Monday, November 13, 2017

በኢትዮጵያ ማናቸውንም የተቃውሞ ስልፍ ማድረግ ተከለከለ

ዋዜማ ራዲዮ- የሀገሪቱ የፀጥታና ደህንነት ምክር ቤት ትናንት ባደረገው ስብስባ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚስተካከል አዲስ ስልፍና ተቃውሞ የማድረግ መብትን የሚያግድ ክልከላ ጥሏል።
አዲሱ የሰልፍ ገደብን የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ቢያቀርብበትም ከብዙ ክርክር በኋላ ስምምነት ተደርሶበታል።
በተለይ የፀጥታ ሀይሎች “እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ” መባሉ የኦሮሚያን ክልል እንደሚያሳስበው ገልጿል።
በአዲሱ የፀጥታ ዕቅድ መሰረት ሀገሪቱን በተለያዩ ዕዞች በሚመሩ የፌደራል መከላከያ ስራዊት አመራር ስር በማድረግ ለመቆጣጠር ታቅዷል።
አደረጃጀቱ ከዚህ ቀደም የኮማንድ ፖስት በመባል የሚጠራውን መዋቅር የሚከተል መሆኑን በስብሰባው የተካፈሉና ስለ እቅዱ በቅርበት የሚያውቁ የዋዜማ ምንጭ ነግረውናል።
በተለይ የክልልና የልዩ ሀይል እንዲሁም የፌደራል የፀጥታ ሀይሎች መካከል ያለውን አለመናበብ ለማስወገድ ማናቸውም መመሪያ በፌደራሉ ዕዝ ብቻ የሚወሰን እንደሚሆን ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
“አስቸኳይ አዋጅ ተብሎ ያልወጣው አለማቀፉ ማህበረሰብ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ናት ብሎ ያስባል፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝምንም ያዳክማል” በሚል መሆኑን ምንጫችን ተናግረዋል።
በፌደራል ፀጥታ አካላቱና በክልል ርዕሰ መስተዳድሮች መካከል ከፍተኛ አለመግባባትና አለመተማመን መከሰቱንም ከስብሰባው የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
“ሰው በመግደል ተቃውሞን ከማባባስ በቀር መፍትሄ አይመጣም፣ ፖለቲካዊ መፍትሄ ቢበጅለት የተሻለ ነው” በሚል የተከራከሩም ነበሩ።
በተለይ ብሄርን ማዕከል ባደረገ ጥቃት ከፍ ያለ አደጋ ተጋርጦብናል ያሉ ክልሎች መለዮ ለባሹ ጣልቃ ካልገባ ብዙ ጥፋት ይደርሳል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ማህበራዊ ሚዲያን በሚመለከትም ስፊ ክርክር ተደርጓል። “እንደ አስፈላጊነቱ እርምጃ እንዲወሰድ” ከስምምነት ተደርሷል።
ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡትን ሀሳቦች በማካተት አዳዲስ የፀጥታ እርምጃዎች በተከታታይ የሚገለፁ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Sunday, November 12, 2017

አንዳንድ የገዢው ፖርቲና የሼህ አላሙዲ ደጋፊዎች ሼሁ ነገ ከእስር ተፈተው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ በማለት በመዘገብ ላይ ናቸውዜናውን ከገለልተኛ ወ ገ ን ማረጋገጥ አልቻልንም!

አንዳንድ የገዢው ፖርቲና የሼህ አላሙዲ ደጋፊዎች ሼሁ ነገ ከእስር ተፈተው ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ በማለት በመዘገብ ላይ ናቸው
ዜናውን ከገለልተኛ ወ ገ ን ማረጋገጥ አልቻልንም!
አልቻልንም! ይህ ዘራፊ  ወንጀለኛ ሙሰኛ ዛሬ እንኳን ቢለቀቅ ኢትዮጰያ ውስጥ ለሰራው ወንጅል ግን አንድ ቀን የህዝብ መንግስት በሚቋቋምበት ጊዜ ግን ፍርዱን ያገኛል ምንም አትጠራጠሩ አገራችን እንዲህ አይነቱን ወንጀለኛ ዘራፊ ለማስጠጋት ቦታ ሊኖራት አይገባም!

Thursday, November 9, 2017

በኢትዮጵያ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ


Filed under:   
      
ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በአሁን ሰዓት በመንግስት ካዝና ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ አንድ ግለሰብ ባለሀብት ካለው ገንዘብ ጋር እንኳን የማይወዳደርበት ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ በዚህም የተነሳ አገዛዙ ለመስራት አቀድኳቸው ካላቸው ፕሮጀክቶች መካከል አብዛኞቹ ቀጥ ብለው መቆማቸው ታውቋል፡፡ ጉዳዩ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስደንጋጭ ነገር ሊከሰት እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተከሰተው ከባድ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጥላውን ካጠላባቸው የመንግስት ተቋማት አንዱ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተነሳ ከፊል ስራውን ማቆሙም ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ ከውጭ የተበደረውን ገንዘብ መክፈል አቅቶት፣ የአበዳሪዎቹ ዓይን እየገረፈው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተቋሙ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ለመስራት አቅዶት የነበረው ዕቅድ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ሳይሳካ መቅረቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ ተናግረዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ የተቋሙ አጠቃላይ የስራ መዋቅር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
‹‹የካፒታል ወጪያችን አፈጻጸም ዝቅተኛ ነው፡፡›› ያሉት ዶ/ር አንዱዓለም፣ ቀጠል አድርገው ‹‹በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ ግዥዎቻችን በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተይዘው ነው የተቀመጡት፡፡  ግዥዎቻችን የሚከናወኑት ከውጭ ገበያ ነው፡፡ እነዚህን ዕቃዎች ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ዕቃዎች ግዥዎች ባንክ ውስጥ ሠልፍ ላይ ነው ያሉት፡፡›› በማለት በሀገሪቱ ውስጥ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከውጭ ተገዝተው የመጡ የባቡር ሐዲዶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ሀገር ቤት ሳይገቡ ቀርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ስራውን መስራት እንዳልቻለ ያማረረ ሲሆን፣ በሌሎች የመንግስት ተቋማት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደኋላ እየጎተተው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር መጀመሪያ የአንድ ዶላር ዋጋ በ27 የኢትዮጵያ ብር እንዲመዘነር አዲስ ህግ ካወጣ በኋላ፣ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ መቃወሱን መረጃዎች እየጠቆሙ ናቸው፡፡
ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንዳልሆነ በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች አንዱ የሆነው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከሶስት ሳምንት በፊት ከሀገር ውስጥ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ከባንክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለው ውጣ ወረድ እና ሰልፍ አሰልቺ መሆኑን በምሬት ተናግሮ ነበር፡፡ ኃይሌ ‹‹በዚህ ሁኔታ ስራ መስራት ይከብዳል›› ሲልም ተማሮ ተናግሮ ነበር፡፡
BBN News November 9, 2017

ሳውዲ በሙስና ካለአግባብ የባከነው ገንዘብ 100 ቢሊየን ዶላር መሆኑን አጋለጠች ።

ኢሳት ዜና–ጥቅምት 30/2010) በሳውዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለው ጸረ ሙስና ዘመቻ ምርመራ ካለአግባብ የባከነው ገንዘብ 100 ቢሊየን ዶላር መሆኑን አጋለጠ። በሌብነት ተጠርጥረው የተያዙት ሰዎች ቁጥርም 199 መድረሱን የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታውቋል። ባለፈው ቅዳሜ ምሽት የተጀመረው ተጠርጣሪ ልኡላንን፣ሚኒስትሮችንና ነጋዴዎችን ኢላማ ያደረገው የጸረ ሙስናው ዘመቻው በ32 አመቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን የተመራ ነው። በዘመቻው ተጠርጥረው ከተያዙት ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ሼህ መሀመድ አላሙዲን እንደሚገኙበት ይታወቃል። ጠቅላይ አቃቢ ሕጉ ሼህ ሳውድ አል ሞጀብን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው 100 ቢሊየን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሀገሪቱ በተደራጀ መንገድ በተፈጸመ ዝርፊያ ባለፉት ጥቂት አስርት አመታት ባክኗል ብለዋል። ዝርፊያ ስለመፈጸሙ...ም ጠንካራና አስተማማኝ መረጃ አለን ብለዋል። በዝርፊያው የተጠረጠሩት የንጉሳዊ ቤተሰቦችና ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸው በሀገሪቱ ያለውን የዕለት ተዕለት የንግድ እንቅስቃሴ እንዳላወከው አስታውቀዋል። የተጠርጣሪዎቹ የግል የባንክ ተቀማጭ ሂሳብ መዘጋቱንም ተናግረዋል። እስካሁን 1700 የባንክ ተቀማጭ የሂሳቦች መዘጋታቸውም ታውቋል። የጸረ ሙስና ኮሚቴውም ወደ ሚቀጥለው የምርመራ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ሕጋዊ ፍቃድ እንዳለው ተናግረዋል። አቃቢ ሕጉ አክለውም እስካሁን 208 የሚሆኑ ሰዎች ለጥያቄ መቅረባቸውንና ሰባቱ ሳይከሰሱ በነጻ መለቀቃቸውን አስታውቀዋል። በሐገሪቱ ንጉስ ትዕዛዝ የተዋቀረው የጸረ ሙስና ኮሚቴም ስራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል። ባለፉት ሶስት አመታት በተካሄደው ምርመራም 100 ቢሊየን ዶላር በተደራጀ ዘረፋ መባከኑን የሀገሪቱ አቃቢ ህግ ጨምረው ገልጸዋል። የተጠርጣሪዎቹን የሕግ መብት ለመጠበቅ ሲባልም በግለሰብ ደረጃ እያንዳንዳቸው ፈጽመውታል ተብሎ የሚጠረጠረውን ወንጀል ግን ከመግለጽ እንቆጠባለን ሲሉ ተናግረዋል አቃቢ ሕጉ። ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት አንዱ የሆኑት የሼህ መሀመድ ሁሴን አላሙዲ ጉዳይ በኢትዮጵያ ትልቅ የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑ ሲቀጥል የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዝምታን መርተዋል። የሕወሃት ድምጽ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ግን ጉዳዩን በተመለከተ ዘገባዎችን ሲያወጣ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በዲፕሎማሲ መንገድ የሚመጡ መረጃዎችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከዚህ ውጪ ግን ሳውዳረቢያ ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሌላ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።

መረጃ በጨፌ ዶንሳ ው ተቃውሞ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በቃጠሎ ወድመዋል።

መረጃ
በጨፌ ዶንሳ ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ ውሎአል። በርካታ ትምህርት ቤቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች በቃጠሎ ወድመዋል። እስከ 15 የሚደርሱ ወጣቶች ተይዘው ታስረዋል። ከከተማዋ በ500 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሚሳኤል ምድብ እየተባለ የሚጠራው የአየር መቃወሚያን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች የተከማቹበት ቦታ፣ በልዩ ሁኔታ እየተጠበቀ ነው። ተቃውሞው ነገም ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

Wednesday, November 8, 2017

ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ ለአደጋ የተጋለጠው የባለሀብቶቹ ንብረት 33 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ተመልክቷል።

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010)የሳውዲ አረቢያ መንግስት ባለፈው ቅዳሜ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ሼህ መሀመድ አላሙዲንን ጨምሮ የሌሎች ታሳሪዎችን የባንክ ተቀማጭ ሒሳብ አገደ። ከእስሩ ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ለአደጋ የተጋለጠው የባለሀብቶቹ ንብረት 33 ቢሊየን ዶላር እንደሚገመትም ከብሉምበርግ ዘገባ መረዳት ተችሏል። የሼህ መሀመድ አላሙዲን ቃል አቀባይ ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ርምጃው በሳውዲ አረቢያ ውስጥ የተገደበና በሌሎች ሀገራት ያላቸውን ንብረት የማይመለከት መሆኑን ገልጸዋል። ቋሚ መኖሪያቸውን በሳውዳረቢያ ጅዳ ያደረጉት ሼህ መሀመድ አላሙዲን እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ በሳውዳረቢያ ሪያድ በተካሄደው ግሎባል ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ከተገኙ በኋላ መያዛቸውና መታሰራቸውም ተመልክቷል። ከሳውዲ ባሻገር በሞሮኮ፣በሲውዲን...ና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመትን ያላቸው ሼህ መሀመድ አላሙዲን የሳውዲው እስራትና እገዳ በሌሎች ሀገራት ኢንቨስትመንታቸው ላይ ተጽእኖ አይኖረውም ሲሉ ቃል አቀባያቸው ቲም ፓንደር ተናግረዋል። በሳውዲ የተፈጠረውም ሁኔታ የንጉሳውያን ቤተሰቦች የውስጥ ችግር ነው ሲሉ ለብሩምበርግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የ10 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ሀብት ባለጸጋ በሆኑት በሼህ መሀመድ አላሙዲንና በሌሎች ታሳሪዎች ላይ የተጣለው እገዳ የግል ተቀማጭ ሂሳባቸውን ብቻ የሚመለከት መሆኑንም የሳውዳረቢያው ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። የታሳሪዎቹ ኩባንያ ተቀማጭ ሒሳብ አለመታገዱንና ሕጋዊውን የባንክ ስርአት ተከትለው ገንዘባቸውን ማንቀሳቀስ እንደሚችሉም ይፋ ሆኗል። የብሪታኒያው ዴይሊ ሜል ይፋ ያደረገውና በታዋቂው ሪትዝ ካርልተን ሆቴል ወለል ላይ ፍራሽና ብርድልብስ ታድሏቸው የታሰሩት ባለስልጣናት፣ባለሃብቶችና ልኡካን በቁጥር 50 ያህል መሆናቸው ተመልክቷል። የሳውዳረቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንደገለጹት ደግሞ ይህ እስራት የመጨረሻው ሳይሆን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በቀጣይ የሚታሰሩ መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዲቪ ቪዛ ሎተሪ እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት ኢትዮጵያ ተጎጂ ነች ተባለ።

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 29/2010) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዲቪ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ በአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ግብጽ ዋነኛ ተጎጂዎች ይሆናሉ ተባለ። እነዚህ ሀገራት በመርሃ ግብሩ መሰረት ብዙ ኮታ ከሚያገኙት ግንባር ቀደሞቹ መካከል መሆናቸውም ታውቋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥያቄውን ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት አንድ የኡዝቤክስታን ተወላጅ ኒዮርክ ውስጥ ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገሪቱን የተወካዮች ምክር ቤት የዲቪ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር እንዲሰረዝ በጠየቁት መሰረት መርሃግብሩ የሚቀር ከሆነ በአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ግብጽ ዋነኛ ተጎጂዎች እንደሚሆኑ ታውቋል። ባለፈው ሳምንት አንድ ...የኡዝቤክስታን ተወላጅ በእቃ መጫኛ መኪና ባደረሰው ጥቃት 8 ሰዎችን በኒዮርክ ከተማ ከገደለ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወዲያውኑ የሀገሪቱ ምክር ቤት የዲቪ ቪዛ ፕሮግራምን እንዲሰርዝ ጠይቀዋል። የኡዝቤክስታኑ ተወላጅ ሳይፉሎ ሳይፓቭ የዲቪ ሎተሪ እድለኛ በመሆን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 ወደ አሜሪካ መምጣቱ ታውቋል። በዲቪ ሎተሪ ወደ አሜሪካ የመጡ ሰዎች ጥቃት ሲፈጽሙ ይሄ ለ6ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በዚህም ምክንያት ይመስላል የዲቪ ሎተሪ ጉዳይ በአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ዘንድ እንደገና መነጋገሪያ እየሆነ ነው። በተለይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ሰዎች የዲቪ ሎተሪው ወንጀለኞች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ቀላል መንገድ ፈጥሯል ባይ ናቸው። በአሜሪካ ምክር ቤት ያሉ አባላት የፕሬዝዳንቱን ሃሳብ እንደሚቀበሉትም ባልፈው ሰኞ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኒዮርክ የደረሰውን ጥቃት እንደሰሙ ይህ የሎተሪ መርሃ ግብር ሰዎች በችሎታቸው ሳይሆን እንደ እድል ዕጣው ስለደረሳቸው ብቻ የሚመጡበት ነው ብለዋል። አፍሪካ በአንደኝነት የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ስትሆን አውሮፓና ኢሲያ ደግሞ ይከተላሉ። ባለፈው አመት ከአፍሪካ ከግብጽ 2 ሺ 855 ሰዎች የዕጣው አሸናፊ ሲሆኑ ከዲሞክራቲክ ሪፖብሊክ ኮንጎ 2 ሺ 778 ሰዎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺ 143 ሰዎች የዕጣው እድለኞች በመሆን በ3ኛ ደረጃ ተመዝግባለች። በየአመቱ ወደ 50ሺ የሚጠጉ ሰዎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንደሆኑም ታውቋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2001 በኒዮርክ ከደረሰው የአሸባሪዎች ጥቃት 10 አመት ቀደም ብሎ በ1990 በፕሬዝዳንት ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽ ፍርማ ህግ ሆኖ የወጣው የዳይቨርሲቲ ቪዛ ሎተሪ መርሃ ግብር የዕድሉ ተጠቃሚ ሆነው የሚመጡ ጥቂት ሰዎች እያደረሱ ባለው የሽብር ጥቃት ምክንያት መርሃ ግብሩ እንዲያከትም ግፊት እየተደረገ ይገኛል።