ይህ ግፈኛ የፋሽስት አገዛዝ በመላው ኢትዮጵያ ዜጋ ላይ የፈፀማው እና በመፈፀም ላይ የሚገኘው ግፍና በደል ተዘርዝሮ አያልቅም። «ዐማራው ጠላቴ ነው» በማለት ዘሩን ለማጥፋት እና ለማጽዳት የተነሳው ከ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን ዘመቻው ሊያባራ እና ሊገታ ባለመቻሉ፣ የመላውን የዐማራ ተወላጅ ልብ ሰብሮታል፤ ዝምታውንም አደፍርሶበት ይገኛል። የዚህን ዓመት የፋሲካ በዓል በምናከብርበት ወቅት በስጋት እና በፍርሃት የተወጠሩ ወገኖቻችንን ትጥቅ በማስፈታት ሌት ተቀን በመጨፈጨፍ ላይ ይገኛሉ። የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የሠቲት እና ዋልድባ ወገኖቻችን ከተወለዱበት መንደራቸው ተፈናቅለው መድረሻ አጥተው ከግድያ የተርፉት በውክበትና በልቅሶ ላይ ናቸው። የጋምቤላ፣ የአፋር እና የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ህጻናት እና ሽማግሌዎች በትግሬ-ወያኔ ታጣቂዎች ያለምንም ርህራሄ በግፍ መጨፍጨፋቸው ተዘግቧል።እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ የሱዳን እስላማዊ አገዛዝ እና የትግሬ-ወያኔ በሚሠራው የፖለቲካ ቁማር ስሌት ታሪካዊ እና ለም መሬታችን ዐይናችን እያዬ ጀሮአችን እየሰማ በችሮታ ተሰጥቷል። ከዛሬ ፵(አርባ) ዓመታት በፊት አንድ ብር የማታወጣዋ አንድ ዶሮ ዛሬ ዋጋዋ ከመቶ ብሮች በልጧል፣ በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም. «500,000 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተራቡ» ተብሎ አብዮት ሲፈነዳ ባለፉት ፳፭(ሃያ አምሥት) ዓመታት ግን በየዓመቱ በትንሹ ከ፳(ሃያ) ሚሊዮን የማያንሰው ሕዝባችን ለርሃብ ችግር ተጋልጦ ይገኛል። እንግዲህ በትግሬ-ወያኔ የአገዛዝ ዘመን የተገኘው «ዕድገት» ይህ ነው። ስለዚህ ይህ ሕዝብ የትንሣኤውን በዓል ትርጉም እና ዓላማ ለማንሰላሰል የሚችልበት አቅም የለውም። በአጠቃላይ «ትግራይን ከቀሪዋ ኢትዮጵያ ነፃ አወጣለሁ» በሚል ሰበብ አገር የሚያተራምሰው የትገሬ-ወያኔ ቡድን አገራችንን እንዳልነበረች አድረጎ በማፍረስ ጀግናውን ሕዝብ በባርነት ቀንበር ስር እንዲወድቅ አድርጎታል።
ውድ ኢትዮጵያን፦
የኢትዮጵያ ትንሣኤ መቼ ነው? የንፁሀን ደም ይጮሃል! የትንሣኤው ነጻነት ያለው በእኛው በኢትዮጵያውያን እጅ እይደለንምን? ምድራችን በትግሬ-ወያኔ በግፍ የተጨፈጨፉ ከአምስት ሚሊዮን የማያንሱ የዐማራ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ደም በውስጧ አምቃ በምጥ ላይ ትገኛለች። የግፉ እና የበደሉ ጽዋ ሞልቶ እየፈሰሰ ነው። ቅድስት አገራችን የሲዖል አምሣል ሆናለች። በአጭሩ በቁማችን ሞተናል፣ ተቀብረናል። ሰለሆነም ትንሣኤ ያስፈልገናል። የመቃብራችንን ድንጋይ የሚፈነቅልልን በአንድነት የሚቀጣጠለው የሠፊው ኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣ ስለሆነ «አሁንስ በቃኝ» በማለት በኅብረት ለነጻነት የሚያበቃ ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሳ እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይባርክ!
No comments:
Post a Comment