Wednesday, April 6, 2016

ኢትዮጵያና የአስር ዓመታት የኢንተርኔት አፈና ( በአጥናፉ ብርሃኔና በዘላለም ክብረት

ሐሙስ ጠዋት ግንቦት 10፣ 1998 መንግስታዊው የቴሌኮም ድርጅት የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኤጀንሲ በጊዜው አሉኝ ካላቸው አንድ መቶ አስራ ሶስት ሽህ የኢንተርኔት ደንበኞቹ መካከል ጥቂቶቹ ከምርጫ 97 ማግስት የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ በተወሰደው አፈና ምክንያት አማራጭ እየሆኑ ከመጡት ጥቂት ጦማሮችና የዜና ድረ ገፆች ላይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለማየት ከኮምፒውተሮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ቢሞክሩም አብዛኞቹ ሊሰሩላቸው አልተቻላቸውም ነበር፡፡ በጊዜው በአንድ ሌሊት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ከተዘጉት አስር ገደማ ጦማሮችና ድረ ገፆች መካከል አንዱ የሆነው ሰምና ወርቅ ጦማር ግንቦት 09፣ 1998 አመሻሹ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን ሰምና ወርቅ ጦማርን ጨምሮ ሌሎች ጦማሮችንና ድረ ገፆችን በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማድረጉን ገልፆ ነበር፡፡
ይህ ከሆነ ከአስር ዓመታት በኋላ አያንቱ የተባለውና የኦሮሞ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚፅፈው ድረ ገፅ የካቲት 24፣ 2008 ባወጣው ፅሁፍ ምንም እንኳ እየጨመረ የመጣውን የአንባቢዎቹን ቁጥር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ አቅሙን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ቢሆንም ከየካቲት 23፣ 2008 ጀምሮ ድረ ገፁ በኢትዮጵያ ውስጥ በድጋሚ እንዳይታይ መታገዱን ዘግቦ ፅፏል፡፡
የኢንተርኔት አፈናው (Internet Censorship) ከተጀመረ አስር ዓመታት ቢያስቆጥርም ትናንት ዛሬን፣ ዛሬ ደግሞ ትናንትን በእጅጉ ይመስላሉ፡፡
የአፈናው አፍሪካዊ ፈር ቀዳጅ
ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት አንፃር በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓለም ጭራ ሀገራት አንዷ እንደሆነች ዓለማቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ሕብረት (International Telecommunication Union) በየዓመቱ የሚያወጣውን ሪፖርት ብቻ በመመልከት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሃያ አመታት ውስጥ ከሶስት በመቶ በላይ መሔድ ያልቻለው የኢትዮጵያዊያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ሀገሪቱ በዚህ ዘርፍ ያለችበትን አሳዛኝ ሁኔታ የሚገልፅም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment