Saturday, May 6, 2017

ከ‹አንበሳው› ምድር የተገኘው አንበሳ ልጅ አሰፋ ጫቦ በክብር አረፈ

    


የጀግና ዕረፍቱም ያስተምራል
ከ‹አንበሳው› ምድር የተገኘው አንበሳ በክብር አረፈ//
ዛሬ እኩሌ ቀን ላይ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ኢትጵያዊያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት … ሳይከፋፍላቸው ተሰባስበው በዛሬው 76ኛ የድል በዓል ዕለት አንድ ‹ጋሞ› በክብር አሳርፈዋል፡፡ አጋጣሚውን/ግጥምጥሙን የጀግናው ዕረፍት በዚህ በዓል ዕለት እንዲሆን ፈጣሪ የፈቀደው ጀግንነቱን ሊመሰክርለት ነው ብሎ ‹ማሰብ› ይቻላል፡፡

‹ጋሞ› ማለት በአማርኛ ‹አንበሳ› ነው፡፡ ዛሬ በክብር የሸኘነው የኢትዮጵያ ‹ብርቅ› (ኖረና ሞተ የሚባል ሁሉ አያገኘውምና) ልጅ አሰፋ ጫቦ ደግሞ ‹‹ጋሞነቱና ኢትዮጵያዊነቱ ያልተጋጩበት›› የጋሞ በረከት ጋሞ ነው፤ አንበሳ ነው፡፡ ጋሞው እንኳን ቆሞ ‹‹ በድኑና የሙት መንፈሱ›› ህወኃት/ ኢህአዴግን የሚያርበደብድ ጀግና ነው ( ቀብሩ ከተገኘበት የጋሞ ምድር እንዲፈጸምና ሥጋው ከተፈጠረበት የጋሞ አፈር እንዲቀላቀል የቀረበውን ኃሳብ ህወኃት/ኢህአዴግ አልቀበልም ብሎ አዲስ አበባ እንዲቀበር መደረጉን አስከሬኑ አገር ቤት እንዲያርፍ ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት የተገኘው መረጃ ያመለክታል) ፡፡ ጠንካራ እምነቱ፣ የኢትዮጵያ ፍቅሩና ኢትዮጵያዊ መንፈሱ እርሱ ባይለውም እኔ የምላቸው ‹ጠላቶቹን› የሚያርበደብድና እንቅልፍ የሚነሳ ፣ ወዳጆቹንና በኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ለሌለባቸው ሁሉ የጽናት ሥንቅ ፣ የማንነትና ኢትዮጵያዊነት ጥምረት በረከት ነው፡፡ ጋሼ አሰፋ በህይወት ዘመኑ በጻፋቸው ሲመግበን የኖረውን ዛሬም ‹አስከሬኑን› ከበን ባደመጥነው የህይወት ታሪኩ ( ወዳጁ አቶ ዘገዬ ሞላ ከተለመደው የህይወት ታሪክ አቀራረብ በተለየ መንገድ በቤተሰቦቹ የተዘጋጀውን መልዕክት ሳግ እየተናነቀው በትረካ መልክ ያስደመጠን ) ‹ እውነትም ይህ ‹ጀግና › በዕረፍቱም ስለ ሰብዐዊነት/የሰው ልጅ እና ኢትዮጵያዊነት ይተርካል፣ ሁላችንም ሄደን ፣ሄደን በአዳምና ሄዋን ልጆች አንድ ስለመሆናችን፣ ልዩነቱ ከዚያ ወዲህ/በኋላ የመጣ መሆኑን ያስተምራል፤› አስብሎናል፡፡ ጋሼ አሴ ካንተ ብዙ ተምረናል፤ ባንተ ገና ብዙ እንማራለንና ‹ ብታልፍም › በመንፈስህ . በአስተምሮህና በተሞክሮህ በተውካቸው በረከቶች ሁሌም አብረሄን ትኖራለህ፣ በጽናትህ ታሪክህን አጽንተሃልና ፤ በዚህ እንጽናናለን ፡፡
የአንዱ አሰፋ ‹ቃል/ሃሳብ› አገዛዞችን (ደርግ፣ ህወኃት) ከባታሊዮን ጦር በላይ እንደሚያስፈራ ከእናቱ እቅፍ ከተለየ/ከወረደ በኋላ በምድር ካሳለፈው ዕድሜ ግማሹን (35 + ዓመት – በደርግ እስር ቤትና ህወኃት አሳዶት በስደት) ከሚወዳት አገሩ ተነጥሎ እንዲኖር መሆኑ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ ህወኃት/ ኢህአዴግ ሆይ ለአገራቸውና ወገናቸው ይጠቅማል የሚሉት ካንተ የተለዩ ባለኃሳብ ‹ ጀግኖቻችንን › አሰቃይተህ ( እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ ፣ በቀለ ገርባ ፣ መረራ ጉድና፣ አበበበ ቀስቶ፣ . . .) አሳደህ፣ አሰድደህ ፣አስከሬናቸውን ለማወራረጃነት (ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ጄ/ል ዋቆ ጉቱ፣. . .) ማስረከቡን፤ ሥጋቸውንም ማሰደድ ( የመኢሶኑ ሙሌ፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ተስፋዬ ለማ . . .) ትተህ ከነሃሳባቸው በአገራቸው ምድር ፣በህዝባቸው መሃል በነጻነት እንዲኖሩ ስለማድረግ ፣እንደልደታ ንፍሮ የተበተኑትን ወደ አገራቸውና ህዝባቸው እንዲመለሱ ማሰብ ይጠቅምሃልና አስብበት፡፡ ይቅርና ለነጻነትና ክብራቸው የሚታገሉ፣ አገሬን ሲሉ ሥጋቸው በሰው አገር / በስደት የቀረ ኢትዮጵያዊያን ነጻነታችንና ክብራችን ሲመለስ፣ የአገራችን ባለቤት ስንሆን ለአገራቸው መሬት ይበቃሉና፣ ይህም ሩቅ ባለመሆኑ በዚህም እንጽናናለን፡፡
‹‹ ጋሞ ሃይቀና፣›› አንበሳ አይሞትም እንዲሉ ሆኖ ጋሼ አሴም አብሮን ይኖራል፣ ባመነውና በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ፣ ለአገሬ ይበጃል ብሎ ያመነውን ማንንም ሣይፈራ፣ሳይሰስትና በሆዱ ሳያስቀር በግንባርና፣አደባባይ ተናግሮና ጽፎ፣ በወደደውና በፈቀደው መንገድ ኖሮ፣ ጥላቻንና ጠባብነት ተዋግቶ፣ መቻቻልና አንድነትን ሲያስተምር ደክሞት ‹‹ አረፈ›› እንጂ አልሞተም፤ ጀግና አይሞትምና ፡፡ በጋሼ አሰፋ ትዕዛዝ መሰረት ( ካገለገለበት የጨንቻ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ባለማረፉ ብንቆጭም ) በጋሞ ባህልና ወግ መሰረት ‹ጨፍረን› ፣ባደገበት የቤተክህነት ህግ መሰረት በዝማሬና ውዳሴ <አሳረፍነው> እንጂ አልቀበርነውምና ከእርሱ የተገኘው በረከት አብሮን ይዘልቃል፡፡
እንግዲህ ጋሼ አሰፋ የሁላችን ነውና ከልጆቹና መንድምና ቤተሰቦቹ በቀር ማናችን ማንን ‹ታሳ› እንደምንል አላውቅም፡፡ ‹ታሳ› ማለት ከጋሞኛ ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹እኔን/በእኔ-የእኔ – ይሁን › ማለት ነው፡፡
ከጋሼ አሰፋ ቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ያገኘኋቸውን በረከቶች በተከታታይ ይዤ እቀርባለሁ፡፡
እስከዚያው በቸር ያገናኘን፡፡ 27/08/09.

አስደንጋጭ ዜና ከወልቃይት ፀገዴ


“እስር ቤት ውስጥ ሞተ ተብሎ አስክሬን ተሰጠን” – የሟች እናት ከጽዮን ግርማ
በአማራ ክልል በተለይ በወልቃይት ፀገዴ ለወራት የዘለቁ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ፤ በቁጥጥር የሚውሉና የደረሱበት የማይታወቅ ሰዎች መበራከታቸውን በሰሜን ምእራባዊው ግዛት የባህልና ማንነት ጥያቄ አንስተው ይንቀሳቀሱ የነበሩ የማህበረሰብ ለውጥ አቀንቃኞች ይገልጻሉ። ዘነበ ጫቅሌ ዩሃንስ የተባለ የሁለት ልጆች አባትና የ32 ዓመት ወጣት ዳንሻ ከብት ገበያ ውስጥ ከብት በመነገድ ላይ እያለ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም በፖሊሶች ተይዞ ከተወሰደ ከሁለት ሳምንት በኋላ በእስር ቤት መሞቱን ቤተሰቡና በቅርብ የሚያውቁት ለአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ገልጸዋል። ሟች ለፋሲካ በዓል ለቤተሰቡ ደውሎ የቀረበበትን ክስ በፍርድ ቤት እንደሚሟገት ተናግሮ እንደነበል ወላጅ እናቱ ተናግረዋል።
እንዴት ሞተ? ቤተሰቦቹ የተሰጣቸው ምክንያት ለማመን የሚያስቸግር እንደሆነ ገልጸው፤ አስከሬኑ መመርመሩን ተነግሯቸው ውጤቱን ግን እንዳልሰሙ ተናግረዋል። በወልቃይት ፀገዴ የማንነት ጥያቄ ላይ የተሳተፉ፤ ከመሪዎቹ ጨምሮ በእስር ላይ መሆናቸውንና ደብዛቸው የሚጠፋና ድንገት የሚሞቱም አሉ ሲሉ የእንቅስቃሴው አደራጆች ገልጸውልናል።
የፀገዴ ወረዳና የሽሬ ፖሊስ እንዲህ የሚባል እስረኛ “እኛ ጋር አልነበረም። የኛ እስር ቤቶች የእስረኛ ዴሞክራሲያዊ መብት የሚከበረባቸው ናቸው” ብለዋል። የእንዳ አባ ጉና ፖሊስ ሃላፊ በበኩላቸው በአካል ካልተገኘን ምንም መረጃ እንደማይሰቱን ገልፀዋል።

Friday, May 5, 2017

ህወሓት: በነፃ ፕሬስ መቃብር ላይ የቆመ አገዛዝ!




  • ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት ከዓለም 150 ደረጃ ላይ ትገኛለች!
  • አገሪቱ የነፃሚዲያ ባለቤት የምትሆነው በህወሓት መቃብር ላይ ነው!
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ድጋፍንም ሆነ ተቃውሞን ምክንያታዊ በሆኑ ነገሮች መግለጽ የሚችልና ፖለቲካዊ ንቃት ያለው ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ትግል፤ ካለ ነፃ ፕሬስ ተዋፅኦ ስሙር ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ ገዥው ኃይል የግሉ ፕሬስ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና አሳታፊነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር የራሱን በጎ ሚና እና አበርክቶ እንዲወጣ ምቹ የሥራ ምህዳር ከመፍጠር ይልቅ በትዕግስት አልባ ባህሪው የተነሳ በነፃ ፕሬሱ ላይ የተለየ ሃሳብና የፖለቲካ አመለካከት በተንፀባረቀ ቁጥር በመደንበር ሚዲያዎቹን በመዝጋት፣ በግልፅ የተደነገገውን ህግ በህብዑም ሆነ በግላጭ ሲንደው ታይቷል፡፡
በውጤቱም፤ በየዓመቱ የዓለም አገራት የጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ይዞታን እየገመገመ ደረጃ በማውጣት የሚታወቀው ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በፕሬስ ነፃነት ኢትዮጵያን ከ180 የዓለም አገራት በ150 ደረጃ አስቀምጧታል፡፡ በገዥው ኃይል ጫና ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች የመፃፍ ነፃነትን በመንፈግ እንደ ኤርትራ፣ ሶሪያ ፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ማይናማር (በርማ)፣ . . . ካሉ አገራት ጋር ሥሟ የሚጠራ አፋኝ አገር እንደሆነች የፕሬሱ ጠበቃ የሆኑ ድርጅቶች በየጊዜው ከሚያወጡት ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡
ጋዜጠኞች በፃፉት ፅሁፍና በህትመት ውጤቶቻቸው በተስተናገዱ ፅሁፎች ብቻ ተከሰው እስራትና የገንዘብ ቅጣት የሚፈረድባቸው አገር የህወሓቷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ለነፃ ጋዜጠኞች የተመቸች አገር አልሆነችም፡፡ ስደት ወይም እስር የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች ዕጣ ፈንታ ነው፡፡
ህወሓት ባሳለፈው ረዥም የትጥቅ ትግል፣ ሚዲያ ከፕሮፓጋንዳ አኳያ ለትግሉ የነበረውን አስተዋፆ በድምፀ – ወያኔ በኩል ተረድቶታል፡፡ የህትመት ውጤቶችን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በተመለከተ ደግሞ በነ “ታጠቅ”፣ “ወይን” በኩል የፕሮፓጋንዳን ዋጋ አስተውሏል፡፡ ድርጅቱ በተፈጥሯዊ ባህሪው ብቸኛ የአገሪቷ አዳኝ መሆኑን በበዛ “እርግጠኝነት” ያምናል፡፡ ከዚህ ስሁት አመኔታው ተነስቶ ከርሱ ውጪ የሚቀርቡ ሃሳቦችም ሆነ ይህንን የተለየ ሃሳብ ይዘው የሚከራከሩትንና የሚሞግቱትን ነፃ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ተቋማት በተለያዩ ጫናዎች ከገበያ እንዲወጡ አልያም በ“ህግ” ሽፋን መጨፍለቅ የሩብ ክፍለ ዘመን ተሞክሮው ገላጭ ማሳያ ነው፡፡ ይህ “እኔ ብቻ የእውነት ባለቤት ነኝ” ርዕዮተ ዓለማዊ በሽታ፣ ጉልበት ብቸኛ አማራጭ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በዚህ አፄ – በጉልበቱ ባህሪው ህዝባዊ አደባባዩን ጭር አድርጎታል፡፡ የነፃ – ፕሬሱ አፈና የማህበራዊ ድረ – ገፆችን የአመፃ መንገድ ቢወልድበትም ቅሉ፡፡
ህወሓት መራሹ ገዥ ኃይል ከምርጫ 97 በኋላ ነፃውን ፕሬስ ለማፈን ሁለት አዋጆችን በማውጣት ለአፈናው መሳሪያነት ሳያሳልስ ተጠቀሟል፡፡ የመጀመሪያው አዋጅ “ተሻሽሏል” በሚል የወጣው የፕሬስ አዋጅ መሆኑ ይነሳል፡፡ ይህ አዋጅ የአገዛዙ የግራ ጥፍር የሆኑ የጋዜጣ ባለቤቶች (አማረ አረጋዊንና መሰሎቹን ልብ ይሏል) “አስደሳች” ሲሉ ያወደሷቸው አንቀፆች ግራ እንዳጋቡን እያስታወስን፤ ቅጣቶችን በተመለከተ ያስቀመጣቸው የህግ ማዕቀፎች ክፋት አከል ናቸው፡፡ አዋጁ እንደሚለው ለአነስተኛ የሥም ማጥፋት ክስ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር ድረስ የገንዘብ ቅጣት እርከን አስቀምጧል (ተከሳሹ ጋዜጠኛ ቅጣቱን መክፈል ካልቻለ ወደ እስር ይቀየራል) በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የቅጣት ህግ ጠጥቶ በማሽከርከር የሰው ህይወት ያጠፋ አሽከርካሪ በስም ማጥፋት ተከሶ ከሚቀጣው ጋዜጠኛ በእጥፍ ያነሰ የገንዘብ ቅጣት ነው የሚወሰንበት፡፡
ይሄ አዋጅ አንድ የክፋት ዓላማ አለው፡፡ እሱም የነፃውን ፕሬስ አባላት በቅጣት ሥም የገቢ አቅም ማሽመድመድ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ ተጨማሪ የነፃ ፕሬሱን የገቢ አቅም ማዳከሚያ መንገድ ደግሞ “የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መንፈግ” የሚል ይሆናል፡፡ በመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም. በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተፃፈ የሚነገርለት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትግል እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በሚለው ሰነዱ፤ ጉዳዩን እንዲህ ሲል ያብራራል ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ተቋሞች በተለይም የመንግስት ድርጅቶች እና ልማታዊ ባለሃብቶች ማስታወቂያቸውን ለሥርዓቱ አደጋ በሚሆኑ የሚዲያ ተቋሞች ላይ ማውጣታቸውን” እንዲተው ሰነዱ ያሳስባል፡፡ ዜጎችም በሂደት ሥርዓቱን ለአደጋ የሚጥል ሚዲያ መጠቀም በራሳቸው ላይ እባብ መጠምጠም መሆኑን ተገንዝበውሚዲያዎቹን ከመጠቀም (ከመግዛት) እንዲቆጠቡ ያዝዛል፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለማዊ በሽታ የሚመራው ህወሓት/ኢህአዴግ ከላይ ከተጠቀሰው የፕሬስ አዋጅ በተጨማሪ ብዙ ዜጎችን ወደ ቃሊቲ ለመወርወር ጥቅም ላይ ያዋለውን “የፀረ- ሽብርተኝነት ህግ” በመጠቀም የነፃውን ፕሬስ ቤተሰቦች ለማጥቃት ረዥም ርቀት ተጉዟል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ያሻውን የነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማቸውን በፈቀደው ጊዜ የፈለገውን ያህል የሐሰት ክስ በመዘርዘር ጋዜጠኞቹን ማሰርና የሚዲያ ተቋማቱን መዝጋት የአገዛዝ መለያ ባህሪው ነው፡፡ በእስካሁኑ ተሞክሮውም “ህገ – መንግስቱን በኃይል ለመናድ፣ በመንግስት ላይ የሀሰት ወሬ በማውራት ህዝቡ እምነት እንዲያጣ ማድረግ” እና “ከሽብር ቡድኖች ጋር ተባብሮ መስራት” የሚሉ ዋጋ አልባና ፍሬ ከርስኪ ነገሮችን በመደርደር “ክስ” ብሎ የሚዲያ ተቋማቱን ዘግቷል፡፡ ጋዜጠኞቹን አስሯል፡፡ እንዲሰደዱ ገፍቷል፡፡
አሁን በአገሪቱ ላይ ካሉት የህትመት ሚዲያዎች ውስጥ ሞጋች የሆኑ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች አደባባዩ ላይ ተቀብረዋል፡፡ “አለን” የሚሉትም በፋይዳ ቢስ አጀንዳዎችና ገዥውን ኃይል በነቃፊ – ደጋፊ አሰላለፍ የወገኑ ተለጣፊ የህትመት ውጤቶች ናቸው፡፡ የህወሓቱ ቋሚ ዘብ አማረ አረጋዊ “ሪፖርተር” ልፋጭ ዜናዎችና ሚዛናቸውን የሳቱ ከንቱ ፖለቲካዊ “ትንተናዎች”፤ የ“አዲስ አድማስ” በፍርሃት የተሸበቡ የፖለቲካ ዜናዎች፣ በተረት የታጨቁ “ርዕሰ አንቀፆች”፤ የጠቅላይ ኢኮኖሚ በዝባዡ አላሙዲን ዜና መዋዕል የሚፃፍበት “ሰንደቅ” ጋዜጣ፤ የኮሪደር ሃሜት የሚያስተናግደው “ፎርቹን” ጋዜጣ፤ የዝነኛ አርቲስቶችን ውሎና አዳር እየዘገቡ ገንዘብ የሚለቃቅሙ የፀጉር ቤት መፅሔቶች፤ . . . አገሪቱ አሁን ካለችበት አገራዊ ቅርቃር አኳያ የህትመት ውጤቶቻቸው ይዘት በህዝብ ደም ላይ እንደመረማመድ ያለ ድፍረት ነው፡፡ አገር ውልቅልቋ እየወጣ ወደ ርስ በርስ ጦርነት እየተጠጋን ባለበት ሁኔታ አቀርቅሮ የማስታወቂያ ገንዘብ መሰብሰብ ምን የሚሉት ብኩንነት እንደሆነ እንደዜጋ አይገባንም፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ ቀዳሚ ተግዳሮት ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ አቻቻይና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ባለበት አገራዊ አውድ፤ በሙያው መርህ ላይ በመቆም ከኢኮኖሚ እና ባህል ተኮር ከሆኑ አገራዊ ክስተቶች አንፃር የሚመጡ ማነቆዎችን በመሻገር ሙያዊ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል፡፡
እውነታው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አቻቻይ ሳይሆን የእኔን እውነት ብቻ ተቀበል” የሚል ጨፍላቂ ፖለቲካዊ አገዛዝ በመስፈኑ የጋዜጠኝነት ጉዳይ የህዝብን የመረጃ ጥማት ማርካት ብቻ ሳይሆን አፋኙን ገዥ ኃይል የሚገዘግዝ መንገድን መምረጥና በፅናት መሞገት ምርጫ የሌለው የሙያው መንገድ ነው፡፡ በርግጥም አገር እየፈረሰች ባለችበት ሁኔታ ስለሙያው መርህ ማሰብ የበዛ አገራዊ ዝንጉነትና አድርባይነት ነው፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚያድገውም ሆነ የሚበለፅገው አገር ስትሰነብት ነው፡፡ አገር በብተና ውስጥ ሁና የሙያውን መርህ በሚዛናዊ ዘገባ ልተርጉም ማለት ዘበት ነው፡፡
የዘንድሮው የፕሬስ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ባለበት በዚህ ሳምንት እንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ በእስር እየማቀቁ ያሉ ጋዜጠኞች ከደርዘን በላይ ናቸው፡፡ ሞጋቾቹ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ውብሸት ታየ፣ ጌታቸው ወርቁ፣ ኤልያስ ገብሩ፣ ጌታቸው ሽፈራው፣ ዘላለም ወርቅአገኘሁ (ጦማሪ)፣ ደርሴማ ሶሪ፣ ካሊድ መሐመድ፣፣ . . . ከብዙ በጥቂቱ ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ በእስር እየማቀቁ ያሉ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
አሳፋሪ በሆነ የ“ክስ” አቀራረብ በ“ሽብር ወንጀል” የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበት፤ ቃሊቲ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በተከታታይ ዓመት አራት ጊዜ “የዓለም የፕሬስ ነፃነት ጀግና” ሽልማት ተቀዳጅቷል፡፡ የነፃውን ፕሬስ ሞጋችነትና የተደበቀውን ፈልፍሎ የማውጣት ባህሪውን በተለየ ፅናት በማሳደግ የምናውቀው እስክንድር ነጋ፤ ለአቻዎቹም ሆነ ለተከታዮቹ የሙያው ሰዎች የእስክንድር ሞዴል ልንለው የሚቻለን የፅናት መንገድ አስተምሯል፡፡ ፈለጉን የተከተሉ የሙያው ሰዎች ሁሉ ዕጣ ፈንታቸው ስደት አልያም እስር መሆኑን ስንታዘበው የኖርነው እውነት ነው፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ከህወሓት/ኢህአዴግ የልማት ፕሮፓጋንዳ ጀርባ ያሉ ሐቆችን በተጠየቃዊ አጀንዳዎች ተንትነው የሚያቀርቡ የነፃው ፕሬስ ውጤቶች በገበያው ላይ እንዲኖሩ አይፈለግም፡፡ የፕሬስ ተሟጋችነት ሚና አስፈላጊነቱ የማይካድ ቢሆንም፣ ግራ ዘመሙ ህወሓት/ኢህአዴግ ያለ ትችትና ነቀፌታ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚዲያ ህግ መሰረት የአገሪቱን ዜጎች ከአንድ ሚዲያ ብቻ መረጃ እንዲያገኙ የመጠርነፍ ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ህወሓት ከአናሳ ዘውግ የመውጣቱ እውነታ ተጭኖት ያለቅጥ ከለጠጠው የዘውግ ፖለቲካው በተጨማሪ ህብረተሰቡን በመደብና በአመለካከት “ጠላት”፣ “አጋር” እያለ እንደከፋፈለው ሁሉ በነፃ – ፕሬስ ላይም ይህን ብያኔ ገቢር በማድረጉ፣ ድርጅቱ በሥልጣን እስካለ ድረስ ሞጋችነት የሚንፀባረቅባቸው የነፃ ፕሬስ ውጤቶችን ማየት የማይታሰብ ሆኗል፡፡
የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች መከራ ህወሓት/ኢህአዴግ እስካለ ድረስ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ አገዛዙ ሥልጣኑን ካፀናባቸው የአፈና ግብሮቹ አንዱ ነፃውን ፕሬስ የማፈንና የመጨፍለቅ መንገድ ተጠቃሽ እኩይ ድርጊቱ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙዎች የነፃው ፕሬስ ቤተሰቦች “ህወሓት/ኢህአዴግ በነፃው ፕሬስ መቃብር ላይ ቁሟል” ሲሉ የሚከሱት በርግጥም አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ አገሪቱ የነፃ – ሚዲያ ባለቤት መሆን የምትችለውም ሆነ የህዝብ የመረጃ ጥማት የሚረካው የትግራይ እንክርዳድ በሆነው ህወሓትና ከአምሳያው አሳንሶ የፈጠራቸው ተለጣፊ የግንባሩ አባል ድርጅቶች መቃብር ላይ ነው፡፡
የዓለም የፕሬስ ቀንን ስናስብ ስደት ወይም እስር ዕጣ ፈንታቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ቤተሰቦችን ማስታወሱ ተገቢ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለከፈሉት ዋጋ እንደዜጋ ባለዕዳ መሆናችንንም አንዘነጋውም!!

Thursday, May 4, 2017

የእኛ ሰንድቅ ዓላማ ከፍ ሲል` የእነሱ ዝቅ አለ !

   
የእኛ ሰንድቅ ዓላማ ከፍ ሲል` የእነሱ ዝቅ አለ !! ይድነቃቸው ከበደ
“ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቀሉ ! ”
“እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ
በቀስተ ዳመናሽ ሰማይ መቀነቱን ባንዲራሽን ታጥቆ
አርማሽ የታተመ እንኳን ባለም መዳፍ በአርያም ታውቆ”

ብላቴናው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ !የጀግኖች አርበኞቻችን የመታሰቢያ ክብር በአል ለ76ኛ ጊዜ ሊከበር የተወሰኑ ቀናት ሲቀሩ፣አምስተኛ የሙዚቃ አልበሙን “ኢትዮጵያ” የተሰኝ  ምርጥ ሥራውን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አቅረቦልናል፡፡ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ! ይህ በታሪክ የራሱን አሻራ አስቀምጦ የሚቀረው ድንቅ ሥራው ፣በተለይ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው የጥበብ ውጤት፤ የብዙ ነገር መገለጫ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከፍ አድርጎ ያሳየ ነው፡፡ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍ ብሎ የተውለበለበው ብላቴናው ቴዲ አፍሮ በዜማው ያወደሳት የእናት ሃገር መለያ ባንዲራችንን ነው፡፡
—-
ኢጣሊያ በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ታሪካዊ ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር የማይነጣጠለው የኢትዮጵያ ባንዲራ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማችንን ዝቅ አድርጎ፣ድንበር ተሻግሮ በፋሺስታዊ መንግሥታት ድጋፍ አማካይነት ሚያዝያ 1928 ዓ.ም የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ፣ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ- መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን ነው ፡፡ከዚህ ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ለአምስት ዓመት ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡ ከአድዋው ዘመቻ (ከ40 ዓመት) በፊት ብዙም ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያ፣ የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ጦር በፅናት ተዋጋች ፡፡
—-
“ኢትዮጵያ ሀገሬ
ኢትዮጵያ ሀገሬ
ባንቺ አይደል ወይ ክብሬ
ባልፍም ኖሬ ስለናት ምድሬ
እሷናት ክብሬ አረ እኔስ ሃገሬ”

አሁን ላይ ድምጻዊ ቴዲ! “ኢትዮጵያ” በሚለው ዜማ የተቀኘላት የእናት ሃገር ክብር ያኔም የሆነው ይሄ ነው ፡፡ ጀግኖች አርበኞቻችን ብንሞት ለሃገር፣ ለሃገር መሞት ደግሞ ክብር ነው፡፡ በማለት በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት ቆፈጠን ብለው፣ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እምቢ ለነፃነቴ፣አረ እኔስ ለሃገሬ በማለት የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃትቸውን ቀን ከለሊት በፅናት በመቆም አፋፋሙ፡፡ ወራሪዊ የጣሊያን ጦር ክፉኛ ተሸነፉ፡፡በየቦታው ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ፡፡ የጠላት ጦር አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡በዚህ ታሪካዊ የድል ቀን ! በጄኔራል ካኒንግሂም እና በጄሪራል ኘላት የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ለኢትዮጵያዊያን አርበኞች ያደረጉት ድጋፍ በታሪክ የሚወሳ ነው፡፡
—-
በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ተበሰረ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ! ሚያዝያ 1928 ዓ.ም የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ የሰቀለውን፣የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ሃገር ሰንደቅ ዓላማ አውርደው፣ በከፍተኛ አጀብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት ሰቀሉ፡፡በዚህን ጊዜ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ባንዲራ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንድቅ ዓላማችን ክፍ ሲል የእነሱ ዝቅ አለ ! ለዚህ ታላቅ ድል ላበቁን ጀግኖች አርበኞቻችን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላላም ትኑር !!!

(ይድነቃቸው ከበደ)

Wednesday, May 3, 2017

ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው !

   


ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው !

[[ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበው በሃገራችን የተፈጸመው የሰብዓዊ ጥሰት ፣ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው ። ታዲያ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ “የፖለቲካ ልዩነት ሣይገድበን እሳቸው እንዲመረጡ ድጋፍ እንስጥ”የምትሉ ይህን እውነት የት ሸሽጋቹት ነው ?! ]]

ዘረኝነትን አጥብቄ እቃወማለሁ! እኔ በግሌ የሰው ወገን የሆን ሁሉ አንድ ነን ብዬ አምናለሁ ! የራሴን ምክንያታዊ ሃሳብ ለማቅረብ ወይም የሌላውን ሃሳብ በአመክንዮአዊ አመለካከት ለመሞገት፤ እኔ እና የእኔ ቤተሰቦች የምንናገረው ቋንቋ ፣ የምናመልከው አምላክ እና የምንከተለው ሐይማኖት፣ እንዲሁም የቆዳ ቀለማችን ፈጽሞ መመዘኛ አይሆነኝም።አንድን ሰው በሃሳቡ ወይም በሥራው ለመቃወም ሆነ ለመደገፍ የነገሩ ጠቃሚነት ወይም ጎጂነት ብቻ መስፈርቱ ሆኖ ያገለግለኛል ። ዘረኝነት “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሣ ራስን የተሻለ አድርጎ በመገመት ሌላውን መናቅ መጨቆን የበታች አድርጎ ማየት” እንደሆነ ይነገርለታል፤እንዲህ አይነቱ አጸያፊ ነገር የምጠየፈው ቆሻሻ ነው።

ቆሻሻ በሆነው በምጠየፈው ዘረኝነት፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት (WHO) መሪነት የሚያደርጉትን ውድድር ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም እንደ-ምክንያት አያገለግለኝም።እኔ የእሳቸውን መመረጥ የማልደግፍበት ከዚህ የተሻለ በቂ ምክንያት አለኝ። የእሳቸው መመረጥ ሌሎቹ እንደሚሉት የፖለቲካ ልዩነት እና ብሔራዊ ክብር ይለያል፣የእሳቸው መመረጥ እንደ- ሃገር ክብር ነው፤በማለት እራሴን ለማሞኘት የምዳክር ሞኝ አይደለሁም ። እንደ-ሃገር አልጠቅም ያለው እሳቸው እና ጓደኞቻቸው የሚከተሉት የፖለቲካ ሃስተሳሰብ የተግባር ውጤት እንጂ ሌላ ምን ሆነና ?! ስለዚህም ለእኔ ከዚህ የሚበልጥብኝ ምንም ምክንያት የለኝም።

እሳቸው የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ለአገዛዙ ሥርዓት እስካልጠቀም ድረስ ሊገድብ የሚችል መንግሥት መስራች እና በተለያየ ቦታ በኃላፊነት የሰሩ ሰው ናቸው።እሳቸው ባለፉት 26 ዓመታት ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በኢትዮጵያ ልተፈፀሙ ፣ እስር እና እንግልቶች ተጠያቂ የሚሆን መንግሥት ባለሥልጣን ከሆኑት ውስጡ አንዱ ናቸው። እሳቸው በኃላፊነት የሚመሩት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፣ ኢትዮጵያዊያን ላይ በደቡብ አፍሪቃ፣ በሳዊዲ አረቢያ ፣ በየመን ይደርስባቸው ለነበረ ሞትና እንግልት፣ በየአገሩ የሚገኙ ኢምባሲዎችና ቆንፅላ ጽ/ቤቶች ያሳዩት የነበረው ቸልተኝነት እሳቸው ከባላይ ሆነው የሚያዙት መሥሪያ ቤት ነበር። በቅርብ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገሮች ውስጥ 669 (ይህ ቁጥር) መንግሥት በይፋ ያመነው ነው። ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሞተዋል። 336 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ። የዜጎቻችን ሞት እና የአካል ጉዳት መንስኤ”የመልካም አስተዳደር እጦት”እና እሱን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ መንግሥት በተለያየ ወቅት በተለያየ መንግድ አምኖ ሲግልጽ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። መልካም አስተዳደር በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የሚመዘንበት ዋና መስፈርት ነው። በመስፈርቱ መሰረት ዶ/ር ቴዎድሮስ የሚያገለግሉት መንግሥት እና እሳቸው ! በሃገራችን ለታየው የመልካም አስተዳደር እጦት እና እሱን ተከትሎ ለመጣው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ናቸው።

ከምንም በላይ በሃገራችን የተፈጸመው የሰብዓዊ ጥሰት ከእኛ ኢትዮጽያዊያን አልፉ ፤ የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሳስቧቸው በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል ። ይህ አይነቶ አለም አቀፍ ትኩረት የሳበ የሰብዓዊ ጥሰት የተካሄደው እሳቸው እና ጓደኞቻቸው በሚመሩት መንግሥት ነው። እንዲህ አይነቱ አሳሳቢ የሰብዓዊ ጥሰቶች የተፈጸሙት ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት ነው ። ታዲያ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ “የፖለቲካ ልዩነት ሣይገድበን እሳቸው እንዲመረጡ ድጋፍ እንስጥ” የምትሉ ይህን እውነት የት ሸሽጋቹት ነው ?! ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት (WHO) መሪነት የሚያደርጉትን ውድድር እኔ በግሌ አልደግፍም። የእኔ አለመደገፍ በውድድሩ ውጤት ላይ የሚያመጣው ልውጥ ምንም ይሁን ምን፣ እኔ ግን ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው ! — (ይድነቃቸው ከበደ)

ቴዲ ለምን ይወደዳል? – ኢትዮጵያዊነት በአንጻረ ጎሰኝነት (ዶር ፍቅሬ ቶሎሳ)

   



“ቴዎድሮስ ካሳሁንን እና ሙዚቃውን ለምን ህዝብ ይወዳቸዋል?” ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ “እሱ እና ሙዚቃው ኢትዮጵያዊነትን ስለሚዘምሩ ነው፤” የሚል ነው። በሌላ አነጋገር፥ ጎሰኝነትን ስለማያራምዱ ነው።
ባለፉት 48 ዐመታት በተማሪዎች ቆስቋሽነት የተጀመረው ጎሰኝነት ባለፉት 25 ዐመታት እንደ ሰደድ እሳት ተዛምቶ ፥ በኢትዮጵያዊነት ላይ የማያቋርጥ ዘመቻ አካሂዶ፥ ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ አለማክተሙ እና ማንሰራራቱ የሚያስገርም ነው። ኢትዮጵያዊነትን ለሚጠሉ ደግሞ አስደንጋጭ መርዶ ነው። እውነት ይህን ያህል ህዝብ ጎሰኝነት አንገፈገፈኝ ብሎ ኢትዮጵያዊነትን ናፍቋልን? መልሱ አዎንታዊ ይመስላል።
በእርግጥም ኢትዮጵያን ሊያድናት የሚችለው ኢዮዬጵያዊነት ነው። ለመሆኑ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል ምንድነው? ኢትዮጽያስ ለምን ኢትዮጵያ ተባለች? ኢትዮጵያ ማለት በሱባ (ከግእዝ በፊት የነበረ የጥንት ወገኖቻችን ቋንቋ) ብጫ ወርቅ ስጦታ (ለእግዚአብሄር) ማለት ነው። የዛሬ 4000 ዐመት የኖረው የንጉሥ ንጉሥ የካህን ካህን በመሆን ዐለማዊና መለኮታዊ ማእረግ የነበረው አባታችን ኢትዮጵ በዚህ ስም ይጠራ ስለ ነበር ሀሪረቱን ኢትዮጵያ አሰኛት። የኢትዮጵያን ስልጣኔ ጆቹቸ በመላው አፍሪካ በማዳረሳቸው እስከዛሬ 600 ዐመት ድረስ መላው አፍሪካ ኢትዮጵያ ይባል ነበር። አሁንም በኢትይጵያውያን አፋሮቻችን ምክንያት አፍሪካ ይባላል። ዞሮ ሮሬ ከእኛ ስም አልወጣም።
ኢትዮጵ 10 ወንዶች ልጆች ወልዶ 10ስሩ ተባዝተው ዛሬ ሁላችንም ከነሱ ተገኘን። ስለዚህ በእያንዳንዳችን ደም ስር ውስጥ የኡዮጵ ደም እየፈሰሰ ሁላችንንም እዛምዶናል ማለት ነው። ትውልደ ኢትዮጵያ የሆንን ሰዎች ሁሉ ወደድንም ጠላንም አመንን አላመንም፣ እውስጣችን የእዚህ ትልቅ ሰው እና የክብርት ሚስቱ የንግሥት እቁዮያጳግዮን ደም ይፈስሳል። ይህም እጅግ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም። ይህን የማይቀበል ክቡር። እና ግዙፍ የሆነውን ማንነቱን የማያውቅ ብቻ ነው። ወይም በፓለቲካ ልቦናውን የታወረ ነው።
ጎሳስ ምንድነው? ጎሳ አንድ ቋንቋ። የሚየናገሩ ሰዎች ማለት ነው። ዘርፉ ከቋንቋ እንጂ ከዘር አይደለም። የአማራ ወይም የኦሮሞ ጎሳ ማለት አማርኛ ወይም ኦሮምኛ የሚናገር ሰው ማለት እንጂ ዘሩን አይጠቁምም። ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ብቻ ነው እንጂ በደም የሚያገናኝ አይደለም። በደም፥ ያው ከፍ ብዬ እንዳልኩት የኢትዮጵ ልጆች ነን። ኢትዮጵያ ውስጥ 82 ቋንቋዎች ተናጋሪዎች አሉ። በዘራቸው ግን አንድ ናቸው። የመነጩት ከኢትዮጵ ደም ነውና። ስለዚህ ሁሉንም ትውልደ ኢዮያጵያውያንን በስጋ የሚመያዛምዳቸው ኢዮያጵ ነው እጂጀ ቋንቋው አይደለም። የዚህን ዝርዝር ለማየት “የኦሮሞ እና አማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘውን መጽሀፌን መመልከት ይጠቅማል።
እንግዲህ ኢትዮጵያዊነትን በአሁኑ ሰዐት ሰው ሁሉ የፈለገው ውስጡ ያለው ደመነፍስ ኢዮጵያዊነቱን ስለ አረጋገጠለትና ጎሰኝነት ዋጋቢስ መሆኑን ስለተገነዘበ ነው። ከአሁን በኋላ ኢዮዮጵያዊነት ለምልሞ ያብባል እንጂ ጠውልጎ አይደርቅም።

ጀርመን በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጠየቀች


(ቢቢኤን ዜና) በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጀርመን ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቀረበች፡፡ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል፣ ትላንትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጨማሪም፣ በመንግስት ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች፣ ጥያቄአቸው በተገቢው መንገድ መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳና ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማድረግ የገባውን ቃል እንዲተገብር ጠቅላይ ሚንስትሩን በድጋሚ አጥብቀን ጠይቀናል፡፡›› ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል፣ በመንግስት በኩል በደል ደርሶብናል ብለው የሚያምኑ አካላትም፣ ቅራኔያቸው በአግባቡ ይፈታ ዘንድ ለመንግስት ጥያቄ ማቅረባቸውን ውጭ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የሚችለው በሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ሲኖር መሆኑን ያስረገጡት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን ምቹ አለመሆኑን ለመንግስት ባለስልጣናት ገልጸውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ውይይታቸውም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበት አጥብቀው ለመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸውን የተናገሩት ሲግማር ጋብርኤል፣ በሀገሪቱ አስታራቂ የሆነ ፖለቲካዊ ድባብ እንዲፈጠርም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ይፋ ተደርጎ ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ፣ በድጋሚ በመጋቢት ወር ለአራት ወራት እንዲራዘም በተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነሳ በርካታ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ የታሰሩም በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡