Friday, February 3, 2017

አርበኛ አብሲቴ – ኄኖክ የሺጥላ

 


አርበኛ አብሲቴ – ኄኖክ የሺጥላ
ሃሳብን መሞገት ሲዳግት ፥ ቀዳዳ ፈልጎ ትንኮሳ አንዳች ለውጥ አያመጣም ። ለምሳሌ ብርሃኑ ነጋ አብሲት እንደሚጥል ተናግሯል ። አብሲት መጣሉ ወንጀል አይደለም ። ከይህ በፊት እንዳልኩት ለጦሩ ሚንስ ቤት ሁነኛ ሰው ሆኖ ሊሰራ ይችላል። አብሲት በመጣሉ አርበኛ አብሲቴ አላልኩትም ! ቢሳካለትም ባይሳካለትም ያው አርበኛ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ነው የሚባለው። እኔ የተቃወምኩት ስለ አብሲት ያወራበት ሰዓት ጎንደር ውስጥ ሰዉ ትንቅንቅ ላይ በነበረበት ወቅት ነው ! ጎጃም ውስጥ አማሮች ወገኖቻችን ከወያኔ ጋር እየተፋለሙ ባሉበት ወቅት ነው ነው ! ይህንን በመቃወሜ ሙቅ ስለማሞቅ ተከታዮቻቸውን ፥ አልፎ ተርፎ እዚህ ካልፎርኒያ በኪኒን የሚኖሩ በሽተኞችን ሳይቀር እየደጎሙ ፥ ከኔ አልፎ ልጆቼን እና ባለቤትን ፀያፍ በሆነ ቃል ያሰድባሉ። እነሱ ከደሙ ንፁ ለመምሰል ይሞክራሉ ! ዋናው ነገር ግንቦት ሰባቶች እንዴት እንደሚሰሩ አውቃለሁ።
ለምሳሌ እዚህ ሳን ሆዜ የሚኖር አንድ ሃብታሙ የሚባል የኢሃፓ አባል በፅሁፍ ስለተቃወማቸው ብቻ ፥ ይህንን ሰው ከስራው ለማባረር መስራቤቱ ድረስ ደውለው አመልክተዋል ። ይህ ሰው ልጆች አሉት ፥ የዚህ ሰው ከስራ መባረር ልጆቹን ጎዳና ላይ እንዲጥል ያደርገዋል ። በወቅቱ ህንን ለማድረግ ሲያስቡ « እናንተ አብዳችኋል እንዴ ? » ብዬ ተቃውሜያቸው ነበር ። ሃሳቡን ስለገለጠ ከስራ ይባረር ማለት ከወያኔነት በምን ይለያል ? እነዚሁ ሰዎች ቤ/ክ በራፍ ላይ አስተናጋጅ ሆነው ፥ ገቢ ወጪውን ሰላምታ ሲሰጡ ይውላሉ ! አውሬዎች ስለሆነ አምላክ እንኳ የላቸውም !
በመጨረሻ
እኔ መሪ ነኝ አላልኩም ! ስለዚህ መሪ ነኝ ብሎ ስለ ሃብሲት መጣል የሚያወራውን እተቸዋለሁ! እቃወመዋለሁ ! ምክንያቴ ደሞ አላማውን የሳተ ስለመሰለኝ ! ያም ቢሆን አሁንም አርበኛ እብሲቴ ለማለት ግን አልደፍርም ! ነውር ስለሆነ !
እንዲያ ብናየው ጥሩ ነው !
ኄኖክ የሺጥላ

(ሳተናው) መኢአድ፣ ሰማያዊን ጨመሮ አምስት ድርጅቶች ለድርድሩ በጋራ እየሰሩ ነው



ገዢው ፓርቲ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንወያይ በሚል ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በአገር ዉስጥ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች (ሰማያዊ፣ መድረክ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኦራፓ …) ለዉይይት ዝግጁነታቸውን ገልጸው ከሁለት ሳምንታት በፊት ለአንድ ቀን መነጋገራቸው ይታወቃል። በወቅቱ ተቃዋሚዎቹ በዚህ ዉይይትና ድርድር ኢሕአዴግ ስብሰባውን መምራት የለበትም፣ ሌላ ሶስተኛ አካል መኖር አለበት የሚል አቋም በመያዛቸውና ገዢው ፓርቲም ያንን በመቀሉ ፣ ሶስተኛ አካል ማን ይሁን በሚለው ላይ ሁሉም  ሐሳቦች ይዘው ከመጡ በኋላ በሌላ ጊዜ ዉይይት እንዲቀጥል ተወስኖ ነበር።
በዚህ መሰረት ቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር የሚካሄድበትን ስነ-ስርዓት አስመልክቶ አማራጭ ሃሳባቸውን በጋራ ተመካክረው በአንድ ደብዳቤ አስገብተዋል ። 7 ገፅ ያለው ደብዳቤ የእጩ አደራዳሪዎች ስም ጥቆማና የአደራዳሪዎችን ሚና ፣ የእጩ ተዛቢዎችን ጥቆማና የታዛቢን ሚና ፣ የስብሰባ ስነ-ስርዓትንና የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ፣ ከሚዲየ የሚኖርን ግንኙነትና ውጤት እንዴት ለህዝቡ ይገለፅና ልዩ ልዩ ጉዳዮች የሚልን ያካተተ ነው ።
በጋራ ደብዳቤ የጻፉትም በጋራ ተሰባብሰው የመከሩት ድርጅቶች አምስት ሲሆኑ፣ ስድስት አገር አቀፍና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ ፣ ተመሳሳይ ፕሮግራሞች ያሏቸው ድርጅቶች ናቸው። እነርሱም የሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ኢራፓ(የኢትዮዮጵያ ራእይ ፓርቲ)፣ መኢዴፓ(መላው ኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ) እና ኢብአፓ(የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ) ናቸው።

Thursday, February 2, 2017

የአዲስ አበባ ሥራ አጥ ወጣቶችን የማባበል ዘመቻ በይፋ ተጀመረ


  • መንግሥት “ጥያቄያችሁ ተሰምቷል” የሚል ማስታወቂያ እያስነገረ ነው
ዋዜማ ራዲዮ- ከትናንት ማለዳ ጀምሮ በእድር ጡሩንባ ጭምር በመታገዝ የአዲስ አበባ ወጣቶች በነቂስ ወጥተው ለሥራ እንዲመዘገቡ ቅስቀሳ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ይሁንና ምዝገባው ላለፉት ጥቂት ወራት ዉስጥ ዉስጡን ሲካሄድ የቆየ እንደነበር የገለጹ አስተያየት ሰጪዎች እንዲህ በይፋና በዘመቻ መልክ በከፍተኛ ቅስቀሳ ታጅቦ ሲካሄድ ግን የመጀመርያው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ በወረዳዎች የሚገኙ የወጣት ማእከላት በባንዲራና በመፈክር አሸብርቀው ታይተዋል፡፡
እስከዛሬ ይፋ ባልሆነ መንገድ ሲካሄድ የነበረው ምዝገባ የሚፈለገውን ያህል ወጣት ተመዝጋቢ ሊያስገኝ እንዳልቻለ ይነገራል፡፡ ፈቃደኛ ተመዝጋቢዎቹም እንደታሰበው ከኢህኤደግ ቁጥጥር የራቁ አዳዲስ ወጣቶች ሳይሆኑ ቀድሞም የወጣት ሊግ አባላት የነበሩ፣ በወረዳዎች መዋቅር ዉስጥ የተሰገሰጉ መሆናቸው ምዝገባው በአዲስ መንፈስ በመስተዳደሩ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በኩል በተሟሟቀ ሁኔታ እንዲካሄድ አስገድዷል፡፡
መንግሥት የወጣቶቹን ጥያቄ ሰምቶ ሥራ ሊሰጣቸው አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የሚገልጸው ይህን ክፍት የሥራ  ማስታወቂያ መስተዳደሩ ሁሉንም የመገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች ተጠቅሞ እያስነገረ ነው፡፡ ከተለመዱ የማስታወቂ ዘዴዎች በተጓዳኝ በእድሮች በኩል፣ በኮንዶሚንየም የነዋሪዎች ማኅበራት፣ እንዲሁም የወረዳና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች የሚይዟቸው ማዝዳ ፒክ አፕ መኪናዎችን ጭምር በመዋስ በሀሎ ሀሎ ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡ የተንቀሳቃሽ ድምጽ ማስታወቂያዎች በከተማው እምብዛምም አገልግሎት መስጠት ባቁሙበት በዚህ ወቅት ጆሮ በሚበጥሱ ሞንታርቦዎች አዲስ ዘመቻ መከፈቱ ነዋሪዎችን አስገርሟል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራት በተጓደሉ የክፍለ ከተማ የይዞታ አስተዳደር ቢሮ ክፍት ቦታዎች ወጣቶች ብቻ እንዲቀጠሩ ትእዛዝ ወርዶ እንደነበር የዋዜማ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ 10 ዓመት የሥራ ልምድ ለሚፈልጉ ቦታዎች ሳይቀር “አዲስ የተመረቁ ወጣቶችን ቅጠሩ፣ እየሰሩ ይለምዳሉ” ተብለናል ይላል ለዋዜማ ሀሳቡን ያጋራ የጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ባለሞያ፡፡
አሁን በአዲስ መንፈስ የተጀመረው የሥራ ተመዝገቡ ቅስቀሳ ያልተለመደና ሥራው ምን እንደሆነ በዉል ያልተገለጸበት ነው፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቂርቆስ የገበያ ማዕከል መግቢያ አካባቢ አይሱዙ ላይ በተሰቀለ ድምጽ ማጉያ የባህል ልብስ የለበሱ ወጣት ተወዛዋዦች የመኪና ጭነት ላይ ቆመው ከበሮ እየደለቁ የአካባቢው ወጣቶች ለሥራ ፈጥነው እንዲመዘገቡ እየቀሰቀሱ ታይተዋል፡፡ በርካታ ነዋሪዎቹ ምን መጣ በሚል ከያሉበት ወጥተው ክስተቱ በአግራሞት እየተመለከቱ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የድምጽ ማጉያ ግዙፍ ሞንታርቦዎች የተገጠሙላቸው ለጽሕፈት ቤትና ለወረዳ ሥራ አስፈጻሚ ሹማምንት ታድለው የነበሩ ወርቃማ ቀለም የተቀቡ መኪናዎች በዋና ዋና ጎዳናዎች እየተዟዟሩ የምሥራች እየለፈፉ ሲሆን በየመሐሉ ለወጣቶች የሚስማሙ ሙዚቃዎች በዲጄዎች እየተለቀቁ ነበር፡፡
ትናንት ረፋድ ላይ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድን የሚወክል ባነር የለጠፈ አንድ ነጭ ማዝዳ ፒክ አፕ ተሸከርካሪ ‹‹መጪው ጊዜ የወጣቶች ነው፣ ኢንቨስተር ወጣቶችን በአጭር ጊዜ እንፈጥራለን›› የሚል መፈክር ለጥፎ በቅስቀሳ ላይ ታይቷል፡፡ ይኸው ተሸከርካሪ በተለምዶ ተረት ሰፈር በሚባለው አካባቢ በመዘዋወር ‹‹የምሥራች ወጣት ሥራ አጥ ለሆናችሁ የወረዳችን ነዋሪዎች፣ በመጨረሻም ጥያቄያችሁ ተሰምቷል…” የሚል አስገራሚ ቅስቀሳ ሲያደርግም ነበር፡፡
ማስታወቂያው በዋናነት ሁሉም ሥራ አጥ ወጣቶች በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የወጣት ማዕከል በመሄድ አልያም ቤት ለቤት ምዝገባ ለማካሄድ ለሚመጡ ሠራተኞች መረጃ በመስጠት ቀና ትብብር እንዲያደርጉ የሚለማመን እንጂ የሥራውን አይነት የለየ አይደለም፡፡
በከተማዋ ሁሉም የኤፍ ኤም ጣቢያዎች ከማለዳ ጀምሮ በተደጋጋሚ ያለ ክፍያ እንዲተላልፍ በተደረገ ተመሳሳይ የሬዲዮ ማስታወቂያ ደግሞ መስተዳደሩ ሥራ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን እየመዘገበ እንደሚገኝ ከገለጸ በኋላ መስፈርቶቹን ይዘረዝራል፡፡ እድሜው ከ18 በላይ የሆነ (የሆነች)፣ የቀበሌ መታወቂያ ያለው ወይም ያላት፣ በየትኛውም መሥሪያ ቤት ከዚህ በፊት ያልተቀጠረ (ያልተቀጠረች)፣ ሥራ አጥ ስለመሆኑ (ስለመሆኗ) ማረጋገጥ የሚችል (የምትችል)…እያለ የሚቀጥል ይዘት አለው፡፡
ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን ተከትሎ ርዕሰ ብሔሩ የሁለቱን ምክር ቤቶች አዲስ የሥራ ዘመን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር መንግሥት ለዘነጋቸው ሥራ አጥ ወጣቶች ልዩ ተዘዋዋሪ ፈንድ እንደሚዘጋጅ ቃል ከገቡ ወዲህ አብዛኛዎቹ ክልሎች ከፍተኛ ገንዘብ ለወጣቶች ሥራ በሚል ለመመደብ ተገደዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል 7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለወጣቶች ሲመድብ፣ አማራ ክልል 3 ቢሊየን፣ የትግራይ ክልል በበኩሉ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተመሳሳይ ዓላማ መድበዋል፡፡
ገንዘቡ እንዲሰጥ የታሰበው ወጣቶች አንድ ለአምስት ከተደራጁ በኋላ ሊሰሩ ያሰቡትን ሥራ በማስረዳት ብቻ ያለምንም የባንክ ማስያዣ (collateral) ገንዘቡ ፈሰስ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ የእሳት ማጥፋት ዘመቻ መልሶ ፓርቲውን እንሚያንኮታኩተው የሚተነብዩ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ገንዘቡ ሲለቀቅ ሌላ ጦስ ይዞ እንደሚመጣ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ለዚህ ዓመት ከያዘው 275 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ያልተካተተ የወጣቶች ፈንድ ሌላ 10 ቢሊዮን ብር ሲታከልበት፣ ለሠራተኛ የደሞወዝ ጭማሪ የሚያስፈልገውን ወጪ ጨምሮ ሁኔታው ብሔራዊ ባንክ ብር እንዲያትም ሊያስገድደው እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ይህ መጠን ያለው ገንዘብ አሁን ባለው የገንዘብ ዝውውር ላይ ሲረጭ ለኢኮኖሚው ግሽበትን የሚያስከትል መርዝ ሊሆንበት እንደሚችልና አገሪቱ ከዚህ ወዲህ ወደ ግሽበት ከገባች ደግሞ መውጫው ቀላል እንደማይሆን ይገምታሉ፡፡
እስከዛሬ ለወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተበተነው ገንዘብ ያመጣው ለውጥ አለመኖሩን የሚያትቱ ሌሎች ባለሞያዎች በበኩላቸው የገንዘብ አቅርቦት ብቻ ስላገኙ ራሳቸውን የለወጡ ወጣቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ጠፍተው የቀሩ እንደሚበዙበት አስረድተዋል፡፡
አምስት ወጣቶች ገንዘብ ስለተሰጣቸው ብቻ ሕይወታቸው ላይ ተአምር ይፈጥራሉ ብሎ ማሰብ አስቂኝ እንደሆነ የሚናገሩ  በርካቶች ናቸው፡፡ “ሥራ ፈጠራ ከገንዘብ አቅርቦት የበለጠ ክህሎት፣ ልምድና ተነሳሽነትን የሚፈልግ ነው፡፡” በሚል አስተያየቱን ያካፈለ በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ዉስጥ ባልደረባ የነበረ የኢኮኖሚ ባለሞያ “ለኔ የሚገባኝ መንግሥት አጣብቂኝ ዉስጥ መግባቱን ብቻ ነው” ይላል፡፡
ባለሞያው “ሥራ አጥነት ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ በዚች አገር ስለተፈጠረ የመጣ ችግር እንዳልሆነ” ካብራራ በኋላ ችግሩ የሁሉም ታዳጊ አገራት ራስ ምታት ቢኾንም ልዩነቱ የሚመጣው ችግሩን በሚፈቱበት ስልት ላይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የአረብ ፀደይን ተከትሎ አንዳንድ አረብ አገራት ለወጣቶቻቸው ገንዘብ በመበተን ጊዝያዊ መተንፈሻ ለማግኘት እንደሞከሩና የተወሰኑት እንደተሳካላቸው ያስታወሰው ይኸው የምጣኔ ሀብት ባለሞያ የኢህአዴግ መንግሥትም አማራጭ በማጣት ተመሳሳይ ስሌት ዉስጥ ገብቷል ብሎ እንደሚያምን ይገልጻል፡፡
ባለሞያው ጨምሮ እንዳብራራው መንግሥት አሁን ሊሄድበት የሞከረው መንገድ ራስን በገመድ ጠልፎ ከመጣል እንደማይተናነስ ያብራራል፡፡ ከዚያ ይልቅ ዘላቂነት ያለው በርካታ ወጣቶችን መቅጠር የሚችለውን የግል ዘርፉን ማገዝ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ቢያደርግ  አገሪቷን ወደተስፋ ሊመልሳት እድል ነበረው ብሎ ያምናል፡፡
በኛ አይነቱ ልል ኢኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በጥድፊያና በአንድ ጊዜ ፈሰስ የሚደረግ ፈንድ የምጣኔ ሐብት ቧልት (Farce in a ridiculous economy) ኾኖ እንደሚሰማው አስታውሶ “ኢህአዴግ ይህ ይጠፋዋል ብዬ ግን አላምንም፤  ምናልባት ፋታ እንኳ ባገኝ በሚል እየገባበት ያለ ትብታብ ሊሆን ይችላል” ሲል ሀሳቡን ይቋጫል፡፡
በተያያዘ ዜና ከወጣቶች ሥራ ፈጠራ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ግራና ቀኝ የመኪና ማቆምያ ክፍያ ተመን በእጥፍ እንዲጨምርና ከክፍያ ነጻ የኾኑ ጎዳናዎች ሁሉ ተለይተው ለወጣቶች ገቢ እንዲያስገኙ መንገዶቹን የመለየት ሥራ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡ አሁን በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የመኪና ማቆምያ ማማዎች ሲጠናቀቁም የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲያስተዳድሯቸው  ይደረጋልም ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከሁለት መቶ ሺ ያላነሱ ሥራ አጥ ምሩቃን እንደሚገኙ ይገመታል፡፡

በቢሊየን ብር የግብር ዕዳ ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩት አቶ ዮሀንስ ሲሳይ ተፈቱ



ዋዜማ-አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግብር በመሰወር ተጠርጥረው ላለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ የነበሩት ከፍተኛ ባለሐብቱ አቶ ዮሐንስ ሲሳይ ትናንት ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸው ተሰምቷል፡፡
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ግለሰቡን የከሰሳቸው የገቢ ግብር፣ የቫት እና የዊዝሆልዲንግ ግብር በቤተዘመድ በተቋቋመ  ኩባንያ ጋር የአሻጥር ንግድ በመነገድ ሰውረዋል በሚል ነበር፡፡ ለእስር የተዳረጉትም በመጋቢት 2004 ዓ. ም ነበር፡፡ የክሱ የገንዘብ መጠን በገቢዎችና ጉምሩክ የክስ ታሪክ ትልቁ የሚባል ነው፡፡ 
የየሱ ኩባንያ 93 በመቶ ባለቤት የኾኑት አቶ ዮሐንስ ገቢን በመሰወር በተጠረጠሩበት ወቅት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ተክሉም በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር፡፡ አቶ ኢሳያስ አሁንም እስር ቤት ናቸው፡፡
ከአቶ ዮሐንስ እስር ጋር አብረው በቁጥጥር ሥር ዉለው የነበሩት የቤተሰባቸው አባል ወይዘሮ ሂሩት እንዳለ፣ አቶ አበራ መንግሥቱ፣ ጀምበር ተካ፣ አቶ ኃይሉ አሰፋ በተለያየ ጊዜ የዋስ መብት ተከብሮላቸው ከእስር መለቀቃቸው ይታወቃል፡፡
ወይዘሮ ሂሩት የአቶ ዮሐንስ ሲሳይ የአጎት ልጅ ስትሆን፣ አቶ ኃይሉ አሰፋ ደግሞ ሸበል ፒኤልሲ የተሰኘ የየሱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ካምፓኒ እህት ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡ ሸበል በ10 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን የአቶ ዮሐንስ አባት አቶ ሲሳይ ሞላ እና የአቶ ዮሐንስ ወንድም አቶ ያሬድ ሲሳይ በባለቤትነት ሲያስተዳድሩት ቆይተዋል፡፡
አቶ ዮሐንስና ቤተሰቦቹ ከመንግሥት ሰውረውታል ተብሎ የሚገመተው የገንዘብ መጠን ክሱ በተመሰረተበት ወቅት 795 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን በክስ ሂደት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ተጠግቷል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ አቃቢ ሕጎች ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በልዩ የንግድ አሻጥር በአቶ ዮሐንስ ሲሳይ ተሰውሯል ሲሉ ላለፉት ዓመታት ተከራክረው ቆይተዋል፡፡ 
የሱ ኩባንያ በግማሽ ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል በአቶ ዮሐንስ ሲሳይና በወንድማቸው አቶ ያሬድ ሲሳይ የተመዘገበ ረዥም ዓመታትን ያስቆጠረ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ሲመሰረት ቆርቆሮ በማምረት በአገሪቱ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ ድርጅቶች አንዱ ነበር፡፡ ኾኖም በወቅቱ በነበረው የኃይል አቅርቦት እጥረት ፋብሪካው ከሙሉ አቅሙ 30 በመቶ ብቻ ለማምረት ተገዶ እንደነበር ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ የቆርቆሮ ምርት ከፍተኛ የገበያ ድርሻ እንዳለው የሚነገረው የየሱ  ፋብሪካ  ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተገኘ ብድር ነበር የተቋቋመው፡፡ ፋብሪካው የራሱ የኃይል ንኡስ መቆጣጠሪያ ተገንብቶለት በገላን  ከተማ ይገኛል፡፡ እስከአሁንም በቆርቆሮ ምርት ከፍተኛ የሚባል የገበያ ድርሻን እንደያዘ መቀጠል ችሏል፣ የጥራትና ደረጃ ጥያቄ ቢነሳበትም፡፡
በቀን አራት መቶ ቶን ቆርቆሮ ያመርታል የተባለው ይህ ኩባንያ ለረዥም ጊዜ በኪሳራ ላይ እንደሚገኝ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሪፖርት ሲያደርግ እንደቆየ አቃቤ ሕግ ያቀረበው የሰነድ መረጃ ያስረዳል፡፡፡፡
ከ3 ዓመት እስርና የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ መጋቢት 28፣ 2007 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ወንጀል ችሎት አቃቢ ሕግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ከመረመረ በኋላ አቶ ዮሐንስን እንዲከላከሉ በይኖባቸው ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል የመከላከያ ምስክር በማቅረብ ዘለግ ያሉ ቀጠሮዎች ሲሰጧቸው ቆይቷል፡፡
ግንቦት 28፣ 2004 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል አቶ ዮሐንስ በሳምንት 2 ጊዜ ከማረሚያ ቤት እየወጡ ንብረታቸውን  እንዲያስተዳድሩም ተወስኖላቸው ነበር፡፡
የአቶ ዮሐንስን ጉዳይ ላለፉት አምስት አመታት ሲመለከቱ የቆዩት በርካታ ዳኞች ሲሆኑ ከነዚህም ዉስጥ ዳኛ ታሪኳ ተበጀ፣ ዳኛ ኑረዲን ከድርና ዳኛ ከድር መሐመድ ይገኙበታል፡፡ በአንድ ወቅት አቶ ዮሐንስ ኩላሊቴን ታምሜያለሁ ቆሜ መከራከር አልችልም በሚል ለዳኞች የሕክምና ጥያቄን አቅርበው ነበር፡፡  ጠበቆቻቸውም ደንበኛቸው መቆም ሁሉ እንዳቃጣቸውና በግል ሆስፒታል እንዲታከሙ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ አቃቤ ሕጎች በበኩላቸው ተጠርጣሪው ግለሰብ ከፖሊስ ሆስፒታል ሌላ የትኛውም የግል ሆስፒታል መጎብኘት እንዳይፈቀድላቸው ተሟግተው ነበር፡፡ ያም ኾኖ ተጠርጣሪው አቶ ዮሐንስ ቀን ቀን በአጃቢ ሥራ ቦታቸው ይዉሉ እንደነበር ይነገራል፡፡
የአቶ ዮሐንስ ጠበቃ ኾነው የቆዩት አቶ ደሳለኝ ዓለሙ የቀድሞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ የዋዜማ ምንጮች አቶ ዮሐንስ ትናንት ከቤተባቸው ጋር መቀላቀላቸውን ማረጋገጥ ቢችሉም ፍርድ ቤት ግለሰቡን በነጻ ስለማሰናበት አለማሰናበቱ ያገኙት መረጃ የለም፡፡
አቶ ዮሐንስ ሲሳይ በግለሰብ ደረጃ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን ያበረከቱ ኢትዮጵያዊ ባለሐብት ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ስለ ግለሰቡ እስር በዝርዝር የቀረበ ዘገባ እዚህ ማስፈንጠሪያ ላይ ይመልከቱ-

የፊንፊኔ ደላላ-የከርቸሌ ጎበዛዝት

Home Home የፊንፊኔ ደላላ-የከርቸሌ ጎበዛዝት

የፊንፊኔ ደላላ-የከርቸሌ ጎበዛዝት

 
Geremew
Geremew
ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ! የዋዜማ ራዲዮ ወዳጆች……ሌሎችም
ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ዉሎ-አዳሬ ‹‹ብሔራዊ››፣ አመሻሼ ‹‹አብዮታዊ›› ሃሃ፣ ‹‹ላየን ባር›› ቤቴ፣ ‹‹ቴሌ ባር›› ግዛቴ፡፡
ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ…ሄሄሄ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው፤ጌታዬ!
ግን እንዴት ነዎት ባያሌው?
እርስዎም ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ደንበኞቼ መልከ ብዙ ናቸው፡፡ እኔ ግን በጥቅሉ በሁለት ከፍዬ አያቸዋለሁ፡፡ ከርቸሌ የወረዱና ከርቸሌ ያልወረዱ፡፡
ብዙዎቹ ከርቸሌ የወረዱ ደንበኞቼ በዚህ ወቅት ጤና እየራቃቸው ስለመጣ ያሳዝኑኛል፡፡ ስለዚህ በቻልኩት አቅም ሁሉ እየሄድኩ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም እኔን ሲያዩ ዐይናቸው ይበራል፡፡
‹‹ገረመው…አሁን አንተ እያለህ እኛ መታሰር ነበረብን?›› ይሉኛል፡፡ እንስቃለን፡፡
‹‹ገረመው…እንደው እሚፈቱን ይመስልሀል ግን?›› ይሉኛል፡፡ እተክዛለሁ፡፡
‹‹ገረመው! እባክህ ያን ሚኒስትር አንተ ትቀርበዋለህና ንገረው…ከቻልክ በጫወታ ጨወታ ዉለታዬን አንሳበት›› ይሉኛል፡፡ ቃል አገባለሁ፡፡
ብቻ አንጀቴን ነው የሚበሉት፡፡ ያን ሁሉ ሹም ቁጭ ብድግ ሲያስብሉ የነበሩ አሁን አንድ ዉሪ ወታደር ቁጭ ብድግ ሲያሰኛቸው ሳይ እንባዬ ይመጣል፡፡ አንዳንዶቹ ይነግዱ የነበሩት ከሚኒስትር ጋር አልያም ከሚኒስትር ቤተሰብ ጋር በዉስጥ ታዋቂ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ እንኳን ሊታሰሩ…የታሰረ የሚያስፈቱ ነበሩኮ፡፡ ምን ዋጋ አለው…ጊዜ ጣላቸው፡፡ ጊዜ ሲከዳ ደግሞ ርህራሄ የለውም፡፡
ነፍሳቸውን ይማርና እነ ጋሽ ገብረኪዳን በየነ (ሞሮኮ)፣ እነ አየለ ደበላ (አይኤምኤፍ) ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ሳገኛቸው ‹‹ፀልይልን እስቲ ባክህ›› ይሉኝ ነበር፡፡ የሁልጊዜ ሕልማቸው በሕይወት ከከርቸሌ ወጥቶ አንድ መለኪያ ዉስኪ በነጻነት መጠጣት ነበር፡፡ አልተሳካም፡፡ ከታችኛው መንግሥት ፍርድ ወደ ላይኛው መንግሥት ፍርድ በድንገት  ተሰናበቱ፡፡ በድጋሚ ነፍስ ይማር ብያለሁ!
ጓደኛሞቹ ከበደ ተሰራና ከተማ ከበደ (ኬኬ) ወዳጆቼ ነበሩ-አሁንም ናቸው በርግጥ፡፡ በአራት ኪሎና በብሔራዊ ቴአትር ጎዳና እንደገተሩት ሕንጻዎቻቸው እነርሱም ከርቸሌ በሰበሱ፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከዛሬ ነገ እንፈታለን እያሉ ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ አሁን አሁን ተስፋ መቁረጥ ጀምረዋል፡፡ መቼ ለታ ሳያቸው ጠቋቁረዋል፡፡ አንጀቴን በሉት፡፡ ስንቱን ሹም ሽንት በሽንት እንዳላረጉት ጊዜ ጣላቸው፡፡
እንደገባኝ እስር ቤት እንደ ጋሽ አያሌው አይነት የመንፈስ ጥንካሬን ይፈልጋል፡፡ ጋሽ አያሌው ተሰማ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ እጅ አልሰጡም፡፡ ያን ሁሉ ሕዝብ ባለ መኖርያ ቤት አድርገው ሲያበቁ የእርሳቸው መኖርያ ቃሊቲ እንዲሆን በፍጹም አልፈቀዱም፡፡ ስለዚህ ለራሳቸው ጥብቅና ቆሙ፡፡
‹‹የአገሬን አይን ባበራሁ…›› ብለው ለፍርድ ቤት እንባ እየተናነቃቸው ለ2 ሰዓት ተኩል አወሩ፡፡ ተሳካላቸው፡፡ ፍርድ ቤት ነጻ ነዎት አላቸው፡፡ አሁን የሰላም አየር እየተነፈሱ፣ አያት ዞሮ መግቢያዬን እየቸበቸቡ ይኖራሉ፡፡
በአንጻሩ የእድሜ ባለፀጋው የካፒታል ሆቴሉ አለቃ አቦይ ገብረስላሴ  በስተርጅና ቂሊንጦ ወርደው ይኖራሉ፡፡ አብሯቸው አንድ እስረኛ ጉድ ጉድ ሲል አየሁት፡፡ በሄዱበት ይሄዳል፡፡ ከጎናቸው ኩስ ኩስ ይላል፡፡ አስተናባሪያቸው ነው አሉኝ፡፡ ከእስረኞች አንዱን እዚያ በአገልጋይነት ቀጥረውታል ማለት ነው፡፡ ቁርስ፣ ምሳ፣ ዕራት የግል ንብረታቸው ከሆነው ከባለአምስት ኮከቡ ካፒታል ሆቴል እየመጣላቸው ይመገባሉ፡፡  አለቃ…ሲነሽጣቸው መላ እስረኛውን በሬ ጥለው ያበሉታል፡፡ ቁጡ ስለሆኑ ከኔ ጋር ብዙም ግብብት የለንም፡፡ የሩቅ ሰላምታ ብቻ! ልጃቸው የማነ ግን ነፍሴ ነው፡፡ ስንትና ስንት ብረት ያሻሻጥኩለት ባለዉለታው ነኝ፡፡ ሀብታም ሰው ይዘነጋል፡፡ እርሱ ግን ዘንግቶኝ አያውቅም፡፡ ቤቱ ጎራ ካልኩ ፈርሜ እንጂ ከፍዬ በልቼ አላውቅም፡፡
###
ጌታዬ!
አምላክ ሳይቸግረው ‹‹አውርተህ ብላ›› ብሎ የፈጠረኝ ዜጋ አይደሁ? ታዲያ ወፍራም ደላላ እንደመሆኔ ከርቸሌ ስለወረዱ ወፋፍራም ደምበኞቼ ባወሳ ምን ክፋት አለው?
አንድ ደንበኛዬ ከላይ ከዘረዘርኳቸው ሁሉ ይለያል፡፡ በገንዘብም፣ በአቅምም፣ በባህሪም፡፡
እኔ ‹‹ቀጭኑ ጌታ›› እያልኩ እጠራዋለሁ! እርሱ ገሬ ነፍሴ ይለኝ ነበር!  ከመታሰሩ በፊት፡፡
‹‹ዬሐንስ ሲሳይ ሞላ›› ይባላል፡፡ አራት ዓመት አለፈው ከታሰረ፡፡ አሁን የፍርድ ቤት ቀጠሮው ተቃርቧል፡፡ ሰሞኑን ባገኘሁት የማያወላዳ መረጃ ይፈቱታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ጆኒ ወዳጄ!  ቅዱስ ዮሐንስ ካንተ ጋር ይሁን!
‹‹ጆኒ ደግሞ ማን ነው?›› ነው ያሉኝ ጌታዬ? ጆኒማ የቬኑሱ ነጋዴ ነዋ! ባለራዕዩ! ታላቁ…ዕውቁ…ምጡቁ የመርካቶ አራዳ! የፋብሪካው ጌታ! ጅንኑ…ቀጭኑ…
ከአንድ ከ3 ወር በፊት ይመስለኛል…ጆኒ ምን እንደተባለ ልንገርዎ፡፡ ያኔ ነው የርሱን አቅም የሚረዱት፡፡
የመብራት ክፈል ተባለ፡፡ ያውም የታሠረበት እስር ቤት ድረስ የኤልፓ ሂሳብ ሠራተኞች ሄደው ‹‹የመብራት ክፈል›› አሉት፡፡ ‹‹ስንት ቆጠረብኝ?›› አላቸው፡፡ 25 ሚሊዮን ብር አሉት፡፡ እውነቴን እኮ ነው፡፡ 25 ሚሊዮን ብር የመብራት ዉዝፍ ክፈል ተባለ፡፡ ከፈላቸው፡፡ አሃ ልክ ነዋ! ጆኒ ቀጭን ጌታ…ፋብሪካዋ ዉስጥ የራሷን ግልገል ጊቤ የተከለች ጉደኛ ናት እኮ፡፡ እርስዎ የመብራት በወር ስንት ነበር የሚከፍሉት?
ከ4 ዓመት በፊት ደግሞ ልክ በዛሬው ወር ይመስለኛል…ግብር ክፈል አሉት፡፡
‹‹የምን ግብር?››
‹‹ዓመታዊ ግብር››
‹‹እሺ ታዛዥ ነኝ! ስንት መጣብኝ?›› አላቸው፡፡
ለአንድ ቢሊዮን 2መቶ ሚሊዮን የጎደለው ሂሳብ አመጡበት፡፡ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ማለት ነው፡፡ ግብር መሆኑ ነው፡፡ ደነገጠ፡፡ ጆኒ ለመጀመርያ ጊዜ ደነገጠ፡፡ እንዴት አይደንግጥ ጎበዝ!  አንድ ዜጋ እንዴት አንድ ቢሊዮን ብር አምጣ ይባላል፡፡ ለካንስ ያኔ ነገር እየፈለጉት ነበር፡፡ ‹‹ዘቅዝቃችሁ ፈትሹኝ ዱዲ የለኝም›› አላቸው ዐይኑን በጨው አጥቦ፡፡ ቢሉት ቢሠሩት ወይ ፍንክች! ዘብጥያ ወረወሩት፡፡
###
ጌታዬ!
እርግጥ ነው ዮሐንስን የሚያህል ጀግና ነጋዴ በፊንፊኔ ምድር እንደሌለ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ፡፡
ደግሞ ስወደው! ዮሐንስ ሲሳይ ሞላ ብዬ በሙሉ ስሙ ጠርቼው እንኳ አላውቅም እኮ፡፡ ‹‹ጆኒ ቀጭን ጌታዬ›› እያልኩ ነው የማንቆለጳጵሰው፡፡ እሱም እንደዚያው ነው፡፡ ያቀርበኛል፡፡ ሲቸግረኝ አንዳንድ ነገር ሸጎጥ ያደርግልኛል፡፡ ሳይበዛ ነው ታዲያ፡፡ ብዙም ጊዜ የለውም፡፡ ገንዘብ ቆጥሮ ለመስጠት የሚተርፍ ጊዜ የለውም፡፡ ስለዚህ ዘግኖ ነው የሚሰጠው፡፡ ሲለው ደግሞ ለስሙኒ ይከራከራል፡፡ ጆኒ እንደዚያ ነው፡፡ የማይጨበጥ!
ደግሞ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ፎቅም የለውም፡፡ ፎቅ ብቻም ሳይሆን ስጋም የለውም፡፡ አጥንት ነው፤ ንፋስ ነው፡፡ ረዥም ቀጫጫ፡፡ ደግሞ ይሰለባል፡፡ አሁን እዚህ ጋር አይተውት ዞር ሲሉ የለም፡፡ መርካቶ ዉስጥ በስም እንጂ በመልክ የሚያውቀው ስለሌለ እንደልቡ በእግሩ ምናለሽተራን፣ ጆንያ ተራን፣ ሰሀን ተራን ይዞራል፡፡ ራሱ ያመረተውን ዕቃ ተከራክሮ ይገዛል፡፡ ዋጋ ያጣራል፡፡ ጆኒ ቀጭን ጌታ! ጆኒ ነፍሴ!
እርሱ ከነጋዴዎች ሁሉ የላቀው ነው፡፡ ከመርካቶ ወጥቶ ‹‹የሱ›› የተባለ ቆርቆሮ ፋብሪካን ‹‹ሸበል›› በሚል ኩባንያ ስም በግማሽ ቢሊዮን ብር ገላን ላይ ሲያቋቁም ‹‹አበደ›› ያላለው አልነበረም፡፡ እኔ ራሱ ‹‹ተው›› ብዬዋለሁ፡፡ ሰው አይሰማም፡፡ ‹‹እሺ›› ይላል ግን ሰው አይሰማም፡፡ በሐሳቡ ገፋበት፡፡  ‹‹የሱ›› ፋብሪካ ምርት ሲጀምር ‹‹ደረጃ›› የሚባል በጥራቱ እዚህ ግባ የማይባል ቆርቆሮ ማምረት ጀመረ፡፡ ምድረ ዉሪ ደላላ ሁላ ‹‹ጆኒ ወደቀች-አበቃላት›› ሲል አሟረተ፡፡ እሱ በነገሩ ገፋበት፡፡ ደረጃ መዳቢም ዝም አለው፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳዩ በበድሩ አደም በኩል በፓርላማ ሲቀርብላቸው ‹‹እዚህ የግለሰብ ጉዳይ እያነሳን አንፈተፍትም›› ብለው የሕዝብ እንደራሴዎችን አሳቁ፡፡ ዉሪ የግል ጋዜጣ ሁላ ‹‹ኡ ኡ›› አለ፡፡ ቀጭኑን ጌታ ጆኒ ሲሳይ ሞላን ግን የመለሰው አልነበረም፡፡ ገለባ ቆርቆሮ ማምረት ጀመረ፡፡ ምርቱ እንደ ቆሎ መሸጥ ጀመረ፡፡ ዛር ቆመለት፡፡ ብር ሰገደለት፡፡ ያልተጣራ ዕለታዊ ትርፉ 1.5 ሚሊዮን ብር ደረሰ ተባለ፡፡ ልብ ይበሉ! የወር አላልኩም፡፡ የዕለት ትርፍ ነው የማወራው፡፡ የርስዎ የዕለት ገቢ ስንት ነበረ ጌታዬ?
ጆኒ ቀጭን ጌታን እኔና እኔን የመሰሉ ወፍራም የፊንፊ ደላሎች ካልሆንን ብዙ ሰው በመልክ እንኳ አያውቀውም፡፡ ቅጥነቱ የማራቶን ሯጭ እንጂ ነጋዴ አያስመስለውም፡፡ አለባበሱ ተመጽዋች እንጂ መጽዋች እንዳይመስል ረድቶታል፡፡ እሱ ግን ዋረን ቡፌት ነገር ነው፡፡ ሲመጸውት ዐይን የለውም፡፡  ጌታዬ! በመረጃ ነው የማወራዎ! ጆኒ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ ስንት ብር እንደለገሰ ያውቃሉ? ካላወቁ ‹‹አላውቅም›› ይበሉ! 82 ሚሊዮን ብር፡፡ በሟቹ አቡነ ጳውሎስ በኩል ነበር ጥሬ ብሩን የላከው፡፡ በጆንያ አስጭኖ! አንድ ጊዜ የመጸወተው የገንዘብ መጠን ነው ታዲያ ይሄ፡፡ በየጊዜው ሸጎጥ የሚያደርግላቸውን ሊቀ መላዕክቱ ይቁጠሩት፡፡ በቀደም ለታ ፋይል ሳገላብጥ ሟቹ ፓትሪያርክ የጻፉለትን የምስጋና ደብዳቤ ቅጂ አገኘሁት፡፡ ‹‹ልጄ ዮሐንስ! እግዚአብሔር ከማይጎድለው ፀጋው አብዝቶ ይስጥህ›› ይላል፡፡
የፓትሪያርኩ ‹‹ምርቃት›› ደረሰ መሰለኝ ይኸው ቃሊቲ ወርዶም ንዋይ እንደመና ይዘንብለታል፡፡ 
ጆኒ የት ነው ያለው?
ጆኒ ቀጭን ጌታ ዛሬ መገኛው ቃሊት ነው፡፡ ከቂሊንጦ ወደ ቃሊት የተዛወረበት ታሪክ በራሱ ሌላ ጥራዝ ይወጠዋል፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ግድም ቂሊንጦ ሳለ ልጠይቀው ሄጄ ነበር፡፡ እዛም ነግሷል፡፡ የእስረኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አርገው ሾመውታል፡፡ እዚያ አሳሪዎችም ታሳሪዎችም ይሰግዱለታል፡፡ ምን ቢያደርግ ነው ይህ ሁሉ ሽርጉድ ብለን ጠየቅን፡፡ ለቂሊንጦ 300 ሰው የሚይዝ አዳራሽ በራሱ ወጪ ሠርቶ አስረክቧል አሉን፡፡ ኃላፊዎች ወደዱት፡፡ ወደውት አላበቁም፡፡ በሳምንት 2 ቀናት ቢሮ በአጃቢ ሄዶ ሥራ እንዲሠራ በዛም በዚም ብለው አስፈቀዱለት፡፡ ጆኒ በዚህ አልረካም፡፡ ‹‹በየቀኑ በአጃቢ እየወጣሁ ማታ ማታ ብቻ ለአዳር ብመጣስ?›› አላቸው፡፡ ‹‹ይሄማ የማይሞከር ነው አቶ ዮሐንስ፣ እንኳን አንተ ገብረዋዕድም እንዲህ አላለ…›› አሉት፡፡ እንዲህ የሚሉት እኮ ደደቢት የታገሉ የእስር ቤቱ ከፍተኛ አስተዳዳሪዎች  ናቸው፡፡
‹‹የማይሞከር ነውማ አትበሉኝ፣ ደርግን የጣላችሁ ሰዎች፣ መቀሌ እስር ቤት በአንድ ኦፕሬሽን ስንት ሺ እስረኛ ያስፈታችሁ ሰዎች እኔን አንድ ነፍስ ከዚህ ማውጣት እንዴት ይሳናችኋል?›› ብሎ አሳቃቸው፡፡ ከትከት ብለው ከልባቸው ሳቁ፡፡ ሳቃቸው ሲያባራ…
‹‹እስቲ የምንችለውን እንሞክራለን›› ብለውት ሄዱ፡፡
እርሱም ዝም አላለም፡፡ ለሦስቱም የእሥር ቤቱ አለቆች በየስማቸው አንድ አንድ ቤት፤ ለሚስቶቻቸው አንድ አንድ መኪና በምስጢር አበረከተ፡፡ ደነገጡ፡፡ ‹‹ይሄ ሙስና አይደለም፣ ስጦታ ነው›› አላቸው፡፡ ፈገግ ብለው ደነገጡ፡፡ ያልጠበቁት ሲሳይ ቢዘንብላቸው ጆኒን ሳይታወቃቸው ማምለክ ጀመሩ፡፡ የታማሚ ካርድ ከጥቁር አንበሳ አስመጡለት፡፡ በየቀኑ በአጃቢ ወጥቶ ማታ እንዲገባ ተደረገ፡፡ ‹‹የአልጋ ቁራኛ ነው›› እየተባለ ወፍ ሳይንጫጫ ተንከብክቦ ከእስር ቤት ይወጣል፡፡ ደሳለኝ ሆቴል ይሄዳል፡፡ ብዙ ሠርቶና ጥቂት ተዝናንቶ ቂሊንጦ አመሻሽቶ ይመጣል፡፡
ይህ ከሆነ ከስንት ጊዜ በኋላ የበታች ፖሊሶች እርስበርስ ተጣሉ፡፡ የፀቡ መነሾ ‹‹ጆኒን ለማጀብ ተራው አልደርስ አለን›› የሚል ፉክክር ነበር፡፡ ነገሩ ተካረረና ጠቅላላ ግምገማ ተጠራ፡፡ የማረሚያ ቤቱ አለቆች በሙሉ ተገመገሙ፡፡ ግምገማ ግለት ነው፡፡ የበታች ፖሊሶች የጆኒን ጉዳይ አፍረጠረጡት፡፡ 3ቱ የሕወሓት ነባር ታጋዮች በጆኒ ጦስ ከስራቸው ላልተወሰነ ጊዜ ታገዱ፡፡ ጆኒም ወደ ቃሊቲ ተዛወረች፡፡ ቃሊት ከተዘዋወረ በኋላ እኔም ጠይቄው አላውቅም፡፡
ጌታዬ! ከኔ ጋር ነዎት?
የሚገርመኝ…ጆኒ ታይታ አለመውደዱ ነው፡፡ ሰማያዊ ቱታዋን ለብሳ በቂሊንጦ ማረሚያ  ግቢ ሲንጎራደድ ላየው የነሐስ ሜዳሊያ ያመጣ ሚስኪን የማረሚያ ቤት አትሌት እንጂ ታራሚ አይመስልም፡፡ ጆኒ ታይታ ብቻ ሳይሆን ፎቅም አይወድም፡፡ በአንደበቱ እንደነገረኝ ፎቅ የሚሠራ ሀብታም ይፀየፋል፡፡ ‹‹ፎቅ የሚሠራ ሀብታም ብር እንጂ ጭንቅላት የሌለው ነው›› የሚለው ነገር አለው፡፡ አንድ ቀን በቦሌ ጎዳና እርሱ መቼም በማይለውጣት ከርካሳ ፒክአፑ እየሄድን ሳለ በግራና በቀኝ የተገተሩ ፎቆችን አየና-
‹‹ገረመው! ይሄ ሁሉ የአእምሮ ድሀ በከተማው እንዳለ አላውቅም ነበር፣ ለመሆኑ ያንተስ ፎቅ የቱ ነው?›› ብሎ ቀለደብኝ፡፡ ሳቅኩኝ፡፡ ሃብታም ቀልዶ አለመሳቅ ዋጋ ስለሚያስከፍል ሳቅኩኝ፡፡
ጆኒ ፎቅ መስራትን የራስን ምስል በትልቁ ሳሎን ግድግዳ ላይ እንደመስቀል አድርጎ ይመለከታል፡፡ የሱ ሱስ ፋብሪካ መገንባት ነው፡፡ ለዛም ነው ፋብሪካውን ‹‹የሱ›› ብሎ የሰየመው፡፡ ለመዝናናት ሲፈልግ ሸራተን አይሄድም፤ ወደ ፋብሪካው እየበረረ ይሄዳል፡፡ ሞተር ሲጮህ፣ የማሽን መዘውር ሲንጣጣ፣ የጉልበት ሠራተኛ ሲረባረብ ያኔ ነፍሱ ሀሴት ታደርጋለች፡፡
ጆኒ ቀጭን ጌታ! ሲበዛ ተጠራጣሪ ናት፡፡ ራሱ የከፈተውን አምቦ ዉኃ አያምነውም፡፡ አንዴ ከተጎነጨለት በኋላ ሌላ አዲስ አምቦ እንጂ ቢሞት የጀመረውን አይጠጣም፡፡ ቂሊንጦ ሻወር ይወስድ የነበረው ሁለት መቶ የማዕድን ዉኃ ታሽጎ ገብቶለት ነው፡፡ ከቤት ታሽጎ የሚመጣለትን ምግብ አንድም ሰው እንዲነካበት አይፈልግም፡፡ ‹‹ሞሳድ ይከታተለኛል›› እያለ ያስቀን ነበር ድሮም፡፡ ለምን ያን እንደሚያደርግ ግን ዛሬም ድረስ አይገባኝም፡፡ እኔን ካልገባኝ ደግሞ ማንንም አይገባውም ማለት ነው፡፡
ጌታዬ! ከኔ ጋር ኖት?
ያው እንደሚያውቁት የወሬ ሱስ አለብኝ፡፡ አንዳንድ ሰው ደግሞ የሲጃራ ሱስ አለበት፡፡ ጆኒ ደግሞ የፋብሪካ ሱስ ነው ያለበት፡፡ በአንድ ወቅት ታዲያ የፋብሪካ ሱሱን ለመወጣት የአገሪቱን ትልቁን የብረት ፋብሪካ ዱከም ላይ ለመገንባት ጫፍ ደረሰ፡፡ የከተማዋን ጎዳና ተዳዳሪ በሙሉ አንድ ግቢ ሰብስቦ ‹‹የወዳደቀ ብረት ካመጣችሁልኝ በጥሩ ብር እገዛችኋለሁ›› አላቸው፡፡ ወዲያውኑ በከተማዋ የሚገኘው የቆራሌው ቁጥር በመቶ እጥፍ ጨመረ፡፡ ለሁለት ዓመት ድረስ የወዳደቀ ብረት ሲከምር ዱከም የሚገኘው ግቢው  የብረት ተራራ ሆነ፡፡ ጆኒ አበደ ተባለ፡፡ እርሱ ግን ጌታዬ! የሚሰራውን የሚያውቅ ጮሌ ነበር፡፡ የስታፋ ብረትን ጨምሮ የብረት ዘር ዋጋን መሬት ሊያስነካው ጫፍ ሲቃረብ ከዛም ከዚም ብለው ከርቸሌ ከረቸሙት፡፡ ምስኪን ጆኒ!
አሁን መንግሥት ጆኒን አንቆ ይዞታል፡፡ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ክፈለኝ እያለው ነው፡፡  አሁን ጆኒ ለመንግሥት መክፈል ያለበት እዳ ከነወለዱ 3.2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ጌታዬ አልተሳሳቱም፡፡ ያነበቡት ‹‹ቢሊዮን›› የሚል  ቁጥር ነው ፡፡ ይህ ማለት ዘንድሮ መንግሥት  ለሰራተኞች ያደረገውን የገቢ ግብር ማሻሻያ፣ እንዲሁም ለመምህራን ያደረገው የደመውዝ  ጭማሪ ሲደመር እኩል ይሆናል የጆኒ እዳ -እንደማለት ነው፡፡  ይህ ማለት የአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ወጪ ማለት ነው፡፡ ይህን ከከፈለ ዛሬዉኑ ከእስር ሊፈቱት ይችላሉ፡፡ ጆኒ ግን ብትሞት እሺ አትልም፡፡ ይህን ብር ከምትከፍል መቶ ዓመት ብትታሰር ትመርጣለች፡፡ ‹‹የምትሉት አይነት ብር የለኝም፡፡ፋብሪካውን ስገነባ ብዙ ብር አውጥቻለሁ፤ ባይሆን ቀንሱልኝና በአገር ዋጋ ልክፈል›› እያላቸው ነው ይባላል፡፡ ይሰሙታል ብለው ነው? አይሰሙትም፡፡ ለምን በሉኝ…
አንድ ወቅት ከአሁኑ ታሳሪና ከቀድመው የገቢዎች አለቃ ለአቶ ገብረዋእድ ጋር መለኪያ ይዘን ስንጨዋወት ጆኒ ለቤተክርስቲያን የሰጠውን 82 ሚሊዮን ብር ነገርኳቸው፡፡  ከት ብለው ከሳቁ በኋላ ‹‹ ስማ ገረመው! የቄሳርን እዳ ሳይከፍል የእግዜርን እዳ መክፈሉ አግባብ ነው ትላለህ?›› ብለው አሳቁኝ፡፡ ዛሬ በመሳቄ አፀፀታለሁ፡፡ በወቅቱ ግን እርሳቸው ቀልደው እኔ አለመሳቅ አልችልም ነበር፡፡ አሁን ግብር ጠያቂም፣ ግብር ተጠያቂም አንድ ቤት ገብተዋል-ቃሊቲ፡፡ እዛው ሂሳባቸውን ያወራርዱ እንግዲህ…
ጌታዬ! አሰለቸዎት እንዴ! ጆኒ እንዴት እንደተነሳ አውርቼልዎ ባበቃስ?
ጆኒ ሰርቆ አይደለም እዚህ የደረሰው፡፡ በአቋራጭም አይደለም፡፡ መርካቶ ኮንጎ ጫማ ቸርችሮ ነው፡፡ መርካቶ ኮምቦርሳቶ ደርድሮ ነው፡፡ እርግጥ ነው አባቱ አቶ ሲሳይ ሞላ (ነፍሳቸውን ይማርና) ትጉህ ነጋዴ ነበሩ፡፡ 7ኛ አካባቢ ጠጅ ቤት ነበራቸው፡፡ መርካቶም እንደነገሩ ይሞካክሩ ነበር፡፡ ሆኖም እድሜ ተጫናቸውና ሥራውም ተቀዛቀዘ፡፡ ጆኒ አባቱ በተኙበት አንድ የሰንበት ማለዳ የአባቱን ፔጆ አስነስቶ ወደ ሞያሌ ኬንያ ነዳ፡፡ ወደ ኬንያ ተሻግሮ ከአንድ የፕላስቲክ ፋብሪካ ጋር ተደራድሮ ተመለሰ፡፡ በወጣትነቱ ሲበዛ ደፋርና ቆራጥ ነበር፡፡  አባቱ ለቀናት በእግር ስላስኬዳቸው ገሰፁት፡፡ እርሱም ሁሌም እንደሚያደርገው እግር ስሞ ይቅርታ ጠየቀ፡፡
ያቺ ዕለት ጆኒና ቤተሰቡን ከተራ ሀብታምነት መንጭቃ አወጣችው፡፡ ከኬንያ በገፍ የፕላስቲክ ዉጤቶች መግባት ጀመሩ፡፡ በተለይም የኬንያ ባልዲ የመርካቶን ገበያ አስጨነቀው፡፡ ሁሉም የፕላስቲክና የችፑድ ነጋዴ ለነጆኒ እጅ ሰጠ፡፡ ያኔ ነው ጆኒ ሞቅ ያለ ንግድ ዉስጥ የገባው፡፡ ያኔ ነው ሐብቱ እንደባልዲ አፍ እየሰፋ የመጣው፡፡
እየቆየ ሲሄድ አይን ዉስጥ ገባ፡፡ መንግሥት አይን ዉስጥ፡፡ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ከሰዎቹ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመቆይት ተገደደ፡፡ ለኢህአዴግ ክብረበዓል ማድመቂያ ብር ይቀበሉታል፡፡ ለወጣቶች ሊግ ስብሰባ ብለው ብር ይቀበሉታል፡፡ ለየካቲት 11 ብር ‹‹ትንሽ በጥስ›› ይሉታል፡፡
ለምሳሌ የሕዳሴው ግድብ የቦንድ ግዢ  በግለሰብ ደረጃ በመግዛት ከሜድሮክ ቀጥሎ ክብረወሰን የሰበረው ጆኒ ነው፡፡ 30 ሚሊዮን ብር ከፍሏል፡፡ ለአማራ ልማት ማኅበር ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር ካልሰጠከን አሉት፡፡ ‹‹አትጨቅጭቁኝ በቃ ዉሰዱ›› ብሎ የጠየቁትን ስንትና ስንት ሚሊዮን ብር የሠጠ የልማት ጀግና ነበር፡፡  ምን ዋጋ አለው ኪሱን አራቁተው አሠሩት፡፡ የሚራቆት ኪስ ባይኖረውም ቅሉ፡፡
ጆኒ ይሄን ሁሉ ዓመት ስንትና ስንት ብር ገቢ ለራሱም ለመንግሥትም ሲያስገባ ሚስት እንኳን አላገባም፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ እስር ቤት ያገኘሁት ቀን ምን አለኝ መሰለዎ! ‹‹…ገረመው! ምክርህ የገባኝ አሁን ነው…እንደተፈታሁ…ሚስትም አገባለሁ…ፎቅም እገነባለሁ…››
ጌታዬ! ይበሉ ይበርቱልኝ፡፡ ንብረት አፍርቶ ከርቸሌ ከመከርቸም ይሰውርዎ!!
ገረመው ነኝ፣ ከላዮን ባር

ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት መሄድ፣ – ይገረም አለሙ



የመንገዳችን ርዝመት የድላችን ህልምነት ነበር የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳያችን፣ብዙ አይደለንም አጋጣሚ ያገናኘን ሁለት ሰዎች እንጂ፤ተቀራርቦ ለማውራት ብዙ ትውውቅ አላስፈለገንም፣በሁለታችንም ውስጥ ያለው የቁጭትና የብሽቀት ስሜት ከመቅጽበት ተናቦ ለመተዋወቂያ የሚሆን መንደርደሪያ ጨዋታም ሳያስፈልገን ነው ዘው ብለን በወያኔ ሀያ አምሰት አመታት ለመገዛት ስላበቃን ምንነትና እንዴትነት ማውጋት የጀመርነው፡፡
እኝህ ድንገቴ ያገናኘን ወዳጄ ችግሩ የዛሬ ሳይሆን ስር የሰደደ ትውልድ የተሻገረ መሆኑን ገልጸው  እንቆቅልሻችንን  በምሳሌ ሲያስረዱኝ በአይነ ልቦና ሁለት ቦታ ሄድኩኝ፡፡ አንዱ ጌትነት እንየው እኛው ነን የሚለውን ግጥሙን በመድረክ  ሲያነብ፤ ሁለተኛው  ኢሳትና ቭዢን ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት አንድ መድረክ ላይ አቶ ዳኛቸው ተሾመ ሲናገሩ ታዩኝ፡፡  የጌትነትን ልተወውና   ብዙም  ሰው ከቁብ ካልቆጠረው የአቶ ዳኛቸው ንግግር  በልቤ ውስጥ ታትማ የቀረች አንድ አንቀጽ ልጥቀስ፡፡ “  ችግሩ እኛ ራሳችን በራሳችን መሞላታችን ከራሳችን በላይ የሆነ እሞትለታለሁ ለዚህ ብዬ እኔ ልዋረድና የቆምኩለት ሀሳብ ይቀጥል የምንለው አንዳችም ነገር ስለሌለን ነው  ዛሬ የምንገኝበት ውርድት ውስጥ ያለነው ፡፡” አዎ ድፍረቱ ኖሮ በፖለቲካው መቆመሩ፣ በታሪክ ማደናገሩ መነገዱ ቆሞ በትክክል ራስን ማየትና እንደ አቶ ዳኛቸው በድፍረትና በሀቅ መናገር ቢቻል የችግራችን ችግሮቹ እኛው ራሳችን ነን፡፡ ወደ ፊት ጋት የማንራመድ  አስርም ይሁን መቶ አመት የኋልዮሽ እያየን አካኪ ዘረፍ ለማለት ወደር በራሳችን ምህዋር ሰንሽከረከር ሶስት ትውልድ የሞላን ለጎዞአችን እንቅፋቶቹ እኛው ነን፣
ወዳጄ አገዛዝ የሚፈራረቅብንና የዴሞክራሲ ባይተዋሮች የሆንበትን ምክንያት ከመጽኃፍ ቅዱስ እያጣቀሱ ሊነግሩኝ ሲጀምሩ የሀይማኖት ሰባኪ አይደለሁም አሉኝ፣ችግር የለውም አልኩዋቸው፤ ለእኔ የኢትዮጵያውያን ነገር በመጽኃፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው እስራኤሎች ከግብጽ ወደ ተስፋዋ ምድር ካደረጉት ጉዞ ጋር  ይመሳሰልብኛል በማለት ወጋቸውን ቀጠሉ፡፡ እግዚአብሄር አምላክ የመረጣቸውን እስራኤላውያንን  በግብጽ መኖራቸው አብቅቶ ወደ ከነአን እንዲገቡ ነገራቸው፤ ሙሴንም መሪ አድርጎ ሰጣቸው፣ ቀይ ባህርንም ከፍሎ አሻገራቸው፡፡ እስራኤላውያኑ ግን የኖሩባትን ግብጽ ያውቃሉና ስለሚሄዱበት ሀገር ግን የሚያውቁት ነገር አልነበረምና የማያውቁት ሀገር ሆኖባቸው ፤በፈጣሪ ላይ ያለቸው እምነትም የጸና አልነበረምና  እግራቸው ወደ ፊት ቢራመድም ልባቸው  ወደ ኋላ ወደሚያውቋት በግዞት ወደ ነበሩባት ሀገር  ግብጽ ነበር፡፡ ለምን ከግብጽ አወጣችሁን ብለውም  ፈጣሪን አማረሩት ሙሴንም በእጅጉ አስቸገሩት፡፡ ይህን ያየ ፈጣሪም እነዚህ ትእዛዜን አልተቀበሉም ከንአን  ቢደርሱም ቃሌን አይጠብቁም አለና ቃሉ በእነርሱ ሳይሆን በልጆቻቸው እንዲፈጸም ወስኖ እነርሱ እስራኤል እንዳይገቡ መንገዱን አረዘመባቸው፡፡  ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት ሲጓዙ የ11 ቀኑ መንገድ አርባ አመት ፈጀባቸው፡፡  እስራኤል የደረሱትም ከግብጽ የተነሱት ሳይሆኑ ልጆቻቸው ሆኑ፡ አሉና ከእኛ ነገር ጋር እያዘመዱ አወጉኝ፡፡
ከርሳቸው ተለይቼ ቤቴ እንደደርስሁ መጽኃፍ ቅዱስ  ገለጥሁ እንዲህ የሚል ቃልም አነበብሁ፤ “..  ሙሴንም በግብጽ መቃብር ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን፣ከግብጽ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው፣ በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻለናል ተወን፣ለግብጻውያን እንገዛ ብለን በግብጽ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን አሉት፡፡ (ዘጸአት 14/11-12)
“ለምርኮ ይሆናሉ ያላችኋቸው ህጻናቶቻቸሁ ዛሬ መልካሙን ከክፉ መለት የማይችሉ ልጆቻሁ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፣ምድሪቱንም ለእነርሱ እሰጣለሁ፣ይወርሱአታልም፣እናንተ ግን በኤርትራ ባህር መንገድ ወደ ምድር በዳ ሂዱ፡፡ ( ዘዳግም 1/39-40)
ሰውየው ያዩበት ያነጻጸሩበት መንገድ አስገረመኝ፡፡ እውነት ነው የኢትዮጵያውያን ነገር እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ  ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት  ነው የምንጓዘው/የምንታገለው  ሲሉ ይሰማሉ፤አንዳንዶቹ ደግሞ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ነው የምንፈልገው ይላሉ፡ (ማን ሰርቶ እንዲሰጣቸው እንደሚፈልጉ ባይታወቅም) ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣሉትን ትተን ሌሎቹ ብናይ ምንም ይበሉ ምን ቢያንስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፈልግ ይመሳሰላሉ፡፡  ነገር ግን ከእነዚህ አብዛኞቹ የሚናገሩት የሚጽፉትም ሆነ የሚሰሩት ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚያስጉዝ አይደለም፡፡  በአፈ ታሪክ ሲነገር  የሰሙትን ወይንም   በኢትዮጵያ በሚቀኑ  ሰዎች ተጽፎ ያነበቡትን የአባት አያታቻውን ዘመን ወደ ኋላ እያሰቡ መሻታቸው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሙግትን ነው ምርጫቸውም ስራቸውም ያደረጉት፡፡
ወደ ኋላ ማየቱ ከትናንት ተምሮ ወደ ፊት ለመረማጃ መንገድ መቀየሻ ቢሆን ክፋት አልነበረውም ክፋቱ ለዛሬም በማይበጅ ለነገም ምንም ፋይዳ በሌለው ሁኔታ  ልዩነት ለመስበክ፣ለበቀል ለማነሳሳት በጥቅሉ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት አንዳትሸጋገር እንቅፋት  ለመፍጠር እየዋለ መሆኑ ነው፡፡ የሚናገሩ የሚጽፉትም ሆነ ታሪክ ብለው የሚጠቅሱት እውነት እንዳልሆነ በመረጃና ማስረጃ ሲነገራቸው ደግሞ በእርዳ ተራዳ ጩኸት ባልትገራ ብእርና አንደበት አገር ይቃጠል ይላሉ፡፡  ይህም እንደ በጎ ነገር ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ርምጃችንም ሆነ እያታችን ሰራችንም ሆነ ሀሳባችን ወደ ፊት ላይ ማተኮር ባለመቻሉ እነሆ ለእስራኤላውያን  የ11 ቀኑ ጉዞ 40 አመት እንደፈጀባቸው እኛም የዴሞክራሲ ጉዞ ከጀመርን ሶስት ትውልድ ደርሷል፡፡ ምን አልባት ጉዞውን ሀ ብሎ የጀመረው ትውልድ የፈጣሪን መንገድ ምሪት አልቀበል ያለ፣ ለቃሉም መገዛት ያልቻለ ሆኖ  እናንተ ቀርቶ የልጅ ልጆቻችሁ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን አያዩም ፣ቃሌ ግን ይፈጸማል ከሶስተኛው ትውልድ በኋላ ተብለን  ይሆን!
ከአብዛኛው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ የምናይ የምንሰማው በቃልም በግብርም ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መድረሻ  ዘዴውን መሄጃ መንገዱን ለጉዞ የሚያስፈልገውን ከማሰብ ከመዘጋጀትና  ወደዛው ከማምራት ይልቅ ትናንትም ሆነ ዛሬ የኋልዮሽ እይታን ነው፡፡ ወደ ፊት ማየቱ ቀርቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማለምና ለዛ የሚቻለውን ማድረግ ቀርቶ  የአያቶቻችንን ዘመን እያነሱ መዋቀስ መካሰስ ለማንና ለምን እንደሚበጅ የሚያውቁት ፈጻሚዎቹ ናቸው፡፡ ከዚህ አድራጎት ውጪ ባለው ሰው እምነት ግን  በእገሌ የሥልጣን ዘመን ይህ ሆኗል በዛኛው እንዲህ ተደርጓል እያሉ  ሆኖ እንኳን ቢሆን አድራጊዎቹ በሌሉበት ዛሬ መወነጃጀል ወደ ፊት ለመጓዝ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እኛ ባንሆን ልጆቻችን ይደርሱባት ዘንድ ወደ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚደረገውን ጉዞ እንደ እስራኤላውያን  የግብጽ ከንአን ጉዞ  ያስረዝመዋል እንጂ፡፡
እስራኤሎች ፈጣሪያቸውን ያማረሩት መሪያቸውን ሙሴንም ያስቸገሩትና  ልጆቻችሁ እንጂ እናንተ እየሩሳሌም አትገቡም ለመባል የበቁት ከማናውቃት እየሩሳሌም የምናውቃት በግዞት የምንኖርባት ግብጽ ትሻለናች ብለው ወደ ፊት እየሄዱ ወደ ኋላ በማየታቸው ነው፡፡ ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን መሆኑ ነው፡፡ የእኛ ግን ከዚህ ግራ ነው፡፡ወደ ኋላ የምናየው መነታሪኪያና መወነጃጀያ ያደረግነው የምንጠላ የምናወግዘውን ነው፡፡ የጠሉትና ለምን ሆነ ብለው በቁጭት የሚናገሩለት ነገር ዛሬ እንዳይደገም ለማድረግ መስራት እንጂ  ያንኑ እያነሱ ውሀ መውቀጥ የማናውቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምትሉት ይቅርብን የምናውቀው የለመድነው  የወያኔ ግዞት ይሻለናል ከማለት በምን ይለያል? ወደ ፊት ለመሄድ የሚደርግን እንቅስቃሴ  ማወክ ያለው እንዲቀጥል መፈለግ የማይሆንበት ምን ማሳመኛ ማቅረብ ይቻላል?
ኢትዮጵያን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለማሻጋር በየዘመናቱ የተነሱ ሙሴዎችም  የከፋ ተግዳሮት የገጠማቸው  ከሚታገሉት ኃይል በላይ ወደ ዴሞክራሲ እየተጓዝን ነው ከሚሉ  ወገኖች ነው፡፡ ለትግሉ ራሳቸውን ሰጥተው፣ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት ቆርጠው፣ እንደ ሙሴ በብትርም ባይሆን በሰላማዊ መንገድ ወይንም በጠመንጃ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ቆርጠው የተነሱ ወገኖችን ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሁሉም ዴሞክራሲ የናፈቀወና አገዛዝ ያስመረረው  በሚችለው በመደገፍ ከዛም ያለፈው ከጎናቸው በመሰለፍ ጉዞውን ማፋጠን በተገባ ነበር፡፡ የእኛ የትናት ታሪክም ሆነ የዛሬ ተግባር ግን ይህን አያሳይም፡፡ ተለያይቶ በትናንት መነታረክ እንጂ ተደጋግፎ  ስንዝር ወደ ፊት የመራመድ ነገር የለም፡፡
ከሆያ ሆየው ጨዋታ ወጣ ብሎ ከወገንተኝነት ተላቆ ከስሜት በነጻ ሁኔታ ማየት ከተቻለ ወደ ፊት ከማየትና ከመስራት ይልቅ  ከትናንት ጀምሮ ወደ ኋላ ማየት ላይ ብቻ የማተኮሩና በዚሁ የመነታረኩ  አብይ ምክንያት ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ሆና ማየትን ካለመፈለግ ነው፡፡  እስቲ አስቡት ኢትዮጵያ ለዛ ብትበቃ በተቀዋሚ ስም በተለያየ አይነትና መንገድ የተሰለፈው ምን ይሆናል? ሰዎቹን አጢኑአቸውና  ሁኔታቸውን ገምግሙና በየራሳችሁ ፍርድ ስጡ፡፡ እኔ ግን ፈቃዳቸው ይሁንና አቶ አሰፋ ጫቦ ትንሽ ገለጥለጥ የሚል ርእስ በሰጡት ጽሁፋቸው ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ  ያሉትን አንድ አንቀጽ በዋቢነት ልጥቀስና ልሰናበት፡፡
“ “ያጋራ ቤታችንን”  ጨርሼ በ10 ቀን ውስጥ አደባባይ አዋጣለሁ። አማራና ኦሮሞ የሚመለከት ነው የሚል  Facebook  ላይና ሌላም ቦታ ጠቃቀስኩ። ይህ እርግማንና ዘለፋ የተጀመረው ገና ባልታየ፤ባልተነበበ ጹሁፍና አስተያየት ላይ ነበር። ያ ነው ይበልጥ የገረመኝ። ከማንውቀው ይሰውረን ማለት ይሆን ? ከምናውቀው ግን ከሸሸነው እውነት ሰውረን ነው? አውቀን የካንደነውን እውነት አታስታውሰን ማለት ይሆን?  ይህንን ደህና ያጧጧፍነውን ሥራና ገበያ ይሻማብናል ማለት ይሆን? ሥራ ያሰኘኝ በተለየ አንዳንድ ዲያስፖራው ኗዋሪዎች መተደዳደሪያም ወደመሆን የተቃረበ የሚያስመስል ፍንጭ ስለሚታይ ነው። በተፈጠረው የሕዝብ አመጽ ሳቢያ ታዋቂ ሆነን፤አገር አውቆን ፣ፀሐይ ሞቆን፤ አንቱ የተባልንበትን ልታፈርስብንም ነው  የሚል ስጋት ፈጥሮ ይሆን? የሚል መላ ምት ይፈጥራል። ”
በተቀዋሚነት ስም ያገኙትን/የሚያገኙትን ክብርም ይሁን ብር ይዞ ለመዝለቅ ወያኔ በሥልጣን መቆየት አለበት፡፡ለዚህ ደግሞ አንድ ከጳጳሱ ቄሱ እንዲሉ ሆኖ ዋንኛ የወያኔ ተቀዋሚ መስሎ የቃላት አረር መተኮስ፣ከተግባሩ ቦታ አለመድረስ፤ሁለት ከምር ወያኔን ለመጣል የሚታገሉትን መሀከላቸው ገብቶ መናጥ፣ከጎን ሆኖ ማደናቀፍ፣ከኋላ ሆኖ መጎተት፡፡ ሶስት ህዝቡ በአንድ እምነት ተስማምቶ፣በአንድ ሀገር ልጅነት ተማምኖ  ትኩረቱን እየገደለው እያሰረና እያሰቃየው ባለው ወያኔ ላይ እንዳያደርግ የሀሰት ታሪክ እየፈጠሩ የጥላቻ መርዝ መርጨት፡፡ በዚህ ስራቸውም የራሳቸውን ጥቅም የወያኔንም እድሜ ያስጠብቃሉ፡፡
ፈጣሪ የወሰነው ቀን ሲደርስ ከብዙ መንከራተት በኋ እስራኤላውያን ሂዱ ወደአላቸው ሀገር ደርሰዋል፤እነሆ ዛሬ አይበገሬ ኃያል ሀገር ለመሆን በቅተዋል፡፡  ኢትዮጵያንም አይረሳትምና የወሰነላት ቀን ሲደርስ ለዴሞክራሲ መብቃቷ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዞውንም ታሪክ ይመዘግበዋልና ያኔ ሁሉም አንደ ስራው ክብረትን ወይንም ውርደትን ያገኛል፡፡ እና ባንደርስ ልጆች የልጅ ልጆቻን ይኮራሉ ወይ ያፍራሉ፡፡ ልጁ የልጅ ልጁ የሚያፍርበት ወላጅ ላለመሆን ዛሬ ከራስ በላይ እናስብ ገንዘብ እቃ የምንገዛበት እንጂ እኛ የምንገዛበት አይሁን፤ «..ስለዚህ እላችኋላሁ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይንም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡» (የሉቃስ ወንጌል ም.2 ቁ.!2)

[ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን] በማሸነፌ ተደስቻለሁ፣ በማሸነፌ አልተደሰትኩም !!



ከፍሬው አበበ
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ጠቅላይ መንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በኩል «ስሜ ጠፍቷል» ብለው ከመሰረቱብኝ የወንጀል እና የፍትሐብሄር ክስ በአንዱ (በወንጀሉ) በነጻ የመሰናበቴ ጉዳይ ተሰምቷል፡፡ ብዙ ወዳጆቼና ጓደኞቼ እንደወጉ «እንኳን ደስ ያለህ» ሲሉኝ እኔም እንደ ወግ ልማዱ «እንኳን አብሮ ደስ አለን!» ስል ሰንብቻለሁ፡፡ ነገሩ ግን በፍርድ አደባባይ ባላንጣን እንደመርታት የሚያስፈነድቅ፣ የሚያስደስት ነገር የለውም፡፡
ሲጀምር ከሳሽ የሃይማኖት አባቴ ናቸው፡፡ የሀገር አባት፣ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ በቅዱስ መጽሐፉ አስተምህሮ የሠላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የይቅርታ ተምሳሌት ናቸው፡፡ በዚህ እሳቤዬ ምክንያት ነው፤ ክሱ ሲመሰረት ትንሽ እንደአለማመንም፣ እንደመገረምም አድርጎኝ የነበረው፡፡ ነገሩ ውሎ አድሮ ሲርየስ መሆኑ እስኪገባኝ ድረስ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር፡፡ ከሳሽ የጸሑፉን ባለቤት ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን አጣምሮ መክሰስ ይችል ነበር፣ ግን አላደረገውም፡፡ እኔን አንድ ምስኪን ጋዜጠኛ የ100 ሺ ብር ካሳ ከሚጠይቀኝ ተቋሜን አብሮ ቢከስ የበለጠ ያዋጣው ነበር፣ ይህንንም አላደረገም፡፡ ከምንም በላይ የገረመኝ ይቅር ባይነትን በምታስተምር ቤተክህነት መሪ የሆኑትን ትልቁ አባቴን መልካም ስም አጎደፍክ ተብዬ አለማዊ ፍ/ቤት መቆሜ ነበር፡፡ የህሊና ጫናው ልቋቋመው የምችለው ዓይነት አልነበረም፡፡
እናም ምን አደረግን!?
«ተው ግዴለህም….ነገሩ በይቅርታ ይለቅ» ያሉኝን ተቆርቋሪ ወዳጆቼን ምክር መስማት ነበረብኝ፡፡ እኔም ብዙ ርቀት ሄጄ መንፈሳዊ አባቴን ይቅርታ ያደርጉልኝ ዘንድ ለመለመንም ወስኜ መንቀሳቀሴ የሚደበቅ አልነበረም፡፡ ለምን ይህንን አሰብኩኝ? ምክንያቴ ግልጽ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጥፋት አለ ብዬ ባላምንም አቡኑ መንፈሳዊ አባቴ ናቸውና ቅር ስለተሰኙ ብቻ ይቅርታ መጠየቄ የእግዚአብሔር መንገድ ነው ብዬ በጽኑ በማመኔ ነበር፡፡ ምናልባት ይህ ሙከራዬ በከሳሾቼ ዘንድ እንደሽንፈት ተቆጥሮ «ዋጋውን እናሰጠዋለን!» የሚል መታበይ ውስጥ ከቷቸው ይሆን? እንጃ ማን… ያውቃል? እናም የይቅርታ ጥያቄዬ ነገ ዛሬ እየተባለ፣ እየተጓተተ ምላሹ ራቀ፡፡ «አጓተቱት» ከማለት ይልቅ «እምቢ አሉ» የሚለው ነገሩን የበለጠ ሳይገልጸው አይቀርም፡፡ በቃ!… የነበረኝ ብቸኛና አስገዳጅ አማራጭ በዚያው በፍ/ቤት መድረክ እውነታውን መጋፈጥ ብቻ ሆነ፡፡ እናም የሙያዊ አበርክቶቱን ለማድረግ ከጎኔ ከተሰለፈው ጠበቃዬ ነቢዩ እና ሌሎች ወዳጆቼ ጋር እየተመካከርን ያለፉትን 9 ወራት የፍ/ቤት ደጅ ስንጠና ለመክረም ተገደድን፡፡
በክርክራችን ለፍ/ቤቱ ለማስረዳት ከታገልንባቸው ነጥቦች አንዱ በጋዜጣችን ላይ የተስተናገደው ጹሑፍ ስም የሚያጠፋ ሳይሆን የተለመደ ትችት ወይንም ሒስ የመሆኑን ጉዳይ ነው፡፡ ትችት ደግሞ የፕሬስ ነጻነት አንዱ መገለጫና የተፈቀደ ነው የሚል ይዘት ያለው ክርክር ያቀረብን ሲሆን ይህን ለማስረዳት ካቀረብናቸው ሶስት የሰው ምስክሮች (ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን ጨምሮ) በተጨማሪ የተቋማት ምስክርነት እንዲሰጥ ጠይቀን በተፈቀደው መሰረት ሁለት መንግሥታዊ ተቋማት እና አንድ የሙያ ማህበር በጋዜጣው ላይ የወጣውን ጹሑፍ ገምግመው የጹሑፉ ይዘት ሒስ ነው ወይንስ የስም ማጥፋት ነው የሚለውን ሙያዊ ምስክርነታቸውን በጹሑፍ እንዲሰጡ አደረግን፡፡ ተቋማቱ በአጭሩ በጋዜጣው ላይ የወጣው ጹሑፍ ትችት ወይንም ሂስ እንጂ ስም ማጥፋት አይደለም አሉ፡፡ በስተመጨረሻም ፍ/ቤቱ ግራ ቀኙን መዝኖ «የጠፋ ስም የለም!»በሚል ልክ ያለፈው ሳምንት በዛሬዋ ቀን በነጻ ሊያሰንብተኝ በቃ፡፡
በፍትሐብሄር የቀረበብኝ የ100 ሺ ብር የህሊና ጉዳት ካሳ ይከፈለን ክስ ግን ገና መቋጫ አላገኘም፡፡ በዚህም ክስ እግዚአብሄር ከእኔ ጎን እንደሚቆም አንዳች ጥርጥር የለኝም፡፡
በሁኔታው ምን ተሰማህ ብላችሁ ደጋግማችሁ ለጠየቃችሁኝ፡- በክሱ ሒደት ጠቃሚ ውሳኔ ስላገኘሁኝ እንደሰው መደሰቴ እውነት ቢሆንም ፓትርያርክን ያህል አባት አሸነፈ ተብሎ መነገሩ ግን አያስደስትም፡፡ ይህ ዓይነቱ ቡረቃ እንደእኔ ላለው ለመንፈስ ልዕልና ዋጋ ለሚሰጥ ሰው የሚገባ አይደለም፣ ያሸነፍኩት እኔ ሳልሆን የእውነት አምላክ እግዚአብሔር ነውና፡፡
በመጨረሻም፡-…
ክሱ የተነሳ ሰሞን በፌስቡክ፣ በቲውተር፣ በብሎግ…. ቁጣችሁን፣ ሃዘናችሁን፣ ግርምታችሁን ያካፈላችሁን ወዳጆቼ፣ በተግባር ደግሞ «አይዞህ» ብላችሁ ከጎኔ በመቆም ፍ/ቤት አብራችሁኝ ለተመላለሳችሁ፣ ለዘገባችሁ፣ እንደወዳጄ ጠበቃ ነቢዩ ምክሩ ወልደአረጋይ ሙያዊ ድጋፍችሁኝ ሳትሰስቱ፣ በዋጋ ሳትተምኑ ላበረከታችሁልኝ፣ «ይህቺ ለትራንስፖርት ትሁንህ» ብላችሁ እጃችሁን ለዘረጋችሁልኝ ወዳጆቼ፣ ጓደኞቼ፣ የሥራ ባልደረቦቼ…. እግዚአብሄር ደግነታችሁን፣ ቸርነታችሁን ያስብልኝ፣ ይባርክልኝ እላለሁ፡፡

ግራ አጋቢዎቹ የቂሊንጦ ቃጠሎን የተከተሉ ክሶች – ከበፈቃዱ ዘ-ኃይሉ

 


በነሐሴ 2008 የቂሊንጦ እስር ቤት ባልታወቀ ምክንያት በእሳት ከተቃጠለ በኋላ መንግሥት 23 ሰዊች ሞተዋል ሲል፣ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ፕሮጀክት ደግሞ ከ70 ሰዎች በላይ ሞተዋል ብሏል። መንግሥት ለቃጠሎው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምክንያት ናቸው ያላቸውን ሰዎች በሦስት መዝገብ ከሷል።
ሀ) 38 ሰዎች በሽብር ወንጀል (ቀደም ብለው ከእስርቤት የማምለጥ ዕቅድ ሲያወጡ ነበር፣ ቃጠሎው የዛ ዕቅድ ቀጣይ እርምጃ ነው በሚል)
ለ) 121 ሰዎች በከባድ ነፍስ ማጥፋት (“የዱርዬው ቡድን” በሚል ተደራጅተው በቃጠሎው ሟቾችን እሳት ውስጥ ጨምረዋል በሚል)
ሐ) 5 የጥበቃ አባላት በሙስና (ለተጠቀሱት እስረኞች ገንዘብ በማስገባት ተባብረዋል በሚል)
የሚገርመው ለምሳሌ የመጀመሪያውን ብናይ አንደኛ ተከሳሹ (የአየር ኃይል መቶ አለቃው ማስረሻ ሰጤ) በቃጠሎው ወቅት ከተቃጠሉት ዞኖች ገለል ብሎ የሚገኝ ቅጣት ክፍል ውስጥ ከውጭ ተቆልፎበት ነበር። እዚያው መዝገብ ላይ ፍቅረማርያም አስማማው ተፈርዶበት ዝዋይ ወኅኒ ቤት ነበር። እንግዲህ እኔ የማላውቃቸው ሌሎቹም በተመሳሳይ በቦታው ያልነበሩ ይኖራሉ።
እዚያው መዝገብ ውስጥ አዛውንቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩንም (እኔ እዚያ ግቢ ውስጥ ለዓመት ያህል እስከማውቃቸው) በእንዲህ ዓይነት ነገር መጠርጠር በጣም ከባድ ነው። ሚስባህ ከድር የሚባለው ተከሳሽም እኔ ቂሊንጦ በነበርኩበት ጊዜ ውስጥ መቅዱሴ (ገበታ ተቋዳሼ ነበር)። በእንዲህ ዓይነት ወንጀል መጠርጠሩ በራሱ እሱን ለሚያውቅ ፈፅሞ አሳማኝ አይደለም። ሌሎቹስ?
ከትላንት ወዲያ 121ዱ ቀጠሮ ነበራቸው። ከችሎቱ ፈቃድ ውጪ “ገድላችኋል” ለተባሉት ሰዎች ነፍስ የኅሊና ፀሎት አድርገዋል። አብዛኞቹ ጠበቃ ሲጠየቁ የመላዕክትና ፃድቃን ሥም ሲጠሩ ነበር። ሰው ምድራዊ ፍትሕ እንደማያገኝ ተስፋ ሲቆርጥ ከሰማይ እንዲወርድለት መመኘቱ አይገርምም። ዛሬ ደግሞ 38ቱ ቀርበው ነበር። ለደረሰባቸው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ያቀረቡት አቤቱታ መልስ ሳይሰጣቸው፣ ዛሬም አቤት እያሉ ችሎቱ በአጭር ቃል ለየካቲት 22 ቀጥሮ (ለጫጫታው እንደቅጣት) አሰናብቷቸዋል። ተከሳሾቹ ከመቼውም የበለጠ ልዩ የፌዴራል ፖሊስ እጀባ ተደርጎላቸው ነበር።