይታክት መሥራቱ ነዉ ። በዚህም እስከ ዛሬ በርካታ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ቀጭቷል። ቁጥር ያላቸዉን ሀገራዊ የዐመጽ ጅምሮችን ከተቀሰቀሱበት ክልል ሳይሻገሩ በእንጭጩ ጨፍልቋቸዋል ።
በቅርቡ፤ አዲስ አበባን በማልማት ስም በሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በተፈናቀሉበት ዐይን ያወጣ ወያኔያዊ ዘረፋ መነሾ በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ የአልገዛም ባይነት ቁጣ ይህን መሰሉ ዕጣ ከደረሳቸዉ እንቅስቃሴዎች በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባዉ ነዉ ። በክልሉ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዉስጥ በሚማሩ ተማሪዎች የተጀመረዉንና ወደተቀረዉ ኅብረተሰብ በፍጥነት የተዛመተዉን ይህንን ድንገተኛ የተቃዉሞ ማዕበል ለመግታት ዘረኛዉ አገዛዝ ልዩ ገዳይ ኃይሎቹን በማሰማራት ዘግናኝ የግፍ ርምጃዎችን ወስዷል ። አያሌ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችንን በጭካኔ ገድሏል ፤ አቁስሏል ፤ ወደ እስር ቤቶችም ወርዉሯል ። ተፈጥሮአዊ ባህሪዉ ነዉና፤ ለወደፊቱም በርካታ ዜጎቻችን በአሸባሪነት ወይም ፤ ራሱ ወያኔ ቀድሞ እንዳልሰየጠነበት፤ በጠባብነት ተፈርጀዉ እንደሚሳደዱና በስዉር እንደሚገደሉ የሚጠበቅ ነዉ።
ርግጥ ነዉ ፤ወያኔ በግፈኛ አገዛዙ ዳፋ የተጫረበትን እሳት፤ ቋያ ሰደድ ሆኖ አመድ ሳያደርገዉ በፊት ለጊዜዉ ሊከላዉ ችሏል ፤ ሙሉ በሙሉ ባያጠፋዉም እንኳ። ሆኖም ሕዝባችን የአገዛዙን መሰሪነት በመገንዘብ ፤ አንዱን ብሔረሰብን በሌላዉ ላይ ለማስነሳትና የትግሉን አቅጣጫ ለማስለወጥ በሠርጎ ገብ ካድሬዎቹ አማካይነት ያደረገዉን ጥረት በማጨናገፍ ብስለቱንና አርቆ አሳቢነቱን ማስመስከሩ በራሱ የአምባገነናዊዉ ዘረኛ ሥርዓት ማክተሚያ ሩቅ አለመሆኑን የሚያመላክት ትልቅ እመርታ ነዉ። የሥርዓቱ ዕድሜና ዘለቄታ በኢትዮጵያ ሕዝብ ክፍፍል ላይ መሆኑ እየታወቀ ፤ ግጭቶች ከተፈጠሩ በኋላ የአንድነት ጠበቃ መስሎ የመቅረብ እስስታዊ ባህሪዉ ብዙዎችን ደጋግሞ ማሳሳቱን አንዘነጋዉም።
ብዙዎች ኢትዮጵያዉያን በለጋ ዕድሜያቸዉ የወደቁበት ይህ ሰፊ መሠረት ያለዉ ሕዝባዊ የአልገዛም- አሻፈረኝ ባይነት በዘረኞቹ አገዛዝ ተንገፍግፎ ለተነሳዉ ሕዝብና ለሀገር አንዳች ግልግል ከማስገኘት ይልቅ የከፋ እመቃና ጭቆና የሚያስከትል ሆኖ መደምደሙ ያሳዝናል ። መነሾ ያደረጋቸዉ ወያኔያዊ የመሬት ዘረፋና ተያያዥ ጉዳዮችም ሆኑ ሌሎቹ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች በመላይቱ ኢትዮጵያ የሚዘወተሩና በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ የሚመላለሱ ሆነዉ ሳለ ዐመጹ ሀገራዊ ስፋት ሳይይዝ ብቻዉን ለጨካኙ የገዢዎች ጥቃት እንዲጋለጥ ሆኗል። ለዚህ ሰበብ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም እንደ ሕዝብ ለሚወርድብን መከራና ለተነጠቅነዉ መብት ምክንያት በሆነዉ አገዛዝ ላይ በጋራ ለመቆምና ለመታገል አለመቻላችን በዐቢይነት ሊጠቀስ የሚገባዉ ነዉ። ለዚህ ደግሞ፤ ወያኔ በሕዝቡ መሀል ያሰማራቸዉ ቅጥረኞችና ከዉድቀታቸዉ የማይማሩ ጥራዝ ነጠቆች ከሩቅ ሆነዉ ዐመጹን ከጽንፈኛ አቋማቸዉ በስተኋላ ለማሰለፍ ሌትና ቀን የነሰነሱት መርዝ በተቀረዉ ሕዝብ ዘንድ ባጫረዉ ጥርጣሬ፤ ትግሉን ከመሀልም ሆነ ከዳር ተገቢዉን ሕዝባዊ ድጋፍ አሳጥቶታል ። ለዐመጹ መዳፈንም ሆነ በትግሉ በወያኔ ለተቀጠፈዉ ሕይወትና ለደረሰዉ ጉዳት፤ እነዚሁ እኩያን የወያኔዉን አገዛዝ ያህል ተጠያቂዎች ናቸው።
እንደ አንዲት አገር ሕዝብ፤ ኢትዮጵያዉያን ሞታችንም ሆነ ሽረታችን በአንድ ላይ ነዉ። ምዕተ ዓመታትን የደረመሰዉ ታሪካችን የተጻፈዉ በጋራ የደማችን ቀለም ነዉ። ባህር አቋርጠዉ ከመጡ ወራሪዎች አስጥሎ በነጻነት ያዘለቀንም ያ ነዉ ።
ሕዝባዊዉ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያቸንፋል! በነጻነቷ ኮርታ፤ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!
http://www.eprpyl.com/resources/ethiopia%20newspaper_February_%20march%202016.pdf
No comments:
Post a Comment