እነዚህ ወገኖች የታሰሩት ወንጀል ሰርተው አይደለም። የታሰሩት ለሕዝብ ብለው ነው እንጂ። በማእከላዊ፣ በቂሊንጦ ..በመሳሰሉ ወህኒ ቤቶች ሲሰቃዩ ከጎናቸው ማን እንደቆመ፣ ልጆቻቸውን ማን እንደደገፈ እግዚአብሄር ነው የሚያውቀው።
የፖለቲካ መሪዎች ከመታሰራቸው በፊት እና ታስረው ከተፈቱ በኋላ “ሆይ ሆይ” የምንል ብዙ ነን። ግን እሥር ቤት እያሉ የሚያስባቸው ሰው ፣ ከጎናቸው የሚቆምሙ ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው ።
የሚታወቁ የሕሊና እስረኞች ብዙ ጊዜ ስማቸው ይጠራል፤ ግን ለትግሉ ዋጋ የከፈሉ ተረስተው የሚማቅቁ ፣ ያልተዘመረላቸው እስረኞች ግን እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።ስለ ተመስገን ደሳለኝ፤ ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ስለ አብርሃ ደስታ ..ብዙ ይጻፋል። ግን ማን ነው እስቲ ስለ አስቴር ስዩም፣ ስለ እንግዳው ዋኘዉ፣ ስለ በላቸው አወቀ፣ ስለ ሉሉ መለሰ …. የሚያውቀዉና የሚጽፈው ?
አያችሁ ወገኖች፣ በትግል ዉስጥ ከጎናችን የወደቁትን እየረሳን ፣ የታሰሩትን እየረሳን፣ የሚደረግ ትግል የዉሸት ትግል ነው። ታጋዮች ሰልፍ ሲመሩ ማድነቅ ብቻ አይደለም፤ ታጋዮች ለትግሉ ከፊት ፊት ሲቀድሙ ማድነቅ ብቻ አይደለም። ታጋዮች ሲታሰሩ ከጎናቸው መቆም ያስፈልጋል። ትግሉ የትም ሊደርስ ያልቻለው ፣ አሁንም ትግሉ ድንክ ሆኖ የቀረው ጀግኖቻችንን አሳሰረን፣ ዝም የምንል አደርባዮች በመሆናችን ነው። ራስ ወዳዶች፣ ፈሪዎች በመሆናችን ነው። ሌላው ሞቶ በሌላ ሬሳ ላይ ተረማምደን እንዲያልፍልን የምንፈለግ ደካሞች በመሆናችን ነው …..በጣም በጣም ነው የምናዛዝነው።
ይህን ስጽፍ በየጊዜው እስረኞችን ሄዳችሁ የምትጠየቁ፣ የእስረኞች ቤተሰቦችን በገንዘብ የምትደገፉ፣ ቤተሰቦችን የምታበረታቱ ፣ የእስረኞች ሁኔታ እየተከታተላችሁ ለሕዝብ የምታቀርቡ እንዳላችሁ አውቃለሁ። እናንተን እግዚአብሄር ያክብራችሁ። ትልቅ ሰዎች ናችሁ። ግን እናንተ ከባድሊ በማንኪያ እንደሚቀዳ ዉሃ ናችሁ። ከሚሊዮኖች መካከል እጅግ በጣም ጥቂቶች ናችሁ። አብዛኞቻችን እናንተ እያደረጋችሁት ያለዉን ጥቂቷን ጥረት ብናደርግና የድርሻችንን ለመወጣት ትንሽ መነሳሳት በዉስጣችን ቢኖር፣ ይሄን ጊዜ የትናየት በደረሰን ነበር። እኛ ግፍ ሲሰራ ዝም ባንል ኖሮ ወያኔዎች አይቀልዱብንም ነበር። ኢሰብአዊ የሆነ ግፋቸው ማስቆም እንችል ነበር።
ወገኖች መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለዉጦች ያስፈልጋሉ። ፕራዮሪታችንን በጣም ማስተካከል አለብን። ይሄ ዝባዝንኪ ፣ ወሬ ብቻ የሆነ የፖለቲካ ስብሰባዎች፣ ዉይይቶች ላይ ጊዜና ገንዘብ ማጥፋት የለብንም። አንዱ ደርጅት ይነሳና ስብሰባ ይጠራል፤ ሌላው ድርጅቶ ደግሞ ይነሳና ሌላ ስብስባ ይጠራል። በቃል ወሬ ብቻ !!!!!! ኤዲያ…..
ያ መቆም አለበት።፡ ፈረንጆች እንደሚሉት we have to go to the drawing board.
በዚህ አጋጣሚ ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ። ወንድም ሃብታሙ አያሌው እስር ቤት እያለ በተለይም በማእከላዊ የደረሰበትን ሁላችንም የምናወቀው ነው። ከዚያም የተነሳ ከፍተኛ ሕመም ሸምቶ በስቃይ ላይ ነው የሚገኘው። ሃብታሙ ሕክምና ያገኝ ዘንድ ፣ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት እየተደረገ ነው። ወደ 256 የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ተባብረዋል። የቃሌ ፕላቶክ ክፍል ፣ የአዲስ ድምጽ ራዲዮ እና የ ሳተናእ ድህረ ገጽ (satenaw.com) በዚህ ዙሪያ ላሳዩት እጅግ በጣም የሚያኮራ ኢትዮጵያዊ ሥራ በጣም ላመሰግናቸው እና አድናቆቴን ልግልጽላቸው እወዳለሁ።
ሌላ ልቤን በጣም የነካው ነገር አለ። ከ256 ሰዎች መካከል ስድስት ዶላር ያዋጡ ነበሩ። ስድስት ዶላር …!!! ሰው የአቅሙን ነው። የዶላሩ ማነስ መጠን አይደለም። ግን ትንሽ ብትምስልም፣ የድርሻን ለማበርከት መነሳቱ በራሱ ትልቅነት ነው። ስድስት ዶላር ምን ታደርጋለች ተብሎ ምንም አለማድረግ ይቻል ነበር። የኔ ደርሻም ለዉጥ አያመጣም ብለን ተስፋ ቆርጦ ዝም ማለት ይቻል ነበር። ግን ስድስት ዶላር ከሌሎች ጋር ተደምራ ነው ሺሆች የደረሰችው፡ እኛ ሚሊዮኖች ነን። ጥቂቶች ብዙ መስዋኣትነት ከፍለው ለዉጥ እንዲያመጡ ከምንጠብቅ፣ ትንሽም ትሁን የድርሻችንን ለማበርከት እያንዳንዳችን ብንነሳ ተዓምር እንሰራ ነበር።
No comments:
Post a Comment