Tuesday, May 2, 2017

ሕገ-መንግስቱን በሚጥስ አዋጅ የኦሮሚያን “ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም” ማስከበር አይቻልም! ስዩም ተሾመ

   



ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ዙሪያ የተለያዩ ፅሁፎችን አውጥቼያለሁ። “ማስተር ፕላን፡ የችግሩ መነሻ እና መድረሻ” በሚለው ፅሁፍ የአዲስ አበባ ከተማ ገና ከአመሰራረቷ ጀምሮ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ያላረጋገጠች መሆኗንና ማስተር ፕላኑ ደግሞ ይሄን የሚያስቀጥል ስለመሆኑ፣ “የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ማቋረጥ ስህተትን እንደ መሳሳት ነው” በሚለው ፅሁፍ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ችግር ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው የችግሩን ዋና መንስዔ መለየት ሲቻል እንደሆነ፣ በመቀጠል “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ ደግሞ የኦሮሚያ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ሲደረግ እንደሆነ በዝርዝር ገልጬያለሁ።
ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ፅሁፎች በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለው ግንኙነት ከጭፍን ደጋፍና ተቃውሞ በፀዳ መልኩ እንዲመራ እና የክልሉ ሕዝብና የከተማዋ ነዋሪዎች መብትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ ለዚህ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) አስፈላጊው የሕግ አዋጅ እና የአፈፃፀም መመሪያ መዘጋጀት አለበት በሚል መርህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ስለዚህ፣ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም የሚያስከበር አዋጅ መውጣት አለበት እያልኩ በፅሁፎቼ ተከራክሬያለሁ። በጉጉት ስጠብቀው የነበረው ረቂቅ አዋጅ ግን እንዲህ ቅስሜን ይሰብረዋል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር።
በመሰረቱ፣ በሀገር ወይም ክልል ደረጃ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በሚል የሚወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በምንም መልኩ ቢሆን ሕገ-መንግስታዊ መርሆችንና ድንጋጌዎችን መፃረር የለባቸውም። ሕገ-መንግስቱ በማንኛውም አካል ቢሆን ለሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች እንደ መነሻ ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ። “ሕገ-መንግስቱ በራሱ ክፍተቶች ስላሉበት አንቀበለውም” የሚሉ ወገኖች መኖራቸው እርግጥ ነው። ነገር ግን፣ “በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ራሱ ሕገ-መንግስቱ ላይ በተደነገገው አግባብ መሰረት መቀየርና ማሻሻል ይቻላል” የሚል ፅኑ አቋም አለኝ።

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተመለከተ

   


አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተመለከተ

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ወረቀት አልባ ስደተኞችን ከሀገሩ ለማስወጣት ይፋ ያደረገውን የሶስት ወራት የምህረት አዋጅ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ይገባሉ ተብለው የተጠበቁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀነሱ ታወቀ፡፡ በሳኡዲ አረቢያ ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ያለ ወረቀት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የምህረት አዋጁን ተጠቅመው ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
‹‹ሀገር ቤት ሔደን ምን እንሳራለን፡፡›› የሚሉት ስደተኞቹ፣ ‹‹የሶስት ወራቱ የምህረት አዋጅ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በወረቀት አልባ ስደተኞች ላይ የሚጣለውን ማንኛውንም ቅጣት ተቀብለን ሳኡዲ መኖር እንፈልጋለን፡፡›› ብለዋል፡፡ አስተያየቷን ለቢቢኤን የገለጸች በሳኡዲ የምትኖር አንዲት ወረቀት አልባ ኢትዮጵያዊት፣ እሷን ጨምሮ አብዛኛው ህገ ወጥ ስደተኛ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ተናግራለች፡፡ ‹‹በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ካለው አጠቃለይ ሁኔታ አንጻር ወደ ሀገር ቤት መመለስ የማይታሰብ ነው፡፡›› ያለችው ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ይህች ስደተኛ፣ ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ያሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥርም፣ ኢዚህ ካለው ወረቀት አልባ ስደተኛ ቁጥር አንጻር እጅግ አናሳ መሆኑንም ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሳኡዲ የሚኖሩ ወረቀት አልባ ስደተኞች እና ወደ ሀገራቸው እየገቡ ያሉ ስደተኞች ቁጥር ከጠበቀው በታች እንደሆነበት ገልጾ፣ በቀሩት የምህረት አዋጅ ቀናት ውስጥ ዜጎቹ ተጠቃለው ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ የምህረት አዋጁ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሚደርስባችሁ አደጋ ኃላፊነቱን ማን ሊወስድላችሁ ይችላል የሚል ጥያቄ ከቢቢኤን የቀረበላት ስደተኛዋ ‹‹ማንም፡፡›› ስትል በሲቃ ድምጽ መልሳለች፡፡ ከዚህ ቀደም በሳኡዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በሀገሪቱ ፖሊሶች እና በአንዳንድ ጎረምሶች የደረሰውን ግፍ ያስታወሰችው ስደተኛዋ፣ በወቅቱ እዚያው ሳዑዲ እንደነበረች በመግለጽ፣ ከምህረት አዋጁ መጠናቀቅ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ተመኝታለች፡፡ የሳአዲ አረቢያ መንግስት ይፋ ያደረገው የምህረት አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡

በማዕከላዊ እስር ቤት በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰትንና በህክምናው ላይ የተጋረጠን ሌላኛውን እሾክ በድጋሜ ስለማውገዝ፤

   



በማዕከላዊ እስር ቤት በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰትንና  በህክምናው ላይ የተጋረጠን ሌላኛውን እሾክ በድጋሜ ስለማውገዝ፤
ከዐማራ ሀኪሞች ማኅበር Branna MediA

ዶ/ር ጋሹ ክንዱ የህክምና ዶክትሬት ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት የተመረቀ ወጣት የዐማራ ሀኪም ነው። ከተለያዩ ሀገራት የህክምናና የመሪነት ልምድን አካብቷል። ብዙ የግል ጥቅሞችን በመተው ወደሚያፈቅረው ገጠራማ የዐማራ ክፍል በመሔድ አገልግሏል። የቡሬ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ነው። የዐማራ ሃኪሞች ማኅበር ግንባር ቀደም መስራችና ፕሬዚዳንት ነው። እርዳታ በሚያስፈልጋቸው የተለያዪ የዐማራ ክፍሎች የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል። ጥሪ በተደረገበት ቦታ ሁሉ በአፋጣኝ በመድረስ ብዙ ህይወትን ታድጓል።  የዐማራዉን ስር ሰደድ ድህነት፣ የሕክምና እጦትና መፍትሄዎች በበርካታ የዳሰሳና የምልከታ ጥናቶች አስደግፎ ለታዳሚው የሚያስተምር ምስጉን ሀኪም ነው።  አዋጭ የጤና ፖሊሲዎችን የሚተነትን ባለራዕይ የዐማራው ተስፋ ነው።  ምክንያቱም የዐማራ ሕዝብ  የጤና ሁኔታ ከሀገራችንና ከዓለማችን ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛው ነው:: በዚህ ታላቅ ነባርና ቀደምት ሕዝብ  ላይ ከባድ የበሽታ ሸክም ተንጃቦበታል፤ የጤና ሽፋን መጠኑ ከ42 በመቶ አይበልጥምና።  ባለው የደህንነት ስጋትና ቀውስ ምክንያት ዐማራው የሕክምና ባልሞያ  እንደልብ የማይገኝበት ነው።  ሁኔታውን ከባድና አሳሳቢ የሚያደርገው ሌላኛው ክስተት የህክምና ስነ-ምግባርን የጣሰ፣ ሀኪምን በእስር ቤት ማሰቃየት ነው፤  ዶ/ር ጋሹ ክንዱ ከወራት በፊት በኮማንድ ፖስት ከባህር ዳር ታፍኖ ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ እስር ቤት የተወስደ መሆኑ ይታወቃል። ያለምንም ፍርድ ለ3ኛ ጊዜም ተቀጥሯል።
በራሱ አንደበት የተነገረ ና የሚታይ አካላዊና ስነ- ልቦናዊ ኢሰብዓዊነት እየተፈፀመበት ነው።  ይህ ድርጊት ከ ‘ሜዲስን ፎር ፒስ’ (MFP, Cruelty and Denial, Medical Evidence for State-Sponsored Torture in Ethiopia ) ሪፖርት የተለየ አይደለም፤ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ አካላዊ ማሰቃያ ስልቱ በህቡዕና በብሄራዊ ደረጃ መዋቀሩን ያትታል፤ አብዛኞቹ ምሁራን  መሆናቸውንና እስከ 52%ቱ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ መታሰራቸውን ይገልጻል። ከ50 በመቶ በላይ ከድብደባ እስከ ‘ፋላንጋ’ ና ‘ቴሌፎኖ ‘  የማሰቃያ ዘዴዎች እንደሚደርሱባቸው የተረጋገጠ ነው።  በዶ/ር ጋሹ ክንዱ ላይ ከዚህ የተለየ እጣ ፋንታ አልተለየዉም።
ዶር ጋሹ ከላይ በተገለፀው ማንነቱ የሚታወቅ እና የዐማራው ሁለገብ የጤና ቀውስ የሚያሳስበው እንጅ ለእስራት የሚያበቃ መረጃ አልተገኘበትም። ይህ ዶክተርን ፣ ቤተሰቡንና ተገልጋዩን የሚጎዳ አፋኝ እርምጃ መሆኑን የዐማራ ሀኪሞች ያምናሉ።
ህክምና በሞያው ፀባይ የሕዝብ  መሪ ማድረጉ አሁን ላይ ለመንግስት ፖለቲካዊ ስጋት አሳድራል።  የህክምና ባለሞያን ማጥቃት መዘዙ ብዙ መሆኑ ሁልጊዜ ም መታወቅ አለበት። የሰው ልጅ በበሽታ እንዲሰቃይና ሞቱ እንዲፋጠን ምክንያት ይሆናል። ህይወትን የማዳን ሩጫው እንዲገታ ይደረጋል።  በተባበሩት መንግስታት የጸደቀውና በሁሉም የህክምና ማህበራት የሚተገበረው እኩልና የላቀ ጤና የማግኘት መብት የተጣሰ ይሆናል።  ሀገራት የዜጎቻቸውን የጤንነት ሁኔታ ለመጠበቅ ለሀኪሞች ምቹ የመስሪያ ቦታ እና አስደሳች ጥቅማጥቅሞች እንዲያመቻቹላቸው ይደነግጋል። በሀገር ደረጃም በኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር በ 2010 የጸደቁ  የጤና ህግጋቶች አሉ፤  ማህበሩና ተከታይ ሃኪሞች የሚያከብሯቸው የቶኪዮና ጀኔቫ ስምምነቶች ናቸው። በሀኪምና ቤተሰቦቹ ላይ የሚጋረጥባቸውን ማንኛውንም ጭቆና መፍትሄና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ከላይ በተጠቀሱት መረጃወች መሰረት ዶ/ር ጋሹ የህሊና እስረኛ ብቻ ያደርገዋል። በዚህም መሰረት የሚከተሉት ህግጋቶችን በማክበር ሁሉም ሀኪምና ማህበራት የዶ/ር-ጋሹ-ክንዱን እስራትና ስቃይ በአስቸኳይ ለማስፈታት ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የዐማራ ሀኪሞች እናምናለን።
1ኛ. በጅኔቫ የ1949 ዓ.ም አንቀጽ 6.1 መሰረት ሀኪም የህክምና ስነ ምግባርን አክብሮ እስካከመ ድረስ ማንም ይሁን ማን በምንም ምክንያት መቀጣት የለበትም።
2ኛ. የዓለም የህክምና ማኅበር የ1956; 1957 እና 1983 ዓ.ም ደንብ የሀኪም ተቀዳሚ ተግባር ሞያዊ ግዴታውን መወጣት ሲሆን፣  ህሊናውን ብቻ ተገዥ ያደርጋል፤ ይህን በማድረጉ በምንም ሁኔታ ወቀሳን ሊያመጣ አይገባም።
3ኛ. የኢትዮጵያ የህክምና ማኅበር አንቀጽ 7; 2010:  ዶክተር በሽታን ለመከላከልና ጤናን ለመገንባት የሚያስችል መረጃ መሆኑን ካመነበት ለሕብረተሰቡ ማስተማር ይችላል።
የህክምና ስነ-ምግባር መርሆችን በማክበር የሀኪምን እስራትና ስቃይ እንታደግ!
ሚያዚያ 2009 ዓ.ም
ከዐማራ ሀኪሞች ማኅበር
አዲስ አበባ

Monday, May 1, 2017

ቀጨኔም ጉልበት አግኝታ – ማሞ ማስረሻ




 
የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል “ተጠና” የተባለውን ባለ 46 ገጽ ወረቀት አንብቤ ጨረስኹ። “ለካንስ ያለነገሩ አይደለም ሲያዝቃዠኝ የነበረው” እንደምትለው እናቴ – ለካንስ ያለነገሩ አለነበረም በጠዋት “መሳቁን ይስቃል ጥርሴ መች አረፈ፣ ልቤ ነው በጣሙን እጅግ ያኮረፈ” የሚለውን የጥላሁንን ዜማ ለብድ ለብድ ያሰኘኝ።
 
ምን አግኘቼ መሰላችሁ፦ እትብቴ የተቀበረባት የሰፈሬ ስም ከሰንጠረዥ መሀል ዱቅ ብላለች። ያው አብዛኞቻችሁ እንደምታውቁት “ቀጨኔ” ሲባል ወደ አእምሯችሁ የሚመጣው “ቡዳና ሰው ከመብላት ጋራ” የተያያዘ ታሪክ ነው። እኔም ብዙዎች ስለ መጨቆን፣ ስለ መገለልና ስለመጨፍለቅ ሲያወሩ ቀጨኔን እያሰብኹ እጄን ባፌ ላይ ጭኜ የትዝብትና የስላቅ ሳቅ እስቃለሁ።
 
እና “ጥናቱ” ምን ቢል ጥሩ ነው፦ ቀጨኔ በኀይል ስሟን ያገኘቸው ከዶቢ ቀምታ ነው። ቀጨኔም ጉልበት አግኝታ የመንድር ስም ቀምታለች ተባለ።
 
ለነገሩ
 
“ሰው ሁሉ እንዳይኾን ፍጹም ደመኛዬ
እያጣራ ይስማ ስግብግብ ጆሮዬ”
 
የሚለውንም ዜማ ሰምቻለሁና እጽናናለሁ።
 
እንግዴህ ይኼ የአዋጅ ረቂቅ ተግባራዊ የሚኾን ከኾነ – የቀጨኔ ልጅ መኾኔ ይቀርና “የዶቢ ልጅ” ልባል ነው።

ቅዳሜ ምሽት በባህር ዳር የደረሠ ፍንዳታ የሠው ሕይወት አጠፋ…… (ትዝታ በላቸው-VOA)



ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት በባህር ዳር መስቀል አደባባይ በሚገኘው ሚሊኒዬም የወጣቶች ስፖርት ማዕከል ውስጥ ፍንዳታ ደርሶ የሁለት ሰው ሕይወት ማጥፋቱን ቢያንስ አምስት ሠዎች መቁሰላቸውን ከአካባቢው ያነጋገርናቸው ምንጮች ገልፀውታል፡፡
ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ምሽት በባህር ዳር መስቀል አደባባይ በሚገኘው ሚሊኒዬም የወጣቶች ስፖርት ማዕከል ውስጥ ፍንዳታ ደርሶ የሁለት ሰው ሕይወት ማጥፋቱን ቢያንስ አምስት ሠዎች መቁሰላቸውን ከአካባቢው ያነጋገርናቸው ምንጮች ገልፀውታል፡፡ፍንዳታው የደረሠው ታዋቂ አርቲስቶች በተገኙበት የሙዚቃ ዝግጅት ላይ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ሰለተገደሉትና ሰለቆሰሉት ሠዎች ማንነትና ቁጥር ለማጣራት ጥረት ተደርጓል፡፡
ወደ አማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንግሡ ጥላሁን ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አልተሳካም፡፡ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡

ባለፈው ሳምንት በጎንደር በፈነዳው ቦምብ አንድ የውጭ አገር ዜጋን ጨምሮ አምስት ሰዎች መጎዳታቸው ተገለጸ



ኢሳት (ሚያዚያ 23 ፥ 2009)
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ ደርሶ በነበረው የእጅ ቦምብ ፍንዳታ አንድ የውጭ ሃገር ዜጋን ጨምሮ አምስት ሰዎች መጎዳታቸውን ሰኞ ይፋ አድርጓል።
ይሁንና የብሪታኒያ መንግስት ጉዳት የደረሰበትን የውጭ ዜጋ ማንነት ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባሰራጨው የጉዞ ማሳሰቢያ አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ የእንግዶች ማረፊያ ሆቴል ላይ የደረሰውን የቦምብ ፍንዳታ አስመልክቶ ኢሳት የአይን ዕማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘገባ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።
የብሪታኒያና የአሜሪካ መንግስታት በተከታታይ የቦምብ ፍንዳታ መድረሱን በማረጋገጥ ለዜጎቻቸው የጉዞ ማሳሰቢያን እያሰራጩ ይገኛል። በክልሉ እየደረሰ ያለው ጉዳት አካባቢውን በሚጎበኙ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች ዘንድ ስጋት ማሳደሩም ይነገራል።

መልስ ያላገኘው የሠራተኛው ጥያቄ ? – (ይድነቃቸው ከበደ)




ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) እ.አ.አ ከ1890 ተጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል። የዘንድሮ የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በዓለም ለ128ኛ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሠራተኛው መሰረታዊ የነፃነት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ለ42ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው ። የሠራተኛው በነፃ የመደራጀት መብት ከፅንሰ ሃሳብ ባለፈ ለተግባራዊነቱ ዳተኝነት የሚያጠቃው የገዢው ሥርዓት መንግሥት፣ እንዲህ ዓይነቱን የቡዱን መብት አክብሬ አስከብራለው በማለት ቀን ከለሊት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከመለፍለፍ ባለፈ ለሠራተኛው ሙሉ ነፃነት የሚሰጥ አንዳችም ጠብ ያለ ነገር የለም። ይባስ ብሎ የሠራተኛው በነፃ የመደራጀት መብት ተደፍጥጦ ይገኛል።

የሠራተኛው መደብ ለመብቱና ለጥቅሙ በመደራጀት ፣ጥያቄዎች የማቅረብ እና ምላሽ የማግኘት የማይገደብ መሰረታዊ መብቱ አሁን ላይ በእጅ አዙር እንዲሁም በቀጥታ ጫና እየተደረገበት ነው። ለዚህም ብዙ እርቀት መሄድ ሣያስፈልግ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መመልከት በራሱ በቂ ነው። (ኢሠማኮ) የማሀበሩ ስያሜ ከመሆኑ በስተቀር ፣ ለአገዛዙ ሥርዓት ፣ የሠራተኛው መብትና ጥቅም መውሰጃና መመለሻ የአቋራጭ መንገድ ቀይ ምንጣፍ ከመሆኑ ያለፍ እዚህ ገባ የሚባል ጥቅም የሌለው ማህበር ነው። ሠራተኞች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ በማህበር በማደራጀት መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስከበርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም በሃገር ጉዳይ በጎ አሰተዋአዖኦ ማበርከት ተቀባይነት ያለው ዓለም አቀፍ ጤናማ ሂደት ነው።